ሀገር ትኩሳት አታጣም..የሆነ ቦታ ላይ ሕመምና ቁርጥማት፣ ውጋትና ወለምታ አያጣትም። ዋናውና ትልቁ መፍትሔ ሊሆነን የሚችለው ነገር ያ ትኩሳት፣ ያ ቁርጥማት፣ ያ ውጋትና ወለምታ በምን ምክንያት እንደተነሳ ማወቁ ነው። ምክንያቱን ሳናውቅ ለሀገራችን የምንሰጣት ኪኒን፣ መነሻውን ሳናውቅ ለሀገራችን የምንሰጣት መድኃኒት ፈውስ አያመጣልንም። ትኩሳቶቻችን እንዲበርዱ ፤የትኩሳቶቻችንን መነሻ ምንጭ ማወቅ አለብን።
እስከዛሬ ዋጋ ያስከፈሉን ችግሮቻችን መነሻቸውን ሳናውቅ መፍትሔ ለመስጠት የሄድንባቸው ርቀት ነው። በየትኛውም መስፈርት ብንለካው የሀገራችን ትኩሳት ፈጣሪዎች እኛው ነን። ሀገር በራሷ አትታመምም። ሀገር በራሷ አትፈወስም። የፈውሷና የስቃይዋ ምንጭ እኛ ዜጎቿ ነን። ሐኪም ሆነን ትኩሳቷን ማዳን አሊያም ደግሞ ወጌሻና አዋቂ ሆነን ችግሯን መጋራት የእኛ ምርጫ ነው። ባተኮሳት ቁጥር መጋኛ ነው እያልን ያልተገባ መድኃኒት የምንሰጣት ከሆነ፣ ወለም ባላት ቁጥር ብርድ ነው እያልን አጥሚት የምናሞቅላት ከሆነ ልንፈውሳት አንችልም። ይልቁንም ሌላ ችግርና ሌላ በሽታን ነው የምንደርብባት።
ትኩሳቶቻችንን ለመፈወስ መነሻ ምክንያቱን ማወቅ ግዴታችን ነው። በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በብዙ ነገር ላይ ታመን ሰንብተናል። ሕመሞቻችን ሌላ ሕመም እየፈጠሩ ዛሬ ላይ ደርሰናል። የሕመሞቻችንን ምንጭ፣ የትኩሳቶቻችንን መነሻ መርምረን የማያዳግም መፍትሔ መስጠት ከመንገዳገድ ያወጣናል ብዬ አምናለሁ። ይሄ ብቻ አይደለም አሁን ላይ እዛም እዚም የምንሰማቸው ለማንገዳገድ የማይበቁ አሉባልታዎች የሻረውን ቁስላችንን እንዳያመረቅዙብን እፈራለሁ። መታከም ካለብን ችግራችንን በሚያደርቅ መድኃኒት ይሁን። ማስታገሻ መድኃኒት አያስፈልገንም..እንደ ሀገር፣ እንደ ማኅበረሰብ የሚያስፈልገን መዳኛ መድኃኒት ነው።
የምንድንበትን ለማወቅ ደግሞ የምንታመምባቸውን ማወቅ አለብን። እንዲህ ሲሆን ነው የምንድነው። አንዳንድ ጊዜ ልንታመምባቸው አቅም በሌላቸው ነገሮች ነው የምንታመመው። አንዳንድ ጊዜ ሊያንገዳግዱን ጉልበት በሌላቸው ነገሮች ነው የምንገዳገደው። ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ታሪክ ያላት ሀገር፣ በብዙ አንድ አይነት ባህልና ሥርዓት የተሳሰረ ማኅበረሰብ ትንሽ ነገር ሲንገዳገድ ሳይ ምን ነካን እንድል ያደርገኛል።
የምንገዳገደው አጽንቶ የሚያቆም የመፍትሔ ሀሳብ ስላልፈጠርን ነው። የምንገዳገደው ሁልጊዜ ስለችግር ስለምናወራና ለችግሮቻችን የሚሆን የውይይት ጠረጴዛ ስለሌለን ነው። የምንገዳገደው በአንድ ሀገር ላይ አንድ አድርጎ የሚያኖር የአንድነት ሀሳብ መፍጠር ስላቃተን ነው። የመንገዳገዳችን ምስጢር ይሄ ነው። ሁሌ የምንታመመው፣ ሁሌ የሚያተኩሰን ለዚህ ነው። ሰው እኮ ልማዱን ነው። ሰው እኮ ያደገበትንና የኖረበትን ነው። ሰው የሚመስለው እኮ ትላንቱን ነው። ትላንታችን ምን አይነት እንደሆነ ደግሞ ሁላችንን የምናውቀው ነው።
የመጣንበት..የኖርንበት ጎዳና አንድ አይነት ነው። ለዚህ ነው በጽናት የሚያቆም የመፍትሔ ሀሳብ ያጣነው። እንንቃ..ትናንሽ ሀሳቦች እንዲያንገዳግዱን ዕድል መስጠት የለብንም። ትናንሽ ችግሮች እንዲለያዩን መፍቀድ የለብንም። ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከሀሳብ በላይ ናት። ትናንሽ ሀሳቦች ሊያንገዳግዷት ከቶ አይቻላቸውም።
በዓለም ላይ ያለ ችግር የሚኖር ሀገር የለም። ሁሉም መጠኑ ይለያይ እንጂ የየራሳቸው የሆነ ችግር..ትኩሳት አላቸው። ዋናው ነገር ግን እንዴት ያን ትኩሳት ማብረድ ቻሉ የሚለው ነው። እኛና ሌሎች ሀገራት /መፍትሔ ተኮር ሀገራት/ የምንለያየው በችግሮቻችን መጠን ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻችን በምንሰጠው ምላሽም ጭምር ነው። እኛ ሀገር ችግር እንጂ መፍትሔ ብዙም ትኩረት አይሰጠውም ። ቢሰጠውም ለችግሩ የሚመጥን አይደለም ።
መቶ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ሁለት መቶ ዓመታትን አስታውሰን — ሩቅ ትላንቶችን በርብረን የምንጋጭባቸው ችግሮች አሉን፤ትላንትን ለትላንት መተው ያቃተን ነን። ትላንትን ለትላንት ብንተወው ዛሬን እንዴት መኖር እንዳለብን አይጠፋንም ነበር። ድሮን ለድሮ ብንተወው ዛሬ ላይ የምንፈልጋትን ሀገር መፍጠር ይቻለን ነበር። ከትላንት ያልወጣ ጭንቅላት ዛሬ የለውም። ከትላንት ያልወጣ አስተሳሰብ ለዘመኑ የሚመጥን ወቅታዊ እሳቤን ማራመድ አይቻለውም። ለዛም ነው በሀሳብ እየወደቅን በችግር የምንቆመው። ለዛም ነው በመፍትሔ እያነስን በችግር የጎለመስነው። ለዛም ነው በለውጥ እየኮሰስን በነውጥ የቀደምነው።
በአንድ ሀገር ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል ፣ጥልቁ ጉዳይ ለችግሩ የምንሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ነው ።እሱ ነው የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊወስን የሚችለው። ያለፉት አራት ዓመታት እንደሀገር በብዙ ነገሮች ላይ የተንገዳገድንባቸው ናቸው። ደግነቱ ግን ተንገዳግደን አልወደቅንም። እንዳንወድቅ ሆነን ቆምን እንጂ። ችግሩ መንገዳገዳችንና አለመውደቃችን አይደለም። ችግሩ ወቅታዊም ሆነ ለነባር ችግሮቻችን አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠታችን ነው።
ኮሮና የአንበጣ መንጋ የአንድ ወቅት ሰሞነኛ ችግሮቻችን ነበሩ። የህዳሴ ግድባችን፣ የግብጽና ሱዳን አተካራ የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ አጀንዳዎቻችን ነበሩ። ከዛ ስንወጣ የሰሜኑ ጦርነት መጣ..ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የአሜሪካና የምዕራባውያን ጫና ተከተለ። በአግዋ፣ በኤች አር 16 አበሳ አየን። ይሄ ብቻ አይደለም የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብና ክልከላ ተከተለ። ይሄ ብቻ አይደለም ጦርነቱን ታኮ የኑሮ ውድነት፣ የታሪፍ ጭማሪ ተከተለ። በሰሜኑ ጦርነትና ይዟቸው በመጣው የምዕራባውያን ጣጣ እየተሰቃየን ሁለት ዓመታትን በመከራ አሳለፍን። ከብዙ ትግል በኋላ ሰላም አገኘን።
ሰላማችንን አጣጥመን ሳንጨርስ የተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ በፈረጀው ሸኔ በወለጋና በአጎራባች አካባቢዎች ብሔር ተኮር የሆነ የንጹሓንን ሞትና እልቂት ሰማን..መስማት ብቻ አይደለም ደጋገምንው። ከዚህ ሕመም ሳናገግም የባንዲራ መሰቀል ጉዳይ ሌላ ትኩሳት ሆኖ መጣ። በዚህ ሳናበቃ በሃይማኖት ጉዳይ አተካራዎችን መስማት ጀመርን። ይህ በእንዲህ እንዳለ ስር የሰደደ የሙስና ጉዳይ ወቅታዊ ዜና ሆኖ ቤታችን መጣ። ትኩሳቷ በማያልቅ ሀገር ላይ ነን..ሌላ ትኩሳት ላለመስማታችን ምንም ማረጋገጫ የለንም።
የሚጠቅመን የትኩሳት ዜና መስማት አይደለም..የሚጠቅመን ትኩሳት የሌለባትን ሀገር ቢኖርባትም ቶሎ የሚሽርባትን ሀገር መፍጠር ነው። እየተንገዳገድን ወዴትም መሄድ አንችልም። መሄድ ያለው በመቆም ውስጥ ነው። ለመሄድ መቆም አለብን..ለመቆም ደግሞ መንገዳገዳችንን መተው አለብን። ላለመንገዳገድ ደግሞ የሚያንገዳግዱን ችግሮቻችንን በመፍትሔ ማስወገድ አለብን። በቃ ይሄው ነው።
ያቃተን ምንድነው? ችግር ፈጣሪ አዕምሯችን መፍትሔ ማምጣት ለምን ተሳነው? እስኪ ወደመፍትሔዎቻችን እንያ..ካስተማሩን፣ ካቆሰሉን ታሪኮቻችን ተምረን አዲስ ዛሬን፣ አዲስ ሀገርን እንሥራ። ሁልጊዜ ሞት፣ ሁልጊዜ መከራ ለምን? ሁልጊዜ አበሳ..ሁልጊዜ ኃዘን ለምን? አጀንዳ እየፈጠርን ሁልጊዜ መናቆር..ሁልጊዜ መገፋፋት ለምን? እስኪ ደግሞ የሰላምና የአብሮነት አጀንዳዎችን እንቅረጽ። እስኪ ደግሞ ሊያስታርቁንና ሊያፋቅሩን የሚችሉ የጋራ ታሪኮቻችንን እናውራ።
ትኩሳቶቻችን ሊድኑ በሚችሉ ነገሮች ላይ ብቻ እናተኩር። እንደ ሀገራዊ ምክክር ሊያግባቡን የሚችሉ ውይይቶች ያስፈልጉናል። ስንወያይ ለመግባባትና የአንድነት ሀሳብ ለመፍጠር እንጂ ትኩሳት ለመፍጠር አይሁን። እኛ ሀገር ካልሆነ በየትኛውም የምድር ክፍል ውይይትን ከሰላም ውጪ ለትኩሳት የሚጠቀም ፖለቲከኛ አላውቅም። እስከዛሬ የተቀመጥናቸው ስብሰባዎች፣ የተወያየናቸው ውይይቶች ሰላም ፈጣሪ ቢሆኑ ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር። ግን ለስብሰባ በተቀመጥን ማግስት ወደ ጦርነት የምንገባ ነን። ተወያይተን አጨብጭበን በጨረስን ማግስት የማይሽሩ ጠባሳዎችን የምንፈጥር ነን።
መማር ከቻልን የመጣንባቸው መንገዶች አስተማሪዎቻችን ናቸው። ማንም ሳይነግረን፣ ማንም ምዕራፍ ሳይጠቅስልን ልንማርባቸው የሚገቡ ብዙ ታሪኮች አሉን። ዛሬ ላይ እነዛን ታሪኮች መድገም ሀገር ከመሸጥ ባንዳነት የሚለይ አይደለም ። የሚያስፈልገን ሰላም ብቻ ነው። የሚያስፈልገን ችግሮቻችንን በውይይት እየፈታን የጋራ ሀገር መገንባት ብቻ ነው። የሚያስፈልገን ሀገራዊ ምክክር፣ ሀገራዊ እርቅ፣ ሀገራዊ አንድነት ነው። የሚያስፈልገን ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ነው።
ለፖለቲካ ንግድም ሆነ ለስልጣን ማራዘሚያነት እየተባሉ እዚህም እዛም የሚፈበረኩ የውሸት ዜናዎች ሀገር ከመጉዳት ባለፈ ፋይዳ ስለሌላቸው ይበቁናል። በብዙ ነገር ላይ ደክመናል። በብዙ ነገር ላይ ታክተናል። አሁን ሰላም ነው የሚያስፈልገን። አሁን እፎይ የምንልበት ፖለቲካና ፖለቲከኛ ነው የሚያስፈልገን። ልማት፣ብልጽግና ነው የሚያስፈልገን። ፍቅር ወንድማማችነት ነው ግድ የሚለን። በእነኚህ እውነት ውስጥ ስንቆም ነው ትኩሳቶቻችን የሚበርዱት..መፍትሔ የምናመጣው።
አንገት እንቅርትና ጆሮ ደግፍ ታክሎበት፤ ሀገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አየር ወለድ ችግሮች ተደራርበውባት አስቧት..? በሁሉም መስክ እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን አስተናግደን ቆይተናል። ወይ እንቅርት ወይ ጆሮ ደግፉ ይበቃናል.. ለሁለት የሚበቃ አንገት እንደሌለ ሁሉ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊም ችግሮች የምትበቃ ሀገር የለችም። ችግሮቻችንን በውይይት እየፈታን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ መከራችንን መቅረፍ ይኖርብናል።
ለመግባባት ከተወያየን፣ ለመስማማት ከተቀመጥን ችግሮቻችን አይከብዱንም። ችግሮቻችን እየከበዱን ያሉት ለመስማማት ስለማንቀመጥ ነው። ትኩሳቶቻችን ሌላ ትኩሳት እየወለዱ የሚያቃጥሉን ለመግባባት ስለማንወያይ ነው። ስንዝር ለማይሞላ አንገት እንቅርትና ጆሮ ደግፍ ምኑ ነው? በኢኮኖሚዋ ዳዴ ለምትል፣ በፖለቲካው ባልበረታች ሀገር ላይ እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ እነዚህ ሁሉ ትኩሳቶች ከአቅሟ በላይ ናቸውና ልናስተውል ይገባል። ሀገር ሰው ናት..እንደ ሰው ናት። ስሜት አላት..ከተቻለ ድህነቷን የሚቀርፍ፣ ኋላ ቀርነቷን የሚያስቀር ሀሳብና ተግባቦት እናውርሳት። ካልተቻለ ደግሞ ለድህነቷ የሚመጥን ትኩሳትን እንጂ ከአቅሟ በላይ የሆነ መከራን አንስጣት።
አንዳንዴ ጭር ሲል አንወድም አይነት እየሆነብን ነው። ጭር ሲል አጀንዳ እየቀረጽን፣ አሉባልታ እየነዛን የሀገርን ሰላም፣ የማኅበረሰቡን መረጋጋት የምናውክ ከሆነ ልክ አይደለንም። መልፋት ያለብን፣ መድከም ያለብን ለሰላም ብቻ ነው። በደቡብ አፍሪካው የሰላም ድርድር በመጣው ሰላም ደስ ያልተሰኙ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉባልታ ሲያሰራጩ ነበር። አሁንም ሰላም ሆኖ የሰላም አየር በሚነፍስበት ሰማይ ላይ አንዳንድ ጭር ሲል አልወድም አይነት ሁኔታዎች እየታዩ ነው።
እኚህ ችግሮች ትኩሳት ከመፍጠር ባለፈ ፋይዳ ስለሌላቸው ሊቆሙ ይገባል። ወቅታዊውና ይዘንው የመጣነው ሀገራዊ ትኩሳት ይበቃናል። ሌላ ትኩሳት ለማስተናገድ የሚሆን አቅም የለንም። ሀገር በመፍትሔ እንጂ በአጀንዳ አትቀጥልም። ሀገር ተቀራርቦ በመነጋገር እንጂ ተራርቆ በመፎካከር አትቀጥልም። ለሀገራችን ሰላም፣ ለሀገራችን አንድነት እጃችን ላይ ካለው ውዱን እናዋጣ። ካለሰላም ቤት የምንሠራበት፣ ሀገር የምናስቀጥልበት ሌላ አማራጭ የለንም። ካለፍቅር ትኩሳቶቻችንን የምንፈውስበት ሌላ መድኃኒት የለንም። በፍቅር ማጣት እንደመጡ ሁሉ የሚድኑትም በፍቅር ነው። ከእንግዲህ የምንለፋውና የምንደክመው ለሰላም ብቻ ነው። ከእንግዲህ የምንታትረው ትኩሳቶቻችንን ለማከም ብቻ ይሁን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015