በሀገራችን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ከሚገኙ ታላላቅ ሥራዎች መካከል አንዱ የተፋሰስ ልማት መሆኑ ይታወቃል። የተፋሰስ ልማት መካሄድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ልማቱ እንደ ኮንሶ ባሉ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድ ባሕል ተደርጎ ሲሠራበት የኖረ ሲሆን፣ በሌሎች ማኅበረሰቦችም በስፋት ይከናወናል።
የተፋሰስ ልማቱ በማኅበረሰብ ደረጃ የተለመደ ቢሆንም፣ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ግን በመንግሥት ፕሮጀክት፣መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በማኅበረሰብ ተሳትፎ፣በስፋት ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል። በመንግሥት ደረጃ በስፋት መከናወን ከጀመረም በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በደርግ መንግሥት የተፋሰስ ልማት በተለይ እርከን በመሥራት ይፈጸም ነበር። በኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ ልማቱ ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ በዘመቻ መልክ እንዲሁም በሴፍትኔት መርሐ ግብር ሲከናወን ቆይቷል። የዓባይ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ በሚል ሰፊ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሲከናወንም ነበር። የተፋሰስ ልማቱ በተለይ ከጥር ወር አንስቶ ለአንድ ወር ይካሄዳል። በልማቱም በተፈጥሮ፣በሰው ሰራሽና በተለያየ ምክንያቶች የተጎዱ መሬቶች አገግመው ለልማት መዋል መቻላቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ። የተፋሰስ ልማት ሥራ ዘንድሮም እንደ ሀገር ይካሄዳል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው እንደ ሀገር በስፋት እንደሚካሄድ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት በልማቱ እየተከናወነ ስላለው ተግባር በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ሊድ ኤክስክዩቲቭ ክፍል የተፋሰስ ልማት ዴስክ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ዮሴፍ አሰፋ ጋር ቆይታ ያደረግነውን ቆይታ በዛሬው ግብርና ዓምዳችን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ዮሴፍ እንዳሉት ፤ በተፋሰስ ልማት ሥራ ውስጥ የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉ በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ። የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል የእርከን ሥራ፣የተለያዩ የዕፅዋት ችግኞችን የማዘጋጀትና ተያያዥ ተግባራት ይፈጸማሉ። የተፋሰስ ልማቱም የሚከናወነው በአነስተኛ ተፋሰስ ሲሆን፣ለጅረት እና ለትላልቅ ወንዞች የሚጠራቀም ውሃ የሚይዝ የመሬት ስፋትም ይለያያል።
አንድ የተፈጥሮ ገጽታ ያለው መሬት ከዝናብ የሚገኝ ውሃን ሰብስቦ የሚይዝ መሆኑንና ለወንዝ መፈጠርም ምክንያት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዮሴፍ፣ አንድን ወንዝ፣ ወንዝ የሚያሰኘው በዚህ መልኩ ከተለያየ አካባቢ የተጠራቀመ ጅረት ውሃ እንደሆነ ያመለክታሉ። በዚህ መልኩ በተጠራቀመ አነስተኛ ተፋሰስ ልማቱ እንደሚከናወን ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ፤ የተፋሰስ ልማት ሥራ በባሕላዊ መንገድ ሲከናወን የቆየ ቢሆንም፣ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ግን በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ የማኅበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። በተሠሩት ሥራዎችም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፋሰሶች አገግመዋል። በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የተፋሰስ ልማት አስፈላጊነት ግንዛቤ ጨምሯል።
በመንግሥትና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለተፋሰስ ልማት ሥራው ልዩ ትኩረት እየተሰጠው ነው። በልማቱ ለውጦች ቢመዘገቡም ገና የተፋሰስ ልማት ሥራ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በመኖራቸው አሁንም የተጠናከረ ሥራ ይጠበቃል። ልማቱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ እንዲሁም በማኅበረሰብ ንቅናቄ እየተሠራ ይገኛል፤ ሥራዎቹም መንግሥት ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት በሚያገኘው የገንዘብ ብድርና ድጋፍ የሚከናወኑ ሲሆን፣ ግብርና ሚኒስቴር ሥራ ላይ ለማዋል የነደፋቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች በዚህ መልኩ ታግዘው ነው ሥራ ላይ የሚውሉት።
የፕሮጀክት ድጋፉ እንደሚለያይ የጠቆሙት አቶ ዮሴፍ፣ አንዳንዱ ፕሮጀክት በቀጥታ ክፍያ በመፈጸም የሚከናወን ሲሆን፣ክፍያውም የሚፈጸመው በተፋሰስ ልማቱ ላይ በሥራ ለሚሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው። እንዲህ ያለው ፕሮጀክት ለልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የምግብ ችግር ባለበት አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ክፍተት በመሙላት በልማቱ በማሳተፍ ማኅበረሰቡ ክፍያ እንዲያገኝ ይደረጋል። ሌላው ፕሮጀክት ደግሞ ለተፋሰሱ ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት፣ የማኅበረሰብና የልማት ሠራተኛን በስልጠና ግንዛቤ ለማዳበርና ለማብቃት እንዲውል የሚያስችል ነው።
በግብርና ሚኒስቴር በተቀረጸ ለአምስት ዓመት ለሚተገበር ፕሮጀክት የዓለምባንክ ወደ 500 ሚሊዮን /አምስት መቶ ሚሊዮን/ ዶላር አካባቢ ብድር መስጠቱን አቶ ዮሴፍ ይጠቁማሉ። ወደ ሥራ ከገባ ሁለት ዓመት ባስቆጠረው በዚህ ፕሮጀክት ወደ አምስት ሺ ተፋሰሶችን ለማልማት መታቀዱን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ፤ የተፋሰሱ ልማቱ በማኅበር በተደራጁ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚከናወንና ለማኅበራቸውም ተቀማጭ ገንዘብ ይሰጣል። ማኅበራቱ ተቀማጭ ገንዘቡን ለአባሎቻቸው በብድር በመስጠት ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ እገዛ ያደርጋሉ። ተፋሰሱ ከለማ በኃላም መልሶ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፣ በተለይም በተፋሰሱ ውስጥ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን በመተግበር በተለያየ መልክ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በዚህ መልኩ ታቅዶ እየተተገበረ ባለው በዚህ ፕሮጀክት ከአፋርና ከሶማሌ ክልሎች በስተቀር በተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ሁለቱ ክልሎች በፕሮጀክቱ ያልተካተቱት በሌላ ፕሮጀክት በመታቀፋቸው ነው። ፕሮጀክቱ ከተጠቀሱት ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች መተግበሩ ይታወቃል። ፕሮጀክቱ በተተገበረበት ጊዜ ደግሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ከፍል በነበረው ጦርነት አብዛኞቹ አካባቢዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ ነበሩ።
በዓለም ላይ የተከሰተው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝም በልማት እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ መፈጠሩ አይቀርም። ይህን አስመልክተው አቶ ዮሴፍ እንደገለጹት፤ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ከነበሩት ውጭ የተፋሰስ ልማቱ ሥራ አልተቋረጠም። ኮቪድ በጉዳት ደረጃ የሚገለጽ ችግር አላስከተለም። ፕሮጀክቱ ገና በመሆኑ ወደኋላ የቀሩትም ቢሆኑ ወደፊት ሊሸፈኑ የሚችሉበት እድል ይኖራል። በጦርነቱ ምክንያት ለልማቱ የሚደረገው እንክብካቤ በመቋረጡ፣ዕፅዋቶችም የመቆራረጥና እርከኖችም የመፍረስ ሁኔታ ስለሚያጋጥማቸው ውድመቱ አይቀርም።
በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በሴፍትኔት የሚካሄዱ ፕሮግራሞች ሳይደራረቡ ራሳቸውን ችለው እንዲሄዱ በማደረግ ነው የልማት ሥራው የሚከናወነው። የተፋሰስ ልማት ፕሮግራሙ የሚከናወነው ለክልሎች ኮታ በመስጠት ሲሆን፣ ክልሎች ለወረዳ፣ወረዳ ደግሞ ለቀበሌ በመስጠት በቅደም ተከተል ችግሩ በሚብስባቸው አካባቢዎች እንዲተገበር ይደረጋል። ግብርና ሚኒስቴርም የልማቱ ሥራ በተቀመጠለት የአሠራር ስልትና መርሐግብር መተግበሩን በመከታተልና በመቆጣጠር፣በስልጠናና በተለያየ ድጋፍ ኃላፊነቱን ይወጣል።
የተፋሰስ ልማት ሥራን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው በእቅድ መምራት ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ ክልሎች የየራሳቸውን እቅድ አውጥተው ወደ ሥራ እንደሚገቡም አቶ ዮሴፍ ይጠቁማሉ። እቅዱ የሚመራበት አሠራርም በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር መዘጋጀቱንና ያንን መሠረት በማድረግ ሥራው እንደሚከናወን ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አንድ የተፋሰስ ልማት ከሁለት መቶ ሄክታር ያላነሰ፣በአማካይ ደግሞ ከአንድ ሺ ያልበለጠ ሄክታር ይለያል። ለዚህም የአምስት ዓመት እቅድ ይዘጋጃል። በየዓመቱም ምን ያህል እንደሚከናወን በእቅዱ ይካተታል። እቅዱ በማኅበረሰብ ተሳትፎ ወይንም በፕሮጀክትና በፕሮግራሞች ሊተገበር ይችላል።
የማኅበረሰብ ተሳትፎን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ድጋፍና ትብብር ሲከናወን ከቆየው የተፋሰስ ልማት ውጤታማ ሆኖ የተገኘው በየትኛው ተሳትፎ እንደሆነ አቶ ዮሴፍ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤የፕሮጀክቶች የቆይታ ጊዜ አጭር በመሆኑና ፕሮጀክቱ ሲያበቃም ሥራው እንዲቀጥል በማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ተሞክሮዎች ያሳያሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎ አዋጭነቱ የተሻለ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ለመሬት ለምነት ማጣት፣በጎርፍ ለመሸርሸር በአጠቃላይ ለመሬት መጎዳት የሚያጋልጡ ችግሮች ምን እንደሆኑና በሀገሪቱም ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ አቶ ዮሴፍ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፤በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኝ ‹‹ዋተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር››በተባለ ክፍል በተለይ ተራራማ በሆኑ (ኃይላንድ) አካባቢዎች ላይ ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፣በተለያየ ጊዜ ሌሎች ጥናቶች ሠሰራታቸውንም ተናግረዋል። በእነዚህ ላይ ተመሥርተው በተደራጀ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ጠቅሰው፣ ካለው ተሞክሮ ግን በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ የተጎዱ መሬቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ተራራ የሚበዛባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው። ለአብነትም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላስታ፣ዋግ አካባቢዎች በመሬት መራቆት የተጎዱ ናቸው። የመሬት አያያዝ በተለይም በተደጋጋሚ የሚታረስ መሬት፣የዕፅዋት ሽፋን መመናመን እየከፋ መሄድም ለጉዳት የመጋለጥ እድሉን እንዲጨምር ያደርጋል። መሬቱ ተዳፋታማ ከሆነና የሚያስፈልገው የአፈር ጥበቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ካልተሠራ በአጠቃላይ ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገ መሬቱ ይጎዳል።
እስካሁን በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ በመሬቱ ለምነትና ምርታማነት ላይ ያመጣው ለውጥ በጥናት፣ልማቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ከማኅበረሰብ በተሰበሰበ መረጃና በባለሙያዎች የመስክ ምልከታ መሻሻሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ አቶ ዮሴፍ ይጠቅሳሉ። ለአብነትም ትግራይ፣በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ፣በአማራና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች በተሠራው ሥራ ያገገሙ አካባቢዎች መኖራቸውን ያመለክታሉ። እነዚህ መረጃዎች የተበታተኑ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቅሰው፣ የተደራጀ መረጃ ለመስጠት ግን በጥናት የተደገፈ መሆን ይኖርበታል።ወደፊትም ሰፊ የጥናት ሥራ ይጠይቃል ሲሉ አስታወቀዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራ አንዴ ከተከናወነ በኋላ ወደ ኋላ ሊመለስ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖግ አቶ ዮሴፍ ይገልጻሉ። በ1970ዎቹ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሲጀመር እቅድ የሚነደፈውም ሆነ አጠቃላይ ሥራው በማዕከል ነበር የሚከናወነው ያሉት አቶ ዮሴፍ፣ በወቅቱ በነበረው አሠራርም ብዛት ያላቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ያስቻለ አልነበረም ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በወቅቱ ማኅበረሰቡንም በበቂ ሁኔታ ለማሳተፍም አልተቻለም። ዕቅዱም በባለሙያዎች ነበር የሚዘጋጀው። ይታቀድ የነበረውም በ30 እና 40 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ነበር። የልማቱን ሥራ ለመሥራት የማያስችሉ አንዳንድ እንቅፋቶች ሲከሰቱም የተሠራው የልማት ሥራ የወደመበት አጋጣሚም አለ። ይሄ ልማቱ ወደኋላ እንዲመለስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው።
በሥራ ሂደት አሠራሩ የማያዋጣ ሆኖ በመገኘቱ አሠራሩን መከለስ የግድ እንደሆነም ገልጸዋል። ማኅበረሰብን ያሳተፈ ሥራ ሲሠራ ችግሮች የቱ ጋ እንደሆኑ ማየት ይቻላል ያሉት አቶ ዮሴፍ፣ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ ሲጀመር አቅም መፍጠር መቻሉን ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ሥራ ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶችን መቅረፍ ተችሏል። የጎላ ችግርም አላጋጠመም ሲሉም ያመለክታሉ።
ኃላፊው በክትትልና ቁጥጥር ልማቱን ማስቀጠል ይጠበቃል ሲሉም ያስገነዝባሉ። እንደ እሳቸው ገለጸ፤ በተለይም ማኅበረሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ መሆን ሲችል ውጤታማነቱ የበለጠ ይሆናል። በባለቤትነት ስሜት ስለሚሠራ ልማቱን ይጠብቃል፤ ለመሥራትም ይነሳሳል።
ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በአንዳንድ ፕሮጀክቶች በተከናወኑት የሙከራ (ፓይለት) የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ገቢ በማስገኘት ለውጥ ያመጡ እንዳሉም ይጠቅሳሉ። ጎጃም ውስጥ በፕሮጀክት ድጋፍ ተደርጎላቸው በጣም የተጎዳ መሬት እንዲያገግም በማድረግ ውጤታማ መሆን የቻሉ እንዳሉ በአብነት ጠቅሰው፣ ማኅበረሰቡ የተከናወነው የተፋሰስ ልማት በከብቶች እንዳይጎዳ ማኅበረሰቡም አላአግባብ ዛፍ እንዳይቆርጥ በማድረግ ጭምር ነበር ተሳትፎውን አጠናክሮ የሠራው ሲሉ ያብራራሉ። ይህ በመሆኑም የመሬቱ ምርታማነት ከመጨመሩ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ለከብቶቹ ግጦሽ እና ማገዶም ማግኘት ችሏል ይላሉ። ከልማቱ ጎን ለጎን ከብት ማድለብና ንብ ማነብ ሥራ እንዲሠሩም ዕድል ፈጥሮላቸዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ፤ የልማቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ አምስት ሺ የማኅበረሰብ ተፋሰሶችን ለማልማት ከሁለት ዓመት በፊት በተጀመረውና ለአምስት ዓመት በተቀረፀው ፕሮጀክት፤ማኅበረሰቡ በኅብረት ሥራ ማኅበር ተደራጅቶ እንዲያለማ እየተደረገ ነው፤ ማኅበረሰቡ በፕሮጀክቱ ድጋፍ ተደርጎለት በራሱ አቅዶ እንዲንቀሳቀስ ነው የተደረገው።
ይህም ቀደም ሲል ተስተውሎ የነበረውን የባለቤትነት ማጣት ክፍተት ለመቅረፍ እንደ አንድ ስልት የተያዘ መሆኑን አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል። በተፋሰስ ልማቱ በአማካይ በአንድ ተፋሰስ አምስት መቶ ሄክታር እንደሚሸፈን የጠቆሙት አቶ ዮሴፍ፣ ይሄ በአምስት ሺ የተፋሰስ ማኅበረሰብ ሲሰላ ሽፋኑ ከፍተኛ እንደሆነም አመልክተዋል።
በሌሎች ፕሮጀክቶች የሚከናወነው ሲጨመር ደግሞ ልማቱ ሰፊ ይሆናል ብለዋል። የተፋሰስ ልማት ሥራው በበጋ እንደ እርከን ያለ ውጫዊው ሥራ፣ በክረምት ደግሞ የዕፅዋት ተከላ እንዲሁም በሁለቱም ወቅቶች የሚሠሩ ሥራዎችን በማከናወን ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ እንደሚካሄድበት አስረድተዋል። በተፋሰስ ልማት ሥራው እንደ ጥንካሬና ክፍተት የሚነሱትንም አቶ ዮሴፍ አብራርተዋል።በአንዳንድ አካባቢዎች ልማቱ የሚፈልገውን በቂ ግንዛቤ ይዞ ያለመሥራት አንዱ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሥራውን ለመሥራት የሚያስፈልግ የገንዘብና የተለያየ አቅም በበቂ ሁኔታ አለመኖር ደግሞ ሌላው ክፍተት መሆኑን ይገልጻሉ። የፀጥታ መደፍረስም ለልማቱ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ማኅበረሰቡ ልማቱን እንደ ባህል ይዞ ማስቀጠሉ በጥንካሬ ይነሳል። አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ለልማቱ አስተዋፅዖ አድርጓል። መንግሥትም በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑም ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው። አሁን ወቅቱ የአፈር ጥበቃ ሥራ የሚከናወንበት ጊዜ እንደሆነም ጠቅሰው፣ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ሥልጠናዎች በመሰጠት አጠቃላይ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በጥር ወር ሁሉም ክልሎች ወደተፋሰስ ልማት ሥራ እንደሚገቡም አመልክተዋል።
የዚህ ወቅት ሥራም ፊዚካል የሚባለው ወይም ውጫዊው የልማት ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑም ገልጸዋል። ግብርና ሚኒስቴርም ሥራው በጥራት መሠራቱንና አስፈላጊ ድጋፎችንም ለማድረግ ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ በቦታው ተገኝቶ ክትትል እንደሚያደርግ አመልክተዋል። እንደ ሀገር ለተያዘው ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረትም በጉዳት ከልማት ውጭ የሆነ መሬት የአፈር ጥበቃ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመሬት አቅርቦትን የማሻሻል ሥራ ባለፉት ሦስት ዓመታት መሥራቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴሩ የክትትል ሥራውን ለማጠናከር የመረጃ ቋት ወይንም መሰብሰቢያ ሥርዓት(ዳታቤዝ) መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ በዚህ ዘዴም መረጃ ከሁሉም አካባቢዎች ወደ ማዕከል እንደሚገባ ተናግረዋል። በሀገሪቱ የሚከናወነውን የተፋሰስ ልማት በኮድ (በመለያ) መዝግቦ ለመያዝ ሥራ መጀመሩንም አመልክተዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015