የማዋዣ ወግ፤
“ትዝታ” እና “ታሪክ” በማናቸውም ግለሰብ ሕይወት ውስጥ ታትመው የሚኖሩ የነበር ቅርሶች ውርስ (“Legasi”) ናቸው:: ሁለቱም የሚጠቀሱት ትናንት፣ ከትናንት ወዲያ፣ አምናና አቻምና እየተሰኙ በኃላፊ የጊዜ ቀመር ውስጥ ነው:: ትዝታ በዋነኛነት በግለሰብ ሕይወት ውስጥ የታተመ የኃላፊ ትውስታ ሰነድ ሲሆን፤ ታሪክ ግን ከግለሰብም ሆነ ከቡድን ጉዳይነት ዘለግ ብሎ በሀገር ላይ በጎም ይሁን አይሁን ተጽእኖ የማምጣት አቅም ሊኖረው ይችላል::
“ትዝታ” ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች መካከል አንዱና ተወዳጁ ቅኝትም ነው:: በትዝታ የተቃኙ ዜማዎች ስሜትን ሰርስረው የመግባት አቅማቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው:: ያባባሉ፣ ያስተክዛሉ፣ ያብሰለስላሉ፣ ያረሰርሳሉ፣ ሲበረታም ያስነባሉ:: በሕይወታችን ውስጥ ታትመው የሚኖሩት ትዝታዎቻችን የሚቀሰቀሱበት በርካታ ምክንያቶችና ሰበቦች ቢኖሩም በዋነኛነት ግን መሰልና ተቀራራቢ ድርጊቶች በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ ተፈጽመው ስናይ ወይንም በተመሳሳይ ድርጊት ሲስተዋሉና ሲደመጡ “የእኔ” የምንላቸው ትዝታዎች ነፍስ ዘርተው ስሜታችንን ማዋዠቅ ይጀምራሉ:: ባእዳኑ ብሂለኞች “Awaking a sleeping giant” እንዲሉ መሆኑን ልብ ይሏል::
ትዝታ የመልካም ገጠመኞችና ኩነቶች የሃሳብ ስብስብ ውጤት ብቻ ሳይሆን መልካም ያልሆኑትንም ይጠቀልላል:: ታሪክም እንደዚያው ክፉም ደግም እየተባለ መጠቀሱ የተለመደ ነው:: ደራሲ በዓሉ ግርማ “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ውስጥ በርካታ ያልታተሙ የታሪክ መጻሕፍት ክምችቶች ይገኛሉ” – (አባባሉን በጥቂቱ ለማጎላመስ ተሞክሯል) በማለት ያስተላለፈልን ልብ ጠለቅ ጥቅስ በዚህ ቦታ ቢታወስ ተገቢ ይመስለኛል:: የራሳችንም ብሂል ቢሆን “ትዝታ አያረጅም” በማለት የነበር ትውስታችንን ማሞካሸቱ የሚዘነጋ አይሆንም::
የትዝታና የታሪክ ማዋዣ ወጋችንን እዚህ ላይ ገታ በማድረግ በዋነኛነት ትኩረት ለመስጠት ወደተፈለገበት ጉዳይ በማቅናት ኮስተርና መረር የሚሉ የሀገራዊ ውሎ አምሽቶ ትዝብታችንን ሰፋ በማድረግ ለመዳሰስ እንሞክራለን::
ጸጸት እያደር ይመሠረት፤
ይህ አምደኛ በሀገር ውስጥ በሀገር ልጆች ተጽፈው የታተሙ እና በባእዳን ጸሐፍት ለኅትመት የበቁ “ግለ ታሪኮችን” ለማንበብ ሞክሯል:: ጥቂት ለማይባሉ የሀገር ውስጥ ደራስያንም የሙያ ምክር፣ የአርትኦት አገልግሎት ለመስጠትና ሂሳዊ ዳሰሳ ለማድረግ በርካታ እድሎች ገጥመውታል:: ከብዙ ደራስያንና ደራስያት ጋር ባደረጋቸው ምክክሮችም አብዛኞቹ ጸሐፍት “ትዝታዬና ታሪኬ” የሚሉትን ሁለት ቃላት ደጋግመው ሲጠቀሙ አስተውሏል፣ በሥራዎቻቸው ውስጥም በብዛት ተጠቅሰው አንብቧል::
በተለይም በሕዝብ አስተዳደርና በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰቦች ያለፈውን የአገልግሎት ዘመናቸውን መለስ ብለው በቃኙባቸው መጻሕፍታቸው ውስጥ የጠቀሷቸው ትዝታዎችና ታሪኮች ብዙ የሚጻፍላቸው ናቸው:: ክፉም ይሁን ደግ ትዝታዎቹና ታሪኮቹ ከሕይወታቸው ጋር ተቆራኝተው ሊለዩአቸው እንዳልቻሉ የተረዱት ድርጊቶቹ ከተፈጸሙ በኋላ እንጂ በተፈጸሙባቸው እለታትና አጋጣሚዎች ይታዩ የነበረው እንደ ዋዛ እንደነበር በግልጽነት የመሰከሩም ብዙዎች ናቸው::
“አንደ ሀገር በጥቅሉ፣ እንደ ግለሰብ ራሴን ወክዬ በዚህና በዚያ ጉዳይ ተጸጽቻለሁ” በማለት በመጻሕፍታቸው ውስጥ የተሸማቀቁባቸውን ትዝታቸውን የተረኩ፣ የተበላሹ የታሪክ ክስተቶችን በዝርዝር ያስታወሱ ብዙዎች ናቸው:: ምናልባትም ዳግም እድሉን ቢያገኙ ለመካስና የፈጸሟቸውን ስህተቶች ላለመድገምም በልባቸው መመኘታቸው የሚቀር አይመስለንም:: ይህ ግምት እንጂ ማስረጃ የሚቀርብለት አይደልም:: ባህር ማዶኞች “You never get a second chance to make a first impartation” እንዲሉ መሆኑ ነው::
ሀገር እያንዳንዱ ዜጋ አሻራውን የሚያትምባት ሰሌዳ ነች:: አሻራው አንድም በበጎነት የሚጠቀስ፣ አንድም አሉታዊ ገጽታው የጎላበት ሊሆን ይችላል:: የአንዳንድ አርአያ ሰብ ዜጎች አሻራ ደግሞ ከአሻራዎች መካከል ጎልቶና ደምቆ ሲፈካ ይስተዋላል:: የአንዳንዱ አሻራ በአመጽ፣ በሴራ፣ በተንኮልና በክፋት “ቀለማት” የተኳለ ስለሆነ በእጅጉ የዳመነና የጠቆረ ነው:: “በጥቁር ሰነድ መጠረዙ” እንደተጠበቀ ሆኖ ትዝታውም ትዝታ ነው፤ ታሪኩም ታሪክ እየተሰኘ መጠቀሱ ግን ሊቀር የማይችል የግድ ይሉት ዕዳ ነው::
“ልጄ ሆይ እንደምትኖር ሆነህ ለትውልድ ሥራ፤ አንድ ቀን እንደምትሞት ሆነህም ኑር” የሚለውን የጠቢባን ምክር በተግባር ለመተርጎም የሚፍጨረጨሩ ዜጎች በትዝታቸውም ውስጥ ሆነ በታሪካቸው ውስጥ እጅግም ጸጸት ላይበዛበት ይችላል:: በአንጻሩ በጎ ለማድረግ አቅሙና ችሎታ እያላቸው “ከራስ በላይ ነፋስ” በሚል የእኔነት ፍልስፍና ለነፍሳቸውና ለሥጋቸው ብቻ ሲዳክሩ የኖሩ ግለሰቦች የሕይወታቸው ፍጻሜ የሚደመደመው እጅግ በከፋ ጸጸት ተገንዞ ነው:: ጸጸቱ እንዲህ በዋዛ የሚቋቋሙት ላይሆን ይችላል:: ምክንያቱም እንደ ሻህላ የውስጥ ማንነትን ሊያመነዥግ፣ ትዝታውም እንደ እንቆቆ እየመረረ ሊያንገሸግሽ፣ ታሪኩም በእፍረት አንገትን ሊያዘልስ ይችላል::
ጥቂት የማይባሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ወዲያ አሽቀንጥረው በመወርወር የሕዝብን ሀብት በመዝረፍና በመግፈፍ ለራሳቸው ምቾትና ለቤተሰባቸው ተድላ የሚፈጽሟቸው የተለያዩ “የአደራ በል” ድርጊቶች በፍትሕ መንበር ፊት ብድራታቸውን ቢቀበሉም እንኳን ውሎ አድሮ በአሳፋሪ ትዝታ እንደሚቀጡ፤ በጥቁር ፋይል ውስጥ ታሪካቸው ተመዝግቦ እንደሚያልፍ የተረዱት አይመስልም::
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሰነፍ ሰው፡- “ነፍሴ ሆይ ደስ ይበልሽ! ለብዙ ዘመን የሚቆይ ብዙ ሀብት አለሽ፤ እረፊ ብይ፣ ጠጭ፣ ደስ ይበልሽ” እያሉ ሲፋንኑ ሞት ወይንም ውርደት ቤታቸውን አንኳኩቶ ታሪካቸው በጥቁር ቱቢት፣ ትዝታቸውም መራራ እንደሆነ ማለፋቸውን የተረዱትም አይመስልም::
የሕዝብን እምባ እንዲያብሱ ቢሾሙም ተገልጋይን በማስለቀስ ሥራ ላይ ተጠምደው የሚውሉ ሹመኞች እንዴትና በምን መልኩ ሊታረሙ እንደሚችሉ ማሰቡ በራሱ ከሕመምም የከፋ ፈውስ የለሽ ደዌ ነው:: የሰሞኑ በዓል ያሰባሰበን ጥቂት ወዳጆች እንደ ተለመደው ስለመከረኛይቱ ሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ እየተወያየን ሳለ ከመሃከላችን አንዱ እምባው ቅርር ብሎ “ሀገር! ሀገር! የምትሉትን ይህንን መዝሙር ብታቆሙ ይሻላል!” በማለት ባለተለመደ ባህርይው ድንጋጤ ላይ ጣለን::
ይህ ወንድማችን ለዓመታት ላቡን ጠፍ አድርጎ የቋጠረውን ጥሪት አራግፎ በኢንቨስትመንት ላይ ካዋለ ዓመታት አስቆጥሯል:: ያለመታደል ሆኖ በአጋጣሚ ሳይሆን በጥናት ላይ ተመስርቶ ሀብቱን ያፈሰሰበት ክልል በማናችንም ዘንድ በሚታወቅ የፀጥታ ችግር ምክንያት ኢንቬስትመንቱ መቆም ብቻ ሳይሆን ሀብቱና ንብረቱ ተዘርፎና ተቃጥሎ እጁን አጨብጭቦ ከተቀመጠ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል::
ችግሩን እንዲፈታ የሚጠበቀው መ/ቤት የመንግሥት ሹመኛ ከመሰል ጓደኞቹ ጋር በከፍተኛው የአስፈጻሚ አካል የተወሰነለትን ጉዳዩ ለማስፈጸም ቢሯቸው ድረስ ደጋግመው በመሄድ ሊያነጋግሯቸው ቢሞክሩም እንኳን ግቡ ብለው አክብረው ሊቀበሏቸውና በመንግሥት ዘንድ በሚገባ ለሚታወቀው ችግራቸው መፍትሔ ሊሰጡ ቀርቶ በራፍ ላይ ባቆማቸው ቦዲ ጋርዶች አማካይነት እየተገፈተሩ የተዋረዱባቸውን ቀናት በቁጥር ነገሮናል::
በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ እኚሁ ባለሥልጣን በቀደም የተከበረውን ሃይማኖታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ “ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያንና” በኢንቬስትመንት ሥራ ላይ ለተሠማሩት ባለሀብቶች የመልካም ምኞት መግለጫ ማስተላለፋቸው ይበልጥ የሚያሳዝን ነው:: አሉ ለመባል ካልሆነ በስተቀር ምኞታቸው ዋጋ የሚሰጠው አይደለም:: መንግሥታዊው ተቋማቸው በሀገራቸው ላይ ኢንቬስት ላደረጉና ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ በራቸው ክፍት መሆኑን የገለጹበት ስላቅም ከሁሉም ጉዳት የከፋ መሆኑን በምሬት የገለጸልን ይሄው ተጎጂ ወዳጃችን ነበር::
ለመሆኑ ሕዝብን እንዲያገለግሉ በተሻለ ወንበር ላይ መቀመጥ ብቻም ሳይሆን ከሕዝቡ በሚሰበሰብ ታክስና ግብር የተንደላቀቀ ኑሮ እንዲኖሩ ዕድሉ የተመቻቸላቸው መሰል ሹመኞች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ምን ቢደረግ እንደሚሻል ግራ የሚያጋባ ነው:: ሲመረጡና ሲሾሙ “በድመት ባህርይ በመቅለስለስ” መሃላ ይፈጽማሉ:: በወንበራቸው ላይ ተረጋግተው መቀመጣቸውን ሲያረጋግጡም “የነብርን ባህርይ ተውሰው” እንዳሻቸው የተገልጋዩን ስሜትና ቅስም ለመስበር ይበረታሉ:: ምን ይሉት ተቃርኖ ነው?
የሥልጣናቸው ጀንበር ስትጠልቅ ተራ ሰው ሆነው በተራ ዜጎች መሃል እንደሚኖሩ የሀገሬ ባለሥልጣናት ስለምን ይሆን እውነቱን ሊረዱ ያልቻሉት? ሰሞኑን ልደቱን ያከበርንለት ክርስቶስ እንኳን ራሱ አምላክ ሆኖ ሳለ “ቀን ሳለ አብ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” (ዮሐንስ 9፡4) በማለት የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም መጨከኑን አረጋግጦልናል::
እድልና ጊዜ በሥልጣን ወንበር ላይ ያስቀመጣቸው ሹመኞች ላከበራቸው ሕዝብ ዋጋ ሰጥተው ከመከበርና የመፍትሔ ሰው ከመሆን ይልቅ ስለምን የብሶተኞችን እምባ ለመጥገብ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ፣ ስለምንስ ምድር ጠበበን እንደሚሉና ከራሳቸው የምቾት ቀጣና ወጥተው ለሕሊናቸውና ለገቡት ቃል ኪዳን እንደማይኖሩ ማሰቡ በራሱ ሌላ ሃሳብ ላይ ይጥላል::
ማንም ሰው መሽቶ በጠባ ቁጥር የትዝታ ምርት ማዝመሩና የታሪክ አሻራ እያተመ ማለፉ እርግጥ ነው:: በተለየ ሁኔታ ግን ሕዝብን ለማገልገል አደራ የተቀበለ የመንግሥት ሹመኛ ትዝታውም ሆነ ታሪኩ እንደ ማንኛውም ዜጋ በነበር ታስቦ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን “ተራ ዜጋ” ሆኖ የሚኖርበት አይቀሬ ቀን ሲመጣ በአገልግሎት ዘመኑ የፈጸማቸው ዶሴዎች በግላጭ እንደሚነበቡ ሊያስታውስ ይገባል:: በጎ ተግባራት የፈጸመ ከሆነ በአርአያ ሰብነት መዘከሩ እንዳለ ሆኖ ኃላፊነቱን ለራሱ ጥቅም በማድረግ ዘመኑን ፈጅቶ ከሆነም ውሎ አድሮ መዘዝ እንደሚመዘዝ ማወቁ ብልህነት ነው::
“ሪፎርም” የሚሉት ቋንቋ በሀገራችን መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ቃል ብቻ ሳይሆን ባህል ወደመሆን ደረጃ የተሸጋገረ ይመስላል:: “ኃላፊውን ለማነጋገር ፈልጌ ነበር?” ተብሎ ሲጠየቅ “ሪፎርም ላይ ስለሆኑ ባለጉዳይ አያነጋግሩም” መባል በፋሽንነት ተገልጋይን የማባረሪያ ብልሃት ከሆነ ሰነባብቷል:: ቀደም ሲል የነበረውን “ስብሰባ ላይ ናቸው” ሰበብም ሙሉ ለሙሉ የተካ ይመስላል::
“ክቡር/ክብርት አከሌ” እያሰኙ በጠረጴዛቸው ላይ ስማቸውን በጉልህ ከመጻፍ ይልቅ በተግባራቸው ተከብረው፣ በአገልግሎታቸው አንቱ ተሰኝተው ቢያልፉ ክብርም ሞገስም ይሆንላቸዋል:: ልብ እንበል! የማናችንም ትዝታና ታሪክ እንደ ጥላችን ከኋላ እየተከተለ እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ይጓዛል እንጂ፤ ተመለስ ብለን በመገሰጽ ልናርቀው አንችልም:: ሰላም ይሁን!
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም