የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስተዳደራዊ በደል የደረሰባቸውን ዜጎች እንባ በማበስ ትክክለኛውን ፍትህ እንዲያገኙ የሚያደርግ ተቋም ነው። ባለፉት ረጅም ዓመታት በደል የደረሰባቸውን የበርካቶችንም እንባ አብሷል። ሆኖም ግን ይሄ በቂ አይደለም፤ ስልጣኑም ጥርስ የሌለው አንበሳ አይነት ነው የሚሉ ቅሬታዎች በብዛት ይደመጣል። ለዛሬ ‹‹የተጠየቅ አምዳችን›› እነዚህንና ሌሎች ሀሳቦችን በማንሳት የተቋሙን አጠቃላይ የስልጣን ደረጃ በመዳሰስ፤ መረጃን ለማይሰጡ ተቋማት እስከምን ድረስ ሄዶ መረጃ ያሰጣል ? የሚሉትን ጭምር በማንሳት ከኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ከሆኑት ከዶክተር እንዳለ ሀይሌ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣንና ኃላፊነት ምንድነው?
ዶክተር እንዳለ:- የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተግባርና ሀላፊነት የሚነሳው ከኢፌዴሪ ህገ መንግስት ነው። ሌላው በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ከእነዚህ ሁለት አዋጆች የሚመነጭ ስልጣንና ተግባራት አሉት። በሁለቱም አዋጆች መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አብዛኛው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የማይገነዘቡት ተቋሙ በህገ መንግስቱ እና ባወጧቸው ህጎች መሰረት መስራታቸውን የመከታተል ስልጣን አለው።
በዚህም መሰረት አስፈፃሚ አካላቱ ባወጧቸው ህጎች የማይገዙ ከሆነ፤ የአስተዳደር በደል ደርሶብናል ሲሉ የመጡ አካላት ካሉ፤ የመፍትሄ ሀሳብ የመስጠት ማለትም ህጉን መቀየር ወይም ማሻሻል ይችላሉ። እኛ ህግ አክብሩ የህግ የበላይነት እንዲከበር ስሩ በማለት አቅጣጫ እናሳያለን። ከዚህም በተጨማሪ አቤቱታ በመመርመር፣ በቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ጥናት በማድረግ ጭምር ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎችን ተቋሙ ይሰራል።
አዲስ ዘመን:- አስተዳደራዊ በደል የደረሰባቸውን ግለሰቦች እንባ በማበስ ተቋሙ ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር እንዳለ:- የመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸውን ህጎች፤ ደንቦችና መመሪያዎች ሰራተኛውም ሆነ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ብሎም ሌሎች ዜጎች በእነዛ ህጎችና ደንቦች ይገዛሉ። ህጉን ያወጣው አካልም በወጣው መመሪያ መሰረት አገልግሎት መስጠት አለበት። ይህ ሳይሆን ተገኝቶ የአስተዳደር በደል ደርሶብናል የሚሉ አካላት ሲመጡ፤ በመመሪያው ላይ የተቀመጠው ህግ ሳይፈፀም ሲቀር አስተዳደራዊ በደል ደርሷል ይባላል። በደል የደረሰበት አካልም በደል ተፈጸመብኝ ሲል አቤቱታውን ይዞ ይቀርባል። ተቋሙም አቤቱታውን መርምሮ የመፍትሄ ሀሳብ ይሰጣል።
የመፍትሄ ሀሳብን መስጠት ብቻ ሳይሆን ጉዳይን መርምሮ እስከመጨረሻ ድረስ ያስፈፅማል። በዚህም የበርካታ አቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳይ ተፈፅሞላቸዋል። አሁን በምንመለከተው የስራ አካሄድ የተለያዩ መሻሻሎች ይታያሉ። ለአብነት ያህል 2014 በጀት አመት ላይ ከመጡት አቤቱታዎች ሰባ አምስት በመቶ ለሚሆኑት የመፍትሄ ሀሳብ ተሰጥቷል። ቀሪው ሀያ አምስት በመቶ ደግሞ በተለያዩ ምክኒያቶች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል።
ይህም ሲባል አንደኛ ከተቋሙ የምርመራ ጥናት የሚነሳ ችግር አለ፤ ሁለተኛ መረጃ በቂ ባለማግኘት ሲሆን ሶሰተኛው በተቋሙና በአቤት ባይ መካከል ስምምነት በሚደረስበት ጊዜ ጉዳዮች ላይፈፀሙ ይችላሉ።
የመፍትሄ የመስጠት አቅማችን ሰባ አምስት በመቶ ደርሷል ሲባል ትልቅ ስኬት ነው፤ ነገር ግን ህብረተሰቡ የሚያነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር ስር የሰደደና ከሙስና በላቀ ደረጃ የሰፋና የከፋ በመሆኑ ስኬቱ እንደስኬት ላይታይ ችሏል። ሁሉንም የመልካም አስተዳደር ችግር ለመድረስም ከችግሩ ስፋት የተነሳም ከባድ እንዲሆን ሆኗል።
ከዚህም በላይ የአስተዳደር በደሎችን የሚያየው የእንባ ጠባቂ ተቋም ብቻ ሳይሆን የፍትህ አካላት፤ ፍርድ ቤቶች፤ የፀጥታ አካላትና የመንግስት ተቋማት የሚመለከቱት ሲሆን በእነዚህ ሁሉ ተከፋፍሎ የሚሰራው መልካም አስተዳደርን የማስፈን ስራ የተቋም ስራ ብቻ አለመሆኑን ህብረተሰቡ ሊረዳው ይገባል።
በአጠቃላይ ግን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል ደርሶብናል ብለው ለቀረቡ አቤት ባዮች እንባቸውን የማበስ ተግባር ያከናውናል። ከዚህም በተጨማሪ ህገ መንግስቱ ተጥሶ ሲገኝ አስፈፃሚ አካላትን በሚያነቃ መልኩ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ጥቆማ ይሰጣል።
አዲስ ዘመን:- በተለያዩ ጊዜዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ጠንካራ መግለጫዎችን ታወጣላችሁ። ይህ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ምን ያህል አስተዋፅኦ አድርጓል?
ዶክተር እንዳለ:- መግለጫዎች የሚወጡት ወይም የሚተላለፉት ችግሮችን ለመቅረፍ ብቻ አይደለም። ችግሮችን ለመቅረፍ አንዱ መሳሪያ ሊሆን ይችላል። ከዛ ባለፈ ግን የመንግስት ውሳኔ ወይም ድርጊት ከህገ መንግስቱ እና ከህግ አንጻር ትክክል አለመሆኑን የተቋማችን አቋም ማሳወቅ ነው።
ያወጣችሁት ህግ፣ ያስተላለፋችሁት ውሳኔ ወይም አጠቃላይ አሰራሮች ከዜጎች ህገ መንግስታዊ መብት ጋር የሚቃረን ነው በሚል እናሳውቃለን።
ሌላው በዴሞክራሲ መርህ መሰረት በአንድ ጉዳይ መንግስት አቋሙን እንዲያሳውቅ ተጽእኖ ለማሳደር ነው መግለጫዎች የሚወጡት። ለምሳሌ መንግስት የህግ የበላይነትን በግልጸኝነት እና በተጠያቂነት መርህ እየሰራ አይደለም ብለን መግለጫ ብናወጣ፤ አይደለም መንግስት የህግ የበላይነትን እያስከበርኩ ነው፣ በግልጸኝነት እና በተጠያቂነት መርህ መሰረት እየሰራሁ ነው ይላል። ያንንም በተግባር ለማሳየት ይሰራል በመጨረሻ ህዝብ ፍርድ ይሰጣል ዲሞክራሲ የሚባለው ይህ ነው።
በአጠቃላይ መንግስት ትኩረት የሰጠባቸውን ጉዳዮች ማንሳት ይቻላል ለምሳሌ የብሄራዊ እና ደህንነት የተጠሪነት ጉዳይ፤ 12ኛ ክፍል ፈተና፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ፤ መሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦቶችን ከአቅራቢዎች አንጻር የተለያዩ መግለጫዎች አውጥተን ብዙ የተፈቱ ጉዳዮች አሉ።
መግለጫ ከማውጣትም በላይ የተለያዩ ችግሮች የታዩባቸው አካባቢዎች ላይ ጥናት በማድረግ የችግሮቹን ስፋት እናሳያለን። ለምሳሌ በቅርቡ እየተተገበረ ያለው የነዳጅ ድጎማ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው አይደለም ? በሚል መነሻ የተለያዩ አካባቢዎች የትራንስፖርት ታሪፎችንና ሌሎች ማሳያዎችን በመመልከት ህብረተሰቡ በነዳጅ ድጎማው የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እየሆነ አለመሆኑን በጥናቱ ተደርሶበታል።
አዲስ ዘመን:- የሚዲያ ነፃነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እስከምን ድረስ ነው?
ዶክተር እንዳለ:- የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና የሃሳብ ነጻነት መብት መሰረታዊ የዜጎች መብት ነው የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው? ለምን ይህ መብት ሆኖ በህገ መንግስት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች አካል ሊሆን ቻለ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
ከዚህ አንፃር በየትኛውም ህገ መንግስት ከታየ የአንድ ሀገር ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ህዝብ ነው ይላል። ይህን ካልን ህዝብ መብቱን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል።
የህዝቦች ሉዓላዊ መብት የሚገለፅበት አንደኛው መብት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በሚያደርገው ምርጫ ነው። ሁለተኛው ህዝቡ በመንግስት ውሳኔዎች ፖሊሲዎች እና እቅዶች ላይ በቀጥታ መሳተፍ ሲችል ሲሆን ሶስተኛው መንግስት ለህዝቡ በገባው ቃል መፈጸሙን ለመጠየቅ በአጠቃላይ መንግስት በተጠያቂነት እና በግልጸኝነት መርህ መሰረት መሰራቱን ማረጋገጥ መቻል አለበት።
የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እና የመገናኛ ብዙኃን መረጃን የማስተላለፍ መብት መከበር ያለበት ለዚህ ነው። የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት ህገ መንግስታዊ መብት ሊሆን የቻለው አንቀጽ 24/4 በግልፅ የተቀመጠ መብት ነው።
ከዚህ በመነሳት ከመገናኛ ብዙኃን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፤ ለዜጎች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ስለመከበራቸው እና በህዝቦች መካከል ነጻ ሀሳብ ልውውጥ እንዲኖር የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በአዋጅም በህግም የተደነገገው ከዛ በመነሳት ነው።
ከዚህ አንጻር የሚዲያ ነጻነትን ማስከበርን በተመለከተ ወይም ህገ መንግስታዊ መርሆዎችን እስኪከበሩ፤ የሀገሪቷን ህጎች ባህሎች እሴቶች የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እስካከበር ድረስ፤ መረጃን የመሰብሰብ የመቀበል እና የማስተላለፍ ህጋዊ ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ መብት አላቸው።
ከኢትዮጵያ አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ ከሚዲያዎች አደረጃጀት አንጻር ነው። በተለይ የመንግስት ሚዲያዎች ቦርድ አባላት የሚባሉት በፖለቲካ የሚሾሙ መሆናቸው ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዳይሰሩ ተጽእኖ ይኖርባቸዋል? ወይስ አይኖርባቸውም የሚለው ሀሳብም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው።
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ክልላዊ አደረጃጀት በመሆናቸው የክልላቸውን ብሔር ባህል እሴቶች ማንነት እና ፍላጎት ማንጻባረቅ አለባቸው። ግን ደግሞ ፌደራላዊ ሀገር መሆናችንን ዘንግተው ከአንድነታችን ይልቅ በልዩነቶች ላይ ሲሰሩ ውለው ያድራሉ። ይህም በመሰረታዊነት ነፃነቱ በተገቢው መልኩ እንዳይተገበር ያደረገው ችግር ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አስፈጻሚ አካላት በእጃቸው ያለውን መረጃ ያለ ስስት እየሰጡ አይደለም። አስፈፃሚ አካላት በእጃቸው ያለውን ማንኛውም መረጃ እንደተቋም ወይም እንደ ሀገር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የሚያውክ፤ የወጣቶችን ሰላምና ደህንነት የማይጎዳ እስከሆነ ድረስ፤ ወይም መረጃው ሚስጥራዊ ነው ተብሎ እስካልተለየ ድረስ በእጃቸው ያለ የመረጃ ሃብት የህዝብ ሀብት መሆኑን በማወቅ መስጠት ተገቢ ነበር። ነገር ግን አብዛኛው ተቋማት ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም።
ሌላው የመረጃ ነፃነትን እንዲያስተገብሩ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች የመረጃ ነፃነትን እንዲያስተገብሩ ስልጣን ተሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል። አሁን ባለው ሁኔታ የትኛው የህዝብ ግንኙነት ነው የአንድ ተቋም ልዩ ምልክት ሆኖ የሚታየው ? ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ተቋማት ሞዴል ወይም ምልክት የሚሆኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሀላፊዎች ነበሩ።
ከህብረተሰብ እድገት አንጻርም በሰጠኸው ነጻነት ልክ መብትና ግዴታውን መሸከም ይችላል ወይ በማለት መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህም ሲባል የሚዲያ ነፃነትን የሚሸከም ህብረተሰብ ሊኖር ይገባል። ህብረተሰብ ሚዲያን የሚያወቅ፣ አጠቃቀሙን የሚገነዘብ፣ የተላለፉ መረጃዎችን የሚመረምር ሊሆን ይገባል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰሞኑን የፖለቲካ ገበያው መስፋት አለበት የሚል ሀሳብ ሲያነሱ ነበር። ይህ የፖለቲካ ገበያው መስፋት አለበት ሲባል ከገበያ የሚገዛው የመንግስት ወይም የብልጽግና ሃሳብ ብቻ አይደለም። የሁሉም ሃሳብ የብልጽግናን ጨምሮ ወደ ገበያ ይወጣል ከዚያ ህዝብ ገዥውን ሃሳብ ከገበያ ይሸምታል። ዴሞክራሲ የሚያድገውም በመሳሪያ ወይም በጡንቻ ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት ነው።
ለዚህ ደግሞ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት መለመድ አለበት። መንግስት እንደ ግለስብ ማሰብ የለበትም፤ ሆደ ሰፊ እና ታጋሽ መሆን አለበት። ይህ ሲባል የዜጎችን መብት መደፍጠጥ መብቱ ነው ማለት አይደለም።
እኔ በግሌ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምመኝላቸው እንደ ከ1801 እስከ 1809 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን የአሜሪካ ዴሞክራሲ አባት እንደተባሉ ሁሉ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አባት እንዲባሉ ነው። አባይ ግድብን ብንመለከት የቀድሞ ጠቅላይ ሚነስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጀምረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ለመጨረስ እየሰሩ ነው።
የፖለቲካ ገበያው ፍትሀዊ እና ነጻ እንዲሆን የሚዲያ ነጻነት መጠበቅ አለበት። ይህ ባልሆነበት የፖለቲካ ገበያው እንደ ሸቀጥ ደላሎች የሚመሩት ገበያ ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በማጠቃለያነት ያቀረቡትን ሃሳብ ወደ ፖሊሲ እቅድ እና ፕሮጀክት መለወጥ ካልቻሉ ሃሳባዊ ሆኖ ይቀራል።
አዲስ ዘመን:- ለመገናኛ ብዙኃን መረጃን ለሚከለክሉ ተቋማት የህዝብ እንባ ጠባቂ እስከምን ደረጃ ሄዶ ያስገድዳል ? መረጃ ያሰጣል ? ባይሰጡስ ሊያስጠይቅ የሚያስችል ህግ አለው ?
ዶክተር እንዳለ:- መረጃ የሚከለክሉ ተቋማትን ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ የለንም። በአዋጅ 590/2000 አንድ የመገናኛ ብዙኃን ተገቢ ያልሆነ ነገር አስተላልፎ ቢገኝ በገንዘብም በእስራትም የሚቀጣውን ቅጣት በግልፅ አስቀምጧል። በአንፃሩ ደግሞ አንድ አስፈፃሚ አካል መረጃ ባለመስጠቱ የተነሳ ተጠያቂ የሚያደርግ የህግ መሰረት የለም።
ነገር ግን ተቋሙ መረጃ መከልከልን እንደ አንድ አስተዳደራዊ በደል በመውሰድ በአዋጅ ቁጥር 1142 ተጠያቂ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። ይህንን ያደረጉ አገልግሎት ሰጪዎችን በሚዲያ ከማጋላጥ አንስቶ ክስ እስከመመስረት ድረስ የሚደርስ ሁኔታ አለ።
እዚህ ጋ ግን አንድ ሚዲያ አንድን መረጃ የሚፈልገው ለዜና ወይንም የሆነ ወቅቱን ለጠበቀ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ህጉ የሚያስቀምጠው አንድን የመንግስት አስፈፃሚ አካል መረጃ አልሰጠህም ብሎ ለመክሰስ ከ90 ቀን እስከ 120 ቀን መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህም መገናኛ ብዙኃን ወደ ተቋሙ እንዳይመጡ ወይም ክስ እንዳይመሰርቱ አንዱ እክል ነው። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ አዲሱ አዋጅ ይረዳል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ የመረጃ ነፃነትን ሊያስጠብቅ ይችላል ተብሎ የታመነበት አዋጅ ተረቆ ወደ ስራ እየገባ ነው። ይህም መረጃ አልሰጥም ያሉትን ለመክሰስ፤ ከ90 አስከ 120 ቀናት መጠበቅ አለበት የተባለውን ቀን የሚቀንስ እንዲሆን እየተሰራ ነው። አዋጁ ላይ እንደተቀመጠ በ10 ቀን ውስጥ መስጠት አለበት ካልሆነ ግን ክስ የሚቀርብበት ሁኔታ አለ።
አዲስ ዘመን:- መረጃ አልሰጥ አሉን ብሎ የከሰሰ ጋዜጠኛ ወይም ተቋም እንዲሁም ለጋዜጠኞች አልሰጠህም ተብሎ የተጠየቀ ተቋም ካለ ቢገልፁልን?
ዶክተር እንዳለ:- ዘንድሮ አንድም የሚዲያ ተቋምም ሆነ ጋዜጠኛ ወደ ተቋሙ መረጃ ተከለከልኩ ሲል አቤቱታ አላቀረበም። ከዚህ ቀደም ግን ፕሬስ ድርጅት፤ ኢሳትና፤ ኢትዮጵያ ቴሌቨዥን አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር።
እንደምሳሌ ባነሳለሽ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ህዝብ ግንኙነት ጋር ደውሎ መረጃ ባለማግኘቱ የተነሳ ያቀረበው አቤቱታ ነበር። ይህን አቤቱታ ይዘን ዋና ስራ አስፈፃሚው ጋር ባደርግነው ግንኙነት የተነሳ ችግሩ እንዲፈታ ሆኗል።
የወንጀል ነክ ጉዳዮች ሆነው ጉዳዩ ፍርድ ቤት እያለ ፖሊስ ጋር መረጃ ተጠይቆ መረጃውን ማግኘት አልቻልኩም የሚል ክስ ወደተቋሙ ሲመጣ ያለውን ሁኔታ አጣርቶ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ወደሆነው ተቋም ጥቆማ ተሰጥቷል። ከተቋማት ጋር በሚኖር ግንኙነት የሚፈቱ ችግሮች አሉ፤ ሪፎርም ውስጥ ቆይተው ሪፎርሙ ሲጠናቀቅ መረጃ እንዲሰጣቸው የተደረገበትና ሌሎችም አሉ።
አዲስ ዘመን:- ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ሀሳብ የሚያስተላልፉ፤ የሌሎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ በምን ይጠየቃሉ? አንዳንዶች ማህበረሰቡን የሚጎዳ ንግግር እየተናገሩ ህጋዊ እርምጃ ሲወሰድባቸው የመናገር ነፃነታችን ተነፈግን ሲሉ ይደመጣሉ። ይሄ በምን አግባብ ይታያል ?
ዶክተር እንዳለ:- ይህንን ጉዳይ የሚያነሳው መንግስት ወይንስ ህዝብ ነው የሚለው ጉዳይ ተለይቶ መቀመጥ ይኖርበታል። አንድ የመንግስት ተቋም እገሌ የሚባል ሚዲያ አለአግባብ ስሜን አጥፍቷል ብሎ ቢጠይቅ ያንን ያስተላለፈው ሚዲያ መረጃውን እንዲያስተባብል ይደረጋል።
ከዛ ባለፈ ወደ ክስ ወይም ጋዜጠኞችን ወደ ማሰር ከተሄደ ኢ- ህገ መንግስታዊ ነው። ተገቢ አይደለም። የወጣቶችን ደህንነት የሚነካ፤ መልካም አስተዳደር ላይ ተጽእኖ የሚፈጠር፤ የሀገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል፤ የግለሰቦችን ክብር በሚነካ መልኩ የማንቋሸሽ ስራ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ካሉ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር አዋጅ ቁጥር 11/85ና በወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሚታይ ይሆናል።
መገናኛ ብዙኃን እነዚህን ተግባር ፈፅመው ሲገኙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የመቆጣጠርና በአዋጁ መሰረት ተጠያቂ የማድረግ ስራን ይሰራል። አብዛኛው ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃንን መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህንን ችግር ለማስቀረት ህብረተሰቡ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለልማት፣ ለሰላም፣ ህብረተሰብን ከህብረተሰብ ጋር ለሚያቀራርብ ነገሮች እንዲያውሉ ግንዛቤ መስጠትም የተሻለ መፍትሄ ነው። አንድ ሰው ሊቀጣ ወይም ሊታሰር መቻሉ ግን ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት ባለመቻሉ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊናን መጨመር ያስፈልጋል።
ሀሳብን በሙዚቃ ወይም በግጥም ወይም በሌላ አይነት የመግለጽ የዜጎች መብት ግን ሃሳቡ ትክክል አይደለም የሚል ወገን ትክክል አለመሆኑን በሃሳብ ነው መግለጽ የሚችለው እንጂ መክሰስ አይችልም።
ለምሳሌ ያህል ከሰሞኑ አንድ ጋዜጠኛ ከቆላ ስንዴ እና ከፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ያነሳው ሃሳብ ፖሊቲሳይዝድ ተደርጎ በየማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር አይተናል። ጋዜጠኛው ለስንዴ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለምን ለድንች ወይም ለሌሎች የግብርና ውጤቶች አልተሰጠም በማለት ይህንን መመርመር እፈለጋለሁ ሲል ይህንን ለመመርመር የፈለከው ምን አስበህ ነው ? በሚል መረጃን መከልከል ተገቢ አይደለም።
የአንድ ጋዜጠኛ ሃሳብ አልፋና ኦሜጋ ነው ያለው ማነው? በምርምራ ጋዜጠኝነት ልመርምር ቢል ከጀርባ የፈለገ ተልእኮ ይኑረው ከጋዜጠኛው የሚጠበቀው ተአማኒና ሚዛኑን የጠበቀ ዘገባ እንዲሆን ማድረግ ነው ።
አዲስ ዘመን:- ተቋሙ በቅርቡ የተለያዩ ጠንካራ ሀሳቦች ያላቸውን መግለጫዎች ሲያወጣ ቆይቷል። አሁን ምን ስለተገኘ ነው ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ወደፊት መምጣት የተጀመረው የሚሉ አስተያየቶች እየተነሱ ነው። በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት?
ዶክተር እንዳለ:- ምንም የተለየ ነገር ስለተገኘ አይደለም። በጦርነቱ ወቅት እንደ አንድ ለሀገሪቱ ሰላም እንደሚጨነቅ አካል ዝምታን መርጠናል። በተቀረ ግን ከዚህ በፊትም ከዚህ የጠነከሩ መግለጫዎች አውጥተናል።
በቅርብ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ላይ የሰጠነው መግለጫ ነበር፤ በአንድ ወቅት በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ለደረሰው የዜጎች ሞትና መፈናቀል ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በላይ ሳይሆን በመንግስት ቸልተኝነት የተፈጠረ መሆኑን አንስተን ሞግተናል።
የአሁኑ የገነነው ምናልባትም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ በመሆኑ አዲስ ነገር ሊያስመስለው ችሎ ይሆናል። ህገ መንግስት በመሰረቱ መንግስት ህዝብን የሚቆጣጠርበት ሳይሆን ህዝብ ለመንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት አስተዳድረኝ ይህንን ከላደረግክ በህገ መንግስቱ እጠይቅሃለሁ በማለት ህዝብ መንግስትን የሚቆጣጠርበት ነው።
ስለዚህ ህገ መንግስቱ በተገቢው መልኩ አገልግሎት ላይ ካልዋለ፤ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ስራቸውን እየሰሩ ነው፤ እየሰሩ አይደለም የሚለውን ይጠይቃል። ህገ መንግስቱ ሊሻሻል ይችላል። ህገ መንግስቱን እስካላሻሻላችሁ ድረስ በህጉና በህገ መንግስቱ መሰረት መሰራት አለበት በማለት መንግስትን እየሞገትን ነው ያለነው።
ዋናው ነገር መንግስት ከለውጡ በኋላ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ ግን ደግሞ በህግ መሰረት እንዲሰሩ ነጻነት ሰጥቷቸዋል። በመሰረቱ ይህን መብት ሊሰጥም ሊነፍግም መብት የለውም። ግን የዴሞክራሲ ተለማማጆች በመሆናችን መንግስት ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ እንቆጥረዋለን። ይህን እድል ያለመጠቀም የመሪዎች ድክመት ነው ፤ ተቋም መገንባት አለመቻል የተቋማቱ ድክመት ነው።
በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ሌላ መብቱን የሚያስጠብቅለት አካል ከመጠበቅ ይልቅ በየደረጃው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቃወም፤ በእጅ መንሻና በሌሎች ጉዳዮች ጉዳይን ከመፈፀም ይልቅ በመብቱ መገልገልን ቢለማመድ ሀገሪቱ እውነተኛ ዲሞክራሲ ይሰፍንባታል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፤ ውድ ጊዜዎን ሰውተው ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ በአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ስም ከልቤ አመሰግናለሁ።
ዶክተር እንዳለ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015