በአንድ አገር የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እድገት ሳይመጣጠን ሲቀር የሕዝብ ቁጥር ለአገር ሁለንተናዊ ብልጽግና አቅም ከመሆን ይልቅ በዚያ አገር አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አውዶች ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች እና በዘርፉ ላይ አተኩረው የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ።
መረጃዎቹ እንደሚያመላክቱት፤ በአንድ አገር ውስጥ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ያልተመጣጠነ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ካለ፤ በዚያ አገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማድረግ ለእድገት የሚደረጉ ግስጋሴዎችን ይገታል።
ምክንያቱም ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ያልተጣጣመ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ሲኖር በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ለኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት የሚያስፈልጉ ሀብቶችን በሟሟጠጥ ድህነት ሥር እንዲሰድ ያደርጋል። በዚህም ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል የሚደረገው ጥረት የተፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት ይሆናል። ችግሩን ለማቃለል የነፍስ ወከፍ ገቢን ከፍ የሚያደርገውን አጠቃላይ ምርታማነት በእጅጉ ለማሣደግ ቢሞክር እንኳን፤ የሕዝብ ቁጥር ካልተመጣጠነ በስተቀር የታለመውን ዕድገት ማምጣት አያስችልም፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችንም በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ እንቅፋት ይሆናል።
ይህ የሚሆነው ደግሞ ፈጣን የሆነ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ሂደት ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና፣ ከሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ከሌሎችም ሴክተሮች ጋር ጠንካራ ቁርኝት ስላለው ነው። ይህ ቁርኝት ደግሞ አንዱ በአንዱ ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖዎች እንዲኖሩት ያደርጋል። ምክንያቱም የሕዝብ ሥርጭት፣ ቁጥር፣ የዕድሜ እና የጾታ ስብጥር እንዲሁም ተዛማጅ ጉዳዮች በማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች አቅርቦቶች ላይ የሚኖረው ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለ። ይሄን ያላገናዘበ የትምህርት፣ የጤናም ሆነ ሌሎች የልማት ስራዎችና እንቅስቃሴዎች ግባቸውን ሊመቱ አይችሉም። በመሆኑም ማንኛውም የልማት ዕቅድ ሲታቀድ የሕዝብ ቁጥርን (የሥነ-ሕዝብ ሁኔታውን) ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል።
በኢትዮጵያም ይሄው የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል። ዛሬ ላይ ከ110 ሚሊዬን መሻገሩ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ታዲያ፤ እድገቱን የሚመጥን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ስሪቶች አብረውት ካላደጉ የሚኖረው አሉታዊ ጫና አጠቃላይ በአገር ሰላምና ደህንነት ላይ ጭምር የሚገለጽ ነው የሚሆነው።
ይሁን እንጂ የሕዝቡን ቁጥር እድገት ወይም አጠቃላይ የሥነ-ሕዝብ አውዱን ተገንዝቦ ይሄንን የመጠነ ስራ መስራት ከተቻለ ደግሞ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለአገር ሁለንተናዊ እድገት አቅም እንጂ ችግር ሊሆን አይችልም። ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት “ሕዝባችን ዐቅማችን” በሚል ርዕስ የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ መካሄዱም ለዚሁ ነው።
በመድረኩ የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን፤ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በከተሞች አካባቢ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮችን ይፈጠራል የሚለው አንዱ ነው። ይሄም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋለውን ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰትም ሆነ በከተሞች በሚኖረው ህዝብ በራሱ የሚፈጠር የሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት፤ ከተሞች ለህዝቦች በሚያደርሱት ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ ጫና እየፈጠረ ስለመገኘቱ የሚያስረዳ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ከሚፈጠሩ ችግሮች መካከል የሰላምና ጸጥታ ችግር ተጠቃሽ ነው። ምክንያቱም የሕዝብ ቁጥር በጨመረ መጠን እና ይሄንን ተከትሎ የሚፈጠርን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ ጥያቄዎቹ ከፍ ብለው መነሳታቸውና በኋላም ወደ ፀጥታ ችግርነት ማደጋቸው አይቀርም። ሆኖም የሕዝብ ቁጥር ጭማሪው ከፈተናዎቹ ባሻገር የራሱ እድሎች ይዞ የሚመጣ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።
በተለይ ችግሩን የመጠነ ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን ለመፍጠር እድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለጸው። ከዚህም በላይ በእውቀት፣ በክህሎትና ሥነምግባር የታነጸ፣ ጤንነቱና አካላዊ ብቃቱ የተጠበቀ ዜጋን ማፍረት ከተቻለ፤ በአገር ሁለንተናዊ የእድገት ግስጋሴ ውስጥ የራሱን አሻራ የሚያኖር አምራች ዜጋ ባለቤት የሚያደርግም ነው። ሆኖም የጸጥታ ስጋቶችን ከመቀነስ አኳያም የሰላም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የሚገባ ሲሆን፤ የሲቪክ ባህልን በማሳደግ በስነምግባር የታነፀ ትውልድ መፍጠርም እንደሚገባም በመድረኩ የተሳተፉ ምሑራን አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሕዝብ ቁጥር በተገቢው መልኩ መያዝና አቅም እንዲሆን ማድረግ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን መንግስት እንደሚገነዘብ ያስረዱ ሲሆን፤ ይሄን መነሻ በማድረግም የሕዝብ ቁጥር አቅም መሆን እንዲችል የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ዘርፎች በቅንጅት መስራት ስላለባቸው የፖሊሲ ማጣጣም አሰራር መዘጋጀቱን፤ እንዲሁም በትምህርት እና ጤና ፖሊሲዎችን የማናበብ ስራም መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ይሄ የሚኒስትሯ ገለጻና ማብራሪያም ሆነ የምሑራኑ ምክረ ሃሳብ የሚያስረዳው ታዲያ፤ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ከስጋት ይልቅ አቅም እንዲሆን ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካል በየዘርፉ የሕዝብ ቁጥር መጨመር የሚፈጥረውን ስጋት በመቀነስና ሕዝብን አቅም በማድረግ ሂደቱ ላይ የራሱን ሚና መጫወት ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ጥር 4 /2015