የተወለዱት ደሴ ከተማ ዳውዶ የሚባል ሰፈር ነው። አባታቸው ፖሊስ ነበሩ። ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም አላቸው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታውን ጦሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ በቅዳሜ ገበያ ትምህርት ቤት እንዲሁም ዘጠነኛ ክፍልን በሆጤ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ከ10ኛ እስከ 12ኛ ያለውን ደግሞ በወይዘሮ ስህን ትህምርት ቤት በቮኬሽናል ትምህርት ዘርፍ ተከታትለዋል።
አባታቸው በልጅነታቸው ስለሞቱ የቤተሰቡ መተዳደርያ 50 ብር ብቻ ነበር። እድሜቸው ከፍ ሲል የቤተሰቡን ኑሮ ለመደጎምና ለደብተር መግዣ በሚል እንቁላል መነገድ ውስጥ ገቡ፤ የቀን ሥራም ሞካክረዋል።
በ1977 ዓ.ም ብሄራዊ ውትድርናን ተቀላቀሉ፤ ያኔ ገና 17 ዓመታቸው ነበር። የሁለት ዓመት ግዳጃቸውን ጨርሰው ቢመለሱም፣ ነገሮች እንዳሠቡት አልሆንላቸው አሉ። ድጋሚ ወደ ግንባር እንዲሄዱ ጥሪ ተደረገላቸው። እርሳቸው ግን ያንን ማድረግ አልፈለጉም። አካባቢያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። በዚያም ያገኙትን ሁሉ መሥራት ውስጥ ገቡ፤ በአንድ ብር ከ95 ሳንቲምም የቀን ሥራ ሰርተዋል። የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ መኮንን ብርሃኑ።
በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ተደርጎ ነገሮች ሲረጋጉ ወደ ቤተሰባቸው የተመለሱት አቶ መኮንን፣ በደሴ የመምህራን ማሰልጠኛ ገብተው የመምህርነት ስልጠና ተከታትለው በ1984 ዓ.ም በሰርተፍኬት ተመርቀዋል። ከዚያም በ443 ወርሃዊ ደመወዝ በመምህርነት ተቀጠረው ደሴ ዙሪያ ‹‹ግልብጤ›› በሚባል ትምህርት ቤት ተመደቡ።
ዳሩ ግን ትምህርት ቤቱ የፈረሰ በመሆኑና ተማሪም ስላልነበረው 1984 እና 1985 ዓ.ም እንዲሁ ትምህርት ቤት በመመላለስ አሳለፉ። በወቅቱ ብዙ ትርፍ ጊዜ የነበራቸው አቶ መኮንን እቁብ ገብተው ባገኙት 800 ብር ከደሴ እንቁላል ገዝተው ወደ አዲስ አበባ እያመላለሱ መነገድ ጀመሩ። ይህም ብዙም አትራፊ አልሆንላቸው አለ። ከዚያም ደሴ ከተማ ማርዮን በሚባል ጣሊያናዊ ጣውላ አምራች ቤት መስራት ጀመሩ። ቀጥሎም በዚሁ ጣውላ ቤት ጣውላ እያሰነጠቁ ለአካባባቢው ሰው ቡፌ፣ ቡፌ ቁምሳጥን፣ ረከቦትና የመሳሰሉትን በራሳቸው መስራት ውስጥ ገቡ።
ይህ ሁሉ ሲሆን መምህርነቱ እንዳለ ነው፤ በ1988 ዓ.ም በየወሩ 100 ብር እቁብ እየጣሉ 1000 ብር እቁብ አገኙ። በዚህን ጊዜ ጓደኞቻቸውን ጥድ ገበያ የሚባል አካባቢ ወፍጮ እንትከል ብለው አማከሯቸው፤ ዳሩ ግን ሃሳቡን ሳይቀበሏቸው ቀሩ። እሳቸው ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጡም።
በ1990 ዓ.ም ከደሴ በዝውውር ኮምቦልቻ ዙሪያ ‹‹ንባራ ሀገር›› የሚባል ትምህርት ቤት ተመድበው መሥራት ጀመሩ። በቮኬሽናል ትምህርታቸው እንጨት ሥራ ተምረው ስለነበር እንጨት ስራውን አጧጧፉት። ቦርከናን በእግር እየተሻገሩ ግማሽ ቀን አስተምረው ግማሹን ቀን እንጨት ሥራውን ተያያዙት፤ ገበያው ደራ። በ1994 ዓ.ም ትልቅ ማሽን ያለው ቤት በ1000 ብር ተከራይተው ስራውን አስፋፉት፤ ሰው ቀጥሮ መስራት ተጀመረ።
ትዳር መስርተው 1995 ዓ.ም ልዑል የሚባል የበኸር ልጅ አገኙ። ለስራቸው ሲሉ ገጠር ይመላለሱ የነበሩት አቶ መኮንን፣ እየደከማቸው ይቸገሩናም ለመጓጓዣ የሚሆናቸውን ነጭ ሰጋር ፈረስ በ400 ብር ይገዛሉ። ፈረሱን ክረምት ላይ ቀለቡ ሲቸገራቸው ሸጠውት በመስከረም ሌላ ፈረስ ገዙ።
ህዳር 1996 ዓ.ም መምህራን ሙሉ ቀን መሥራት አለባችሁ የሚል አቅጣጫ ወረደ። ይህ ከሥራቸው ጋር አልስማማ አላቸው። በመጨረሻም ቤተሰባቸውን አሳምነው መምህርነቱን ትተው የእንጨት ሥራቸውን አጥብቀው ያዙት።
ጥር 1996 ዓ.ም የዶሮ ጫጩትና የአንድ ቀን የዶሮ ማሳደሪያ አስፈልጎት የከተማው ግብርና ጨረታ አወጣ። እሳቸውም ብዙ ሂደቶችን አልፈው በ57ሺ ብር የጨረታ ሥራ ሠሩ። ይህን እየሰሩ ሚያዚያ ወር ላይ ደግሞ ሌላ ስራ መጣ፤ የንብ ቀፎ የሚሠራ ድርጅት ተፈልጎ አካባቢው ያሉ የእንጨት ባለሙያዎች እንዲሰበሰቡ ይደረጋል። ስራም ይሰጣቸዋል። በዚህ ጊዜ እርሳቸው ሥራቸውን በፍጥነት አጠናቀው አስረከቡ፤ ጥሩ ገንዘብም አገኙበት።
ይህን ስራቸውን ሚዲያዎችም ሰፊ ሽፋን ሰጡት፤ መረጃው ተናፈሰ። ይህን የሰሙ ሰዎች ከወረዒሉ የሽመና መሳሪያ ሥራልን የሚል ጥያቄ አቀረቡላቸው፤ ይህንንም በመስራት ጥሩ ገቢ አገኙ። ዘመናዊ ማረሻ በጨረታ አሸንፈው ሰርተዋል። ይህ ሁሉ ሂደት የገንዘብ አቅማቸው እንዲፈረጥም አረጋቸው።
1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ቫት ተመዘገቡ። አዲስ ዘመን ጋዜጣን ማየት ጀመሩ። አማራ ክልል 1000 ጥቁር ሰሌዳ የሚሰራ ይፈልግ ነበር። በዚህ ጨረታ ተሳትፈው ጨረታውን ቢያሸንፉም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወድቅ ተደረገባቸው፤ ይሁንና ግን ከዚህም የሕይወት ዘመን ትምህርት እንደወሰዱበት አቶ መኮንን ይናገራሉ።
1997 ዓ.ም የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ለቁም ሳጥንና ጠረጴዛ ስራ ያወጣውን ጨረታም በ100ሺ ብር አሸነፉ። ሥራውን በተባለው መሠረት ቢሰሩም፣ በተባለው ልክ ተጠቃሚ መሆን ግን አልቻሉም፤ 20ሺ ብር ሳይከፈላቸው ቀረ።
በአንድ ወቅት ደግሞ ጉምሩክ የመኪና ሽያጭ ለማድረግ ጨረታ ያወጣል፤ እሳቸውም ጨረታውን አሸንፈው ለስራቸው የሚያግዝ መኪና በ25ሺ ብር ገዙ፤ ሥራውም ይበልጥ አደገ። በ1998 ዓ.ም የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ስር የነበረውን 30 አልጋ ያለውን ብሄራዊ ሆቴል በ1ሺ800 ብር ወርሃዊ ኪራይ መነሻ ጨረታ አወጣ። በብዙ ውጣ ውድ ጨረታውን በ2000 ብር አሸንፈው በመጀመሪያ ልጃቸው ሉዑል ሥም ሰይመውት ሥራውን ጀመሩ፤ ሆቴሉ ያለበት ቦታ የመንገደኞች መናኸሪያ ያለበት ስለነበር ገበያውም እየተበረታታ ብር ያገኙበት ጀመር።
1999 ዓ.ም ወርኃ ታህሳስ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የሚሳተፉበት የአንድ ወር ስልጠና ስለነበር ምግብ ለሚያቀርቡ ሆቴሎች ጨረታ ይወጣል። እርሳቸውም በብዙ ፍትጊያ የጨረታው አካል ሆነው ምግብና ለስላሳ መጠጦች ማቅረብ ጀመሩ። ለአንድ ሰው ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እና ሁለት ለስላሳ ብሎም በሣምንት አራት ቀን ሥጋ ወጥ ለማቅረብ በአንድ ሰው በቀን 29 ብር ጨረታ ለ340 ሰው ማቅረብ ጀመሩ። ለዚሁ ሥራም 30 ሰዎችን ቀጠሩ። በዚህም የምገባ እውቅና አተረፉ።
ሁለተኛ ዙርም ተመሳሳይ ጨረታ ወጣ። በዚህ ጊዜ ግን እሳቸውን ለማግለል መፈለጉን አቶ መኮንን ያስታውሳሉ። እሳቸውም ይህን ስለተረዱ ቀድሞ ለአንድ ሰው በቀን 29 ብር ይጠይቁ የነበረውን 25 ብር ቁርስ ፣ምሳ እራት አቀርባለሁ ብለው ጨረታ አስገቡ፤ ብቸኛም ሆነው አሸነፉም። በዚህም ከ1000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ምግብ ማቅረቡን ተያያዙት።
ይህን ስራቸውን ለማጠናቀቅ አራት ቀን ሲቀራቸው ሌላ ችግር የገጠማቸው አቶ መኮንን፣ በሴራ ሥራውን እንዲያቋርጡ መደረጉን ይናገራሉ። ፖለቲካዊ ጫናም ተደርጎባቸው ሥራውን ትተው ወጡ። 1000 ለሚሆኑ ሰዎች ተዘጋጅቶ የነበረው እንጀራም ተረካቢ አጣ። እንጀራውን ቤተክርስቲያን አካባቢ ወስደው ለአቅመ ደካሞች ሰጡ።
የሆነው ሆኖም በሥራው 400ሺ ብር አግኝተው ስለነበር ለሥራ መንቀሳቀሻ አነስተኛ የቤት መኪና በ110ሺ ብር ፣ የመኖሪያ ቤት ደግሞ በ105ሺ ብር ገዙ። ቀሪውን ደግሞ ለባለቤታቸው ስቴሽሪና መሸጫ ሱቅ ለመክፈቻና ለሌላ ዓላማ አዋሉት። መኪናዋም ለሠርግ መከራየት ጀመረች።
በ2000 ዓ.ም ደግሞ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮምቦልቻ ካምፓስ ዘይት፣ ስጋ እና ሌሎች ግብዓቶችን ማቅረብ ጀመሩ። ዩኒቨርሲቲው በ2001 ዓ.ም እንጀራ ለሚያቀርብ ያወጣውን ጨረታ አሸንፈው ለ3000 /ሶስት ሺ / ሰዎች እንጀራ ማቅረብ ጀመሩ፤ በዚህም ጥሩ ገቢ አገኙ። የሆቴላቸውንም ሥራ እየሠሩ መሰል ግዙፍ ድርጅቶችን እየተዋወቁ የሥራ መስካቸውንና የገንዘብ አቅማቸውን አጎለበቱ።
በ2002 ዓ.ም በጨረታ አሸንፈው እየሠሩበት ያለውን ብሄራዊ ሆቴል ሽጡልኝ ብለው ጠየቁ። 400ሺ ብር መግዛት ትችላለህ ቢባሉም፤ አቅማቸው ስላልፈቀደ ቀንሱልኝ በሚል ደጅ መጥናት ጀመሩ። ይህ ግን ሳይሳካ ቀረ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ በከተማዋ ጣና የትራንስፖርት ድርጅት ይዞት የነበረው ሰፊ ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ ገንዘብ ስለነበረበት ጨረታ ወጣ። አቶ መኮንንም በጨረታው ተሳትፈው በ250ሺ ብር 4000 ካሬ ሜትር የሚጠጋ መሬት በርካቶችን አሸንፈው ቦታውን የራሳቸው አደረጉ። ከባንክም ተበድረው የበለጠ ሥራ ይሰሩበት ጀመር። በሂደትም ይህን ቦታ አፀዱት፤ ትንሽ ግንባታ አካሄዱበት። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው በዚህ ቦታ ላይ በኮኮብ ደረጃ የሚመጥን ሁኔታ ሆቴል አስገነቡበት።
ሆቴሉን ‹‹ልዑል መኮንን›› የሚል ስያሜ ሰጡት። ለሆቴሉ የሚመጥኑ ግብዓቶችን ለመግዛት ወደ ቻይና ተጉዘው ከ45 ቀናት በላይ ቆይተው እያንዳንዱን ግብዓት አሟልተው ተመለሱ። ሆቴሉም አስፈላጊዎቹ ሁሉ ተሟልተውለት ስራውን ጀመረ። ይህ ሆቴል የብዙዎች የዓይን ማረፊያ፣ የውጭ ዜጎችም ምርጫ ሆነ። በእርግጥ ሆቴሉ ሲገነባ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከባንክ ተበድረዋል። ሆቴሉ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
ሆቴሉ ሲመረቅ ግን ባለስልጣናት ወይንም ታዋቂ ግለሰቦች እንዳልጠሩ ነው አቶ መኮንን የሚናገሩት። ገንዘቡን ያገኘሁት፤ ለዚህም ደረጃ የደረስኩት ከደሴ፣ ኮምቦልቻና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ሆኜ ነው፤ ማንኛውም ሰው መጥቶ መመረቅ ይችላል በሚል እሳቤ ነበር ይላሉ። እንዳሰቡትም በርካታ ሰዎች ሆቴሉን መረቁት። በኋላ ግን የወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር ወደ ኮምቦልቻ ለሥራ በሄዱ ጊዜ በይፋ እንዲመርቁት ተደርጓል።
እነዚህ ሁነቶችና ሂደቶች አልፈው ስራቸውን ማቀላጠፉን ተያይዙት። ዳሩ ግን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነትና በአካባቢው በተፈጸመው ወረራ ልዑል መኮንን ሆቴል ቀዳሚ ዒላማ ተደረገ፤ ቀደም ሲል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የሀገር መከላከያ መኮንኖች ያርፉበት ስለነበር ጭምር ነው ወራሪዎች ኢላማቸው ያደረጉት። በወረራው ከህንፃው በስተቀር ሆቴሉ ሙሉ ለሙሉ ተዘረፈ፤ ንብረቱ ወደመ።
አቶ መኮንን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌላ ስፍራ ሸሹ። ከምቦልቻ በመንግስት ሀይሎች ነጻ ወጥታ ሁኔታዎች ሲረጋጉ እሳቸውም ወደ አካባቢው ተመልሰው ስራቸውን ያቀላጥፉት ጀመር። አቶ መኮንን ሆቴሉ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩበትም፣ ሰላም ከመጣ ዕዳው ገብስ ነው ብለው መትጋታቸውን ቀጥለዋል።
በጦርነቱ ብዙ ሚሊዮን ብር ያጡት አቶ መኮንን፣ መንግስት ጉዳዩን እንዲመለከተው በተደጋጋሚ እየጠየቁ መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይም ጉዳቱ የከፋ መሆኑን በመጥቀስም ባንኮችም የብድር አከፋፈልና ብድር ሥርዓቱን መከለስና መመልከት እንዳለባቸው ይጠይቃሉ። ይህም ሆኖ አሁንም በሥራቸው ላይ እየተጉ ነው።
አቶ መኮንን በዚህ ብቻ አላበቁም ። 35 ሚሊዮን በሚጠጋ ብር የገዙት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አላቸው። ነገ የተሻለ እንደሆነም ይገልፃሉ። በአሁኑ ወቅት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስመንት እያካሄዱ ነው። በቀጣይም ብዙ ሥራ ለመሥራት ራእዩ አላቸው።
ከእንግዲህ በኋላ ለሀገሬ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት አስባለሁ የሚሉት አቶ መኮንን፤ ብዙ ውድቀትና መነሳት ቢኖርም፣ ነገ የተሻለ ነገር አለ በሚል ፈተናዎችን አልፈዋል። በቀጣይ ግን ብዙ ያልማሉ፣ ይተልማሉ። በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ ዕድል መፍጠር፣ ለመንግስትም ከፍተኛ ግብር ከፋይ መሆን ፈልገዋል። በኢንቨስትመንትም ቢሆን የሀገሪቱን ችግር የሚፈቱ ችግሮች ላይ መሳተፍ የሁልጊዜ ህልማቸው ነው።
በቀጣይ ግን ከሁሉም በላይ ስለሠላምና አንድነት መሥራት አለብን የሚለው ከእግር እስከ ፈረስ፣ ወታደርነት እስከ መምህርነት ከመምህርነትም እስከ ሚሊየነርነት የተጓዙት የረጅም ህልም ባለቤቱ የአቶ መኮንን ብርሃኑ መልዕክት ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም