የሰው ልጅ በምድር ሲኖር፤ በጸብ ፈንታ ፍቅርን፣ በልዩነት ፈንታ አንድነትን፣ በስንፍና ፈንታ ታታሪነትን፣ በቂምና በቀል ፈንታ ይቅር ባይነትና እርቅን፣… ይላበስ ዘንድ የተገባ ነው፡፡ ሆኖም ለጽድቅ የተፈጠረው ሰው ሐጢያትን፣ ለፍቅር የተፈጠረው ሰው ጸብን፣ ለአብሮነት የተፈጠረው ሰው መገፋፋትና መለያየትን፣ ለሰላም እና ይቅር ባይነት የተፈጠረው ሰው ቂምና በቀልን፣ ሰርቶ በላቡ እንዲኖር የተፈጠረው ሰው ሌብነትና ቀማኛነትን፤… በመምረጡ ጽድቁ ወደ ሃጥያት፤ ሰላሙም ወደ ጭንቀት፣ ፍርሃትና ጦረኝነት፣ ክብሩም ወደ ውርደት፣ ልጅነቱም ወደ ተቅበዝባዥነት እንዲለወጥ ሆነ፡፡
በዚህም የሰው ክቡርነት፣ የሰው ኃያልነት፣ የሰው መልካምነት፣ የሰው የጽድቅ መንግስት ወራሽነት ተሽሮ፤ የሃጢያት ደብዳቤ ተጻፈበት፣ የሞት ፍርድ ወደቀበት፡፡ ይሁን እንጂ ፈጥሮ ፍጥረቱን የማይዘነጋ አምላኩ በይቅርታ ሊመልሰው፤ በምህረት ሊጎበኘው ፈቅዶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ እና ከሰው ወገን ከሆነችው ድንግል ማርያም ተወልዶ የምህረቱን ልክ፣ የይቅርታውን ጥግ ገልጦ አስተማረው፡፡ ዛሬ በመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ የሚውለው “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ” የልደት በዓል ይሄንኑ በሃጢያት የወደቀና በሞት ፍርድ ውስጥ የነበረን የሰው ልጅ የማዳን ሥራን በልደቱ አንድ ብሎ የጀመረበትን ድንቅ ስራ የሚያሳስብ ነው፡፡
የልደቱን ዕለት የማሰብ ሂደቱ ቀዳሚው ጉዳይ የሰው ልጅ በደሉ ተሰርዮ ከሞት ወደ ሕይወት እንዲሸጋገር የመደረጉ ሥራ ይሁን እንጂ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ሥራ የሰው ልጅ ቀደም ባሉት 5ሺህ 500 ዓመታት ጉዞው ታሪክ የቀየረበት፤ ቂሙን በይቅርታ፤ መለያየቱን በአንድነት እንዲተካ ያደረገበትም ጭምር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የሚከበረውን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በክርስቲያኖች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የዕርቅ መጀመሪያ ተደርጎ ይታሰባል” ሲሉ መግለጻቸውም ለዚሁ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሰፈሩት፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በፈጣሪና በፍጡር፣ በሰማይና በምድር፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ታላቅ የጠብ ግድግዳ ተገንብቶ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። በመሆኑም የልደት በዓል “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለው የፈጣሪ ቃል በተግባር መፈጸም የጀመረበት፤ በአምላክና በሰው ልጆች መካከል ዕርቅ የተወጠነበት ዕለት ነው። መለያየት የጠፋበት፣ ኅብረትና አንድነት የጸናበት፤ መለኮትና ሥጋ፣ ህያውና ሟች፣ ዘላለማዊና ጊዜያዊ፣ ፈጣሪና ፍጡር፣ ሰማያዊና ምድራዊ፣ ምሉዕና ውሱን፣ ተዋህደው አንድ ሆነው አዲስ የምሥራች የተበሰረበት ነው፡፡ ዕለቱ የሰማይና የምድር ፍጡራንን በደስታ ሞልቶ በቤተልሔም ከተማ በአንድነት እንዲዘምሩ አድርጓል። ተራርቀው የሚኖሩትን አሰባስቦ በአንድነት እንዲዘምሩ ያደረጋቸው ጉዳይ ከትናንት ለየቅል ታሪካቸው ይልቅ የነገ የጋራ ተስፋቸው ብሩህ ሆኖ ስለታያቸው ነው።
ዛሬም በኢትዮጵያ ይሄንን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታና እርቅ ተግባር አብዝተው የሚሹ አያሌ ጉዳዮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በጠብና በመለየት ምክንያት ኀዘንና ሰቆቃው በዝቶ በሰው ልጆች ታሪክ ጊዜው ዘመነ-ፍዳ ይሰኝ እንደነበረው ሁሉ፤ ዛሬም በኢትዮጵያ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶች፣ ይሄን ተከትለው የተገለጡ አለመግባባቶች፣ መገፋፋቶች፣ መለያየቶች፣ ግጭትና ግድያዎች፣ አለፍ ሲልም የእርስ በእርስ ጦርነቶች ከትናታችን እንዳንሻገር፤ ዛሬ ላይ እንድንፈተን፤ ነገን በጋራ እሳቤ በሙላት እንዳንመለከት እንቅፋት እየሆኑብን ይገኛሉ፡፡ እናም ይሄን የመለያየት ግንብ የሚሰብር፣ የነገ የጋራ ተስፋን ግርዶሽ የሚገልጥ፣ የፍቅርና አንድነት፣ የይቅርታና እርቅን መንገድ የሚጠርግ እሳቤ ያስፈልጋል፡፡
ምክንያቱም በፍቅር እና በይቅርታ የተሳሰሩ ሕዝቦች በወል ተስፋቸው የነገውን በጋራ ከተጋሩት፣ በነገው ላይ ከተግባቡ በትናንቱ ላይ መስማማት አይፈትናቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሉትም፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ መለያየት የመጣው እንዲሁ አይደለም። ሆን ተብሎ ተሠርቶበት ነው። ክፉው ሆን ብሎ የልዩነትን ዘር ዘርቶ፣ የልዩነትን እሾህ አብቅሎ፣ የጠላትነትን ፍሬ እንዲያፈራ አድርጓል። ልዩነቱም ከመለያየት አልፎ ወደ ጠላትነት እንዲሻገር ሠርቷል። … ጦርነትና ግጭትን አትርፏል። በዚህ ሁሉ ጠላት እንጂ ማንም አልተጠቀመም።
እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ከዚህ የልደት ታሪክ ብዙ ትምህርት ብንወስድ ይጠቅመናል። ዛሬ እዚህም እዚያም የምናየው የመለያየትና የመጠፋፋት አባዜ የባህሪያችን አይደለም። የማናችንም ማንነት መገለጫ አይደለም። ይህ የተዘራብን ክፉ ዘር ውጤት ነው። የጠላታችን ዓላማ ደግሞ አንዳችንን ጠቅሞ ሌላችንን መጉዳት ሳይሆን ሁላችንንም ማጥፋት ነው። ጠላታችን አንዱን ሕዝብ ከሌላው በማጋጨት አይቆምም፤ አንዱንም ሕዝብ እርስ በርሱም ያባላዋል። ክልልን ከክልል፣ ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ፣ ጎጥን ከጎጥ፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ባልን ከሚስት፣ ልጆችን ከወላጆች እያባላ ዓለምን ሁሉ የግጭትና የጠብ አውድማ ማድረግ ነው ምኞቱ። ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ። ምክንያቱም ታሪክ ማለፉ አይቀርም። ታሪክ መለወጡም አይቀርም። ቁም ነገሩ “የታሪክ ተከሳሽና ተወቃሽ ወይንስ ተዘካሪና ተሞጋሽ እንሆናለን?” የሚለው ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ከፍ ወዳለው ብልጽግና ለማሻገር ፀብና መለያየትን በመሻር “በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ” ልደት የተገኘውን አንድነት ማጽናት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም