ሀገሮች ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶችን በመስጠት በኩል ያላቸውን አመቺነትና ቅልጥፍና በተመለከተ ያሉበትን ደረጃ የሚያመላክቱ መረጃዎችን አንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ይፋ ያደርጋሉ። የዓለም ባንክ በ2019 እ.ኤ.አ በወጣው ሪፖርት መሠረት የንግድ ሥራን ለመጀመር ባለ አመቺነት (Ease of starting a Business) ኢትዮጵያ ከ190 ሀገራት 167ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሀገሪቱ በንግድ ሥራ አመቺነት (Ease of doing Business) ደግሞ 159ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃው ይጠቁማል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ ባለፈው ሳምንት ለብዙሃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አዲስ አበባን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር ለከተማዋ ይህ ደረጃ እንደማይመጥን ተለይቶ አገልግሎት አሰጣጥን ወደ ማሻሻል ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል።
ከማሻሻያዎቹም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በኦንላይን ተደራሽ ማድረግ ፤ የመንግሥትን እና የተገልጋዩን ጊዜ፣ ወጪ እና እንግልት መቀነስ፣ ተወዳዳሪና ቀልጣፋ የንግድ አሰራር መዘርጋት ሀገራችን በንግድ ሥራ መጀመር አመቺነት ያላትን ደረጃ ማሻሻል በእዚህ አገልግሎትም ከመጀመሪያዎቹ ምርጥ 100 ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ተቅዶ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።
ቢሮው የተቋሙን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የተገልጋዩን እርካታ የማረጋገጥ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለብልሹ አሠራሮች በር የሚከፍቱ አሠራሮችን ለይቶ የአሠራር ማሻሻያ ማድረግ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በአዋጅ 84/2016 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በከተማዋ ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የንግድ አገልግሎትን ለማስፈን የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል፤ በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ በፍትሃዊነት የሚሰራበት ምቹ ምህዳርን በማመቻቸትና በቀላሉ ወደ ንግድ ሥርዓት የሚገባበትን ሥርዓት በመዘርጋት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ የንግድ ሥርዓቱን ጤናማና በውድድር ላይ የተመሰረተ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 ዓ.ም፤ ተቋማትን ከሌብነትና ብልሹ አሠራሮች ማፅዳት፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች ከደላላና ከየትኛው ትስስር የፀዱና ተገልጋዩን እርካታ ያረጋገጡ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት ሊከናወኑ እንደሚገባ ግልፅ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰው፣ ይህ ተግባር የእያንዳንዱ አመራር ተልዕኮና መመዘኛ እንዲሆን መደረጉን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰዋል።
አቶ ፍሰሃ በቢሮው የሚሰጡ አገልግሎቶች ነፃ፣ ግልፅና የተገልጋዩን እርካታ ያረጋገጡ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮች የሚታይባቸውን አገልግሎቶች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከወረዳ እስከ ማዕከል የመለየት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል። ይህንን ክፍተት የሚሞላ እቅድ አዘጋጅቶም የጋራ በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን ያመላክታሉ። ከእነዚህ ብልሹ አሰራርና ሌብነት ከሚስተዋልባቸው አገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹንና ብልሽቱ መታየቱ የተረጋገጠባቸውን አሰራሮች በመለየትም ርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
በዚህም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 19 አገልግሎቶች ውስጥ በ16 አገልግሎቶች የንግድ ማህበረሰቡ ያለ እንግልት በቀጥታ ቢሮ ሳይመጣ አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ተፈጥሯል። ይህም በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል ተጠንቶ እንደ ሀገር የተተገበረ ሲሆን፣ በመዲናዋ በአስራ አንድ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ በ121 ወረዳዎች በድምሩ በ132 ማዕከሎች ከ1200 በሚበልጡ ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጥበት ነው።
አገልግሎቱ ከተጀመረ አንስቶ የተለያዩ ችግሮችን እያረመና እያስተካከለ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይሁንና ከብልሹ አሠራር ያልጸዱ ተግባራት መስተዋላቸውንም አቶ ፍሰሃ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል። በሁሉም ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች እስከ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አገልግሎቱ ሲሰጥ በነበረበት ወቅት አገልግሎቱን ማሳደር፣ ሆን ብሎ ተገልጋዩ ቢሮ እንዲመጣ ማዘግየት፣ መስፈርቶችን ሳያሟሉ ወደ አገልግሎት መስጠት መግባትና ሌሎች መሰል ብልሹ አሰራሮች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በቂ ጥናትና ዝግጅት በማድረግ ወደ አንድ ማዕከል በመሳብ አገልግሎት ለመስጠት ሙከራ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም ውጤታማ መሆን መቻሉን ጠቅሰዋል።
ከአንድ ሺህ 200 በላይ ኦፊሰሮች ይሰሩ የነበረበትን ሁኔታ ከ22 እስከ 30 በሆኑ ኦፊሰሮች ብቻ መሥራት መቻሉ ተረጋግጧል ብለዋል። ከ1200 በላይ አካውንቶች ወደ 28 ዝቅ እንዲሉ መደረጉን ጠቅሰዋል። በዚህም አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ከ1200 በላይ አካውንቶችን በተበታተነ መልኩ የኦዲት ሥራ ከማከናወን ይልቅ በአንድ ማዕከል ኦዲትና ቁጥጥር በማድረግ ሥራውን ማሳካት እንደሚቻል መረጋገጡንም አመላክተዋል።
አቶ ፍሰሃ በዚህ ሂደት በሰባት ክፍለ ከተሞች በተሳሳቱ አካውንቶች መስፈርት የማያሟሉ ግለሰቦች አገልግሎት መውሰዳቸው የተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ ከዚህም የሰፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ አጠቃላይ አሰራሩን በመፈተሽ ኦዲት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ለዚህም ከአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሙያዊ ድጋፍና ኦዲት መጠየቁንም አስታውቀዋል። በዚሁ መሠረት ሙያዊ ብቃትና ዲሲፒሊን በተሞላበት መልኩ አጠቃላይ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባለው አሰራር ላይ ፍተሻ ተደርጓል። የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ከፍተኛ ሙያተኞችን ያካተተ ኮሚቴ በማደራጀት እግዛ አድርጓል ብለዋል።
በዚህ ፍተሻ ወቅት የታዩ ዋና ዋና ችግሮችን አስመልክተው አቶ ፍሰሃ እንደተናገሩት፤ በክፍለ ከተማ ከማዕከል እውቅና ውጭ 339 የተሳሳቱ አካውንቶች ተከፍተው ተገኝተዋል፤ በዚህም መስፈርትን ላላሟሉ አገልግሎት ተሰጥቷል። ከሐምሌ 4 ቀን 2016 ጀምሮ ወረዳንና ክፍለ ከተማ ከተሰጣቸው አገልግሎት ውጭ 46 ፈፃሚዎች ያልተፈቀደ አገልግሎት ሰጥተው ተገኝተዋል፤ በዚህም 263 አገልግሎቶች ሰጥተው ተገኝተዋል።
ከዚህ ውስጥ በ57 አገልግሎቶች የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጡ ጥፋቶች የተሰሩ ሲሆን፣ በእዚህም 20 ፈፃሚዎች መስፈርት ሳያሟሉ አገልግሎት ሰጥተው ተገኝተዋል። በእዚህ መንገድ ክሊራንስ ሳይወስዱ፣ የቲን ሰርተፊኬት ሳይጭኑ፣ ኦዲት ሳይደረግ፣ የመመስረቻ ቃለ ጉባኤ ሳይኖራቸው፣ ያልታደሰ መታወቂያ ይዘው፣ ፎቶግራፍ ሳያሟሉ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርገዋል። ከ20 ፈጻሚዎች ውስጥ 9 የሚሆኑት ቀጥታ የመንግሥት ጥቅም የሚያሳጡና ጉዳት የሚያስከትል ድርጊት የፈፀሙ ናቸው። ሌሎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጭ አገልግሎት ሰጥተው የተገኙ 26 ፈፃሚዎችን ጨምሮ 46 ፈፃሚዎች ያልተፈቀደ አገልግሎት ሰጥተው ተገኝተዋል።
ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ መሠረት የሁለት ድርጅቶች ለካፒታል ማሻሻያና ለአዲስ ድርጅትነት ያስመዘገቡት ካፒታል የሚያሳይ የባንክ ማረጋገጫ ሳይኖር ንግድ ፈቃድ የሰጡ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ ለቢሮ ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ ለአንድ ድርጅት የባንክ ሥራ ፈቃድ የሰጡ 3 ፈፃሚዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ 49 ባለሙያዎች በሕግና በዲሲፒሊን ተጠያቂ በሚደረጉበት ሁኔታ ላይም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ ሞያተኞችን ያካተተ ቴክኖሎጂውን የማሻሻል እና የማስተካከል ሥራ እየሰራ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመው፣ ግኝቶቹን ተከትሎ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውንና በዚህም ለውጥ መገኘቱንም ገልጸዋል።
አቶ ፍሰሃ እንደተናገሩት፤ በተሳሳተ መረጃ አገልግሎት በወሰዱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም እንዲሁ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ርምጃ የመውሰድ ሥራ ተጀምሯል። በተጨማሪም ለ10 ነጋዴዎች በቲን ቁጥራቸው ንግድ ፍቃድ የሰጡ 9 ፈፃሚዎች የተለዩ ሲሆን፣ ተጠያቂም ይደረጋሉ። በዚህ አገልግሎት በአጠቃላይ 58 ፈፃሚዎች 70 አገልግሎቶችን አላግባብ ሰጥተዋል።
እስካሁን የተወሰዱ ርምጃዎችን አስመልክተው አቶ ፍሰሃ እንደገለፁት፤ የተሳሳተ አካውንት በመክፈትና በመተባበር ተሳታፊ የሆኑ በሕግ እንዲጠየቁ፣ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸውና በዲሲፒሊን እንደጠየቁ እየተደረገ ይገኛል።
ቴክኖሎጂውን የማሻሻል የተጠያቂነት ሥርዓት በሚያጋረግጥ መልኩ በፌዴራል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል የማሻሻያ ሥራ እየተሰራ ነው። አላግባብ የተከፈቱ አካውንቶች እንዲዘጉ ተደርጓል። አሰራርን ሳይከተሉ አገልግሎት ያገኙ የንግድ ድርጅቶችም እንደ ጥፋት ደረጃቸው ንግድ ፈቃዳቸው ታግዶ እንዲያስተካክሉና በሕግ መጠየቅ ያለባቸውም በቀጣይ እየታየ ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ሥራዎችን ኦዲት በማድረግና የተጠያቂነት ሥርዓት በማስፈን በኩልም እንዲሁ ከሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ አጠቃላይ ከ130 ሺህ በላይ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መሰጠታቸውንም አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ እነዚህ አገልግሎቶች መስፈርቱን አሟልተው የተሰጡ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ በተሰራ ፍተሻ ከ362 በላይ አገልግሎቶች አሰራርን ባልጠበቀና መስፈርትን ባላሟሉበት ሁኔታ መሰጠታቸውን በኦዲት ማረጋገጥ ተችሏል።
ከእነዚህ ውስጥ 32 (ክሊራንስ፣ ኦዲት፣ መመስረቻ ቃለ ጉባኤ…) አገልግሎቶች ዋና ዋና የሚባሉ ናቸው። በዚህም 15 ፈፃሚዎች የመንግሥትን ጥቅም ሊያሳጡ የሚችሉ አገልግሎቶች ሰጥተዋል፤ ከ15ቱ ፈፃሚዎች ውስጥ 8ቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት መስፈርት ያላሟላ አገልግሎት ሰጥተው ተገኝተዋል፤ ሰባት ፈፃሚዎች ደግሞ ባልተሰጣቸው ኃላፊነት ሕግ ወጥ ሥራ ሰርተዋል።
በ330 አገልግሎቶች ላይ በ33 ፈፃሚዎች መለስተኛ ጥፋቶች መፈጸማቸውም ተረጋግጧል። በአጠቃላይ በተደረገው ኦዲት 48 ፈፃሚዎች ቀላል ጥፋትና ከባድ ጥፋት የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጡ ተግባራት መፈፀማቸው ተረጋግጧል። እነዚህ ፈፃሚዎች በተመሳሳይ አሰራሩ በሚፈቅደው መሠረት በዲስፕሊን፣ በአስተዳደራዊና በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ይቀጥላል። የተሰጡ አገልግሎቶችም የማስተካከልና ሕጉን የተከተለ ርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።
አቶ ፍሰሃ ከኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራትና ሌሎች መደበኛ አሰራሮች ጋር በተያያዘ እንደገለፁትም፤ በቁጥጥርና ክትትል ወቅት ያልተገባ ተግባር ከአሰራር ውጭ የፈፀሙ፣ ከቅዳሜና እሁድ ገበያ አካላት ጋር ያልተገባ የጥቅም ትስስር የፈጠሩ፣ የታሸገ ቤት አሰራሩ ከሚፈቅደው ውጭ ገንጥለው ያስገቡ በድምሩ 25 ፈፃሚዎችና አንድ አመራር በድምሩ 26 ከኃላፊነነት ከማንሳት እስከ በዲስፕሊን መጠየቅ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በብልሹ አሰራርና ሌብነትን በመቆጣጠር በኩል መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የንግድ ቢሮው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በማዕከል በአምስት ሠራተኞች ላይ፣ በክፍለ ከተማ 131 ሠራተኞች በድምሩ 136 የሥራ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ላይ የተጠያቂ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ430 በላይ የንግድ ፍቃድ አገልግሎቶች መስፈርት ሳያሟሉ ተገቢነት በሌለው መንገድ አገልግሎት መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ኪሳራው ወደ ገንዘብ ቢቀየር ሌላ ጥናት ማድረግን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። እነዚህም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2106 በሚፈቅደው መሠረት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል። 28 ፈፃሚዎች ጥፋታቸው ከበድ ያለ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰው፣ በሕግ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል ሶስቱ አስቀድሞ ፖሊስ ጉዳያቸውን እያየ መሆኑን ተናግረው፣ አንዱ እስከ አሁን አልተገኘም ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብም ሕግና አሰራርን ተከትሎ አገልግሎት መጠየቅና መስተናገድ እንዳለበት አመልክተው፣ ጥቆማ መስጠቱንና ተባባሪነቱን አጠናከሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። አቶ ፍሰሃ እንዳመላከቱት፤ በቀጣይም በብልሹ አሰራርና ሌብነት ላይ የተጀመረው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው፣ የተቋሙን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የተገልጋዩን ርካታ የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል ብለዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ብቁ ሠራተኞችን በመመደብ ይበልጥ ውጤታማ መሆን በሚያስችል መልኩ እንደሚካሄድ አስታውቀው፣ በሌሎች የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጦች ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን የማስተካከል፣ ለብልሹ አሰራሮች በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለይቶ ማሻሻያ ማድረግ ሌሎች በትኩረት የሚሰራባቸው ተግባሮች መሆናቸውን አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም