አንዳንዴ ‹‹ማር አይጥምሽ›› የሚባሉ አይነት ሰዎች ያጋጥማሉ። ሁሉንም ነገር የሚቃወሙ ፤ ሁሉንም ነገር የሚያንቋሽሹ፤ ሁሉንም ነገር የሚያጣጥሉ ሰዎች ያጋጥማሉ። እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ታዲያ ልብ ብሎ ላያቸው፣ ለተከታተላቸው ወይም ቆየት ያለ ባህሪያቸውን ለመረመረ አንድ እውነታን ያገኛል። ስራ የማይሰሩ፤ ጊዜያቸውን በወሬ እና በእኔ ብቻ አውቃለሁ የሚያሳልፉ ናቸው። ባዶ ጉራ እንደምንለው አይነት ወሬያቸው ሁሉ ከጠለቀ እውቀት የማይቀዳ ባዶ ጉራ ነው። አዋዋላቸውም ከስራተኛ ሰፈር ሳይሆን ሰራተኛን ከሚያብጠለጥሉ፣ የተሰራውን ከሚያናንቁ፣ አድመኝነትን ከሚያጠናክሩ ተርታ የሆኑ፤ ከስራስ አኳያ ከተባለ ምንም የማይሰሩ ናቸው።
ብቻ ውሏቸውን ከእነእከሌ ጋር ከእነ እገሌ ተርታ በማለት ራሳቸውን በሰራተኛ ተርታ የሚያሰልፉ ታዋቂ ነን ባዮች ናቸው። ከመስራት ይልቅ የማውራት አባዜ የተጠናወታቸው። ስለሀገር ሲሏቸው ስለመንደር የሚያነሱ። ስለማህበረሰብ ሳይሆን ስለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚያሳስባቸው ናቸው። እኔ ብቻ ልታወቅ፣ እኔ ብቻ …እኔ ብቻ ባይ ናቸው። ይሄው ለእናንተ ሲባሉ ደግሞ ሜዳው ዳገት የሚሆንባቸው፤ ተራራ ግፉ ተባልን ብለው የሚጮኹ የወሬ ጀግኖች ናቸው።
እኔ ምን ልስራ ? ምን ይጠበቅብኛል? ብለው ራሳቸውን አይጠይቁም። ሀላፊነታቸውን አይወጡም። ሆኖም ግን ሳይሰሩ በወሬ ብቻ መብለጥን ያልማሉ። መስራት እያላባቸው ባለመስራታቸው፤ እውቀት፣ ጉልበትና ጊዜያቸውን ባለመጠቀማቸው ደግሞ ምንም የጥፋተኝነትና የበደለኝነት ስሜት አይሰማቸውም። የእነዚህ አይነቶቹ ስራ ጠሎቸ፣ ወሬ ወዳዶች ታዲያ የማያውቁትን ወይም የማይመለከታቸውን ፖለቲካ ገብተው መተንተን፤ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሲነሳ አውቃለሁ ብሎ መፈትፈት ይሆናል ተግባራቸው።
በማህበራዊ ጉዳዩም አለሁ ባይ ደላላ መሳዮች ናቸው። የሆነ አጋጣሚ ሲያገኙ የመንግስትን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሳይቀር ማንሳት መጣል አንዱ ስራቸው ነው። የሁሉም ነገር አዋቂ የባለስልጣናት ጓደኛ ብቻ ሁሉም ለመሆን ይሞክራሉ። ከትንሹ የእድር አመራር እስከ ባለስልጣን የቅርብ ሰው አማካሪ ቤተሰብ መሆናቸውን አግዝፈው በመናገር ራሳቸውን ይቆልላሉ። ግን ደግሞ የሚወጣቸው አንድም ቁም ነገር አይኖረም። አንድም ተጠቃሽ የሚያደርጋቸውን አበርክቶ ለሀገር እና ለማህበረሰበ ጠብ ሲያደርጉ አይታዩም። እንዳው ብቻ አለሁ … አለሁ…ነው ጨዋታቸው ሁሉ።
እዚህ ቦታ ላይ መንግስት የጀመረውን ፕሮጀክት አየህው አዎ! አውቀዋለሁ። ከጥንስሱ እስከመጨረሻው እኛም አለንበት። እንትን የሚያደርገው እከሌ፤ እንትኑን ደግሞ እከሊት… ብቻ ውስጥ አዋቂነቱ የራስን ቤት እንኳን የዚህን ያህል የሚያውቅ የቤት እመቤት ከሚዘረዝረው በላይ ማወቁን ለማስረዳት ይሞክራል። እመኑኝ ተቀበሉኝ ነው ጨዋታው ሁሉ።
በዚህም ብቻ አይበቃም። አልፎ አልፎም ቢሆን በዜና ፣ በማህበራዊ ሚዲያው፣ በቲክ ቶክ በቴሌግራም፣ በኢንስተግራም …ከመንደር በወሬ የቀራረሟትን እያነሳሱም ይሄም ይህም እኮ ብሎ ጨዋታውን ለማድመቅ የሁሉም ነገር አዋቂ ነኝ ባይነቱን ሁሉም እንዲሰማው ያክል እዚህም እዚያም መርገጡን ይቀጥላል። በዚህም አያበቃም። አንዳንዴ አንዱን፣ ሌላ ጊዜ ሌላውን እያነሳ ይሄ ምን ያደርጋል ብሎ የተሰሩ የሀገር ፈርጦችን፣ የሀገር መታወቂያዎች፣ ለሀገር ትልቅ ገቢ የሚሆኑትን፣ ህዝብን የሚጠቅሙ ለህዝብ የዋሉ ብቻ ከትንሽ እስከ ትልቁ ይነሳል በመሀይም እውቀት ይተነተናል፣ ጉዳዩ የሀገርና ህዝብ ጥቅም መሆኑ ተዘንግቶ የፖለቲካ ጉዳይ ይደረጋል።
ይህም ሆነ ያ የሚሰሩ ስራዎች ፤ የሚለሙ ልማቶች ከጅምሩ እስከ ዘለቄታው ማንን ነው የሚጠቅመው ብሎ ጥያቄ ማንሳት ይገባል። እንደምሳሌ የተነሳውን እኔም ላንሳው ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ነወይ ለዚች ሀገር ቅድሚያ የሚያስፈልገው? ››ሲል ጥያቄ አነሳ አንዱ ወዳጄ በጨዋታ መሀል ገብቶ ። ከአንተ ጋር ክርክር አያስፈልግም። አሁን ለክርክር ጊዜው አይደለም አልኩ። ፓርኮቹ ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ በአይኑ አይቶ እውነታውን እንዲያረጋግጥ ነበር። ግን ደግሞ አላስቻለኝም እና የእኔ ያልኩትን ሀሳብ አነሳሁ። በሀሳቡ መስማት ወይም አለማስማማት ግን መብቱ የባለቤቱ ነው። አንድ ነገር ግን ትክክለኛውን እውነት ማወቅ ነው። ይሄ እንግዲህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ወቅት የነበረ ጨዋታ ነው። ‹‹አሁን ግንባታው ተጀምሮ በተለያየ ቦታ እየተገነባ ነው። በዚህ ስራ ላይ መቼም የሚሳተፉት የውጭ ሀገር ዜጎች አይደሉም፤ ስራ አጥ በዛ ፣ ወጣቱ ስራ አጣ ያልናቸው ዜጎቻችን ናቸው። እነዚህ ሰዎች ስራ አላገኙም?›› ጥያቄውን በጥያቄ ለመመለስ ያክል ነው። ‹‹ከዛም ፓርኮቹ ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ የሚከፈቱት በአብዛኛው ፋብሪካዎች ናቸው። የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ… በዚህ ስራ ላይ ሊቀጠር የሚችለው ማን ነው? ከተማረ እስካልተማረው። ወደ ፓርኮቹ የሚገቡት ባለሀብቶች ከሀገርም ከውጭ ናቸው። የእነዚህ የኢንቨስትመንቱ መስፋፋት ዶላር አያመጣም፣ የእነዚህ መምጣት የውጭ ንግዱን አያስፋፋም። የእነዚህ መምጣት የቱሪስት ፍሰቱን አያበዛም። ሲጠቃለል የሀገር እድገትን አያመጣም። … እና ለምን እንቃወማለን። ›› ድሀ የሚለውን መታወቂያ አያስቀይር ይሆን ብቻ እኔ ደግ ደግ ነገር ይታየኛል አይኔን ገለጥ ሳደርግ። አይኑን ለጨፈነ ግን ያው ጨለማ ነው። ድቅድቅ ጨለማ። ሊነጋጋ ሲል የሚታይ ጨለማ በቃ ይሄ ነው። በነጩ ትልቅ ወረቀት ላይ ጥቁራ ነጥብ ናት የሚታየው። በቃ ይሄ ብቻ ነው የሚታየው።
መቃወም ለሚፈልግ ሁሌም ደህና ነገር አይታየውም፤ ከእነተግባሩ ስሙም መቃወም አይደል። በቃ በውስጥም በውጭም ሆኖ መቃወም ነው። ቅድም እንዳነሳኋቸው ማር አይጥምሽ። መሰረቱ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ተበለጥኩ የሚል ተንኮለኛ ሁሉንም ይቃወማል። ግለኛም፣ ብሔረተኛም ስለሚሆን ምንም ነገር አይጥመውም። ቅና ያለው በእናቱ ይቀናል እንደሚባለው። በእናት ሀገሩ ላይ ይቀናል፤ በልማቱ ይመቀኛል። ሌላውም ይሄንን አባዜ እንዲወርስ ይገፋፋል። የተቃውሞ ሀሳብ ለማሰባሰብ ይሞክራለ። እንዲህ አይነቱ ትንሽ ጊዜ ደጋፊ ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ጆሮ የሚሰጠው አግኝቶ ይሆናል። አጫፋሪዎች ወሬ አራጋቢዎች ከብበውት ይሆናል። ግን አይዘልቅም። ተጠቃሚው ተገልጋዩም ራሳችን ለራሳችን መሆኑ ሲያረጋግጥ ሁሉም ይከሽፋል። ጭንቅላት ያለው ያገናዘበ ይነጠላል። እውነታውን ደግፎ ይቆማል። እንዲህ አይነቱን ማር አይጥምሽ ማሸነፍ የሚቻለው እንዳው እመኑኝ በአርባ አራቱ ታቦት፤ በፈጣሪ ብለህ በልመና አይደለም፤ ደግሞም ጦር ሰብቆ በማስፈራራት አይሆንም፤ መሆን ያለበት ከፍ ብሎ በመብረር ብቻ ነው።
እንዲህ ያለው ሰው ወይም ቡድን ሌላ ማሸነፊያ ያለውን ሀሳብ ማንሳቱ አይቀርም። ‹‹እዚህች ሀገር የከፋ ችግር የለም ?›› ሲል ሌላ ማሳመኛ ሀሳብ ያክላል። ችግርማ ሞልቷል። እሱን ማን ይክዳል እየኖርነው አይደል ፤ ተሸክመነዋል አይደል፤ ችግርማ በፊትም ነበር፤ አሁንም አለ፤ ወደፊትም ይኖራል። የሰለጠኑ የምንላቸው፤ እየረዱን ነው የእንጀራ አባቶቻችን ናቸው የምንላቸው ያደጉት ሀገራትም ችግር አለ። የችግሩ መጠንና አይነት ይለያይ እንደሆነ እንጂ እዛም እዚህም ችግር አለ። መቼ ችግር የለም ተባለ። የተባለው እኮ ከችግር የምንወጣው ችግሩን በመናገር ብቻ ሳይሆን ችግሩን ቀስ በቀስ የሚቀርፍ ስራ በመስራት ነው።
የኮቪድ 19 ወረርሽን በዓለም ላይ በተከሰተ ወቅት የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚውን መሸከም አልቻልንም ብለው ሰራተኛ ሲቀነሱ አይተናል። ሀብት አለን ብለው ሁሉንም ዜጋቻቸውን መሸከም አልቻሉም። እስከዛሬ ድረስ የኮቪድ ጠባሳው ከኢኮኖሚያቸው ላይ አልጠፋም። የኑሮ ውድነቱ አልረገበም። እናም እኛ ከሌላው ዓለም የተለየን አይደለንም። ችግር ሊኖር ይችላል። የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ የሲሚንቶና ብረት መጥፋትና መወደድ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት አለ። ብዙ ብዙ ችግር አለ። ችግርማ ሞልቷል። አሁን ማሰብ ያለብን የሚገባን ከችግር የሚያወጣንን መንገድ ነው፤ ከችግር የሚያወጣንን ጥበብ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚሰራውን ንቆና አናንቆ በመናገር አይደለም። ከተቻለ ሰርቶ ማሳየት ነው። ለሀገር ልማት ተባባሪ በመሆን ነው። ካልሆነ አርፎ መቀመጥ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን አደናቃፊ መሆን እንቅፋቱ ራስንም ጠልፎ ይጥላልና ወደ ቀልብ መመለስ ያስፈልጋል።
ይህን ስል ስለ ንስርና ድንቢጥ የሰማሁት ጨዋታ ትዝ አለኝ። በተለይ ጓደኛዬ የንስርን ነገር የየዕለት ምሳሌዋ አድርጋታለች። ‹‹ንስር እኮ ጠንካራ ናት፤ ችግር ሲገጥማት ችግርን የመቋቋም ሀይልና አቋሟ ይገርማል! ብዙ ነገሮችን ትችላለች። ሞተች ሞተች ተብላ እንኳን እባብ አፈር ልሶ እንደሚባለው እሷም ላባዋን አርግፋ እና መንቁሯን አውልቃ በአዲስ ተክታ ትታደሳለች። ንስር እያንዳንዱ ነገሯን በጥንቃቄ ነው የምታራምደው። እይታዋ ሁሉ ለየት ያለ ነው ፤ ያልታየ ታያለች። ብዙ ጊዜ የንስር አይን ይስጥሽ ሲባል አልሰማሽም ፤ ንስር እይታዋ አስገራሚና አስደናቂ መሆኑን ማሳያ ነው። ግን ደግሞ ያችን ግዙፍ የሆነች ንስርን የምታጠቃት ትንሿ ድንቢጥ መሆኗን አትርሺው፤” ትለኛለች፤ ይሄንንም ስታስረዳኝ “ንስር ክንፍ ውስጥ ድንቢጥ ከገባች ደጋግማ ክንፏን በመምታት ከበረራዋ አስተጓጉላ ከመሬት ትፈጠፍጣታለች። ዋና ደመኛዋ ናት። ገዳዩዋም ናት እናም ድንቢጥ ከክንፏ እንደገባች ካወቀች፤ ንስር ለጠላቷ መውደቂያ የሆነውን ዘዴ መፍጠር ነው። ስለዚህ ድንቢጥ ከከፍታ ላይ ሆና አየር መሳብ አትችልም። መተንፈስ ትቸገራለች። ስለዚህ ንስር የምታደርገው ድንቢጥን አየር ሊያሳጣ በሚችል ከፍታ ላይ መብረር ነው። ያኔ የንስር ጠላት ዱብ ብላ ለሌላ ያሰበችውን ውድቀት ትከናነበዋለች።›› ትለኛለች።
ሀገር ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ላለመቀበል፣ ልማቱን ላለመደገፍ ፤ የሚታዩ ለውጦችን ለመቃወም ለሚፍጨረጨሩ ይሄ ትልቅ ምሳሌ ነው። አሸናፊነት የተጀመረውን ልማት ከፍ አድርጎ መስራት ነው። ከጠላት ከበባ ለመውጣት ለነገ የሚተረፍ አሻራ መተው ነው። መንግስትን ከህዝብ እለያለሁ፤ ህዝብን ከህዝብ አጋጫለሁ።…ብሎ ሌት ተቀን ሲሰራ ሲቃዠ ለሚውለውም የበለጠ ሰርቶ የበለጠ ህዝብን ተጠቃሚ አድርጎ የበለጠ ሀገርን አሳድጎ ማሳየት ነው። ያኔ አይደለም የሚያስተባብረውን ቡድን ራሱም ከስር ይገባል። ወይ እንደ ዲንቢጧ ይፈጠፈጣል።
ለምቀኛ ፣ አላሰራ ላለ አድመኛ ፣ የድሮ ሰዎች እንደሚሉት ‹‹ለቀማኛ ለምቀኛ ›› መድሀኒቱ ከፍ ብሎ መብረር ነው። የሚያነቃ እና የሚያበረታ “ጠላት አያሳጣህ”ን አጠንክሮ፤ ጠላትን ማሸነፊያ ጥበቡ ተላብሶ እንደ ንስር ከፍ ብሎ መብረር የተገባ ነው። ጠላት ጠላትነቱን መቼም አይተውም ከራሱ የተጣላ እንደሚባለው፤ ከራሱ ጋር የተጣላ ሰው በቅቤ አንጨፍጭፈው ቢያበሉት ምነው ቅቤውን አባከኑት አለ ይባላል። ምንም ነገር ቢደረግለት፣ ቢያይ፣ ቢነገረው ማየቱን አያምንም፤ መስማቱን አይቀበለውም። አይጥመውም ወጪውም ብክነት ሆኖ ይታየዋል። እና ለዚህ መድሃኒቱ መንደር ለመንደር ሲተረማመስ፣ ጎጥ ጎጥ ሲል እምነት ምናምን እያለ ቲፎዞ ሲያሰባስበ ባለበት እንደቆመ እንደ ንስር አሞራ ጠላቱን ከጉያው አራግፎ ከፍ ብሎ መብረር ነው።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም