ስለትምህርት በተነሳ ቁጥር “ዓለምን መለወጥ የሚያስችል ብቸኛው መሣሪያ ትምህርት ነው” የሚለው የታላቁ የነጻነት ታጋይና የፖለቲካ መሪ የቀድሞው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ አባባል ሳይጠቀስ አይታለፍም። በእርግጥም ትምህርት ሰው ራሱን፣ አካባቢውን፣ አገሩንና ወገኑን ከፍ ሲልም ዓለሙን መለወጥ የሚችልበት ታላቅ ኃይሉ ነው።
ትምህርት ይህንን ኃይሉን የሚያከናውነው ደግሞ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ አድማሱን በማስፋት፣ ዓለምን የሚመለከትበትን ዕይታውን ወይንም አመለካከቱን በማስተካከልና ነገሮችን የመከወን ክህሎቱን በማሳደግ ነው። ይህም የሰው አዕምሮ ችግር ፈች በሆነ አስተሳሰብ እንዲሞላ ስለሚያደርገው አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ብቃትን ያላብሰዋል።
እስካሁን ድረስ ዓለማችን ያለፈችባቸው የዕድገት ሂደቶችና የስልጣኔ ደረጃዎችም የሰው ልጆች በትምህርት አማካኝነት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታትና ለሕይወታቸው መሻሻል አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ ዕሴቶችን በመፍጠር ወደፊት በድል የመጓዝ ውጤቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ ትምህርት የሚጠበቅበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችልና የለውጥ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ይህንኑ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ መቀረፅና ተግባር ላይ መዋል አለበት። በዚህ ረገድ የሩቁን ትተን ከቅርቡ ብንነሳ እንኳን ከዚያ በፊት የነበረው የደርግ መንግሥት የትምህርት ፖሊሲ “ተገቢና ውጤታማ አልነበረም” በሚል አዲስ ፖሊሲ ተቀርጾ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት በእኛ ሃገር ሲተገበር የቆየው ትምህርት ከላይ የጠቀስነውን የትምህርት ዓላማ ማሳካት የቻለ እንዳልነበረ መገንዘብ ይቻላል። እንዲያውም ከትክክለኛው የትምህርት ዓላማ በተቃራኒ ፍሬ ያፈራ ስለመሆኑ አሁን ላይ ሁሉም በሚባል ደረጃ የሃገሪቱ ዜጎች የሚስማሙበት ሐቅ መሆኑን ታዝበናል።
የትምህርት ሥርዓቱ ትኩረት ያደረገው ትክክለኛውን የመማርና የማወቅ መንገድ ተከትለው፣ መማርና ማወቅ የሚገባቸውን ያህል ተምረውና አውቀው፣ በአግባቡ ተመዝነውና ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ብሎም ግብረ ገብና ሞራል ገንብተው፣ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎትም ለመልካም ነገር ለመጠቀም በሚያስችል መንገድ በሥርዓት ታንጸው፣ ተኮትኩተውና በስለውና በቅተው የሚመረቱ ዜጎችን ማፍራት ላይ አልነበረም።
ከዚህ ይልቅ ለሃገር ጥቅም ሳይሆን ትምህርትን ለዜጎች አስፋፋሁና አዳረስኩ በሚል ርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘትና አላፊ ጠፊ ስልጣንን ለማራዘም ፤ከከንቱ ስልጣኔ አስፋፊዎችና ከንቱ ውዳሴ፣ ከታይታ ዕድገት ደጋፊዎች ከውድቀት የማያስጥል ከንቱ ድጋፍ ለማግኘት በሚያስችል ስሁት ቀመር ላይ የተመሠረተ የትምህርት ፖሊሲ ነበር።
በተቃራኒው የፖሊሲው ዋነኛ ትኩረት ተማሩ ለመባል ያህል ፊደልና ክፍል ብቻ ቆጥረው፣ ለይስሙላ ተመዝነውና በግብር ይውጣ ታንጸው ለርካሽ ዓላማ በርካሽ መንገድ ተምረው በብዛትና በስፋት ለገበያ የሚቀርብ “ርካሽ የሰው ኃይል”ን ማምረት ላይ ነበር ማለት ይቻላል። በመሆኑም ፖሊሲው “የግለሰብንና የማኅበረሰብን የአካልና አዕምሮ ተሰጥዖ በማጎልበት ችግሮችን የማወቅ፣ የመፍታት አቅም፣ ችሎታና ዝንባሌ ያዳበሩ ዜጎችን ማፍራት” በሚል ፍልስፍና ላይ የተመሰረትኩ ነኝ ቢልም መሬት ላይ በተግባር የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር።
በዚህ የተነሳም የትምህርት ሥርዓቱ ለብዛት እንጅ ለጥራት እምብዛም ትኩረት አለመስጠቱ የትምህርትን ዋነኛ ዓላማ ግቡን እንዲስትና ችግር ፈችና የፈጠራ አስተሳሰብንና ክህሎትን የተላበሰ ትውልድ ማፍራት እንዳይቻል ደንቃራ ሆኖ ቆይቷል። “ችግሮችን የማወቅ፣ የመፍታት አቅም፣ ችሎታና ዝንባሌ ያዳበሩ” ዜጎችን ሳይሆን በብዛት ችግር የመፍታት አቅምና አመለካከት የሌላቸው በተቃራኒው ያሉ መልካም ነገሮችን መጠበቅ የማይችሉ በመፍትሔ ፋንታ ችግር የሚፈጥሩ ደካማ ዜጎችን ማፍራቱን ነው የተገነዘብነው።
ይህም አሁን ላይ እንደምናየው በአስተሳሰባቸው ምክንያታዊ ያልሆኑ፣በዕውቀታቸውና በችሎታቸው ሳይሆን በማጭበርበርና በሌብነት፣ በሥራቸውና በጥረታቸው ሳይሆን ሌላው በሠራው በአቋራጭ ለማደግ የሚፈልጉ፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ ጥገኛና አቅመ ቢስ የሆኑ፣ የልማት ሳይሆን የጥፋት መሣሪያ የሆኑ ከንቱ ዜጎችን እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ስንፍናውና ሌብነቱም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እጅጉን አታካች ሆኗል። ሌብነት ልምምድ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት የሚወሰድበት አደገኛ ደረጃ ላይ ተደርሷል። የኢኮኖሚ ነቀዝ፣ የዕድገት ነቀርሳ ሆኗል። በዚህም በገጠሩም በከተማውም፣ በተማሪውም በሠራተኛውም፣ በድሃውም በሃብታሙም፣ በነጋዴውም በባለስልጣኑም፣ በገበያውም በፖለቲካውም ሳይሠሩ መብላት፣ አጭበርባሪነት፣ ቀማኛነት፣ ስርቆትና ሌብነት ሥር ሰድዶ ተንሰራፍቷል።
በተለይም የትምህርት፣ የዕውቀትና የስልጣኔ ማዕከል በሆኑት ከተሞችማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እንዳሉት ሌብነትና ሳይሠሩ በልነትና ሕገ ወጥነት ከመጠን በላይ በመንገሡና ሁኔታውን ወደሠርቶ አደርነትንና ሕጋዊነት ለመመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከእኛም አልፋ የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው በውቧ መዲናችን አዲስ አበባማ ነገሩ ከዚህም የከፋ ሆኗል።
አዲስ አበባ የሌቦቿና ቁጥርና ተግባር እጅጉን ከመብዛቱና አታካች ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ ለብዙኃኑ ነዋሪዎቿ እንደከበረ ማዕድን የሚታዩትና “ወርቅ አልማዝ ሆንሽብኝ እኮ” ተብሎ የሚዘፈንላቸው ለማግኘት እንደሰማይ ሩቅ የሆኑት ቤቶቿ ብቻ ሳይሆኑ ከዚያም በላይ የሆኑት እጅግ ብርቅየዎቹ ሰማይ ጠቀስ ፎቆቿ ሳይቀሩ እንደ ውሾቿ ባለቤት አልባ ሆነዋል። እንዲያው በአጠቃላይ ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ ለሆነው የትምህርት ሥርዓትና አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ማኅበረ ፖለቲካ ሥርዓት አባት የሆኑት ታላቁ መሪያችን እንዳሉትና እንዳለሙት ሌብነት ሥራ ሆኗል።
ይህም ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የሌብነት ባለቤት “ከሕጋዊ ባለቤቶቹ” ከዋነኞቹ ሌቦች ወይንም ግለሰቦች እጅ ወጥቶ የማኅበረሰቡ “የጋራ ዕሴት” ወደመሆን እየተሸጋገረ ይገኛል። በየሁሉም ተቋማት ውስጥ እንደማኅበረሰብ ሌብነትን እየተለማመድን እንገኛለን። በመሆኑም ድሮ ሳይሠሩ የሚበሉ ሌቦች ብቻ ነበር የነበሩት፤ አሁን ግን ሳይሠሩ የሚበሉ ብቻ ሳይሆን የሚሠራውን ሰው መርጠው የሚበሉ፤ ተቀምጠው የሚበሉ፣ ሠው በሚሠራው የሚጠቀሙና የሚያድጉ ብቻ ሳይሆኑ የሚሠራን ሰው በተለያየ መንገድ ጠልፈው የሚጥሉ፤ ሠራተኛ ሰው ብቻ ሳይሆን ሥራን ራሱን የሚበሉ በሁሉም መስክ በስፋት እየታዩ ነው።
ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖ ሃገርን እንደሃገር፣ ሕዝብን እንደሕዝብ ከማጥፋቱ በፊት ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ያሻል። መንግሥት እንደመንግሥት መፍትሔ ይሆናል ያለውን በስድስተኛው መደበኛ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ጉባኤው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። ለዚህም ብሔራዊ የፀረ ሌብነት/ፀረ-ሙስና/ ኮሚቴ ተቋቁሞ በአስቸኳይ ወደሥራ እንደሚገባ ተገልጻል።
በተባለው መሠረትም ከሁለት ቀናት በኋላ ዓርብ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ኮሚቴው መቋቋሙ ይፋ ሆኗል። ጅምሩ ይበል የሚያስብል መልካም ጅምር ነው። የኮሚቴው ተልዕኮ ትርጉም ያለው ፍሬ እንዲያፈራ ግን ሁሉም ዜጋ በጸረ-ሙስና ትግሉ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል።ይህን የማድረግ የሞራልም ፤ የዜግነትም ግዴታ አለበትም። ፈጣሪ ኢትዮጵያን፣ ሠርቶ መብላትን፣ እውነትንና ፍትሕን ለዘላለም ይባርክ። አሜን።
ይበል ከሳ
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015