በአለማችን በቀን 5 ትሪሊየን የፕላስቲክ ከረጢቶች አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይደረጋል። ልብ በሉ አንግዲህ እነዚህ ከረጢቶች ናቸው ። ኢንዲቲቪ የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳመለከተው፤ እአአ ከ1950ዎቹ ወዲህ ብቻ በአለም 8ነጥብ 3 ቢሊየን ቶን ፕላስቲክ ተመርቷል።
ፕላስቲክ ከረጢቶቹ አንዴ አገልግሎት ከሰጡ በሁዋላ የሚጣሉ ናቸው። በቀላሉ የማይበሰብሱ በመሆናቸው ለብዙ አመታት አካባቢን ለአደጋ ሲያጋልጡ ይኖራሉ። ለእዚህም ነው አለማችን በፕላስቲክ ውጤቶች ለስጋት ተዳርጋለች የሚባለው። ችግሩ ከስጋትም ያለፈና በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ።
እንስሳት ከምግብ ጋር እየወሰዷቸው ለሞት እስከ መዳረግ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል። የባህር እንስሳት ሳይቀሩ የችግሩ ሰለባዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በቀጣይም በውቂያኖሶች ውስጥ የሚገኙ የፕላስቲክ ውጤቶች ብዛት ከአሳዎቹ ሊበልጥ አንደሚችል ስጋት ተፈጥሯል።
ሀገሮች የፕላስቲክ ከረጢቶችን በተለይም ስሶቹን መጠቀም ለማቆም እየወሰኑ ህጎች እስከ ማዘጋጀት ቢደርሱም ተግባራዊነት ላይ ግን የሉም። ዛሬም ስስ ፌስታሎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ቀጥለዋል። በሚፈለገው ልክ እየተሰራበት አይ ደለም እንጂ አገልግሎት የሰጡ ፕላስቲኮች የሚወገዱበትን መላም እያፈላለጉ ናቸው። ይህም ቢሆን በሚፈለገው ልክ እየተሰራበት አይደለም። አንዳንዶች ደግሞ የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚተኩ ሌሎች ከአካባቢ ጋር የሚስማሙ ማሸጊያዎችን መጠቀም ውስጥ እየገቡ ናቸው ።
ሰሞኑን ከወደ ታይላንድ የወጣ ዘገባ አንድ የምስራች ይዞ ብቅ ብሏል። በታይላንድ የሚገኝ በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት አንድ ግዙፍ ሱፐር ማርኬት የፕላስቲክ ከረጢቶችን በሙዝ ቅጠል
መተካት ጀምሯል። አለም ለአረንጓዴ ልማት ርብርብ እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ በቺንግ ማይ የሚገኝ ሱፐር ማርኬት የሙዝ ቅጠልን ለፕላስቲክ ከረጢቶች ምትክ አርጎ በማቅረብ ላደረገው ፈጠራም ተሸላሚ እስከ መሆን ደርሷል።
ሱፐር ማርኬቱ በፕላስቲክ ከረጢቶች እያሸገ ለገበያ ያቀርባቸው የነበሩ የአትክልት ምርቶችን በሙዝ ቅጠል እየጠቀለለ ማቅረብ ጀምሯል። ይህም ተግባሩ ለፌስ ቡክ ምስጋና ይግባውና በአለም እየናኘ በመምጣቱም እውቅና ተችሮታል።
ይህ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ ዘይቤ በተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች ዘንድም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሙዝ ቅጠል እየጠቀለለ ለገበያ ያቀረባቸው የፎሶሊያና የመሳሰሉት አትክልቶች ምስል በፌስ ቡክ ከተለቀቀ አንስቶም ከ17 ሺ በላይ በሚሆኑ ወገኖች ታይቷል። በእዚህም ከ600 በላይ ገራሚ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ሱፐር ማርኬቱ ደንበኞቹ በሙዝ ቅጠል የተጠቀለሉ አትክልቶችን እንዲገዙ ከማድረግ ጎን ለጎን የጨርቅ ከረጢቶችን በውሰት ወይም በሽያጭ እያቀረበም ይገኛል።
የሱፐር ማርኬቱ ግኝት ለሀገራችንም ትልቅ ዜና ነው። በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ እኩል ነው ካላልን በቀር ሀገራችን ከሙዝም ቅጠልም በላይ ለተባለው አገልግሎት ሊውል የሚችል ሰፊ የእንሰት /ኮባ/ ሀብት አላት።
በሀገራችን ጫት ለመጠቅለል ብቻ የሚ ያገለግለው የእንሰት ወይም የኮባ ቅጠል በቀጣይ ለአትክልቶች መጠቅለያ ሊውል የሚችልበት እድል መኖሩን ሀገር ቢሰማው ቢጠቀምበት መልካም ነው።
በአትክልት ተራችን ጎመን፣ ፎሶሊያ እና የመሳሰሉትን አትክልቶች በኮባ ቅጠል በመጠቅለል መሸጥ እንዲጀመር ቢደረግ የፕላስቲክ ውጤቶች ለእዚህ አገልግሎት የሚውሉበትን ሁኔታ ማስቀረት ወይም መቀነስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011
በኃይሉ ሣህለድንግል