የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ከግማሽ ክፍለ ዘመናት በላይ የተሻገረ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታትም ሁለቱ ሀገራት የሕዝቦቻቸውን ጥቅም የሚያስከብሩ ተግባራት ከማከናወናቸውም ባሻገር የርስ በርስ መተሳሰብንና መተማመንን በማስቀደም ተምሳሌታዊ ግንኙነት መፍጠር ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥሟትን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመሻገር የምታደርገውን ጥረት በማገዝ ቻይና የበኩሏን እገዛ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ለአብነትም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ 19 በመከላከሉ ረገድ ቻይና ያደረገችው ድጋፍ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለችው የጸረ ኮቪድ 19 ዘመቻ ከ12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ በላይ ክትባት በመለገስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ማሳየት ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ቻይና በኮቪድ ወረርሽኝ በተጠቃችበትና በዚሁ ምክንያትም መላው ዓለም ወደ ቻይና በረራ በሰረዘበት ወቅት በብቸኝነት በረራ በማድረግ በችግር ጊዜም ቢሆን የቻይናና ኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይለያዩ ያስመሰከረበት ታሪካዊ ሁነት መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ በወቅቱም የዓለም ሀገራት ወደ ቻይና በረራ ባቆሙበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት በብቸኝነት የወሰደው ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ከቻይና መንግሥትና ሕዝብ አድናቆት የተቸረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፤
ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን ሰብዓዊ ቀውሶች በማቃለል ረገድም የቻይና መንግሥት ድጋፍ የማይነጥፍ ነው፡፡ በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ለተጎዱ ዜጎች የቻይና መንግሥት ከ30 ሚሊዮን የቻይና ዩዋን በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የተለያዩ ልማቶችን በመደገፍም የቻይናን መንግሥት አበረታች አስተዋፅዖ በማደረግ ላይ ይገኛል፡፡
የቅርቡን እንኳን ብንመለከት በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙትን የአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ማስዋብ ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ የቻይና መንግሥት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ግዙፉ የንግድ ባንክ ሕንጻና የሳይንስ ሙዚየም ግንባታዎች የቻይናውያን አሻራ ያረፈባቸው ድንቅ የልማት ውጤቶች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 90 ሺህ ሜትር ስኩዌር የሚሸፍን ቦታ ላይ ዘመናዊ የሆነ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማ ዕከል ዋና መሥሪያ ቤት ተገንብቶ ለ ምረቃ የተቃረበውም በ ቻይና ድጋፍ ነው ።
ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ በገባችባቸው ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሠረት እንዲጥልና የህዋ ምርምር እንዲዳብር ቻይና ያልተቆጠበ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የቻይና መንግሥት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ETRSS-1 እና ET-Smart-RSS የተሰኙ ሳተላይቶችን ኢትዮጵያ እንድታመጥቅ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ሦስተኛዋን ሳተላይት ለማምጠቅ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡
ከልማቱና ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የቻይና መንግሥትና ሕዝብ በዓለም አቀፍ መድረክ ከኢትዮጵያ ጎን ተለይተው አያውቁም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ ለማድረግ ለማዋል የሚፈልጉ ሀገራት ጉዳዩን ከሚፈለገው በላይ በማግዘፍ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለ12 ጊዜያት ያህል እንዲታይ ሲያደርጉ በሁሉም መድረኮች ቻይና ከኢትዮጵያና ከእውነት ጎን በመቆሟ የተጎነጎኑትን ሴራዎች ለማክሸፍ ትልቅ አቅም ሆኗል፡፡
ዘመን የማይሽረው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ዛሬ ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ በቅርቡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ቺን ጋንግ በሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ የሆነውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ በማድረግ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ዛሬም እንደትናንቱ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።
ይህንኑ ጉብኝት በተመለከተም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ “የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በደኅና መጡ። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁንም ጸንቶ ቀጥሏል። የዛሬው ውይይታችን ይህንን እና በልማት የምንጋራውን ስልታዊ የጋራ ዓላማ፤ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጉልቶ አሳይቷል” ሲሉ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015