የትኛውም ሀይማኖት የሚያስተምረው የአንደበትን ፍቅር አይደለም። በድርጊት የሚታይ ፣ በስራ የሚተረጎመውን ሰላም ነው። መተሳሰብ፣ መዋደድ፣ መከባበርን የሚገልጹት ቃላት አይደሉም ፤ ተግባር ነው። በተግባር መረዳዳት ነው። ላጣ ለነጣው በማካፈል ፤ ከተረፈን ላይ ሳይሆን ካለን ላይ ቆርሶ ማጉረስ ነው። ካለው ላይ አከፍሎ መስጠት ነው። ዓመታዊ በዓላትን አብረን ተደስተን በጋራ መሳለፍ መቻልን ነው። የምንፈልገውን ነገር ለማድረግም በሃገር ላይ ሰላም እና አንድነት ያስፈልጋል።
ሰላም የጥይት ድምጽ አለመስማት ብቻ አይደለም። መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ ለሌሎች ወገኖቻችንም እኛን የሚያስደስተን ነገር እንዲደረግላቸው ማድረግ ነው። በሌላው መልኩ ደግም በራሳችን ላይ እንዲደርስብን የማንፈልገውን ነገር ሌላውም ላይ እንዳይደርስበት ማድረግ ነው። ይሄ ለሁሉም ሰው የውስጥን ሰላም የሚፈጥር ነው። የሁሉም እምነት ተከታዮች አስተምህሮ ነው። መከባበር ፣ መቻቻል፤ ችግሮችን በንግግር መፍታትና ይቅር ባይነትም የሰላም መገለጫ ናቸው። ስለዚህ ሁላችንም መስራት ያለብን ለዚህ ዓይነቱ ተግባር ነው።
ሰላም በህይወት ስንኖር ልናጣቸው ከማይገቡ ነገሮች የመጀመሪያው ነው። እንኳን ለሰው ልጆች ቀርቶ ለእንስሳትና ለእጽዋቱ ጭምር ሰላም አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ሰላም ሲኖር በዓላትም ደምቀው ይከበራሉ። አንተ ትብስ አንቺ ብሎ በጋራ መብላት መጠጣቱ፣ ሲቸገሩ መረዳዳቱ ፣ የታመመን መጠየቁ፣ ያዘነን ማስተዛዘኑ ሁሉ ይኖራል። በተቃራኒው ሰላም ሲጠፋ ሜዳው ሁሉ ገደል ይሆናል። ነገን አርቆ ማለም ይቀራል ፣ በተስፋ ላይ ተስፋ እንቆርጣለን። ሁሉም ነገር ችግር ብቻ ሆኖ ደስታ ከአጠገብ ይርቃል። ሰውነት ልረፍ ቢል እንኳን ጣፋጭ እንቅልፍ አይገኝም። ስለዚህ ሁልጊዜም ስለሰላም መዘመር ያስፈልጋል። የተገኘን ሰላም ጠብቆ ማቆየት ይገባል። የሰላም ዋጋው ውድ ሲገኝም በጥንቃቄ የሚያዝ መሆን አለበት።
ሰላም በሌለበት ሀገር የሚመጣ ባለሀብት ፣ የሚመጣ ቱሪስት፣ የሚካሄድ ንግድና ኢንቨስትመንት ሁሉ አይኖርም። ወጥቶ መግባት አይቻልም። ሰላም ከሌለ ኢኮኖሚው ይጎዳል፤ ከውጪ ወደ ውስጥ ፤ ከውስጥ ወደ ውጪ የሚገባ የሚወጣም አይኖርም።ይሄም በኑሮ ላይ ከሚያስከትለው የኢኮኖሚ ጫና በተጨማሪ የስነልቦና ጉዳቱ የከፋ ይሆናል። በአጠቃላይ ጤናም ይታወካል። ሰላም ሲኖር ዓመታዊ በዓላትም በደስታና በተድላ ፤ ጣፍጠውና ደምቀው ይከበራሉ። እያንዳንዱ ዜጋ ውስጣዊ ደስታ ይፈጥራል። ውስጣዊ ደስታ ደግሞ በሽታን ያርቃል፤ እድሜን ያረዝማል። ስለዚህ ሰላምን አጠብቆ መሻት ይገባል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መደፍረስ ለመላው ሕዝብ ስጋትን የፈጠረ፣ ደስታን ያራቀ፣ ፍርሀትና አለመተማመን ያነገሰ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። በዚህም ብዙ ዜጎች ከህይወት መጥፋት እስከ ንብረት መውደም ያሉ አስከፊ ጉዳቶችን አስተናግደዋል። ጦርነቱ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው እንዲሁም በማህበራዊ ህይወት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖም ቀላል አልነበረም። የስነልቦና ጉዳቱም ከህሊና ቶሎ የሚጠፋ አይደለም። ይሁን እንጂ አሁን በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው የሰላም ስምምነት ለሀገራችን እፎይታን ሰጥቷል። መላው ሕዝብም በዚህ ደስ ተሰኝቷል። ዓመታዊ በዓል በደስታና በመተሳሰብ ማክበር ተችሏል።
ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ በዓላት በዓል ሳይመስሉ በትካዜና በጭንቀት ማለፋቸውን እናስታውሳለን ። ዛሬ ያንን አስከፊ ያለፈውን ጊዜ በምልሰት በማስታወስ የዛሬውን ሰላም በማመስገን ማክበር ተችሏል። ስለዚህ ለነገው ሰላም መጠንከር የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የጦርነት ቀጣና በነበሩ አካባቢዎች ነዋሪዎች ከማንምና ከምንም በላይ የሰላምን ናፍቆት አይተውታል። የጦርነትን አስከፊነትም ተረድተውታል። ስለዚህ ሰላም በህይወት ስንኖር ልናጣው ከማይገቡ ነገሮች መካከል የመጀመሪያው መሆኑን መረዳት ይገባል። ሰላምን በዋጋ መተመን በወርቅና ብር መግዛት አይቻልም። ሰላምን በጥንቃቄ መያዝ ያለብን የነገአችን ተስፋ ጭምር በመሆኑ ነው። ስለሆነም ሁሌም ከሰላም ጎን ልንቆምና ስለሰላም ልንዘምር ይገባል!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015