የዓሳ ሃብት ልማትን የማሳደግ አበረታች ጥረቶች

ኢትዮጵያ እምቅ የዓሳ ሃብት ባለቤት መሆኗን ጥናቶች ያሳያሉ። ከሀገሪቱ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ኩሬዎችና ሌሎች የውሃ አካላት በዓመት ከ94 ሺ 500 ቶን በላይ የዓሳ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ጥናትን ዋቢ ያደረገው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ይህንን ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ግን ሰፊ ክፍተት መኖሩ ይጠቀሳል። የሕብረተሰቡ ዓሳን የመመገብ ባህል ደካማ መሆን ሀገሪቱ ከዚህ እምቅ ሀብት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓት መቆየቱ ይገለጻል።

መንግሥት የምግብ ዋስትናንና የምግብ ስርዓትን ለማረጋገጥ በነደፈው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም ሆነ በግብርና ፖሊሲው ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የዓሳ ግብርና ነው። ለእዚህም ዓሳን ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ ስትራቴጂና የሕግ ማሕቀፎችን በማዘጋጀትም ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የዓሳና የውሃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጋሻው ተስፋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ፤ በኢትዮጵያ 200 የሚደርሱ የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸውን ጥናቶችን ዋቢ አርገው ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 190 የሚሆኑት ሃገር በቀል ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከልም 45ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው። ይሁንና ከእነዚህ ውስጥ ሕብረተሰቡ ለገበያና ለምግብነት የሚጠቀምባቸው ቆሮሶ፣ ነጭ ዓሳ (ናይል ፐርች) አምባዛና ዱባ የተባሉ በጣም ውስን የሆኑትን ዝርያዎች ብቻ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማና ሰፊ የዓሳ ሃብት ባለቤት እንደመሆኗዋ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ያለመሆኗዋ ቁጭት የሚፈጥር ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የዚህ ዋነኛ ምክንያትም የሕብረተሰቡ የአመጋገብ ባህል እንደሆነ ይገልጻሉ። በተለይም ከእምነት ጋር ተያይዞ ባለ አመላካከት ሃብቱ ባለባቸው አካባቢዎችም ሳይቀር ዓሳን በምግብነት የሚጠቀመው የሕብረተሰብ ክፍል ውስን መሆኑን ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ግን በተለይም በከተሞች አካባቢ የተመጋቢው ቁጥር ከፍ ቢልም ዓሳ እንደልብ የማይገኝ መሆኑ ሃብቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደረገው መሆኑን ያመለክታሉ።

ይህም ቢሆን ግን የውሃ አካልን ተጠግቶ በሚኖረው ሕብረተሰብ ዘንድ ዓሳን የመመገብ ባህሉ ከፍ እንደሚል ዶክተር ተስፋዬ ይናገራሉ። አብነት አድርገውም በጋምቤላ 30 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት የዓሳ ዝርያዎች ለምግብነት እንደሚውሉ ይገልጻሉ። ‹‹ወደ ኦሞና ቱርካና ሃይቅ አካባቢ ያሉት የደቡብ ኦሞ አካባቢ ማህበረሰቦችም እንደዚሁ ሰፊ የዓሳ ዝርያዎችን ተመጋቢዎች ናቸው፤ ከስምጥ ሸለቆዎቹ ሃዋሳ፣ ዝዋይና አርባ ምንጭ ሃይቆች ከሰባት የሚልቁ የዓሳ ዝርያዎች ለገበያ ይቀርባሉ›› ሲሉ ያስረዳሉ።

እስካሁን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት አድርገውም ‹ኢትዮጵያ ካሏት የተፈጥሮ የውሃ አካላት ብቻ ከ128 እስከ 130 ሺ ቶን አሳ በዓመት ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳላት ዳይሬክተሩ ያነሳሉ። ‹‹ የግብርና ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው መረጃ እንደሃገር በዓመት እየተመረተ ያለው ከ73 ሺ ቶን አይበልጥም፤ ይህም ያለንን ሃብት ሙሉውን መጠቀም አለመቻላችንን ያሳያል›› በማለት ያብራራሉ። ሃብቱ ጥቅም ላይ ላለመዋሉም ሆነ ምርታማነቱ እንዳይጎለብት ካደረጉትና ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጓዳኝ የአመራረት ሂደቱ ኋላቀርና ባህላዊ መሳሪያዎች ላይ የተንተራሰ መሆኑ ዋነኛው ተግዳሮት እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

‹‹ለዚህ በዋናነት እንደ ችግር ሊነሳ የሚችለው የማስገሪያ መሳሪያዎቻችንን ኋላቀርና ባህላዊ መሆን ነው። ዘመናዊ የሚባሉ መሳሪያዎች ከውጭ የሚገቡ መሆናቸው እንደልብ ለማግኘት አዳጋች ነው›› በማለትም ይናገራሉ። በሕገወጥ መንገድ ከውጭ ገብተው ገበያ ላይ የሚታዩት ማስገሪያዎችም የዓሳ ሃብቱን የሚያመናምኑ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በተለይም ዓሳ አስጋሪዎች በብዛት የሚጠቀሙት ተጎታች መረብ የተባለው መሳሪያ ዓሳዎች በሚራቡበት የውሃ ዳርቻ የሚቀመጥ በመሆኑ ወላድና ጫጩት ዓሳዎችን የሚያጠምድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ተተኪ ዓሳ እንዳይኖር እያደረገ መሆኑን ያብራራሉ።

በዚህም ምክንያት እንደዝዋይና ጫሞ ባሉ ሃይቆች ላይ ያለው የዓሳ ሃብት በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ያመለክታሉ። ‹‹ለምሳሌ ጫሞን ብንወስድ ከአራት ሺ ቶን በላይ በዓመት ይመረት ነበር፤ ዝዋይም ከሁለት እስከ ሶስት ሺ ቶን ዓሳ ይመረት ነበር። አሁን አንድ ሺ ቶን አካባቢ ነው የሚመረተው›› ሲሉ ገልጸዋል፡

ከዚህ ባሻገርም በአሁኑ ወቅት ዓሳ በሚመረትባቸው በውስን ሃይቆች ላይ ያለው የአስጋሪው መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ይናገራሉ። በሃይቆቹ ላይ የሚደረግ ምንም አይነት ቁጥጥርና ለአጥማጁ የሚሰጥ ፈቃድ ባለመኖሩ የሃይቆቹ ስነሕይወት ጭምር አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ። ይህም ችግር በተለይ ዝዋይ፣ ሃዋሳና ጫሞ ሃይቆች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም ከፋብሪካ የሚወጡ ኬሚካሎች በሚያደርሱት ተፅዕኖ ምክንያት ምርቱ የሚቀንስበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ። ‹‹በተለይም ከአበባ እርሻዎች የሚወጡ ኬሚካሎች ሳይጣሩ ተመልሰው ወደ ሃይቅ የሚለቀቁበት ሁኔታ ይታያል፤ ይህም በጫጩቶችና የዓሳ እንቁላሎች ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር የሚፈለፈሉት የዓሳ ጫጩቶች አነስተኛ እንዲሆኑ አድርጓል›› ይላሉ። እንደ ዝዋይ ባሉ ሃይቆች ዙሪያ የሚካሄደው የመስኖ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ጠቅሰው፣ ይህም የሃይቆቹ ውሃ መጠን እንዲቀንስ አደርጎታል፤ ይህም በውሃ ውስጥ ላሉ ስነ ሕይወቶች ሕልውና ስጋት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ዶክተር ተስፋዬ ዘርፉን ለማሳደግ በመንግሥት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ያለበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል። በተለይም በሌማት ትሩፋት ዓሳ እንደ አንድ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መታየቱ በጣም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ በሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ አዳዲስ ግድቦች ላይ የዓሳ ምርታማነት ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የተዳከሙትን ዳግም ለመጠገን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዘርፉ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ጎን ለጎን የዓሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላትን በየክልሉ በማቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ኦሮሚያ ክልል በዝዋይ፣ ሲዳማ ክልል በሃዋሳ፣ በደቡብ ምዕራብ ክልል በአርባ ምንጭ የዓሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላት ተሰርተዋል።

እነዚህ ማዕከላት በሌማት ትሩፋቱና ከውጭ በተገኙ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ተስፋዬ ጠቁመው፤ ይሁንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው የዓሳ ጫጩት ማባዣም ሆነ እንደምርምር ማዕከል ያገለግል የነበረው ሰበታ የሚገኘው በኢንስትቲዩቱ ስር ያለው ብሔራዊ ዓሳ ምርምር ማዕከል ብቻ እንደነበር አንስተዋል። ይህ ማባዣ ማዕከል በዓመት እስከ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ጫጩቶችን እያባዛ ወደ ተለያዩ ግድቦችና ሰው ሰራሽ ኩሬዎች ይጨምር እንደነበርም ያስታወሳሉ። በእነዚህ ተቋማትም ሆኑ በክልሎች እየተሰሩ ያሉ የማባዣ ማዕከላት ስራ ሲጀምሩ የዓሳ ምርታቸው የተመናመነባቸውና አዳዲስ ግድቦች ላይ እየተባዙ ወደውሃ አካላቱ እንዲጨመሩ በማድረግ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ያስገነዝባሉ።

‹‹ኢትዮጵያ 130 ሺ ቶን አሳ የማምረት አቅም አላት የሚባለው በተፈጥሮ ባሏት የውሃ አካላት ብቻ ነው እንጂ ሰው ሰራሽ ግድቦችን አይጨምርም›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ግድቦችን ተጠቅሞ ደግሞ ከ400 ሺ ቶን በላይ አሳ ማምረት እንደሚቻል የግብርና ማስተር ፕላኑ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ከሰው ሰራሽ ሃይቆችና ግድቦች አንፃር በአሁኑ ወቅት ተከዜ ላይ በጣም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ ምርት የሚያመርቱባቸው ማስገሪያ መሳሪያዎች፣ የጀልባ፣ የመረብ፣ እንዲሁም ዓሳው ከተመረተ በኋላ ተቀናብሮ (ፕሮሰስ ተደርጎ) ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችሉ የዓሳ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ጭምር የተሟሉለት መሆኑን ያብራራሉ። በዚህ ረገድም በማህበራት በማደራጀት፤ ማህበራቱ እንዲጠናከሩ በማድረግ ሰፊ ስራ መሰራቱን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅት ምርቱ አዲስ አበባ ገበያ እየቀረበ ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ አሳ በስፋት ለማምረት በመንግሥት ታስቦ የነበረውን ስራ ተጠይቀውም ሲመልሱም ‹‹ አባይ ግድብ ላይ ለመስራት የታቀደው የዓሳ ልማት ስራ በአሁኑ ወቅት በጅምር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፤ ይሁንና ከፍተኛ የዓሳ ሃብት እንዳለ የሰራናቸው ጥናቶች ያሳያሉ›› ብለዋል።

ኢንስትቲዩቱ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ማስተር ፕላን መሰረትም ሰው ሰራሽ ሃይቅን በማስገር ብቻ በዓመት እስከ 10 ሺ ቶን ዓሳ ለማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለው መታወቁን ያመለክታሉ። በተጨማሪ ደግሞ በዓሳ ግብርና ስራ ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ በግድቡ ዙሪያ ማ ምረት እንደሚቻል ይናገራ ሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በአባይ ግድብ ላይ በተሰራው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ላይ ዓሳ ለማምረት ከ70 በላይ ማህበራት ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን እስካሁን ወደ ስራ የገቡት ሶስት ማህበራት ብቻ ናቸው። በተጨማሪም ከአባይ ገድብ ጋር ተያይዞ መከላከያ ውስጥ ያለውና የሰራዊቱ ፋውንዴሽን አባላት ግድቡን እየጠበቁ በዓሳ ልማት ሥራ እንዲሰማሩ ታቅዷል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ 10 ሺ ሄክታር ተረክበዋል። ብሔራዊ ማዕከሉና ግብርና ሚኒስቴር በመተባበር ፋውንዴሽኑ ለሚያከናወነው የዓሳ ልማት የአዋጭነት ጥናት እያካሄዱ ይገኛሉ። ጥናቱ እንደተጠናቀቀም ወደ ማምረት ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። አዋጭ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የተወሰነ የዓሳ ምርት ወደ ውጭ የመላኩ እድል ይኖራል።

ይሁንና በተለይ በተፈጥሮ የውሃ አካላት ላይ እየተከናወነ ያለው የዓሳ ማስገር ሥራ ሥርዓት ሊበጅለትና አስገዳጅ ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ይህ ካልሆነ ሃብቱን ጥቅም ላይ ለማዋልም ሆነ ዘርፉ ለሃገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እንዳይጫወት እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዶክተር ተስፋዬ ይናገራሉ።

‹‹አዳዲስና ሰው ሰራሽ ግድቦች ላይ ከሚከናወኑ የዓሳ ልማት ስራዎች ጎን ለጎን የዓሳና የውሃ አካላቱን ሕልውና መታደግ ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል። ከዚህ አንፃር የወጡ ሕጎችና ደንቦች ላይ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል›› ይላሉ። አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችንም በተጓዳኝ በመውሰድ ማስተማር ይጠበቃል። በተለይም እስከ ወረዳ ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ሕጎች በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲተገበሩ መደረግ አለበት። የቁጥጥርና ክትትል ስራውም መከናወን ያለበት በታችኛው መዋቅር ላይ ባሉ አካላት መሆኑን ከግንዛቤ ማስገባት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር ጋሻው ተስፋዬ

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You