በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም በፌደራል መንግስትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መደረሱ ይታወሳል። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም በሁለቱም ወገኖች በኩል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የሰላም ስምምነቱ የያዛቸው መርሆዎች ወደመሬት ወርዶ ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በተለይም በመንግስት በኩል ከሚጠበቅበትም በላይ በመሄድ በአፋጣኝ ወደ ስራ ተገብቷል። ለውጤታማነቱም በቁርጠኝነትና በጽናት ተንቀሳቅሷል።
የሰላም ስምምነቱ በዋነኛነትና በቅድሚያ ትኩረት ያደረገው ሰብአዊ ድጋፎች ላይ ሲሆን በዚሁ መሰረትም መንግስት ምግብና ምግብ ነክ ያሉ ድጋፎች ወደ ትግራይ በአፋጣኝ እንዲገቡ አድርጓል። ፍጥነት በተሞላው ሁኔታ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የህጻናት አልሚ ምግብ በገፍ እንዲገባም ሆኗል። ሰብአዊ እርዳታዎችን በማቅረብና በማጓጓዝ በኩል አጋር ድርጅቶች ላደረጉት እገዛ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ሰርቷል። ከፍተኛ መጠን ያላቸው መድሀኒት፣ ነዳጅ፣ ገንዘብ ጭምር ወደ ክልሉ እንዲገባ ተደርጓል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበሩ የመሰረተ ልማቶች ተጠግነው ስራ እንዲጀምሩ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ስራ ያቆሙና የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በአፋጣኝ በመጠገን የመብራት፤ የቴሌ፣ የባንክ፤ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎቶች ስራ ጀምረዋል። በዚህም በጦርነቱ ተጎጂ የነበሩ ሕዝቦች እፎይታን አግኝተው የሰላም አየር እየተነፈሱና ብሩህ ተስፋ እያዩ ወደ መደበኛ ህይወቱ መመለስ ጀምሯል። የተራራቁ ቤተሰቦች መገናኘትና ናፍቆታቸውን መወጣት ችለዋል።
አሁንም መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ሲሆን በሰላም ስምምነቱ ከተቀመጡት የጊዜ ገደቦች በቀደመ እና ከሰላም ስምምነቱ ከፍ ባለ መልኩ የልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ በመላክ ጭምር ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ያለውን ዝግጁነትና ቆራጥነት በተግባር ማረጋገጥ ችሏል። በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ መንግስት ባሳየው ቆራጥነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያውያንን ችግር በራሳችን በኢትዮጵያውያን መፍታት እንደምንችል ማሳየት ተችሏል።
ሰሞኑን ወደ መቀሌ የተጓዘው የአትሌቶች ቡድንም የዚሁ የሰላም ፈላጊነት ማረጋገጫ ሌላው ማሳያ ነው። አሁንም ወደፊትም መንግስት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነትም ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ያመላከተ እርምጃ ነው። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ለአገርና ለሕዝብ ያለውን ወገናዊነት በተግባር የሚያረጋግጥ ጭምር ነው።
ሰላም የአንድ ወገን መሻት ብቻ ሳይሆን የሁለት ወገኖች ስምምነት በመሆኑም በሕወሓት በኩልም ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት የሚበረታታና በጎ ጅምር እየታየ ነው። ሕወሓት ለሰላም ስምምነቱ ተገዢ መሆኑን ከሚየሳዩ ተግባራት መካከል ከባድ መሳሪያዎችን ለፌደራል መንግስት ማስረከብ መጀመሩ የሚጠቀስ ነው።
ሕወሓት ከባድ መሣሪያዎችን ለፌዴራል መንግሥት በመጀመሪያ ዙር ባስረከበበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ ታዛቢዎችና የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች የተገኙ ሲሆን ርክክቡ ከመቀሌ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “አጉላዕ ካምፕ” መከናወኑን የአገር መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።
መንግስት የተረከባቸው ከባድ የጦር መሳሪያዎች ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርታሮችን እና ፐምፐንዎችን ናቸው።
ሕወሓት በሰላም ስምምነቱ መሰረት ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከብ መጀመሩ የሚበረታታና ለሰላም ስምምነቱም ተገዢ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ስምምነቱን ለማጽናትም ወሳኝ እርምጃ ነው። ህገመንግስታዊነትን በማጽናት ዘላቂ ሰላምና የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እንዲረጋገጥም ዋስትና የሚሰጥ ነው። ይሄንኑ ለሰላም ስምምነቱ ያለውን በጎ ጅምር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። በሰላም ስምምነቱ መሰረት በቀጣይም በክልሉ የተለያዩ የጦር መሳሪያ ክምችት ባለባቸው ማዕከላት ተመሳሳይነት ያለው ሰላማዊ የጦር መሳሪያ ርክክብ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ይሄ ተግባር በፌዴራል መንግስትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነቱን የሚያጸና ሰላሙንም በአስተማማኝ ሁኔታ ወደመሬት የሚያወርድ ጅምር በመሆኑ መበረታታት አለበት።
የሰላም ስምምነቱ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆንም ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረግና መሥራትም አለበት። የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ፤ ልዩነትን የሚያጠብ፣ ጥላቻና ቂምና በቀልን አጥፍቶ ሕዝብን ወደ ቀደመ አንድነቱና መተሳሰቡ የሚመልስ ነው።
ከዚህም በላይ የወደመ የአገርና የሕዝብን ንብረት መልሶ በመገንባት ሕዝቡ የተሻለና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችልም ነው። በመሆኑም ለዚህ ቅዱስ ዓላማ ሁሉም ወገን የሚችለውን ሁሉ አወንታዊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። መንግስት እያደረገ እንዳለውም በሕወሓትም በኩል የተጀመረው ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የማስረከቡና ሌሎች የሰላም ስምምነቱ መርሆዎች በፍጥነት መተግበር ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም