በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም ከምግብ ክፍሎች ውስጥ አትክልት ቅናሽ ቢያሳይም፤ በአብዛኛው እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ የምግብ ዘይትና ቅባቶች፣ ሥጋና ወተት ጭማሪ በማሳየታቸው አጠቃላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት እየቀጠለ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከምግብ በተጨማሪ ምግብ ነክ ያልሆኑ ልብስና ጫማ፣ ነዳጅና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጭማሪ በማሳየታቸው በኅዳር ወር 2015 ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 35 ነጥብ 1 ከመቶ ተመዝግቧል። አጠቃላይ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ 31 ነጥብ 7 በመቶ መሆኑን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል። የዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ ምክንያት እና መፍትሔውን በተመለከተ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ የዋጋ ግሽበት በመሰረታዊነት ምክንያቱ የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ነው። ይህ የሚከሰተው በብዛት ወደ ገበያው የተለቀቀው የገንዘብ መጠን እና ያለው ምርት ሳይመጣጠን ሲቀር ነው።
‹‹ብዙ ሰው ገንዘብ ይዞ ወደ ገበያ ሲሔድ የገንዘቡን ያህል ምርት ገበያው ውስጥ ከሌለ ብዙ ሸማቾች ለጥቂት ዕቃ የሚያደርጉት ውድድር የምርት ዋጋው ወደ ላይ እንዲወጣ ያስገድዳል›› የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ ናቸው። ሌላኛው ባለሙያ አቶ ዓለማየሁም ተፈሪም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ።
እንደአቶ ወሰንሰገድ ገለፃ፤ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና መሰል የምግብ ሸቀጦች በገበያ ላይ በአንድ ኪሎ እስከ 70 ብር ድረስ ተሽጦ ነበር ፤ ሆኖም ግን መልሰው ብዙም ሳይቆዩ ዋጋቸው ወርዶ አንድ ኪሎ በ20 ብር ደርሷል። ይሔ የብሩ የመግዛት አቅም ጨምሮ ሳይሆን፤ ምርቱ ሲጨምር እና ያንን ምርት ለመግዛት ገበያ ላይ የሚውለው ገንዘብ ከምርቱ ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን ዋጋው ስለቀነሰ ነው።
በተቃራኒው ምርቱ ሳይበዛ ምርቱን ለመግዛት የሚውለው ገንዘብ በጣም በብዛት ከታተመ እና ወደ ገበያ ከተበተነ፤ ገንዘቡ ስለበዛ ሽሚያ ይፈጠራል። ገንዘቡ ሲበዛ የሚመረተውም አብሮ ከበዛ ማለትም ዓመታዊ ምርቱ (ጂዲፒ) ገበያ ላይ ካለው ብር በታች ሳይሆን ተመጣጣኝ ከሆነ የዋጋ ግሽበት አይኖርም ሲሉ ያብራራሉ።
የገንዘብ ገበያው ላይ መበተን እንዴት እንደሚፈጠር የሚያስረዱት የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ወሰንሰገድ እንደሚሉት፤ የኢንቨስትመንት መስፋፋት ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም አለው። ምክንያቱም መንግስትም ሆነ ባለሃብት ትኩረት አድርገው የሚሰሩባቸው ዘርፎች ህብረተሰቡ የሚሸምታቸው ወይም ወደ ውጭ ተልከው ገንዘብ የሚያስገኙ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ አግሮ ኢንዱስትሪ ቢስፋፋ ህዝቡ ይሸምታል፤ ቤት ቢገነባ ህዝቡ ይኖርበታል፤ ነገር ግን ሰራተኛ ተቀጥሮ ገንዘብ ተከፍሎት ሌሎችም ግዢዎች እየፈፀመ የሚመረተው የኢንቨስትመንት ምርት ህዝብ የማይሸምተው ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም እንዳለው ይጠቅሳሉ።
አቶ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የዋጋ ግሽበት እየጨመረ የቀጠለው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ። የዓለም ኢኮኖሚ የተሳሰረ መሆኑን በማስታወስ፤ በምስራቅ አውሮፓ የተፈጠረው ጦርነት እና በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የተከሰተው የምርት ማነስ እንዲሁም ድርቅ እና ጎርፍ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።
ሌላው በአቶ ዓለማየሁ የተገለፀው፤ የዓለም ህዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊየን ደርሷል። መሬት ግን መጠኗ አልጨመረም። ሕዝብ ሲጨምር ፍላጎት ይጨምራል። ሕዝብ ሲጨምር ተመጣጣኝ ምርት መጨመር አለበት። ምርት ካልጨመረ እጥረት ስለሚፈጠር የዋጋ ግሽበት ይከሰታል። በኢኮኖሚክስ ህግ መሰረት አቅርቦት እና ፍላጎት ዋጋን ይወስናል። አቅርቦት እና ፍላጎት ተመጣጣኝ ሲሆኑ ዋጋውን ገበያው ይወስነዋል። ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ ከሆነ ዋጋ መጨመሩ ግልፅ ነው ይላሉ።
ወደ ኢትዮጵያም ሲመጣ ተመሳሳይ ነው የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጨምሯል። ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው። ድርቅ እና የፀጥታ ችግር አለ። ገበሬው በፀጥታ ችግር ምክንያት ማምረት ባለመቻሉ የምርት ማሽቆልቆል ነበር። በዚህ ዓመት የተሻለ የስንዴ ምርት ስለመመረቱ እየተገለፀ ነው። ምናልባት በያዝነው ዓመት የተመረተው እህል ወደ ገበያ ከገባ ዋጋ ሊረጋጋ ይችላል። ሌላው በኮቪድ ምክንያት የፋብሪካ ሰራተኛም ሆነ አገልግሎት ሰጪዎች ሥራ አቁመው ነበር። ይህ ደግሞ በዓለም ምርት መቀነስ ላይ የራሱን ተፅዕኖ አሳድሯል። ይሔ ተያይዞ የዋጋ ግሽበት ላይ የራሱ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ።
የዶላር ዋጋ በየጊዜው መጨመሩ ለዋጋ ግሽበት አንዱ ምክንያት መሆኑን አቶ አለማየሁ ያነሳሉ። ነጋዴው ወጪውን ለማካካስ የልብስ፣ የጫማ፣ የቤት እቃ እና ሌሎችም ምርቶች ላይ ዋጋ ስለሚጨምር የዋጋ መረጋጋት አይኖርም። በዋናነት ግን ገበያውን የሚበጠብጡ ደላሎች መኖራቸውን በማስታወስ፤ በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበት ላይ ራሱን የቻለ ትልቅ ጥናት መካሔድ አለበት ይላሉ።
አቶ ወሰንሰገድ ከአቶ ዓለማየሁ የተለየ ሃሳብ አላቸው። አቶ ወሰንሰገድ እንደሚሉት፤ ዋናው ትኩረት መደረግ ያለበት ምግብ ፣ መጠጥ፣ መጠለያ፣ እና የሚለበስ ምርት ላይ ነው። ከዛ ውጪ በቢሊየን ብር አውጥቶ ሕዝቡ ከሚያስፈልገው መሰረታዊ ምርት ውጪ የሆነ ኢንቨስትመንት ላይ ማዋል፤ ብር በብዛት ወደ ገበያው መበተን በራሱ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆኑን ያብራራሉ።
አቶ ወሰንሰገድ እንደሚገልፁት፤ ማንፋክቸሪንግ ፤ አግሮ ኢንዱስትሪ ወይም ከሰው ሕይወት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ምርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሲኖር የተበተነው ገንዘብ ገበያ ላይ ቢገባም ችግር አይፈጠርም። ሰው ወደ ገበያ ሔዶ የግብርና ምርቱን፤ ወተቱንም፣ ስጋውንም፣ ስንዴውንም ማግኘት ሲችል ዋጋው የሚረጋጋበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። ስለዚህ በእርሳቸው እምነት የዋጋ ግሽበቱ አንዱ መነሻ ኢንቨስት የሚደረግባቸው ዘርፎች በተገቢው መልኩ አለመመረጣቸው እና ከሰው ሕይወት ጋር በቀጥታ የተያያዙ አለመሆናቸው ነው።
ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞም ያለውን ክፍተት ደግሞ ሲያብራሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 20 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ዕቃ በውጪ ምንዛሪ ወደ አገር ይገባል። ወደ ውጭ የሚላከው ግን ከአራት ቢሊየን አይበልጥም። ስለዚህ አገሪቱ የገቢ ምርት ጥገኛ ናት። ከነዳጅ ጀምሮ ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች፣ ልብስ እና አጠቃላይ ጌጣጌጡን ጨምሮ የሚገባው ብዙ ነው። ወደ አገር የምታስገባው ምርት ብዙ የሆነባት አገር፤ የውጪ ምንዛሪዋን ዝቅ እንዲል ማድረግ የለባትም። ዝቅ ካለ ከውጪ የሚገባው ዕቃ በጣም ይወደዳል። በ100 ብር ሲገዛ የነበረው ዕቃ 800 ብር ሊገባ ይችላል በማለት በዚህኛው ሃሳብ ከአቶ ዓለማየሁ ጋር እንደሚስማሙ ያብራራሉ።
አቶ ወሰንሰገድ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ እንደሚናገሩት፤ ከብዙሃን የኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎች መቆማቸው ለጊዜውም ቢሆን መፍትሔ ይኖረዋል። በእዚህ ምክንያት የዶላር መትረፍ እንዳለ ሆኖ ከቀረጡ የሚታጣው ግን ከሚተርፈው አንፃር ብዙ የሚባል ባለመሆኑ ትልቅ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ወሰንሰገድ ሁሉ የውጪ ምንዛሪ ብክነት ለመቀነስ ለጊዜው የቅንጦት ዕቃዎችን ማገዱ መልካም ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የሚገልፁት አቶ ዓለማየሁ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሚሸምተው ነገር ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ ነው። ከተወሰዱ መፍትሔዎች መካከል በየቀኑ በመሰረታዊነት ህዝቡ የሚጠቀምበት ዘይት በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገባ መደረጉ መልካም ትክክልኛ እርምጃ መሆኑን ያነሳሉ። ነገር ግን ዘይትንም እዚሁ ሀገር ውስጥ ማምረት ያስፈልጋል። የቅንጦት ዕቃዎችም ቢሆኑ እንደታገዱ ከዘለቁም ጉዳት አላቸው፤ ኮንትሮባንድ ይስፋፋል። ሰዎች በህጋዊ መንገድ የተከለከሉትን ዕቃዎች ማግኘት ከፈለጉ ህገወጥ መንገድን እንደሚጠቀሙ ይገልፃሉ።
አቶ ዓለማየሁ እንዳብራሩት፤ የአገር ውስጥ ምርት ተትቶ የውጪውን ብቻ መጠቀም በአገር ላይ ጉዳት ያስከትላል። ቢሆንም ግን የአገሪቷ የዋጋ ግሽበት ከ30 እስከ 40 በመቶ ነው። የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ባይኖሩ ግን የበለጠ ከባድ ነበር። ለምሳሌ ዙምባብዌ ገንዘቧ በከፍተኛ መጠን ዋጋ አጥቷል። ግሽበቱም ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል። በሽታውን፣ የተፈጥሮ አደጋውን፣ ጦርነቱን ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ዋጋ ግሽበት እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ በራሱ መልካም ነው ይላሉ።
መፍትሔ ያሉትን አቶ ወሰንሰገድ ሲጠቁሙ ፤ ዋናው የአገር ውስጥ ምርትን ማበረታታት ነው። ይሄ ከውጭ የሚገባን በአገር ውስጥ ለመተካት ያስችላል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። አቅርቦትን ያሰፋል። ስንዴ በስፋት ማምረቱ ትልቅ መፍትሔ ነው። የተትረፈረፈ ምርት በሀገር ውስጥ እንዲመረት ማድረግ ይገባል።
መፅሃፍም ያንተን ፍላጎት ካሟላሁ በኋላ ለወዳጅህ ለመስጠት እንድትችል አብልጠህ ሥራ ይላል። ማዕድ አጋራ ከሚለው ቀድሞ የሚለው አብልጠህ ሥራ ነው። የተመረተው ከተሰጠ አለቀ ማለት ነው። ነገር ግን ከመንፈሳዊ በረከት እና ከመተባበር አንፃር ከታየ ግን መልካም ነው ይላሉ።
አቶ ዓለማየሁ እንደሚገልፁት፤ ዕቃዎች እና አገልግሎቶችን በተመለከተ አቅርቦት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ምርት በአንድ ጎን ሲኖር ገበያው ላይ የሚበተነው ገንዘብም ከፍተኛ ከሆነ የዋጋ ግሽበት ይፈጠራል። ብሔራዊ ባንክ የሚያትመው ገንዘብ ላይ ቁጥጥር ካልተደረገ በራሱ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆኑ አይቀርም። ብዙ አገሮች ገንዘባቸውን ሲያትሙ ፖሊሲ አላቸው። ከአጠቃላይ የአገር ምርት 10 ከመቶ ያልበለጠ ብር ያትማሉ። ከዛ በላይ ከሆነ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ።
ኢንቨስትመንት ከሌለ አገር አታድግም የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፤ ኢንቨስትመንት ሲኖር ምርት ይገኛል፤ አገልግሎት ይጨምራል ፤ የሚገዛ እና የሚሸጥ ነገር ይኖራል። ነገር ግን ከኢኮኖሚው አቅም በላይ ከሆነና ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ከበዙ በእጃቸው ብር ይዘው ወደ ገበያ ይገባሉ። ስለዚህ ኢንቨስትመንቱም ቢሆን ከአቅም በላይ እንዳይሆን ቁጥጥርና ክትትል ያስፈልጋል። ኢንቨስትመንትም በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።
ዋናው መፍትሔ ግን ምርት መጨመር ነው። ገበሬ ብዙ ይለፋል፤ ብዙ አያመርትም፤ ስለዚህ መፍትሔው ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ትራክተር እንዲሁም ኮምባይነር እንዲጠቀም ማድረግ ያስፈልጋል። በዘመናዊ አመራረት ዘዴ በመጠቀም፤ የተወሰኑ ጥቂት ገበሬዎች አገርን እንዲመግቡ መደረግ አለበት። በሌሎች አገሮች ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ምርታማነትን በማሳደግ በአጭር ካፒታል ብዙ በማምረት ለውጥ እንደሚመጣ ታይቷል። ስለዚህ መፍትሔው የሰለጠነ የሰው ሃይልና ዘመናዊ ካፒታል አቀናጅቶ አገር መለወጥ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2015