የቡናን ምርታማነት የሚያሳድግ አዲስ ምዕራፍ

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተወዳጅ የሆነው አረቢካ ቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ቡናን ለዓለም ያበረከተች ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ቡና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት በመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀስ ነው። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገሪቱ ለቡና ተስማሚ የሆነ አምስት ነጥብ 47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት፣ ምቹ ሥነ ምህዳር፣ በቂ የሰው ጉልበት ያላት፣ በልዩ ንጥረ-ነገር ይዘታቸውና ጣዕማቸው በዓለም እጅግ ተወዳጅ የሆኑ የቡና ዝርያዎች ባለቤት መሆኗ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ያላትን ደረጃ ከፍ እንደምታደርግም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹ባለፉት ስድስት ዓመት ቡናን ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር አስተሳስረን በመትከላችን ምርታችን የቡና ምርት በየዓመቱ በ100 ሺህ ቶን እየጨመረ መጥቷል። በባለፈው የበጀት ዓመት በቡና የውጪ ንግድ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች›› ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት ብዛትና ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዷል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 115 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 520 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በእነዚህ ሦስት ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን የሁለት ቢሊየን ዶላር ገቢ ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል አመላካች መሆኑ ተጠቁሟል።

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የቡና ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና ወደ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተፈላጊነት ማሳደግ የሚያስችል ብራንድ የማስተዋወቅ ሥራ በሰፊው መሥራት በመቻሉ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ማስቻሉን ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ የቡና ገበያ መዳረሻ ሀገራት ጀርመን፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጂየምና አሜሪካ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና ጆርዳን የኢትዮጵያን ቡና በስፋት የሚገዙ ሀገራት እየሆኑ መምጣታቸውን የባለሥልጣኑ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ሀገሪቱ ቡና በማምረትና ለዓለም ገበያ ተደራሽ እያደረገች የምትገኘው በአብዛኛው በቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡናውን በማልማት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ ኢንቨስተሮች በልማቱ ተሰማርተዋል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሚድሮክ ኢንቨስት መንት ግሩፕ ነው። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሀገሪቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ሲሆን፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ፣ በቡናና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። በርካታ የቡና እርሻዎች ያሉት ሲሆን፣ ቡና ከመትከል ጀምሮ በማልማትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል። የቡናን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የተለያዩ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱንም የድርጅቱ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ባለፈው ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው ኒውማን ካፌ ግሩፕ ጋር ያደረገው ስምምነትም የዚሁ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው። ስምምነቱ ቴክኒካል ድጋፍና የገበያ ተደራሽነት ላይም ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተመላክቷል። ኒውማን ካፌ ግሩፕ መሠረቱን ጀርመን ያደረገ፣ 60 ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈና በ30 ሀገራት በቡና ገበያ የሚታወቅ ድርጅት ነው።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ትልቅ እምርታ የሚፈጥር ነው። ስምምነቱን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ እንደነበረ ገልጸው፤ በተለይ በቡና ዘርፍ ላይ ትልቅ ሥራዎችን ከሚሰራው ዓለም አቀፍ ተቋም ኒውማን ካፌ ግሩፕ ጋር የተደረገ ስምምነት መሆኑ የኢትዮጵያን ቡና ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

ስምምነቱ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግና የበለጠ ተሞክሮ ለመውስድ ያስችላል። ኒውማን ካፌ ግሩፕ በቡና ገበያው ላይ ያለውን ልምድ ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማጋራትና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ገበያው ላይ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፤ ስምምነቱን ያደረገው ኒውማን ካፌ ግሩፕ ኢትዮጵያን ከልቡ የሚወድ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ መክፈት ብቻ ሳይሆን የኮፊ ፋውንዴሽን ያለው (የአርሶ አደር ማህበራት የሚረዳ) ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ ብራዚል ውስጥ ሰፊ የቡና እርሻ ያለውና በሄክታር 25 ኩንታል ቡና የሚያመርት የቡና እርሻ ባለቤት ነው።

የኒውማን ኮፌ ግሩፕ በቡና ምርቱ ከሚታወቁ ድርጅቶች መካከልም አንደኛው ነው። የቡናን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ለአፍሪካ ሀገራት ቴክኒክ ድጋፍ እያደረገም ይገኛል። ይህም የአፍሪካ ቡና አመራረት ስለሳይንሱ በእጅጉ እንዲያውቅ አድርጎታል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ድርጅቱ አፍሪካ ውስጥ በኡጋንዳና ኬንያ ከአፍሪካ ውጭ ደግሞ በቬትናም ሰፊ የቡና እርሻ ያለውና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ነው። በገበያ ተደራሽነቱም ሰፊ የሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ፣ አውሮፖ፣ በደቡብ ኤዥያ በሚገኙ ከ30 ሀገራት በላይ ትላልቅ ድርጅቶች አሉት። በመላው ዓለም ትላልቅ ድርጅት ካላቸው ሀገራት ጋርም የገበያ ትስስር አለው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ስቶክ ማርኬቶች ላይም አተኩሮ ይሰራል።

ይህንን ድርጅት የተለየ የሚያደርገውና ከሚድሮክ ጋር የሚያገናኘው አንዱና ዋንኛ ጉዳይ ልክ እንደ ሚድሮክ ኩባንያ ባለቤት ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ሚስተር ኒውማን የቤተሰብ ድርጅት መኖሩ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጸሚው፤ ‹‹ስምምነቱ ቤተሰባዊ ግንኙነቱን አጠናክረን ፤ ቤተሰብ ለቤተሰብ ተስማምተን አላማችንን የጋራ መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ እኛ የሚጎድለንን እነርሱ እንዲሸፍኑልን ማድረግን ያለመና ለረጅም ጊዜ ስንፈልገው፣ ስንሞክረው የነበረ ነው›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 45 ድርጅቶችን በኃላፊነት እንደሚያስተዳድር የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ በአግሮ ፕሮስሲንግ ሥር ከሚነሳው ዘርፍ አንዱ ቡና ብዙ ተግዳሮት እንዳለበት ጠቁመዋል። ይህንን ችግር መሻገር ፈተና ሆኖበት መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ቡናን በተሻለ ዋጋ በዘላቂነት ለማቅረብ የተለየ ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅ አመልክተው፣ ይህንን ሥራ በራስ መሥራት ስላልተቻለ ጠንካራ አጋር ፍለጋ መገባቱን ይናገራሉ። ለዚህም ሲል ሚድሮክ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ከኒውማን ኮፊ ግሩፕ ስምምነት መፈጸሙን ይገልጻሉ። ይህ ድርጅት አፍሪካን እንዲሁም ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህም የተፈለገው ዓላማ ግብ እንዲመታ ለማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑ እምነቱ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከቡና ጋር ተያይዞ የሚነሱት ጉዳዮች ዋነኛው የዋጋ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል። ቡና መሸጥ ባይከብድም እንዴት በምን ያህል ዋጋ ተሸጠ የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገር ደረጃ ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ የሚገኘው ገቢ በጣም ማደጉን ጠቅሰው፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግን በዚያ ደረጃ እንዳላደገ ይገልጻሉ። በመሆኑም ሜድሮክ የቡና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸው፣ ይህን ለማድረግ ብዙ ቴክኖሎጂዎች ቢሞከርም የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል። ከኒውማን ካፌ ግሩፕ የተደረገው ስምምነት ቴክኒካል ድጋፍ የሚያስገኝና በገበያ ተደራሽነት ላይም ትኩረት ያደረገና ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

ሚድሮክ ወደፊት ይህንን ተሞክሮ ለምርምር ተቋማትም ሆነ ለማህበራት እንደሚያጋራ ጠቁመው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የቡና ምርት ላይ የራሳችንን ዐሻራ ለማስቀመጥ ይጠቅማል›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ቡናን በምርት መጠን፣ በጥራት እና በተደራሽነት ደረጃ ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረጋል። ኒውማን ካፌ ግሩፕ 60 ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈና በ30 ሀገራት በቡና ገበያ የሚታወቅ ድርጅት መሆኑ ስምምነቱ ከሚድሮክ ባለፈ የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ ይረዳል። ስምምነቱም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ዘርፉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ ያስችላል።

የኒውማን ካፌ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ዴቪድ ኒውማን ካፌ በበኩላቸው፤ በስምምነቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ እና ምቹ ገበያን በመፍጠር ረገድ ከሚድሮክ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና ባለቤት ናት። ድርጅታቸውም በኢትዮጵያን በደንብ ይታወቃል። ቡና ላይ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ከሜድሮክ ጋር የተሻለ ሥራ ይሠራል። ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት የቡና ምርት ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል። የሜድሮክን የቡና ማምረት አቅም በማሳደግ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት ያደርጋል። ድርጅታቸው የረጅም ጊዜ ልምዱን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅም ይሰራል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ ኒውማን ካፌ ግሩፕ ጋር ስምምነት መፈራረሙ የቡና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውና አዲስ ምዕራፍን እንደሚከፍትም ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ለቡና ልማት ምቹ አካባቢ ያላት ሀገር ናት። የኢትዮጵያ ቡና ምርታማነት ግን ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው። የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል።

ስምምነቱ ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያስተዋወቅ መሆኑ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ያስችላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። ከአርሶ አደሮች እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ ከቡናው ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You