የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ቀኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ህዝብ ነው:: ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው::
ሆኖም ኢትዮጵያውያን በጀግንነት እና በእንግዳ ተቀባይነት የሚታወቁትን ያህል ውስጣዊ ሰላማቸውን በመጠበቅ ረገድ የሚያኮራ ባህልና ታሪክ የላቸውም:: በዘመናቱ የውጭ ወራሪዎችን አሳፍሮ በመመለስ እና ሉአላዊነትን በማስጠበቅ ረገድ ያላቸውን ጥንካሬ ያህል ተረጋግቶ እና ከጦርነት ርቆ የመኖር አኩሪ ገድል የላቸውም::
እንዲያውም የኢትዮጵያውያን ታሪክ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያመዝንበት ታሪክ እንደሆነ በርካታ የታሪክ ምሁራን የሚስማሙበት ሀቅ ነው:: የስልጣኔ አካሄድ ተብሎ የሚታሰበው የፖለቲካ ሥርዓት በራሱ ለኢትዮጵያ ከሰላም ይልቅ ይዞ የመጣው ውስብስብ ችግር የእርስ በእርስ ሽኩቻ ውጤት መሆኑን መናገር ይቻላል::
በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ተጀመረ ተብሎ ከሚታሰብበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ ከሀገር ይልቅ የራስን ጥቅም፤ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ ከሀገር ህልውና የፓርቲ ህልውናን ማስቀደም ላይ ትኩረት ያደርጋል:: ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ላልተገባ እሰጥ እገባና ግጭት አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትዘልቅ አድርጓታል::
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው:: ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው:: አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው::
በጋራ ሠርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን በመፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ የፖለቲካ ታሪካችን ነው::
ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህልም ስለሌለን ችግሮች ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የሴረኝነት መነሻ ይሆናሉ:: ቀላል የሚባሉ ችግሮች ሳይፈቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወሳሰቡ ስለሚሄዱ መፍትሄ ለመስጠት እንኳን አዳጋች እስከመሆን ይደርሳሉ::
ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ሶስት አመታት አስቆጥሯል:: በእነዚህ ሶስት ዓመታት እንደ ሀገር ችግሮቻችንን በምክክር ለመፍታት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል:: በአብዛኞቹ ክልሎች የተሳኩ ውይይቶች ተካሂደዋል:: አንዳንዶቹ ውይይቶች የሰላም መንፈስ አስፍነዋል:: መንግሥት በወሰዳቸው ተጨባጭ እርምጃዎችም ወደ ሰላም ፊታቸውን ያዞሩ ታጣቂዎች በርካቶች ናቸው::
ከእነዚህ የሰላም ጥረቶችና ውጤቶች አንዱ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ያደረጉት የሰላም ስምምነት ተጠቃሽ ነው:: ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ የሰላም እጦት እፎይታ ከመስጠቱም በሻገር በአሁኑ ወቅት በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢ የተሻለ ሰላም መጥቷል:: ቀደምሲል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከመንግሥት ጋር በነበረው ቅራኔ በኦሮሚያ አለፍ ሲልም እንደሀገር በርካታ ቀውሶች ደርሰዋል:: በርካታ ሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ አካል ጎድሏል፤ንብረት ወድሟል:: ሆኖም በስተመጨረሻም በዚህ መልኩ ሰላም መውረዱ ለብዙዎቻችን እፎይታ የሰጠ ነው::
በሌላም በኩል ራሱን “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” ብሎ የሚጠራው ኃይል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት መስማማቱን ገልጽዋል። በሀገር ሽማግሌዎች አገናኝነት በተደረገው ውይይት “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት ተስማምቷል።
በቀጣይም በሥራቸው ያሉ እስከ 250 የሚደርሱ አባሎቻቸውን ይዘው መንግሥት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንደሚመለሱም መግባባት ላይ ተደርሷል። ታጣቂዎቹ ከሕዝባቸው ጋር በመቀላቀል ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከቀበሌ መሪዎች እና ከመንግሥት አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብም ታጣቂዎችን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት በልዩ ልዩ መንገድ ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልፀዋል።
እነዚህ የሰላም ጥረቶች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳዩ ናቸው:: መንግሥትም ከየትኛውም ወገን ጋር ቢሆን ሰላም ለማውረድ ያለውን ቁርጠኝነት ያመላከቱ ናቸው::
ሆኖም አሁንም ቢሆን የተሳሳተ አማራጭ ወስደው በየጫካው የሚገኙ ቡድኖች አሉ:: በተለይም በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ መጓደል እየደረሰ ያለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው:: በአማራ ክልል ያለው ግጭት ከተቀሰቀሰ ሁለት አመታት ተጠግተዋል:: በእነዚህ ሁለት ዓመታት በርካታ የመሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተስተጓጉለዋል፤ ሞት፤የአካል መጉደል፤ስደት እና መፈናቀል ተበራክቷል::
በጸጥታ መጓደል ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው:: በተያዘው በጀት ዓመት 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም መሄድ የቻሉት ከ2 ነጥን 5 ሚሊዮን የዘለለ አይደለም:: 4 ነጥብ 5 የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል:: ይህ ጉዳይ ያሳሰበው የክልሉ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር በዚህ ከቀጠለ “ነገ የአማራ እናት ከዩኒቨርሲቲ የምታስመርቀው ልጅ አይኖራትም” ሲል የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል::
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በሰላም ዕጦት ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች ወድመዋል:: እነዚህን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባትም 112 ቢሊዮን ብር እንደሚስፈልግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል:: ቢሮው እንዳስቀመጠውም በክልሉ በተካሄዱ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ሳቢያ ለአብነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 ትምህርት ቤቶች በላይ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል:: በግጭቱ 3 ሺህ 500 የአንደኛ ደረጃ እና 225 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባለመከፈታቸው ተማሪ አልባ ሆነዋል::
በተመሳሳይም የጤናው ዘርፍ በርካታ ችግሮች ተደቅነውበታል:: እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት በብዙ ቦታዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ለማግኘት ህሙማን ወደ ጤና ተቋማት መሄድ አለመቻልን ጨምሮ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ግብዓት እጥረት እንዲሁም የጤና ተቋማት ሥራ ማቆም እየተስተዋለ ነው። የጠፉ በሽታዎች ጭምር እንደገና ማቆጥቆጥ ጀምረዋል::
በክልሉ ያለው ግጭት በእናቶች ጤና አገልግሎት ላይ ጫና ማሳደሩንም ገለጸው፤ የጤና ክትትል ማድረግ ከነበረባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ውስጥ 36 በመቶ የሚኾኑት ከክትትል ውጭ መሆናቸው ተገልጿል:: በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ ካለባቸው እናቶች ውስጥም 44 በመቶ የሚኾኑ ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ በቤት ውስጥ እንዲወልዱ ተገድደዋል ነው ያሉት። ይህም በእናቶች ላይ ዘርፈ ብዙ የጤና ምስቅልቅል እያስከተለ ስለመኾኑ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል::
ግጭቱ በሕጻናት ጤና ላይም አደጋ መደቀኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በክልሉ 14 በመቶ የሚኾኑ ሕጻናት የጀመሩትን ተከታታይ ክትባት እንዲያቋርጡ ተደርገዋል ብለዋል። ይህም የሕጻናትን እና የጨቅላ ሕጻናትን ጤና በእጅጉ የሚጎዳ ስለመኾኑም ቢሮው ተናግሯል።
በክልሉ ያለው ጦርነት የጤና ሥርዓቱን ፈትኗል የሚለው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ፤ የህጻናት ክትባት ከ60 በመቶ እንደማይሻገር እና ክትባትን ጨምሮ የኤችአይቪ፣ የቲቢ፣ የወባ እና የሌሎችም በሽታዎች መድኃኒቶች አቅርቦት እየተቋረጡ መሆናቸውን ከጥቂት ወራት በፊት ለክልሉ የመገናኛ ብዙኃን መግለጹ የሚታወስ ነው::
በአጠቃላይ ግጭት በሚታይባቸው አካባ ቢዎች ያለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው:: የዜጎች ወጥቶ የመግባት ዕድል ጠቧል፤በህይወት የመኖር መብት ተገድቧል፤ ነግዶ ቤተሰብ ማስተዳደር፤አርሶ ቀለብ መቋጠር ዘበት ሆኗል:: በምትኩም ሞት፤አካል መጉደል፤መፈናቀል፤ስደት እና ዋይታ ነግሷል::
ስለዚህም ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ታጣቂዎች ለሕዝቡ አንድ ውለታ ሊውሉለት ይገባል:: ከጦርነት ይልቅ ሰላምን በመምረጥ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ሊክሱ ይገባል:: በረባ ባልረባው በሚነሳ ጦርነት እና ግጭት እየተሰቃየ ያለውን ሕዝብም መታደግ እና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ይገባል::
ከሰላም እንጂ ከጦርነት የሚገኝ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ሁሉም አካላት ፊታቸውን ወደ ሰላም ማዞር ይጠበቅባቸዋል:: ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት አንድነት እና ወንድማማችነት ነው:: ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል በጦርነት የቆሰለች ሀገር በመሆኗ ከዚህ በላይ ጦርነት እና ግጭትን የሚሸከም ትከሻ የላትም::
እንደ ሀገር ምክክር ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ መሆን ሲገባው አሁንም ጥያቄዎችን በመሳሪያ ኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸው ሁኔታውን ግራ አጋቢ ያደርዋል:: ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው የኃይማኖት አባቶች በየጫካው የሚገኙ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም ጎዳና እንዲመለሱ እየመከሩ ነው:: ‹‹የግጭት እና የጦርነት አካሄድ ይብቃ ›› እያሉ እየተማጸኑ ነው::
ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል:: ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል:: አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው::
በኢትዮጵያ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሀሳብ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህን ችግሮችና የሀሳብ ልዩነቶች ለመፍታት የሚካሄድበት መንገድ ደግሞ የኃይል አመራጭ በመሆኑ እንደ ሀገር ብዙ ነገር አጥተናል እያጣንም እንገኛለን።
ከዚህ እሽክርክሪት ለመውጣት እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በአጀንዳ መልክ በመለየት እነርሱ ላይ መመካከር ተመካክሮ ወደ መግባባት መድረስ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሀገሪቱ እንደ ሀገር አሁን ካለችበት ችግር ተላቃ ወደፊት መራመድ የምትችለው።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች በአንድ በኩል የአሳታፊነትና አካታችነት ችግር ስለነበረባቸው በሌላ በኩል ደግሞ በተወሰኑ ሥልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት የሚፈለገውንና መምጣት የነበረባቸውን ውጤት ሳያመጡ ቀርተዋል። ስለዚህም ያለው አማራጭ አዲሱን መንገድ መጀመር ብቻ ነው:: ይህም መንገድ ምክክር እና ውይይት ነው::
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም