ኢትዮጵያ የታሪክ ገናናነቷ ከሚገለጥባቸው ዐውዶች አንዱ በዘመናት ሂደት ውስጥ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት አጽንታ መኖሯ ነው። ይሄ የሥርዓተ መንግሥት ዘላቂነት ከፈጠረላት አቅምና የህሳቤ ልዕልና አንዱ ደግሞ፤ ችግሮችን በራስ እሴት እና አቅም መፍታት ይቻላል የሚለው ነው። ይሄንኑ ህሳቤዋን እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉር አጽንታ የምታቀነቅን ሲሆን፤ አፍሪካ እንደ አህጉር በውስጧ የሚስተዋሉ ችግሮችን በራሷ አቅምና እሴት መፍታት ትችላለች ለሚለው ሃሰብም መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል።
በዚህ ረገድ በአፍሪካ የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ቀድመው የሚታዩ ጉዳዮች ሲሆኑ፤ አፍሪካ የግጭትና ያለመረጋጋት አለፍ ሲልም በመፈንቅለ መንግሥት የመታመሷ ምስጢር በውስጧ የሚታዩ ችግሮችን በራስ አቅም ከመፍታት ይልቅ ለውጪ ኃይሎች ዳኝነት ራሷን አሳልፋ በመስጠቷ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ኢትዮጵያም ይሄን ስለምትገነዘብ እንደዚህ አይነት ችግሮች በዘላቂነት ይፈቱ ዘንድ በውስጥ አቅምና በዜጎች ይሁንታ ላይ ተመሥርቶ የሚከወን መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል የሚል አቋም ን ስታራምድ ኖራለች።
ይሄ ህሳቤ ደግሞ ከብሂል ባለፈ በተግባር የሚገለጥ ሊሆን ስለሚገባውም፣ ኢትዮጵያ በውስጧ ለሚስተዋሉ ችግሮችም ሆነ ድንበር ዘለል መስለው ለሚስተዋሉ ጉዳዮች በቅድሚያ ባለ ጉዳዮቹ ቁጭ ብለው እንዲመክሩ፤ አለፍ ሲልም የአፍሪካውያን ተቋም የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን በባለቤትነት እንዲመራውና ለመፍትሔ እንዲበቃ ስታደርግ ቆይታለች። ኢትዮጵያ አስቦና አቅዶ በራስ አቅም መሥራትና መበልጸግ፤ ይሄን ተከትሎ የሚስተዋሉ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርበው በመነጋገር ችግሮቻቸውን ያለማንም የውጪ ኃይል ጣልቃ ገብነት መፍታት ይቻላል የሚል አቋሟን አደባባይ ያወጣችበት የዓባይ ኃይል ማመንጫ ግድብ ደግሞ የዚህ ህሳቤዋና አቋሟ ውጤታማነት አንዱ ማሳያ ነው።
ከዚህ በላይ ግን በሃገራዊ ለውጡ ዘመን በሃገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ጦርነት ሰላማዊ መቋጫ እንዲኖረው የተደረገበት አግባብ የኢትዮጵያን ህሳቤ አዋጭነት፣ ታላቅነትና ተጨባጭበት ያረጋገጠ ሐቅ ሆኗል። የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ኢትዮጵያም ሆነች የአፍሪካ ኅብረት ይሄን የመፍታት አቅም እንደሌላቸው ተደርጎ በስፋት ሲነገር፤ ችግሩ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ አቅም በላይ ስለሆነም ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማትና ሃገራት ወደራሳቸው ወስደው እንዲያዩትም የበዛ ግፊት፣ ቅስቀሳና ጫናም ሲደረግ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በውስጧ የተከሰቱ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት ይቻላል፤ ይሄ ባይሳካ እንኳን በአፍሪካ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ከራሳቸው ከአፍሪካውያን አቅም በላይ አይደሉምና አፍሪካዊ መፍትሔ ይኖራቸዋል በሚለው አቋሟ ጸንታ ተጉዛለች። እናም ጉዳዩ በውስጥ የሰላም ፍላጎት ታግዞ እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ቁጭ ተብሎ እንዲፈታ በብርቱ ጥራለች። ጥረቷም ለፍሬ በቅቶ በአፍሪካ ምድር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ፊርማን በማኖር መቋጫ አግኝቷል። በኋላም በናይሮቢው መድረክ ታግዞ ስምምነቱ የበለጠ ጸና። ጉዳዩንም ወደ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ተመልሶ ችግሩ አለ በሚባልበት ስፍራ ላይ ያለማንም አመቻችነት በጋራ ቁጭ ብሎ መነጋገር እና መፍታት እንደሚቻል ዓለም እንዲማር የተደረገበት ውይይት ተካሂዷል።
ቀደም ሲል የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተወሰዱ ርምጃዎች፣ ማለትም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ያለገደብ እንዲገባ መደረጉ፤ የወደሙ መሠረተ ልማቶች እንዲጠገኑ እና ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መሠራቱ፤ ይሄን ተከትሎም ስልክ፣ ባንክ፣ ኤሌክትሪክና ሌሎችም የተቋረጡ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀምሩ መደረጉ፤የአየር በረራዎች መጀመራቸው፤… የመንግሥትን የሰላም ስምምነቱን ለማጽናት ያለውን ከፍ ያለውን ከሰላም ስምምነቱም የላቀ ቁርጠኝነት ያረጋገጡ ተግባራት ነበሩ።
በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን ለማጽናት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ በርካታ ርምጃዎች ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ስትናገር የነበረውን እውነት ለዓለም የገለጠችበት፤ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚችሉ ያረጋገጡ ነበሩ። ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ወደ ሰላም በመለወጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ መፍትሔው ያለው በኢትዮጵያውያን እጅ መሆኑን አሳይታለች።
ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ያለው አጠቃላይ ጉዞ ሲታይ የተወሰዱ ርምጃዎች እና ተጨባጭ ተግባራት የመንግሥትን የሰላም ቁርጠኝነት ያረጋገጡ መሆኑን አሳይቷል። ኢትዮጵያም የውስጥ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ለዓለም ማሳየት ችላለች!
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም