ስሜት ማጣት ራሱ ስሜት ነው! ይላሉ
አንዳንዶች:: አዎ መኖር ስሜት ነው:: ትዳር ስሜት ነው:: ጓደኝነት ስሜት ነው:: አብሮ ማሳለፍ፣ አብሮ መኖር ስሜት ነው:: መብላት መጠጣት ስሜት ነው:: ፍቅር ስሜትም ውሳኔም ነው:: ጥላቻም ስሜት ነው:: ሰላም ስሜት ነው:: ሰላም ማጣትም ስሜት ነው:: ሐዘን ስሜት ነው፤ ደስታም ስሜት ነው:: ርሃብ ስሜት ነው፤ ጥጋብም ስሜት ነው:: መጠማት ስሜት ነው፤ ጥምን መቁረጥም ያው ስሜት ነው:: መብላት መጠጣት የርሃብን ስሜት አስታግሶ የእርካታ ስሜትን ማምጣት ነው:: የጥጋብ ስሜትም ያው ስሜት ነው::
የመራብም ሆነ የጥጋብ ስሜት ሁለቱም ገፊ ስሜቶች ናቸው:: ስሜቶቹ የሚፈልጉትን ካላገኙ አደጋ ያመጣሉ:: ሰው ሲርበው ብዙ እንደሚያደርገው ሁሉ ሲጠግብም ጥጋቡ አያስቀምጠውም:: ‹‹ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ›› አይደል የሀገራችንም ብሂል:: እንደው ሌላው ቀርቶ ስሜት ማጣት በራሱ ስሜት ነው:: ስለዚህ ሰዎች በእያንዳንዱ የእለት ተእለት እንቅስቃሲያቸው ከስሜት ውጪ መሆን አይችሉም እንደማለት ነው::
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በሁሉም ነገሮች ስሜት ያጣሉ:: ባዶነት ይሰማቸዋል:: ስሜት ማጣት በራሱ ስሜት ቢሆንም ባዶነት ግን ያሳስባል:: ጣዕም አልባ ሕይወት፤ አልጫ አልጫ የሚል ኑሮ ጨው አልባ ስሜት ነው:: ባይጣፍጥም፣ ባይጥምም ስሜት አለው:: ባያስደስትም፣ ባያረካም ደስ ባይልም ስሜት ነው:: ሰዎች ደስ አለመሰኘታቸውን ያወቁት በዛው ስሜት ነውና:: የመኖር ስሜቱ ያወዛግባቸዋል:: በወዳጅነት፣ ዝምድና፣ ወዘተ ማህበራዊ ግንኙነቶች ስሜት ያጡባቸዋል:: የዓለም ትርጉሙ ስሜት አልሰጥ ይላቸዋል:: የሕይወትህ ዓላማ፣ የመኖራቸው ምክንያት ትርጉሙ፣ ስረ-ስሜቱ ይምታታባቸዋል:: ራሱን ስሜታቸውን ስሜት ባጣ ስሜት ውስጥ ሆነው ሲያጠኑት ውሉ ግራ ይገባቸዋል:: ባዶነትን ሲመረምሩት፣ አለመሙላትን ሲያውቁት ለምን ግን ይላሉ:: ስሜት አልባ ስሜት ይሉሃል ታዲያ ይሄ ነው!
ጥላቻ ስሜት ነው:: ብዙ ሰው በተለይ በዚህ ውጥንቅጥ በበዛበት የፖለቲካና የኑሮ ስንክሳር ወቅት ሰውን ዝም ብሎ ይጠላል:: የሚጠላው በዕውቀቱ ሳይሆን በስሜቱ ነው:: እያወቀ የሚጠላ፣ ተምሮ የሚያወግዝ የበዛበት ዘመን ነው:: እርግማኑ የመነጨው፣ ጥላቻው የተፀነሰው ከስሜቱ ማህፀን እንጂ ከእውቀቱ ማህደር አይደለም:: አንዳንድ ሰው ለጥላቻው ምክንያት ይደረድራል:: ምክንያቱ ግን ከጠይው ስሜቱ እንጂ ከአዋቂው አዕምሮው አይደለም:: እንደዚህ ዓይነት ሰው ከህሊናው ጋር ተጣልቶ ከስሜቱ ጋር የተወዳጀ ነው:: የሚፈልገው መጥላትን ብቻ ስለሆነ ለጥላቻው ትርጉም አልባ ሰበብ ይደረድራል::
አንዳንድ ስሜት ደግሞ አለ በውስጥ የሚርመሰመስ:: ለመውጣት ጊዜ የሚጠብቅ:: አንዳንድ ጊዜ ተለቅሶም ሆነ ተስቆ፤ ተጮሆም ሆነ ተመስጦ የማይወጣ ስሜት በውስጥ ይተራመሳል:: ተናግሮ የማይገለፅ፤ ተፅፎ የማይወጣ፣ ተጸልዮ የማይገለፅ ድብቅ ስሜት በስውር መንፈስ ላይ ረብቦ ስሜት ያሳጣል:: ለቅርብ ሰው፣ ለወዳጅ፣ ለወላጅ፣ ለነፍስ አባት፣ ለሐኪም የማይነገር ስሜት አልባ ስሜት ሊሰማ ይችላል::
አንዳንድ ሰዎች ለቅሶ የሀዘን ስሜታቸውን የሚገልፁበት መንገድ ቢሆንም አልቅሰው የማይወጣላቸው ስሜት አለ:: ሳይበድሉ፣ ሳይከፉ፣ ምንም ሳያጡ፣ ምንም ሳይሆኑ ስሜት አልባ የሚሆኑበት ወቅት አለ:: ከደስታም፣ ከሐዘንም ያልሆነ የባዶነት ስሜት በውስጣቸው ይሰነቀራል:: በሰው ተከበው፣ በወዳጅ ዘመድ ታጥረው ነገር ግን የብቸኝነት ስሜት የሚያንከላውሳቸው ቀን አለ:: ቀኑ ያው ቀን ነው፤ ነገር ግን ስሜታቸው ቀናቸውን ይለዋውጠዋል:: የተለወጠው ስሜታቸው እነሱን፣ ቀናቸውን፣ ሕይወታቸውን፣ አስተሳሰባቸውንና አኗኗራቸውን ያመሰቃቅለዋል::
የተመሰቃቀለ ሕይወት ደግሞ የስሜት ማጣት ውጤት ነው:: እነዚህ ሰዎች ስሜት ያጣው ስሜትዎን ከመረመሩት ግን ሊሰለጥኑበት ወይም ሊማሩበት ይችላሉ:: ባዶነታቸውን በእውነት፣ በምክንያት፣ በዕውቀት፣ በጥበብና በእምነት ለመሙላት ከተፍጨረጨሩ ስሜቱ አዲስ ሕይወት ይሰጣቸዋል እንጂ አያጠፋቸውም::
አንዳንድ ሰው የኑሮውን ስሜት ለማሟላት ሲል በአቋራጭ መንገድ ይነጉዳል:: ዋሽቶም ቢሆን፣ አጭበርብሮም ቢሆን ያሻውን ለማሳካት ስሜቱን ለማስታገስ ሲል ወደውሸቱ ዓለም ይገሰግሳል:: አቋራጩ መንገድ ተሳክቶለት የፈለገውን ቢያገኝ እንኳን ባገኘው ነገር ስሜት ያጣል:: ፍላጎቱ የስሜቱ ወኪል ሆኖ ጉዳዩን ቢያስጨርስለትም እደሰትበታለሁ ያለው ስሜቱ ግን ያልጠበቀው ይሆናል:: መፈለጉና የፍላጎቱን ለማግኘት የሚያደርገው መፍጨርጨር የፈለገውን ሲያገኝ ትርጉም ያጣበታል፤ ስሜቱም ስሜት አልባ ይሆንበታል:: ፍላጎቱንም ሲጨብጥ ዋጋ ያጣበታል:: እንኳን ዋሽተህና አጭበርብረህ ቀርቶ እውነተኛ ሆነህና በጎ ሰርተህ እንኳን ጥሩ ስሜት ላይሰማህ ይችላል ነው ነገሩ::
በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሾፐንሐወር፡- ‹‹የምትዋሸው በፍላጎትህ እንጂ በዕውቀትህ አይደለም:: ስለዚህም ማወቅህ እንዳትዋሽ ካላደረገህ ፍላጎትህ የዕውቀትህ አዛዥ ሆኗል ማለት ነው:: ለዚህ ነው ሃይማኖቶች በላይኛው ቤት ዋጋ ታገኝበታለህ የሚሉት የእውቀትህን ሳይሆን የፍላጎትህን ስራ ነው:: ማመንዘር ብትፈልግ በእውቀትህ ሳይሆን በፍላጎትህ ነው:: ጥላቻንም ብናይ ሰው በዕውቀቱ አይጠላም፤ በፍላጎቱ እንጂ::›› ብሏል::
ስለዚህ ወዳጄ ሆይ! ምን ያህል ሊቅ ብትሆን ስሜትህን መግራት ካልቻልክ ፊደል መቁጠር ከማይችለው ብታንስ እንጂ በምንም አትሻልም:: ዕውቀትህን ስሜትህ ካሸነፈው ዋጋ የለህም:: ፍላጎትህ ጥበብህን ድል ከነሳው የፍላጎትህ ባሪያ ሆነህ ዕድሜህን ትጨርሳለህ:: ምን ያህል ስምና ዝና ቢኖርህ ፍላጎትህን መቆጣጠር፣ ደመነፍስህን ማስተዳደር ካልቻልክ ምንም ነህ:: ባዶነትህን ካልሞላህ እንደጎደልክ ትኖራለህ:: ስሜትህ እንዳሻው እንጂ አንተ እንዳሻኸው አትሆንም:: የስሜት ማጣት ስሜት የአንተነትህ ጌታ ይሆናል:: ማወቅህ ስሜትህ ላይ ካልሰለጠነ፤ ዕውቀትህ ፍላጎትህን ካልተቆጣጠረ፣ ስምና ዝናህ ስሜትህን ካልገራ እንደብረት ድስት ሲጥዱህ ቶሎ ትግላለህ፤ ሲያወርዱህም ቶሎ ትቀዘቅዛለህ:: አንተ ግን ክቡር ሰው ነህ ከብረድስትም በላይ!! ስለዚህ ሰው ሁን!:: ማወቅህ ፍላጎትህን ካልገዛ፤ ጥበብህ ስሜትህን ካልተቆጣጠረ ፍላጎትህና ስሜትህ የዕውቀትህ ገዢዎች ይሆናሉ::
በርግጥ ባዶነት እንዲሰማን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: እነዚህ ጎዶሎነት እንዲሰማን ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች ታዲያ እንደራሳችን ባህሪይ፣ የአኗኗር ዘይቤና የሕይወት ፍልስፍና ይለያያሉ:: ይህ ሲባል ምክንያቶቹ ከራሳችን ባህርይ፣ የአኗኗር ዘይቤና ከምንከተለው የሕይወት ፍልስፍና ጋር በቀጥታ ሊገናኙ ይችላሉ:: ሆኖም እነዚህ ምክንያች ሊሆኑ ቢችሉም ዋናውና መሰረታዊ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ከሌሎች ሕይወት አንፃር መቃኘታቸው ነው።
ጎረቤታችን ጋር ያለው እኛ ጋር ስለሌለ ባዶነት የሚሰማን ከሆነ፣ ለጓደኛችን የተሰጠው ለእኛም ካልደረሰ፣ የቅርብ የምንለው ሰው የሚኖረውን የኑሮ ደረጃ እኛም ካልኖርን በማለት ከአምላክ መሟገት እስካላቆምን ድረስ ሁሌም የጎደለን ነገር መኖሩ አይቀርም። ጉድለቱ ግን ተጨባጭ ሳይሆን የእይታ ጉዳይ ነው። ጉድለቱ እውነት ሳይሆን ምናባችን የፈጠረው ነው። አዎ! ጎረቤትህ ያለው እንዲኖርህ አንተ እርሱን መሆን ይኖርብሃል፤ ምክንያቱም ለእርሱ የተሰጠው ስለተገባው ነው፣ ላንተስ ስለምን እንዲሰጥህ ትፈልጋለህ? ጓደኛህ ያለውን ከፈለክ አንተ ጓደኛህን መሆን አለብህ፤ ለእርሱ የተሰጠው ለሕይወቱ ዋስትና ስለሆነ ነው፤ ላንተስ ስለምን ይሰጥህ?
የተሰጠን ሁሉ የእኛነታችን ማሳያ ምልክት ነው። ጎድሎናል ብለን የምናስበው ነገር ቢኖረን እኛ እኛን አንሆንም ነበር፤ ሌላ እንሆናለን፤ ዳግም ሌላ የሚጎድለንንም እንፈልጋለን። አዎ! ጀግናዬ..! ሕይወት ሙሉ እንደሆነች ካላሰብክ በየቦታው ቀዳዳ ማግኘትህ አይቀርም። የጎደለህን እያሰብክ፣ እንኳን ደስታ በቅጡም ሕይወትን ማጣጣም ሊከብድህ ይችላል።
ስለዚህ በቅድሚያ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከሩ መልካም ነው:: እንደሌለህ የሚሰማህ ምንድነው? እንዲኖርህስ የምትጥረው ምን ያክል ነው? ደስተኛ አይደለሁም የምትልበት ምክንያትስ ምንድነው? በእርግጥ እንደሌለህ የምታስበው ነገር የእውነት ስለሌለህ ነውን? ወይስ ሌሎች ኖሯቸው ስላየህ? እንዳልተደረገልህ የምታስበው ነገር የእውነት ስላልተደረገልህ ነው ወይስ ለሌሎች ስለተደረገ? እንዲሰጥህ የምትፈልገው የምር አስፈልጎህ ወይስ ለሌሎች ሕይወት አስፈላጊ ሆኖ ስላየኸው?
እዚህ ጋር ግን ያለኝ ይበቃኛል እስካላልክ የሚበቃህ ነገር እንደሌለ ልብ ልትል ይገባል:: በእጄ ያለው የፈለኩትን ለማድረግ ያበቃኛል፣ ያስችለኛል ካላልክ ሁሌም ለመጀመር እንደተንደረደርክ ትቀራለህ:: በሌሎች ሕይወት እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር አንተ ጋር ሲመጣ ተራ ውዳቂ ሊሆን እንደሚችል አስብ:: ሌላው ያለርሱ መኖር የማይችለው ላንተ ቢሰጥህ የሕይወትህ መጥፊያ ሊሆን እንደሚችልም አስተውል። አዎ! “ያለንን ብናውቅ የጎደለን የለም” የሚባለውም ለዚህ ነው።
የጎደለን ላይ እንደምናተኩረው ያለን ላይ ብናተኩር የት በደረስን፣ ሕይወታችንስ ምነኛ በተዋበች፣ ምነኛ በጣፈጠች፣ ደስታችንስ ምን ያክል በቀረበን? ስለዚህማ አሁን የሚያስፈልግህና የሚገባህ ነገር ሁሉ አለህና ደስ ሊልህ ይገባል:: ባለህ ነገር ስትደሰት ሌላው የሚያስፈልግህ፣ የሚጠቅምህ ብቻ እንደሚጨመርልህም እመን።
በሌላ በኩል ስኬት በሕይወት ውስጥ ቀጣይነት ያለው ደስታን ማስፋትና ሊጨበጡ የሚችሉ ግቦችን አዳጊ በሆነ መልኩ እውን ማድረግ በሚል ሊብራራ ይችላል:: ስኬት ያለብዙ ድካም ህልምን በቀላሉ የማሳካት ችሎታ ነው:: ይሁንና ሀብት መፍጠርን ጨምሮ ስኬት ሁሌም ጠንካራ የስራ ሂደትንና ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል:: መልካም ነገሮች ሁሉ ወደራስ ከበቂ በላይ እንዲፈሱ ታዲያ ተጨማሪ የስኬትና የባለፀግነት መንፈሳዊ መንገዶች መከተል ይገባል:: ስለዚህ ስሜትን ገታ አድርጎ ለስኬት መንደርደር ያስፈልጋል:: ለስኬት መጣር እንዳለ ሁሉ ያለውን ነገር ማመስገንና ባለው መፅናናት ይገባል::
በመንፈሳዊ ህግ እውቀትና ትግበራ በርካታ የስኬት መገለጫዎች አሉ:: ቁሳዊ ሀብት አንዱ የስኬት አካል ነው:: ይሁንና ቁሳዊ ሀብት የስኬት መንገድ እንጂ መድረሻ ሊሆን አይችልም::
ከልክ ያለፈ ቁሳዊ ሀብት በብዙ መንገድ የስኬት ጉዞን ይበልጥ አስደሳች ሊያደርጉ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ስኬት ቁሳዊ ሀብትን ብቻ ሳይሆን መልካም ጤንነትን ፣ ሀይልን እና በሕይወት ለመኖር፣ ግንኙነቶችን ለማሟላት፣ ለፈጠራ ነፃነት ፣ ለስሜትና የስነ-ልቦና መረጋጋት፣ ለደኅንነት ስሜት ብሎም ለአእምሮ ሰላም መጓጓትን ያጠቃልላል።
እነዚህን ነገሮች ሁሉ አጣጥመን እንኳን በውስጥችን ያለውን ሃይል እስካልተንከባከብነው ድረስ ተሳካልን ልንል አንችልም:: በመሆኑም እውነተኛ ስኬት ሲባል ተአምራትንም ጭምር ማስተናገድ ነው፤ በውስጣችን ያለው መለኮት መገለጥም ነው:: ሕይወታችንን ማየት ስንጀምር አልፎ አልፎ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ የስኬትን ትክክለኛ ትርጉም እናውቃለን። ከዚህ አንፃር ያለውን እያመሰገኑ የጎደለውን ለመሙላት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል::
ማንም ሰው ቢሆን በሕይወቱ ስኬት ለማምጣት ይጥራል:: ሀብት፣ ንብረትና ሌላም ነገር ማፍራት ይፈልጋል:: በዚህ ውስጥም ደስታን ለማጣጣም ይጥራል:: ሁሉንም ነገር ማድረግ ይፈልጋል:: ለዛም ነው የሰው ልጅ ፍላጎት ገደብ አልባ ነው የሚባለው:: ነገር ግን የሰው ልጅ በባህሪው ፍላጎቱ ገደብ አልባ ቢሆንም ስሜቱን መቆጣጠር ይገባዋል:: ሁሉንም ሊያሳካ አይችልምና:: የዛኑ ልክ ደግሞ ያለውን ማመስገን አለበት:: ምክንያቱም ያለውን ሲያመሰግን ሌላው በር ይከፈትለታልና::
ስለዚህ ሰዎች ሆይ አውቀታችሁ ፍላጎታችሁን መግዛት አለበት:: ጥበባችሁም ስሜታችሁን መቆጣጠር አለበት:: ይህ ሲሆን ሕይወት ትርጉም ይኖረዋል:: ያሰቡት ደረጃ መድረስም ይቻላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ያለንን ካመሰገንንና ባለን ነገር ከተደሰትን የጎደለን የለም:: ይህ ከሆነ ታዲያ እኛ ሰዎች የጎደለን የቱ ነው?
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም