ዓለማችን ካስተናገደቻቸውና እያስተናገደቻቸውም ካለችው ፍልስፍናዊ ንትርኮች መካከል ሁለቱ፣ እዚህ በርዕሳችን የጠቀስናቸው አወዛጋቢና የዓለምን ፈላስፎች (ወደ ፊትም ይቀጥላል) ቀልብና ትኩረት የሳቡ ጥልቅና ሰፋፊ እሳቤዎች ናቸው።
ፈረንሳዊው የንድፈ ሀሳብ ቀማሪ፣ በግለሰብ እና መንግሥት (Individual and The State) መካከል ስላለውና መኖር ስለሚገባው ግንኙነት ያለ መቋረጥ የጻፈው ጆሴፍ እኤአ በ1846 “The Philosophy Of Poverty” (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ለምሳሌ Colorado State University ውስጥ በ3 ክሬዲት አዎርስ (Credits) ለ Philosophy and Religious Studies ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ ትኩረቱ (ይዘቱ)ም ስለ ድህነት ምንነት ብያኔ መስጠት፣ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር፤ እንዲሁም፣ የአሳዛኙን ዓለም አቀፍ ድህነት (the tragedy of global poverty) ምንጭ መመርመርና መፍትሔዎችን መጠቆም ላይ ነው) ብሎ ለጻፈው ጽሑፍ በዛን ወቅት ፓሪስ (ከ1843 እስከ 1849) ይኖር የነበረው እና መጽሐፉን ያነበበው ካርል ማርክስ ከፈረንሳይ ተባሮ ወደ ብራስልስ ከሄደ በኋላ ለፈረንሳዊው ፕሉዶን እኤአ በ1847 አጋማሽ “The Poverty Of Philosophy” (በመጀመሪያ የተጻፈው Misère de la philosophie በሚል የፈረንሳይኛ ርዕስ ነው) ብሎ በጻፈው መጽሐፍ ምላሹን ሰጥቷል።
ባጭር ስናስቀምጠው፣ በተቋም (Institute of Marxism Leninism) አማካኝነት ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው The Poverty Of Philosophy መጽሐፍ፣ ሥራዎቹ በገንዘብ እና የኃይል ፖለቲካ ላይ የሚያተኩሩት፤ ጀርመናዊ ፈላስፋ እና የፖለቲካ ተመራማሪው፤ ደመወዝ ተከፋይ ጉልበት ባለበት ሁሉ የመደብ ትግል ይኖራል፤ ይህ የመደብ ትግል ደግሞ በሠራተኞች አሸናፊነትና የበላይነት የሚደመደም ይሆናል የሚል አቋምን የሚያራምደው ካርል ሔንሪክ ማርክስ (5 ሜይ 1818 – 14 ማርች 1883) ለጆሴፍ (Pierre-Joseph Proudhon (1809-1865)) The Philosophy Of Poverty ምላሽ የሰጠበት ተነባቢ መጽሐፍ ነው። ጆሴፍ የፈረንሳይ ሶሻሊዝም አብዮት አራማጅ (ሶሻሊስት)፣ ፖለቲከኛ፣ ፈላስፋ፣ ኢኮኖሚስት፤ እንዲሁም፣ “የመደጋገፍ ፍልስፍና” (mutualist philosophy) መሥራች ፤ “እኔ ሥርዓት አልበኛ (anarchist) ነኝ” ብሎ በማወጅ የመጀመሪያው ሰው፣ በዚህም ምክንያት ”one of anarchism’s most influential theorists”፣ “father of anarchism” የሚል እውቅናን ያተረፈ፤ የ1848ቱን የፈረንሳይ አብዮት ተከትሎ የፓርላማ አባል የነበረ መሆኑ ነው በሕይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው።
ሥርዓተ አልበኝነት ”anarchism” የፖለቲካ ፍልስፍና (political philosophy)፣ ሲሆን፤ “ሥርዓተ አልበኝነት መንግሥት ወይንም ሀገር የተባለ አደረጃጀት ጥቅም የለሽ፣ አላስፈላጊ እና ጎጂ ነው ብሎ የሚያምን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው። ሥርዓት አልበኞች ሁሉም መንግሥታት እንዲፈርሱና በምትካቸው ሰዎች ያለምንም ጉልበት ወይም አስገዳጅ ኃይል፣ በራሳቸው ፈቃድ እየተሰባሰቡ የትብብር ማኅበረሰቦች እንዲመሠርቱ ይታገላሉ። አናርኪስም በአውሮጳ አህጉር በ20ኛ ክፍለ ዘመን ተመሥርቶ ወደ ሌላው ዓለም የተስፋፋ ንቅናቄ ነው።” የሚለው ብያኔ ላይ የጋራ ስምምነት አለ።
ለዚህ፣ ለዛሬው ጽሑፋችን መነሻ የሆነው በአንድ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያው (ወንድወሰን እሸቴ በተባሉ ሰው የሀሳብ መሪነት) የውይይት መነሻ (አልዘለቀም እንጂ ቢቀጥል ጥሩ ነበር) ሆኖ የነበረውና “ኢትዮጵያን ምታት ሆኖ የመታት እና እጀ ሰብ ሆኖ ለብዙ መቶ ዓመታት በችጋር አለንጋ ገርፎ በጣም የሚያሰቃያት የትኛው ነው? ‘የድህነት ፍልስፍና’ ወይስ ’የፍልስፍና ድህነት’?” የሚለው ጠጣርና ምናልባትም አስተማሪ የሆነ ሀሳብ ነው። (ምክንያቱ በርዕሳችን የጠቀስነው ይሁን ወይንም አይሁን በውል ባይታወቅም፣ እኛ ሀገር እንደዚህ ዓይነት አስተማሪ የሆኑ የውይይት ሀሳቦች በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ለሳምንት እንኳን የመዝለቅ አቅም የላቸውም። ሌሎቹ፣ መሰዳደብን የመሳሰሉት ግን …)
እርግጥ ነው፣ የዚህ ጽሑፍ ዓቢይ ዓላማ፣ አስቀድመው እርስ በርሳቸው የተጠዛጠዙትን፣ እነዚህን ሁለት ምድር አንቀጥቅጥ ሥራዎች እዚህ ለመዳኘት ወይም ለማስታረቅ ወይም የበለጠ ለማጠዛጠዝ … አይደለም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በቀጥታ ስለ ሥራዎቹ ለማውራትም አይደለም። የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ዓላማ በእነዚህ ሁለት የዓለማችን እውቅ ሥራዎች ተታክኮ የሀገራችንን ሁኔታ ማስተዋል፤ ነፍሱን ይማረውና ደምሴ ፅጌ የሥነጽሑፋችንን የቁልቁለት ጉዞ አይቶ ”ምን አይነት ዳፍንት ነው ሥነጽሑፋችንን …” ሲል እንዳሄሰው ሁሉ፣ እኛንም ”ምን አይነት ዳፍንት … እንደ ሆነ … እንደዚህ …”፤ ምን አይነት ግርዶሽ እንደ ሆነ እንደዚህ … ለማመልከት፣ ከተቻለም የውይይት ርዕስ ለመክፈት ነው። ከተቻለም፣ የእነ ውብሸትን ጥያቄ ለማፅናትና የውይይት ወሰኑን ለማስፋት።
ይህ ጽሑፍ እነዚህን ሁለት ለምድር የከበዱ ሥራዎች በተመለከተ ማለት የሚችለው አንድ ጉዳይ ብቻ ሲሆን፣ እሱም አንባቢ ሥራዎቹን ፈልጎ እንዲያነባቸው፣ በንባብ ሂዱቱም በአግባቡ ለመገንዘብ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰብ ብቻ ነው።
ድሮ ድሮ የድህነት ጉዳይ የአገር መሪዎችን፤ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ጉዳዮችን የተመለከቱ ፖሊሲ አውጪዎችን ብቻ የሚመለከት ሆኖ ነበር የሚታየው። እነሱም ችግሮችን እኛ ብቻ ነን የምንፈታው በማለት በብቸኝነት ሲዳክሩ ነበር አሉ ዘመናትን ያስቆጠሩት። ይሁን እንጂ፣ጉዳዩ በዚሁ አልዘለቀም። ጉዳዩ ብዙም ሳይቆይ በፈላስፎች ሳይቀር ተጠለፈና መፍትሔውን ፍለጋ መዳከሩ፣ መውጣት መውረዱ የሁሉም ሆነና አረፈው። “የሁሉም …” እንበል እንጂ በጉዳዩ ላይ ከመቆዘም አኳያ ግን ፈላስፎቹን የሚያክል አልተገኘም። ስለ ሰው ልጅ የሚጨነቁቱ፣ ስለ ዓለማችን የወደ ፊት እጣ ፈንታ የሚያብሰለስሉቱ … ሁሉ ይህንን ርዕስ ጉዳይ ጉዳዬ ብለው በመያዝ ለመፍትሔው ሲጨነቁ (መልካም ተመኚውን፣ ከድህነት ለመውጣት በርካታ ኢኮኖሚያዊ አማራጮች መኖራቸውን የሚጠቁመውን፣ የጄፈሬይ (Jeffrey Sachs)ን The End of Poverty: Economic Possibilities for Our Time ሥራ፤ እንዲሁም፣ ”Philosophy and Poverty”ምን መጥቀስ ይቻላል) ነው እየተስተዋለ ያለው። ይህ ደግሞ ተገቢና የሚጠበቅ ነውና የሚገርም አይሆንም። የሚገርም ሊሆን የሚችለው ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው፣ የፖለቲካ አመራሩን ጀልባ የሚቀዝፉቱ ፀጥ ረጭ ማለትና ስለ ግል ጉዳያቸው መጨነቅ፣ መጠበባቸው ነው።
እስካሁን ከርዕሰ-ጉዳያችን ጋር በተያያዘ ወደ ውጭ ስናይ ቆይተናል። ቀጥለን ደግሞ ወደ ራሳችን፣ ወደ ውስጥ እንመልከትና ጉድፍ ካለብን እሱን እናንሳ።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ታላቅ እና የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብትን አብዝታ የታደለች አገር ነች። ይሁን እንጂ፣ ምን አይነት ዳፍንት … እንደ ሆነ ባይታወቅም፣ ሁሌም ከችግር ወጥታ አታውቅም። በድሮውና በአሁኑ መካከል ያለው የችግሩ ልዩነት አንድ ሲሆን፣ እሱም የዘንድሮው ችግር ከድጡ ወደ ማጡ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ይህን ችግር ለማብራራት የግድ ወደ ኋላ መሄድና ታሪክን ማጣቀስ የለብንም። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መሰናበቻ ጀምሮ አሁን እስካለንበት፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ያለው የ”ከድጡ ወደ ማጡ” ጉዞ ብቻ በቂ ነውና እሱው ላይ እናተኩርና ሀሳብ እንለዋወጥ።
ታሪክ በአግባቡ ሰንዶ እንዳስቀመጠው የእርስ በ’ርስ ጦርነት ተለይቶን አያውቅም። መግደል፣ መጋደል፣ መገዳደል … (አንዳንዶች እንደሚሉት፣ የጥላሁን ገሠሠን “ግደል ተጋደል / በርታ ወገኔ …”ን በተሳሳተ መንገድ የተረዳ ትውልድ ሁሉ ተፈጥሯል) የዕለት ተዕለት ሥራችን ሁሉ እስከመሆን ደርሷል። ችግራችን “የድህነት ፍልስፍና” ይሁን፣ ወይም/እና “የፍልስፍና ድህነት”? ቁርጥ ያለውን እሚነግረን ቢጠፋም ከሁለቱ አንዱ፤ ወይም ሁለቱም ስለ መሆናቸው ግን በርካታ አመላካች ክንውኖች አሉ፤ አናነሳቸውም እንጂ ሁለቱም ችግሮቻችን የነበሩበት ወቅት እንደ ነበር ወዳጅም ጠላትም ያውቃል። ”ተከድኖ ይብሰል” ካልሆነ በስተቀር፣ በተለያዩ ጊዜያት ሁለቱም ሰንገው የያዙን ችግሮቻችን እንደ ነበሩ ሳይጠቅሱ መዝለል አይቻልም።
ችግራ(ሮቻ)ችን “የድህነት ፍልስፍና” ይሁን፣ ወይም/እና ”የፍልስፍና ድህነት”? ለይተን ባንናገረውና ባንጋፈጠውም ችግር መኖሩ ላይ ግን እስካሁን የተከራከረ ለማግኘት አልተቻለም። ምን ለማለት ነው፣ ችግር ብቻ አይደለም ችግሮች አሉ።
የአሁኑን፣ “ከድጡ ወደ ማጡ”ን ጉዞ ከድሮዎቹ ለየት የሚያደርገው በርካታ ባህርያት ያሉት ሲሆን ከሁሉም የከፋው ግን ጭካኔው ነው። ችግሩ “የድህነት ፍልስፍና” ይሁን፣ ወይም/እና ”የፍልስፍና ድህነት”? (ሁለቱንም አያድርግብንና እንዳንል አስቀድሞ ሆኗልና) ከስሩ ለይተን ባናሰምርበትም ግን፣ ችግሩ አለ።
እርግጥ ነው ”የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህ ነው። ‘ተከብቤያለሁ’ ላለ ሁሉ ፈጥኖ የሚደርስ ሕዝብ ነው” የሚል ገራገር ይሁን (ወይም፣ አይሁን) አስተያየት አልፎ አልፎም ባይ(ቢ)ሆን ይሰማል። ጥሩ ነው፤ ለተከበበም ሆነ ላልተከበበ መድረስ ችግር የለውም። ምናልባትም ግደል ሲባል መግደልም ችግር የለውም የሚል ሊኖርም ላይኖርም ይችል ይሆን ይሆናል፤ አናውቅም። እንደ አጠቃላይ ግን ችግራችን “የድህነት ፍልስፍና” ይሁን፣ ወይም/እና ”የፍልስፍና ድህነት”? ተለይቶ ቢታወቅ (”ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ አካል ነው” እንዲሉ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች) አይጠቅምም ቢባል እንኳን አይጎዳምና እንደ አማራጭ ቢወሰድ ፋይዳው ለሁሉም ነው።
”ድህነት ኢትዮጵያን የሚጎበኛት በዙር ነው” (cycle of poverty ወይም poverty trap) እያሉ ያሙናል። ሲፈልጉ ደግሞ ”አረንጓዴው ድርቅ” እያሉ ዘጋቢ ፊልም ይሠሩብናል። ይሠሩብንና ዓለሙ ሁሉ ይሳለቅብን ዘንድ ለስክሪን ይዳርጉናል። ”እነዚህ ሰዎች ችግራቸው ምንድን ነው?” ሲሉ ራሳቸውን ይጠይቁና በሆዳቸው ”ችግራቸው ’የድህነት ፍልስፍና’ እና ’የፍልስፍና ድህነት’ ነውን?” ሲሉ መልሰው ራሳቸውን መልስ አከል ጥያቄን ይጠይቃሉ። በዚህ ሳያበቁም ወደ ጦርነት ታሪክና ባህላችን ይመጣሉ።
“እርግጥ የጦርነት ታሪካቸው በጀግንነት የታጀበ፣ በድልም ያሸበረቀ ነው። ወደ እርስ በ’ርሳቸው ሲመጣ (“መ” ይጠብቃል) ግን፣ ይህ የጦርነት ታሪክና ባህላቸው ግን ከደረጃ በታች ያወርዳቸዋል። በደማቁ የተፃፈላቸውን የማንነት፣ የሀበሻነት ታሪካቸውን … ሁሉ ይዞት ገደል ይገባል። ‘ችግራቸው ምንድን ነው?’ ተብሎ ይጠየቅ ዘንድም ግድ ይላል። ‘የድህነት ፍልስፍና’ ወይስ/እና ‘የፍልስፍና ድህነት’? ተብሎ ይጠረጠር ዘንድም ይጋብዛል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ አይነት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባትስ ኢትዮጵያን ይመጥናልን? የሚል ጥያቄ በአዕምሮ ይጫር ዘንድም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።” እያሉ የሚያወሩት፤ በማለትም የሚጽፉት ቁጥራቸው እለት በእለት እየጨመረ ነው።
እንደገናም፣ “ምክንያቱ ምንድን ነው?” ተብሎ ይጠየቅ ዘንድም ያስገድዳል። መልሱንም ሁለቱም (“የድህነት ፍልስፍና” እና “የፍልስፍና ድህነት”) ወይም ”ከሁለቱ አንዱ” ተብሎ ፍርጥ አድርጎ ለመመለስም ያስገድዳል። እውነት እውነት፣ ችግሩ ምንድን ነው ግን???
ድሮ ድሮ በሰላምና በፍቅር አጥብቀው የሚያምኑት ኢትዮጵያውያን ዛሬ ጭር ሲል አይወዱም እያሉም ያሙናል ነው የሚባለው። እውነት ከሆነ በእውነት ያሳዝናል። ችግሩን ለይቶ ለማወቅ ይቻል ዘንድም ችግሩ “የድህነት ፍልስፍና” ወይስ/እና “የፍልስፍና ድህነት”? ተብሎ ይጠየቅ ዘንድም ሁኔታዎች ከታች እስከ ላይ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ … ያስገድዳሉ። ጉዞው ”ከድጡ ወደ ማጡ …” ቢሆንም፣ በሰላም ውሎ በሰላም እያደረ ያለ ስፍራ እስኪገኝ ድረስ ሁሉ ያስኳትናሉ (ካለ)። ይህም ይመስላል በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው ሁለት ጎምቱዎች በ”የድህነት ፍልስፍና” እና በ”የፍልስፍና ድህነት” መካከል ሆነው (ለአንድ ዓላማ?) የተፋለሙት።
መቼም፣ የትም ሆነ የት ችግር ያለ ምክንያት አይከሰትም። ማለትም የማይፈታ ችግር የሌለውን ያህል ምክንያት የሌለው ችግርም የለም። ሳቢያና ውጤት የሌለው ችግርም የለም። ችግሩ እነዚህን ለይቶ፣ ፈልፍሎ ማውጣቱና የችግሩ መንስኤ “የድህነት ፍልስፍና” ነው ወይስ/እና የ”የፍልስፍና ድህነት” የሚለውን ማመልከቱ ላይ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ከላይ እንዳልነው የችግሮቻችን መፍትሔ በግማሽ ተገኘ ማለት ነውና ሴትየዋ ”እልል በቅምጤ” እንዳሉት እልልልልል… ያሰኛል።
ባጠቃላይ፣ ችግሮቻችን ተቆጥረው አያልቁም። በተለይ አሁን አሁን በውክልና የዓለምን ችግሮች ሁሉ እኛ እያስተናገድን ይመስላል። ረሀብ አለ። ጦርነት አለ። የእርስ በእርስ መቆራቆስ አለ። ሙስናው ጣራ ነክቷል። ዘረኝነት ተንሰራፍቷል። የትምህርት ጥራት ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል ከተባለ ቆየ። የኑሮ ውድነት ቅጡን አጥቷል። ሕገ ወጥነት ሕጋዊ እየሆነ ነው። ሕዝባዊ አገልግሎት ከተመሰቃቀለ ቆየ። እዚህ አገር ምን የሌለ ችግር አለ? ምንም። በመሆኑ የችግሮቻችን ሁሉ መንስኤ “የድህነት ፍልስፍና” ወይስ/እና “የፍልስፍና ድህነት” የሚለው ላይ ከምር መነጋገር ያስፈልጋል። ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም