ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫ የሠራው የፈጠራ ባለሙያ

ወጣት ታምሩ ካሳ ይባላል፡፡ ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ነው፡፡ በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮኒክ የትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማውን አግኝቷል፡፡ የፈጠራ ሥራዎች እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል አንዱ አትክልትን በዘመናዊ መንገድ ውሃ ማጠጣት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ለእዚህ ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫም ‹‹ስማርት ጋርደንት ወተሪንግ ቴክኖሎጂ›› የሚል ስያሜ ሰጥቶታል፡፡

ወጣት ታምሩ፤ የፈጠራ ሥራ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነው፡፡ የፈጠራ ክህሎቱን ተጠቅሞ የሚሰራቸውን የፈጠራ ሥራዎች በየጊዜው እያሳደገ መጥቶ አሁን ብዙ የፈጠራ ሥራዎችና ሃሳቦች እንዲኖሩት ማድረግ እንደቻለም ይገልጻል። ከእነዚህም ውስጥ በሁለቱ የፈጠራ ሥራዎቹ እውቅናና የባለቤትነት መብት አግኝቷል፡፡

እውቅናና የባለቤትነት መብት ካገኘባቸው ሥራዎች መካከል የመጀመሪያ የሠራው በ2010 ዓ.ም የሠራው የአስተያየት መቀበያ ሲሰተም /ዌስት ቤዝድ ሰጀሽን / ነው። ይህ የፈጠራ ሥራ ሰዎች አስተያየታቸውን በአስተያየት መስጫ ላይ መጻፍ ሳይጠበቅባቸው በድምጽ /ተናግረው/ አስተያየት መስጠት የሚያስችላቸው ነው፡፡ ማየት የተሳነው ወይም መጻፍ የማይችል ሰው ቴክኖሎጂውን በእጁ ነክቶ አስተያየቱን እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡

ይህ ሲስተም ከኮምፒዩተር ጋር የተያያዘ ነው፤ ለ15ሺ ሰዓት የሚሰጡ አስተያየቶች መዝገቦ መያዝ ይችላል፤ የመሥሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በእጅ ስልኩ ላይ የአስተያየቱን መልዕክት በመቀበል ግብረ መልስ መስጠት ያስችለዋል። በተጨማሪም በሁለት መልኩ ተግባቦትን መፍጠር የሚያስችል ሲሆን፤ ለምሳሌ ድሬዳዋ ያለ ሰው አዲስ አበባ ላለው መሥሪያ ቤት አስተያየት መስጠትም የሚችልበት ነው። በተመሳሳይ አዲስ አበባ ያለ ሰው ደግሞ ድሬዳዋ ላለው አስተያየት መስጠት ያስችለዋል፡፡

ሲስተሙ የራሱ የቴሌግራም አድራሻም አለው፤ ሁለት ዓይነት አገልግሎቶችንም ይዟል፡፡ አንደኛው ድምጹ የሚቀርጽበት ሳጥን ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከመሥሪያ ቤት ውጭ ባለበት ቦታ ሆኖ የሚፈልገውን ለመጠየቅና አስተያየት ለመስጠት የሚያስችለው ነው፡፡

ሁለተኛው የፈጠራ ሥራውና የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ ርእሰ ጉዳይ የሆነው ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫ ሲስተም ነው፡፡ ታምሩ ይህን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት መነሻ የሆኑት በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀስ አትክልቶችን ውሃ ለማጠጣት ሥራ ላይ የዋሉት የአትክልት ማጠጫ መንገዶች መሆናቸውን ይገለጻል፡፡

‹‹በትላልቅ መኪናዎች አትክልት ውሃ እንዲጠጣ የሚደርግበት መንገድ ከፍተኛ የውሃ ግፊት መጠን ያለው ነው፤ ይህም ከፍተኛ የውሃ ብክነት ያስከትላል፤ አትክልቶቹ ውሃ ከጠጡ በኋላ የሚፈሰው ውሃ ከአትክልት ሥፍራው አልፎ አስፓልት መንገድ ላይ ሲተኛ እመለከት ነበር፡፡ ተክሎች ሁሉም ተመሳሳይ ባሕሪ ስለሌላቸው መኪናዎች የሚለቁትን ውሃ መሸከም የማይችሉ አሉ፤ የውሃ ግፊት ከፍተኛነት ተክሎቹን እስከ መንቀልና አፈሩንም ጠርጎ እስከ ማንሳት የሚደርስ ችግር ያስከትላል›› ሲል ያብራራል፡፡

‹‹ይህንን ሁሉ ስመለከት የውሃ ግፊቱን ቀንሶ ውሃ ማጠጣት የሚቻልበትን ዘዴ ስለመፍጠር ማሰብ ጀመርኩ፤ ብዙ ሳወጣ ሳወርድ ቆይቼም መፍትሔ ይሆናል ያልኩትን ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫ ሲሰተም መሥራት ቻልኩ›› ይላል፡፡

እሱ እንዳለው፤ የእሱ ፈጠራ የሆነው አዲሱ ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫ ሲሰተም ግን ተክሎቹ ውሃ ሲያስፈልጋቸው እንደየባሕሪያቸው ውሃ ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ሳርና ዛፍ የሚፈልጉት የውሃ መጠን እኩል አይደለም። አዲሱ ሲሰተም አስፈላጊው የውሃ መጠን ለሚፈለገው ተክል እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፤ የውሃ፣ የጊዜና የጉልበት ብክነትንም ያስቀራል፡፡

ወጣት ታምሩ እንዳብራራው፤ በዓለም ብዙ ዓይነት የአትክልት አጣጣጥ ዘዴዎች አሉ፡፡ እነዚያን ዘዴዎች በሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ አይቻልም፤ አሁን ሥራ ላይ ያሉት በከባድ ተሽከርካሪ በመጠቀም አትክልት ውሃ እንዲጠጣ የሚደረግባቸው መንገዶች አማራጭ በማጣት ሥራ ላይ የዋሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎች በውጭ ሀገሮች እንዳሉ ቢታወቅም ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ በጀት የሚፈልጉ በመሆናቸው ተደራሽ ለማድረግ እጅግ ይከብዳል። በመሆኑም እነዚህ ከውጭ የሚገቡትን ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ በመተካት እዚሁ መሥራት ይቻላል በሚል ሃሳብ ቴክኖሎጂውን እዚሁ መሥራት ተችሏል፡፡

‹‹ይህን ቴክኖሎጂ ከውጭ ከምናስገባ በሀገር ውስጥ ለምን መሥራት አንችልም በሚል በተደጋጋሚ ሙከራዎች በማድረግ እዚሁ መሥራት እንደሚቻል ማሳየት ቻልኩ። የፈጠራ ሥራው አሁን ካለው የከተማዋ ውበትና ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የራሱ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል በመሆኑ እድሉን አግኝቼ ሰርቼ በምችለው ልክ አስተዋጽኦ ማበርከት እፈልጋለሁ›› ሲልም አመልክቷል፡፡

ዘመናዊ የአትክልት ማጠጫ ሲስተሙን በ2010 ዓ.ም መሥራት የጀመረውና በዚያው ዓመትም ከአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት መብት እውቅና ያገኘው ወጣት ታምሩ፤ በ2011 ዓ.ም በአንበሳ ግቢ ፊት ለፊት በገንዘብ ሚኒስቴር አጥር ስር ሙከራ አድርጎ ለአንድ ዓመት አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉንም ይገልጻል፡፡

ወጣት ታምሩ እንደሚለው፤ የአረንጓዴ ሥፍራ ውሃ ማጠጫው ከ50 ዓመት በላይ አገልግሎት መስጠት ይችላል። ሲሰተሙ በመሬት ውስጥ የሚዘረጋ ነው፡፡ በዚህም አትክልቶችን በአጠቃላይ አረንጓዴ ሥፍራዎችን በቀላሉ ውሃ ማጠጣት ያስችላል፡፡ ሲሰተሙ ውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች(ታይቶችን) እና የተለያዩ የውሃ አፈሳሰስ ሂደትን መወሰን የሚችሉ ቁሶችን በመጠቀም ይሰራል፡፡ እነዚህ የውሃ አፈሳሰስ ሂደት የሚወሰኑት ቁሶች 180 ዲግሪ፣ በ360 ዲግሪ እየተሽከረከሩ በራሳቸው ውሃ የሚያጠጡ ነው፡፡

የመሬቱን ቅርጽ ታሳቢ በማድረግ የአጠጣጥ ሁኔታውን መወሰንም ይቻላል፡፡ እንደየቦታው የአጠጣጥ ቴክኒኩ የተለያየ ሲሆን፣ የኳስ ሜዳዎችና የአስፓልት ግራና ቀኝ ቦታዎች የሚጠጡበት ሂደት ይለያያል፡፡ ለዚህም የተዘጋጁ ከ15 በላይ የውሃ አጠጣጥ ቴክኒኮች አሉት፡፡ እነዚህን ቴክኒኮቹ መጠቀም የውሃ ብክነትን መቀንስ ያስችላሉ። በዚህኛ ቴክኒክ ደግሞ ምንም ዓይነት የውሃ ብክነት አይኖርም፡፡

መስተካከል ያለባቸው ቦታዎች ካሉ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ተመሳሳይ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የተለያየ ባሕሪይ ያላቸው ተክሎች ቢኖሩና ልዩነት ቢኖራቸው አንዱ ጋ በማንጠባጠብ ሌላኛው ጋር ደግሞ በከፍተኛ ግፊት ውሃ መጠጣት ካለባቸው እነዚህን ማስተካከል እንደሚቻል ይገልጻል፤ በዚህ ምክንያትም አላስፈላጊ የሆነ ግፊት እንደማይኖር ገልጿል፡፡

የፈጠራ ሥራው ለአትክልቶቹ ያለውን ፋይዳ አብነት ጠቅሶ ሲያብራራም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አሁን እየተተከሉ ያሉ ዘንባባዎች ሥራቸው ወደ መሬት በጣም ጠልቆ ስላልገባና ገና ሥር ያልሰደዱ እንደመሆናቸው በከፍተኛ የውሃ ግፊት ሊጎዱ ይችላሉ ሲል ተናግሯል፤ ተክሎቹ አካባቢውን እንዲላመዱ የሚያደርጉ ፈሳሽ ማዳበሪያዎች ከውሃ ጋር ቀላቅሎ ለመስጠት እንዲቻል አትክልቶቹ የሚጠጡበትን ቴክኖሎጂ ከውሃ ቋቱ ጋር በማገናኝነት ቶሉ ስር እንዲይዙ ማድረግ እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡

እንደ ታምሩ ገለጻ፤ ዘመናዊ የውሃ ማጠጫ ሲስተሙ መሬት ውስጥ የሚዘረጋ እንደመሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያ ቋት /ታንከር/ መሬት ውስጥ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ሲስተሙ አትክልቶቹ ውሃ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ከማጠራቀሚያው እየቆጠበ ወደ መስመሩ ይልካል፡፡ ውሃ በሌለባቸው ቦታዎች ታንከር እንዲኖር የግድ ስለሚል ልክ እንደ ነዳጅ ታንከሩ መሬት ውስጥ ተቀብሮ በውሃ ይሞላል፡፡

ታንከሩ ውሃ ሲጨርስም በተገጠመለት ሲስተም መሠረት አንድ ሺ ሊትር ውሃ ሲቀረው ውሃ የሚያቀርበው መኪና ውሃ እንዲያመጣለት ለሹፌሩ ወይም ለሥራ አስኪያጁ ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡ ውሃ ባለባቸው ቦታዎች ደግሞ ታንከሩ መጠባበቂያ ይይዛል፡፡ ልክ ውሃው እያለቀ ሲመጣ ከዋናው መስመሩ ይሞላል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከፍተኛ ግፊት በመጠቀም የሚደረግ የውሃ ማጠጣትም ሆነ የትራንስፖርት ምልልስ እንዳይኖር ስለሚያደርግ በብዙ መልኩ ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በተገጠመለት ሲሰተም ዩኒት አማካኝነት በታዘዘው መሠረት ውሃ ያጠጣል፤ ለዚህ የሚሆን የቀንና የሌሊት ጊዜ ማስመረጫ ሲሰተም እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ‹‹እኛ ውሃ እንዲያጠጣልን በምንፈልገው ጊዜና ሰዓት መሠረት በየቀኑ ከስንት እስከ ስንት ሰዓት ማጠጣት እንዳለበት ከሞላን በዚያ መሠረት ትዕዛዙ ይፈጽማል›› ሲል ታምሩ ያብራራል፡፡

በተለይ አትክልቶቹ ውሃን ሌሊት ላይ የሚጠጡ ከሆነ ውሃ በትክክል ስለሚያገኙ ውሃው ለተፈለገለት አላማ እንዲውልና ተኖ እንዳያልቅ ያደርጋል የሚለው ታምሩ፤ ይህ ሲስተም ተግባራዊ ሲደረግ ውሃ ለማጠጣት የሚወጣ ጊዜ እና ጉልበት እንደማይኖርም ተናግሯል፤ ውሃ በማጠጣት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ሙሉ ጊዜያቸውን ለሌላ የአትክልት እንክብካቤ ሥራ እንዲያውሉ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ሲል ተናግሯል።

ታምሩ እንደሚለው፤ ሲሰተሙን ለመዘርጋት የተለያዩ ሳይቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ውሃ በሌለባቸው ቦታዎች ላይ /ሁሉም ሳይቶች በአንድ ጊዜ ስለማይጨርሱ/ በሁለት መኪናዎች ውሃ መሙላት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ ሳይቶች የሚያስፈልጉ ሲሆን፣ ፊት ለፊት እይታ ላይ የሚውሉ 15 ሳይቶች ግን ያስፈልጋሉ፡፡

ሲሰተሙ በአራዳ ክፍለ ከተማ አረንጓዴ ልማት፣ ጽዳትና ውበት አማካኝነት በገንዘብ ሚኒስቴር አካባቢ ባለ መናፈሻ ቦታ መፈተሹን የሚያስታውሰው ታምሩ፣ ቦታው ከሲሰተሙ ጋር ሊሄድ የሚችል ሙዚቃ ጭምር እንዲኖረው በማድረግና ሰዎች የሚዝናኑበት እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ እንደነበርም ያስታወሳል፡፡

ይሄኛው ሲስተም ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መልዕክቶች 24 ሰዓት ለማስተላለፍ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነም ይገልጻል። ሲስተሙ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ወደ አካባቢው የሚመጡ ሰዎች ባዩት ነገር ስለመደሰታቸው በየጊዜው አስተያየታቸውን ይገልጹለት እንደነበር ተናግሯል፡፡

እሱ እንዳብራራው፤ የሲስተሙ ሁሉም አካላት በሀገር ውስጥ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ጥገናዎች ቢያስፈልጉ በቀላሉና በፍጥነት ሊጠገን ይችላል፡፡ አብዛኛው መሠረተ ልማቱ መሬት ውስጥ የተቀበረ በመሆኑም የሲስተሙ ደህንነት የተጠበቀ ነው፡፡ ቱቦዎቹ ከፕላስቲክ የተሰሩ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ቶሎ የማይበላሹ በመሆናቸው ለረጅም ጊዜ ያገለግላሉ፡፡

ይህ ሥራ እየተካሄደ ካለው የከተሞች ልማት ጋር ተያይዞ አካባቢን ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ‹‹ስማርት ጋርደን ወተሪንግ ቴክኖሎጂ›› መሆኑን አመልክቷል። ስማርት የተባለበት ዋንኛ ምክንያትም መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሉና ዘመኑን የሚዋጅ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውብትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የሚመለከታቸው አካላት የፈጠራ ሥራውን መመልከታቸውን አስታውቆ፣ አብረው ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውንና እሱም የንድፍ ሃሳብ(ፕሮፖዛል) ማቅረቡን ይገልጻል፡፡

አሁን ሥራ ላይ ያለው ውሃ የማጠጫ መንገድ ቦቴ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁሞ፣ ውሃ የሚያጠጡ አካላት ማጠጣታቸውን ሪፖርት የሚደረጉ ቢሆንም አትክልቱ በትክክል መጠጣትና አለመጠጣቱ በግልጽ አይታወቅም ብሏል፡፡ በአዲሱ ሲሰተም ግን የአረንጓዴ ሥፍራው ውሃ ስለመጠጣትና አለመጠጣቱ ለሚመለከተው አካል በቀላሉ በሚተላለፉ መልዕክቶች አማካይነት እንደሚታወቅ ተናግሯል፡፡

የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየጨመረ ቢሆንም የውሃ እጥረት እያጋጠመ መሆኑ ይስተዋላል የሚለው ታምሩ፣ ይህ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲሆን ውሃ ከመቆጠብም በላይ ብዙ ቦታዎችን ተደራሽ ማድረግ ያስችላል ብሏል፡፡ ለአንድ ሳይት ምን ያህል ሊትር ውሃ ይበቃል፤ በዚያ አካባቢ ምን ዓይነት እጽዋት አሉ? እጽዋቱ በስንት ደቂቃ ልዩነት መጠጣት አለባቸው የሚሉትን መወሰን እንደሚቻል አስታውቋል፡፡

‹‹የፈጠራ ሥራውን ብቻዬን ብስራም ከጎኔ ሆነው በሃሳብ እገዛዎችን የሚያደርጉልኝ ግለሰቦች አሉ›› የሚለው ታምሩ፤ ይህንን ሲስተም በትንሹ ሰርቶ ለማሳየት በ150 ሊትር ውሃ በመጠቀም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመመኮር ማሰቡን ይናገራል፡፡

‹‹አሁን በፈጠራ ከተሰሩት ሥራዎች ያልተሰሩት ይበልጣሉ፤ ገና በጣም ብዙ መሥራት የምንችላቸው ነገሮች አሉ›› የሚለው ታምሩ፣ በአካባቢው ላይ ከሚያያቸውና ከሚያስተውላቸው ችግሮች ተነስቶ ለችግሮች መፍትሔ ማመንጨት የፈጠራ ባለሙያ ሥራ መሆን አለበት ይላል፡፡ ‹‹ወደፊት የማውጣቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፤ ባለሙያዎች እርስ በርሳቸው በመደጋገፍ ብዙ ለሀገር የሚበጁ የፈጠራ ሥራዎች መሥራት ይችላሉ›› ሲል አስታውቋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You