እንደ ሀገር በየዘመኑ ዋጋ እያስከፈሉን ካሉ ችግሮቻችን ወጥተን ለራሳችንም ሆነ ለመጭው ትውልድ የምንመኛትን የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ቆም ብለን ትናንቶቻችንን በሰከነ መንፈስና አእምሮ መመርመር ይጠበቅብናል። ዛሬ ላይ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ካልቻልን በቀጣይ የተመሳሳይ ችግሮች ሰላባ ስላለመሆናችን ማስተማመኛ ሊኖረን አይችልም።
የሀገራችን ታሪክ በስፋት እንደሚዘክረው፤ በአንድ ዘመን እንደ ሀገር ከፍ ባለ የስልጣኔ/የዕድገት መንገድ ላይ የነበርን፤ የዚያኑ ያህል በተንሰላሰሉ ጦርነቶች የስልጣኔ መንገዳችንን አበላሽተን ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ማሳያ ለመሆን የተገደድን ሕዝቦች ነን። በዚህም የከፈልነው እና እየከፈልን ያለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው።
በተለይም ባለፈው የአገዛዝ ዘመን የነበረው ትውልድ የተቃኘበት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ፤ አስተሳሰቡ የወለደው ድርጊት ከሀገር ይልቅ ሰፈርና መንደርን ፤ማንነትንና ከዚህ የሚመነጭ ክብርን መሰረት ያደረገ መሆኑ ለአሁን ዘመን የሰለጠነ አስተሳሰብ ዋነኛ ተግዳሮት በመሆን ሀገር በሚፈለገው መጠን እንዳትራመድ አስገድዷታል። ይህንን ያገነገነ ታሪክ በመለወጥ፣ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለመጻፍ የተደረጉ ጥረቶችም፤በቀደሙት ችግሮች ላይ ተደርበው ሀገርንና ሕዝብን የበለጠ ዋጋ አስከፍለዋል።
ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ያለውን ሀገራዊ እውነታ ብንመለከት እንኳን፤ በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የነበሩ ትውልዶች፤ በአጣብቂኝ ውስጥ ቆማ የቀረችውን ሀገር ከፍርስራሽ ውስጥ አውጥተው ፤አዲስ በሆነ የጉዞ ምዕራፍ ውስጥ ለማስገባት የሄዱባቸው እልህ አስጨራሽ ትግሎች ያልተጠበቀና ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ፋይዳ አልነበራቸውም።
በእነዚህ የታሪክ ዓመታት ውስጥ በነጻነት እና በዴሞክራሲ ስም የተካሄዱ የአደባባይም ሆነ የትጥቅ ትግሎች ፤ በብዙ መፈክሮች፣ የሕዝብ መሻትና ተስፋዎች ታጅበው፤ ብዙ መስዋዕትነት ቢከፈልባቸውም ፍጻሜያቸው ግን የተጠበቀውን ያህል ሀገርና ሕዝብን አዲስ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ማስገባት አላስቻለም። እንዲያውም “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” የሆኑበት ሁኔታ ተስተውሏል።
ይህ ከትናንት ጥፋቶቻችን ካለመማር የመነጨው ሀገራዊ ችግራችን በለውጡ ማግስት መልኩን ሳይለውጥ፣ በተለመደው መንገድ የለውጡ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ሳንወድ በግድ መክፈል የተገደድነውን ዋጋ እንድንከፍል፤ ሀገርን እንደ ሀገር በከፋ መልኩ የመበተን አደጋ ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል። ዛሬም ቢሆን ለሀገራዊ ነገዎቻችን ተግዳሮት ሆኖ እየፈተነን ይገኛል።
ይህን ዘመን እየተሻገረ የመጣ፤ የትውልዶችን ህልም ቅዥት በማድረግ ፤ በማይፈቅዱት የታሪክ ምእራፍ ውስጥ እንዲያልፉ እያስገደዳቸው ያለው ያለ መስከን ፣ ሰክኖ ትናንትን በሰከነ መንፈስ ያለመመርመር እና ከትናንት ስህተቶች ያለመማር ሀገራዊ ችግር በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ ማብቂያ ሊበጅለት ይገባል። ይህ ትውልድ ለዚህ ችግር ተጨማሪ ዋጋ መክፈል አይጠበቅበትም።
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሀገራዊ ስክነት ወሳኝ ነው። ባልሰከነ ማህበረሰባዊ ስብእና የሰከነ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስርአት መፍጠር አይቻልም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ደግሞ የተለወጠ ሀገርና ሕዝብ ማየት የሚታሰብ አይደለም። ስለ ሀገር ከፍ ያለ ሕልም አልሞ ዋጋ መክፈልም ትርጉም የሚኖረው አይሆንም።
ከዚህ በመነሳት መንግስት የወደፊቷን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚነጋገርበትና በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰራ ወደፊት የሚጓዝበትን ምቹ መደላድል መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያምናል። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ወሳኝ ነው።
ይህ መድረክ እያንዳንዱ ዜጋ በጋራ ጉዳዮቹ ላይ በመነጋገር እና ችግሮቹን በውይይት በመፍታት ለጋራ ዓላማ በጋራ ለመሰለፍ ትልቅ መንገድ እንደሚሆን ይታመናል። የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባትም ትልቅ እድል ይፈጥራል።
ከዚህ አንጻር መላው ሕዝባችን ፤በተለይም ደግሞ በሀገራዊ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ተዋንያን የሆኑ ፖለቲከኞች ፣ የመብት ተቆርቋሪዎች እና ሁሉም የኅብረተሰቡ አካላት፤ ሕዝባችን በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ለከፈለበትና ዛሬም እየከፈለበት ላለው ምኞቱ ስኬት ከሁሉም በላይ መስከንና ሀገርን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ መተባበር፤ ከዚህም አልፎ ችግሮችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ የመፍታት ባህልን በማዳበር በሀገር ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ሊረባረብ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015