የኑሮዋን ውጣውረድ የፊቷ ገጽታ ያሳብቃል ። ተጎሳቁላለች፣ ጥርሶቿ ወላልቀዋል፣ እጇቿ በትኩስ ጠባሳዎች ተሸፍነዋል። ደጋግማ ትተክዛለች፣ አንገቷን ደፍታ፣ አገጭዋን ደግፋ አርቃ ታስባለች። ወዲያው በዓይኖቿ ዕንባ ግጥም ይላል። ይህ እውነት የየዕለት ልምዷ ነው። ለእሷ ዕንባና ችግር ብርቅ ሆኖ አያውቅም።ሁለቱም በአንድ ሆነው ከእሷ ኖረዋል።
ሁሌም ውስጧን ለመደበቅ ፣ ከራሷ ጋር ትግል እንደያዘች ነው ። ኑሮዋን ታግላ ህይወትን እያሸነፈች ዛሬ ላይ ብትደርስም ስለነገው አታውቅም። ዘወትር አብሯት ያለው ህመም እንደጥላ ይከተላታል ። በዚህ ምክንያት እንደሌሎች ሰርታ ፣ ሮጣ ለማደር ዕንቅፋቷ በዝቷል።
ቅድመ- ታሪክ ልጅነት
የእህታቸውን መርዶ በድንገት የሰሙት ወይዘሮ ‹‹እዬዬ›› እያሉ ነው። ታናሽ እህታቸው ስለመታመማቸው አስቀድመው ሰምተዋል። እንዲህ በአጭር ጊዜ ሞታቸውን እንደሚረዱ ግን ጠርጥረው አያውቁም ። የአዲስ አበባዋ ሴት አሁን ለሀዘኑ ወደ ቡታጅራ እየሄዱ ነው። ጥቂት ጎረቤቶቻቸው ተከትለዋቸዋል። ከቀብሩ መልስ ሀዘናቸውን በቤታቸው፣ በዕድራቸው ይወጣሉ።
ወይዘሮዋ ውስጣቸው እንዳዘነ ዓይናቸው እንዳነባ ቡታጅራ ደርሰው ከመኪና ወረዱ። ከሀዘኑ ቤት ደርሰው የሟች እህታቸውን ቤተሰቦች በለቅሶ ተቀላቀሉ። ታናሽ እህታቸው በመኖሪያ ዕድሜዋ ልጆቿን በትና መሞቷ ልባቸውን ሰብሮታል።ከሁሉም ግን ከተወለደች ገና ሶስት ወር ያልደፈነችው ጨቅላ ነገር እያሳሰባቸው ነው። ሟች ከማረፏ አስቀድሞ ስለትንሽዋ ልጅ አደራ ብላቸዋለች። እህት ይህን ቃል ፈጽሞ አልረሱም፣አልዘነጉም።
ጨቅላዋ ጡት በወጉ ሳትጠግብ፣ ወዝና ጠረን ሳትለይ እናቷን ሞት ነጥቆባታል። ወይዘሮዋ ህጻንዋን እያዩ አነቡ። ጥቂት ቆይተው ግን በዓይምሯቸው ሲመላለስ የቆየውን ሀሳብ ሊያወጡት ግድ አላቸው። የሟችን ባለቤት ጠጋ ብለው ያሰቡትን ዕውነት አማከሯቸው፡፤
ህጻኗ እናቷን በሞት አጥታለች፣ ከእንግዲህ የእሷ ህይወት አስቸጋሪና ፈታኝ ሊሆን ነው። እናም ካለችበት የተሻለ ሌላ ህይወት ሊኖራት ያስፈልጋል። ይህን ሀላፊነት የመወጣቱ ግዴታ ደግሞ የእሳቸው ይሆናል። አስቀድሞ ጆሯቸው ቃል ሰምቷል። የሙት አደራ አለባቸው።
አባወራው የሚስታቸውን እህት ሀሳብ አልተቃወሙም ።ጨቅላ ልጃቸውን በድንገት አሳልፎ መስጠቱ ቢከብዳቸውም ከእሳቸው ይልቅ አክስት ወሰደው ቢያሳደጓት እንደሚሻል አመኑ ። አባት ዕንባ እያነቃቸው፣ ከሲቃና አደራ ጋር ትንሸዋን ልጅ ለሚስታቸው ታላቅ እህት በአደራ አስረከቡ።
አዲስ አበባ
አሁን ወይዘሮዋ ትንሽዋን የእህታቸውን ልጅ በአደራ ተረክበው አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ከእጃቸው ያለችው ህጻን ከሌሎች ሁሉ ትለያለች።እሷ በወጉ ጡት አላገኘችም። ከእናቷ ጉያ ተወሽቃ ፍቅርን፣ሙቀትን አላየችም። ደጓ ወይዘሮ ከልጆቻቸው ሳይለ ዩ፣ እንደራሳቸው ፍሬ እያሳደጉ እየተንከባከቧት ነው። ትንሽዋ ልጅ አድጋለች፣ ተመችቷታል።
ውሎ አድሮ አሳደጊ አክስቷ ለእህታቸው ልጅ ስም አወጡ ። ‹‹እጅግ አየሁ›› ሲሉ ሰየሟት።አጅግ አየሁ ከአክስቷ ቤተሰቦች ጋር በእኩል አደገች። አንዳች መድልኦ ሳያገኛት፣ በደልና ዱላ ሳይርፍባት ልጅነቷን ገፋች ። ሞት ስለነጠቃት ስለ እናቷ ማንነት አታውቅም። በአክስቷ የተከፈለላትን ዋጋና ፍቅር የተረዳችው ዕድሜዋ ከፍ ሲል አቅሟ ሲበረታ ነበር።
የእጅግአየሁ አሳዳጊ አክስት ኑሯቸው እምብዛም የሚባል ነው። ከእጅ ወደአፍ በሆነው ህይወት ኑሮን ለመግፋት፣ ቤተሰብን ለማኖር እንጀራ ጋግረው ይሸጣሉ። ለእሳችው እንጀራን ሸጦ እንጀራ ለማግኘት ኑሮ አልጋ በአልጋ አይደለም። አህልና ማገዶን መግዛት፣ ያስፈልጋል፣ ለዚህም አቅምና ጉልበት ይጠይቃል ። እጅጋየሁን ጨምሮ ሌሎች የእናታቸውን ፍላጎት ሊሞሉ ሲሮጡ ይውላሉ።
ልጆቹ ለእንጀራው ማብሰያ የአቅማቸውን ማድረግ ግዴታቸው ነው። ከየመንገዱ ካርቶን፣ ቅጠልና እንጨት ይለቅማሉ። ያገኙትን ይዘውም ለእናታቸው ይሰጣሉ ።፡ ህይወት በእነ እጅጋየሁ ቤት እንዲህ ሆኖ ዘልቋል። የእጅግአየሁ አክስት መልካም ሴት ናቸው። ልጆቻቸውን በፍቅር ያሳድጋሉ። እሷንም ቢሆን ከምትሻው ሁሉ ነጥለዋት አያውቁም።፡ የአቅማቸውን ያደርጋሉ ፣ የቻሉትን ያሟላሉ።
እጅግአየሁ ከእክስቷ አንዳች ፍቅር ሳትነፈግ በሰላም በጤና አደገቸ። ልጅነቷን አልፋ ከወጣትነት ከአፍላነት ዕድሜ ደረሰች።
አሳዳጊ አክስቷ የአንድ ልጅ እናት ናቸው። ልጃቸውን ጨምሮ አጅግ አየሁን አስተምሮ ለወግ ለማብቃት ሲጥሩ ኖረዋል። ህይወት ከብዶ እጃቸው ቢያጥርም ልጆቹን ለማስተማር ወደ ኋላ አላሉም። ካላቸው እየቆጠቡ ሁለቱንም ሊያስተምሩ ሞክረዋል። እንደሳቸው ልፋት ባይሆንም እጅ ግአየሁ አስከ ስምንተኛ ክ ፍል ተምራለች።
እጅግአየሁን በቻሉት አቅም ያሳደጉት አክስት ጥረታቸው ተሳክቷል።አሁን ከጀርባቸው ሆኖ የሚያለቅስ፣ዳቦ የሚል ህጻን የለም። እንደትናንቱ ለወተት ብለው አያስቡም። ሁሉም ቤት ያፈራውን ቀምሶ ያድራል። ዛሬ ላይ የሚያሳስባቸው ቢኖር የእህታቸው ልጅ የእጅግአየሁ ጤና ብቻ ነው።
ልጅቷ ካደገች በኋላ የታየባት ምልክት እሳቸውን ጨምሮ መላ ቤተሰቡን አሳስቧል። ደርሶ በድንገት ይጥላታል። ራሷን አውቃ ስትነቃ ያለችበትን አትለይም። ለችግሩ መላ ብዙ ተሞክሯል ። ቆይቶ ግን የእጅግ አየሁ ችግር የሚጥል በሽታ መሆኑ ታወቀ።
እጅግአየሁ ከዚህ ችግር ጋር ዓመታትን ዘለቀች። ብዙዎች ህመሙ ሲነሳባት እንደሚጥላት ያውቃሉ። እሷ በሽታውን እንደ ባህሪው መያዝ ይቸግራታል ፣ ይህ እውነት ለህይወቷ እንቅፋት መሆኑን ጭምር ታውቃለች። እንዲያም ሆኖ ከራሷ እየታገለች፣ ከመድሀኒቱ እየወሰደች ጊዚያትን ቆጥራለች ።
ከጊዚያት በኋላ
አሁን እጅግ አየሁ ወጣት ቆንጆ ሆናለች፡፤ ይህን እድሜ በወጉ ካልያዙት ፈተናው ይበዛል ። በተለይ ሴት ልጅ ማንነቷን አውቃ ራሷን ካልገዛች መሰናክሏ ይበረክታል ፣ ወጥመዷ ይሰፋል ። በዚህ ወቅት ዓይኖች ሁሉ ከውበት ላይ ያፈጣሉ። በየምክንያት ሰበቡ የሚያደንቁ ፣ ወደድን፣ አፈቀርን የሚሉ ጥቂት አይሆኑም። ወጣትነት ሀይል ነው። ዓለምን መዝነው ፍቅርን ያዩበታል። ውበትን አድንቀው በራስ ይዋቡበታል።
አንዳንዴ ግን ይህ ዕድሜ ባልሆነ መንገድ ሊሰድ፣ ሊያሳስት ይችላል ። ይህኔ አቅጣጨን አይቶ የሚመለስ፣ የሚመክር ልባም ከሌለ ውጤቱ ይከፋል ። አሁን እጅግ አየሁና ወጣትነት ተዋውቀዋል ። ለራሷ ጊዜና ክብር መስጠት የያዘችው ወጣት እርምጃዋ ሳይቀር ተለይቷል፤ ሀሳብ ዕቅዷም መጥቋል።
ትምህርቷ ከስምንተኛ በላይ አልገፋም ። ህመሟ ጭምር ሰበብ ሆኖ ከቤት መዋል ይዘለች። ይህ ጊዜ በትምህርት የሚውለውን ድርሻ ለእሷ ብቻ ሰጥቷል ። አሁን ወጣቷ ወጣ ገባ አብዝታለች፣ ባልንጀሮች ይዛለች፣ ቀጠሮዋ በዝቷል፣ ውበት መልኳ አይን ስቧል።
አንድ ቀን
እጅግአየሁ ከቀናት በአንዱ ከዘመድ ቤት ጠበል ተጠርታ ሄደች ። ከቤቱ ስትገባ ብዙ ዓይኖች ተከተሏት። አጋጣሚ ሆኖ ከአንድ ወጣት አጠገብ አረፍ ብላ ጨዋታ ያዘች። ወጣቱና እሷ እህል ውሀ እያሉ ጨዋታቸው ደራ፣ ስለማንነቷ ጠየቃት፣ ነገረችው፣ ስለእሱም እንዲያወራት ፈለገች፡ አልደበቃትም። ትዳር መያዝ ልጆች መውለድ እንደሚሻ አሳወቃት።
እጅግአየሁ የወጣቱ ጨዋታ ልቧን ገዛው፣ ስለ ትዳር ያነሳውን ቁም ነገር በዋዛ መተው አልፈለገችም። ሁለቱም የልባቸውን እያነሱ የፍለጎታቸውን መከሩ።ቀልባቸው ተስማማ፣ ውስጣቸው ተፈላለገ። ዳግም ሊገናኙ ወስነው በቀጠሮ ተለያዩ።
ሁለቱ ደጋግመው ተገናኙ። ቅርበታቸው ፍቅር ሆኖ ሀሳብ ተለወጠ። ልባቸው ቁምነገር ቢያስብ በአንድ ጎጆ ሊኖሩ ፣ ያሰቡትን ሊሆኑ ተስማሙ። ሀሳቡ ጊዜ አልፈጀም። ቤት ጎጆ ማለቱ ቀጠለ። እጅግ አየሁ ራሷን ችላ ትዳር መያዟ አክስቷን አላስከፋም። የልቧ ይሆንላት ዘንድ ምኞታቸው በምርቃት ነው።
እጅግአየሁ ከህመሟ አልዳነችም። አልፎ አልፎ የሚጥላት በሽታ ራሷን ያስታታል።አንዳንዴ ከጉድጓድ ከእሳቱ ይጥላታል፣ ከወደቀችበት ስትነቃ አካሏ በእሳት ተቃጥሎ ፣ ጥርሷ ወልቆ፣ ተሸርፎ ራሷን በጉዳት ታገኘዋለች ። እንዴት ብላ አትጠይቅም ። ምክንያቱን ታውቀዋለች ፤እንዲህ የሆነችው በሚጥል በሽታዋ ነው። ለቀናት ቁስሏን አስታማ ጥቂት ታገግማለች። ዘወትር የጠባሳዋን አሻራ እያየች አንገቷን መድፋት መተከዝ ልምዷ ነው።
፡ ሌላ ቀን ደግሞ ከአስፓልት ዳር፣ ከመኪኖች ጎማ ስር ወድቃ ተጎትታ መውጣቷን ይነገራታል ። ይህኔ ውስጧ ዳግም ይከፋል፤ ዕንባዋ በላይ በላይ ይፈሳል። ዕድሏን አብዝታ ታማርራለች፣ ራሷን ደጋግማ ትረግማለች ። ምርጫ የላትም ። የነገ ዕጣ ፈንታዋን እያሰበች በሀዘን ፣ በትካዜ ትከርማለች።
እጅግአየሁ ‹‹ትዳሬ፣ ቤቴ›› እያለች ነው። ጎጇዋን የሚያደምቅላት፣ ህይወቷን የሚያሰምርላት ልጅ ከወለደች ወዲህ ደስታዋ ጨምሯል። ልጇን እያሳደገች ህይወቷን ልታሸነፍ ትሮጣለች ።፡ የነገን ተስፋ ይታያታል፣ ህይወቷ ባይቀናም ኑሮዋ ባይሞላም በልጇ ስጦታ ጎዶሎዋ ተደፍኗል ፣ጨለማዋ በርቷል ።
ሶስቱ ጉልቻ
የእጅግ አየሁ ትዳር ሰላም ከራቀው ቆይቷል ። ጠዋት ማታ በጭቅጭቅ ውሎ የሚያደርው ጎጆ ሰላም ይሉትን አያውቅም። ባለቤቷ ከእሷ ይልቅ ትኩረቱ ለልጁ ብቻ ሆኗል። የምትለውን አይሰማም ፣ የሚሰራውን አታውቅም። ውሎ ሲገባ በእጁ ያንጠለጠለውን ይወረውርላታል። ከእሱ የሚመጣው ቋጠሮ በቅቷት አያውቅም ። ጎጇዋን ለመሙላት፣ ኑሮዋን ለመግፋት ትሮጣለች።
ሁሌም ከህመም እየታገለች ፣ የልጇን ሆድ ልትሞላ ትታገላለች፤ የራሷን ህይወት ልታቀና አብዝታ ትጥራለች። መርካቶ ገብታ በኪሎ ሀያብር የምትገዛውን ወረቀት በልኩ እየቆረጠች፣ እያሸገች ለሚፈልጉት ታደርሳለች። ገዢዋቿ የእሷን ተቀብለው ለለውዝ፣ ለቆሎና ለሌላም ጥቅም ያውሉታል።የሚከፍሏትን ሳንቲም ይዛ ለጎጇዋ ትደርሳለች። ሲነጋ ሌላ ቀን ነው። እጅግ አየሁ እንደትናቱ ዛሬ እንዳይጎድል ጉልበቷ ይበረታል።
ሁለተኛው ልጅ
እጅግአየሁ የመጀመሪያ ልጇ እያደገ ነው። ስምንተኛ ዓመቱን ባከበረ ማግስት የወለደችው ልጅ ደግሞ ከእሷ ብዙ ይሻል። ህይወቷ ዛሬም አልቀናም።ከችግር ፣ ከድህነት እየታገለች በልታ ለማደር ትተጋለች።
ለህመሟ አማኑኤል ሆስፒታል ክትትል አላት ። በየጊዜው የምትወስደው መድሀኒት ደግሞ በቂ ምግብና እረፍት ይፈልጋል። እሷ ከጎጆዋ ውሎ የሚያድር ቁራሽ የላትም ። ለዚህ ያልታደለችው ሴት የዛሬን ቀምሳ ለነገው ለመድረሰ ልፋቷ የበዛ ፣ ሸክሟ የከበደ ነው።
በዕንቅርት ላይ…
እጅግአየሁ አሳድገው፣ ለወግ ያበቋት አክስቷ ዛሬም ከጎኗ አልራቁም። ሁሌም በምክር ያበረቷታል፣ ‹‹አይዞሽ ፣አለሁልሽ›› ይሏታል።አክስቷ በቅርብ ጊዜ ያደረባቸው ህመም ቤት እያዋላቸው ነው ። አጠገባቸው ያለችው እጅግአየሁ ጊዜ ወስዳ ማስታመም አልሆነላትም። አልጋ ባይዙም ህመማቸው ስጋት ሆኖ ያሳስባቸዋል።
ለእጅግአየሁ እሳቸው ካሉ ሸክም ሁሉ ይቀላል። ከእሳት ቀርባ ምግብ እንድትሰራ፣ ቡና እንድታፈላ አይፈቅዱም። የጎደለውን ሞልተው ከእሳት ከምድጃው ውለው ፣ የልቧን ይሞላሉ፡
አንድ ቀን ግን ይህ ሁሉ ሀሳብ ፣ ክብርና ፍቅር እስከ ወዲያኛው መቅረቱ አርግጥ ሆነ። አክስቷ ከተቀመጡበት ወንበር ሳይነሱ በሞት አሸለቡ። ድንገቴው ሞታቸው የእጅግአየሁን ኑሮ ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› አደረገው። ህይወት ይበልጥ ከበዳት፣ የኑሮ ጫናን ለብቻዋ ልትጋፈጥ ፣ ግድ አላት።
ከባለቤቷ ጋር አሁንም ሰላም አልወረደም ። እንደውም አንዳንዴ በክፉ ንግግሩ ሆድ ያስብሳታል ሁሌም ‹‹እኔ የምኖረው ለልጆቼ እንጂ ለአንቺ አይደለም›› ይሉትን ቃል ለምዳዋለች። ይህን ስትሰማ ከእንግዲህ ለእሷ የሚኖር ፣ ስለእሷ የሚያስብ የሚጨነቅ እንደሌለ ሆኖ ይሰማታል።
እጅግአየሁ አሁን እሷን ወክሎ ከእሳት ከምድጃው የሚጋፈጥ የልብ ሰው የላትም። ልክ ከፊቷ እንዳሉት ችግሮች ሁሉ አጋጣሚዎችን በራሷ አቅምና ሀሳብ መወጣት ግድ ብሏታል። ሁለት ህጻናት ልጇቿ ሀላፊነቷ ናቸው። እነሱን መያዝና መንከባከብ፣ ማብላትና ማስተማር አይቀሬ ነው ።ወይዘሮዋ አሁን ልደታ አካባቢ በተከፈተው የምገባ ማዕከል ተጠቃሚ ሆናለች፡፤ይህን ያወቀው ባለቤቷ ድርጊቷን ከልመና ቆጥሮ እንድትተው አስጠንቅቋታል።
እጅግ አየሁና ትልቁ ልጇ በቀን የሚያገኙትን የአንድ እንጀራ በወጥ በረከት ፈጽሞ ማለፍ አይፈልጉም። አንዳንዴ ከእንጀራ የዘለለ ምርጫ አላቸው። የተሰጣቸውን በምስጋና አጎንብሰው ይቀበላሉ። ልጇ ሰአት ያለፈ በመሰለው ጊዜ እናቱን እየወተወተ ያስታውሳታል።
እጅግአየሁ በየቀኑ ከስፍራው ደርሳ የተሰጣትን ከልጇ ትካፈላለች። እንዲህ መሆኑ በባዶ ሆድ መድሀኒት ለምትወስደው ህመምተኛ ታላቅ መፍትሄ ሆኗል። አሁን ቀምሶ ፣ ተቃምሶ ለማደር እሳትና የጋለ ምድጃን ብቻ አትጠብቅም። ከተዘጋጀው ለእሷ ቆርሳ፣ ለልጇም አጉርሳ በምስጋና ቤቷ ትገባለች።
ዛሬም እጅግአየሁ ህይወትን ለመግፋት፣ ኑሮን ታግሎ ለማሸነፍ እየታገለች ነው። የባለቤቷ በሀሳብ አለመደገፍ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ቢሆንባትም ከትጋቷ ጋር ልጆቿን ማሳደግ ራሷን ማሳደር ቀጥላለች።እሷ ከጠባሳዋ ጀርባ ህይወትን አርቃ፣ታያለች።ካልደነው፣ ካልሻረው ቁስሏ ባሻገር ነገ ሙሉ ተስፋዋ ነው። ፈገግታና ምስጋናም የሁልጊዜ ልማዷ ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም