የበዓለ ልደት ብሥራት፤
ይህ ዛሬ እያከበርነው ያለነው ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ ልዩ ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድነት ተልዕኮውን ለመፈጸም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበት ዕለት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ኪዳን መሠረት የተጣለበት ሁነኛ የመታሰቢያ በዓልም ነው፡፡ ጸሐፊው መላውን የክርስትና እምነት ቤተሰቦች “እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!” በማለት ምኞቱን የሚገልጸው ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን ተፈጽመው የነበሩ አንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶችን በእግረ መንገድ በማስታወስ ጭምር ነው፡፡
ከብሉይ ኪዳን አሥራው መጻሐፍት የመጨረሻው እንደሆነ በሚታመነው ትንቢተ ሚልክያስና በአዲስ ኪዳኑ የመጀመሪያ መጽሐፍ በማቴዎስ ወንጌል መካከል (በመሃከላቸው አዋልድ በመባል የሚታወቁ መጻሕፍት ተጽፈዋል የሚል መከራከሪያ እንዳለ ሆኖ) ያለው የዘመን ርቀት አራት መቶ ዓመታት እንደሚሸፍን በርካታ የሥነ መለኮት ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ እነዚህ አራት ክፍለ ዘመናት በዋነኛነት የሚታወቁት “የእግዚአብሔር የዝምታ ዘመናት” እየተባሉ ነው፡፡ እንደ ዘርፉ ተመራማሪዎች ማብራሪያ ከሆነ የዝምታው መገለጫዎች በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ከዚህ ጽሐፍ ዓላማ ጋር እጅግም ስለማይጎዳኙ ታሪኩን የጥቁምታ ያህል ለማስታወስ እንሞክራለን፡፡
ለመሆኑ “እግዚአብሔር ዝምታን ያውቅበታል ወይ? እንደምንስ አስጨክኖት ለአራት መቶ ዓመታት ያህል ሕዝቡን ባስለመዳቸው መንገድ ሊናገራቸው አልፈቀደም? ወዘተ.” ለሚሉት ጥያቄዎች በርካታ ታሪካዊና ሥነ መለኮታዊ ምክንያቶችን መደርደር ቢቻልም “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” (መጽሐፈ መክብብ 3፡7) የሚለውን ቅዱስ ቃል በማስታወስ፤ በራሱ ሁሉን አወቅ ባህርይ ፈጣሪ “ዝምታን” መርጦ አምላካዊ ተግባሩን ለማከናውን ምርጫው ቢያደርግ ሊደንቀን አይገባም የሚለው ምላሽ ተዘውትሮ ይደመጣል፡፡
“እግዚአብሔር ስለ ምን ዝም ሊል ቻለ?” ተብሎ ለሙግት መደፋፈሩም ጉንጭ አልፋነት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ምንም ይሁን ምን በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ ፈጣሪ በድርጊታችንና በበደላችን ምክንያት በዝምታና በፈቀደው ማስተማሪያ እንዳይቀጣን ወይንም እንዳይፈርድብን ከበደላችንና ከኃጢያት መመለሱ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል፡፡
ይልቅስ “እግዚአብሔር ዝምታውን ሰብሮ” ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በአዲስ ዘመን መባቻ የአይሁዳዊያኑ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወት ምን መልክ እንደነበረው በጥቂቱም ቢሆን አስታውሶ ማለፉ ለዋናው ሀገራዊ የመዳረሻ ሃሳባችን ጥሩ መደላድል ሊሆን ስለሚችል ዋና ዋና አንኳር ክስተቶችን ለመጠቋቆም እንሞክር፡፡
እስራኤላዊያን አይሁዶች እንደ ሕዝብ ተስፋ በተገባላቸው ምድር ላይ ለመሰባሰብና ሀገረ መንግሥታቸውን ከመሠረቱም በኋላ የደረሰባቸው መከራ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ተዘርዝሮ እናነባለን፡፡ በጠላቶቻቸው ተደጋጋሚ አሸናፊነት የባርነትን ኑሮ በሚገባ አልፈውበታል፡፡ በመሳፍንቶቻቸው ዘመን የነበረው የርሃብና የእርስ በእርስ መቆራቆዝም አድቅቋቸዋል፡፡ በምርኮ ተሰደው ሀገር አልባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡ የሃይማኖታቸው ማዕከላዊ ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ የሚቆጠረው ቤተ መቅደሳቸው በማራኪዎቻቸው የፍርስራሽ ክምር ሆኗል፡፡ ሀብታቸው ተበዝብዟል፡፡ ከርስታቸው ተነቅለውም በመላው ዓለም ሊበተኑ ግድ ሆኗል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ዝርዝሩን እንደምናነበው ባቢሎናዊያን (ቅ.ል.ክ 423 – 372) ነገደ አይሁድን ማርከው አሰቃይተዋቸዋል፡፡ የሜዶ ፋርስ ነገሥታትም (ቅ.ል.ክ 372 – 348) ለባርነት አፍልሰው አስገብረዋቸዋል፡፡ የዚህ ገናና መንግሥት ኃይል ሲዳከምም የግሪክ መንግሥት አንሰራርቶ (ቅ.ል.ክ 371 – 141) በብረት በትር ተቀጥቅጠው ተገዝተዋል፡፡ ባህላቸውና ቋንቋቸውም በሄለናዊያን ተጽእኖ ሥር ውድቆ የማንነታቸውን ክብር እስከማጣት ደርሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ሊሆን ግድ ሆኗል፡፡
ሥልጣን አንዴ ወዲህ አንዴ ወዲያ መገለባበጡ የተለመደ ነውና የግሪኮች ጉልበት መላላቱን ያስተዋለው የሮም መንግሥትም (ቅ.ል.ክ ከ69 ጀምሮ) የተረኛነቱ ጊዜ ደርሶ ኃይላቸውን በማሽመድመድ ሌላ ጌታ ሆኖ አስገብሯቸዋል፡፡ በጭካኔያቸው ወደር አልተገኘላቸውም የሚባሉት ሮማዊያን ጌቶቻቸው ካስገበሯቸው በኋላ የፈጸሙባቸው ግፍና የጫኑባቸው የመከራ ዓይነቶች በእጅጉ የሚሰቀጥጡና የዘመኑን የጠለሸ ታሪክ በግልጽ የሚወክሉ ናቸው፡፡ ክርስቶስ የተወለደው ይህን መሰሉ ውጥንቅጡ በበዛበት ዘመን ነበር፡፡
ጆሲፈስን የመሳሰሉ የዘመኑ ታሪክ ጸሐፊዎች በጽሑፍ ያስተላለፏቸው ሰንዶችና የብራና ጥቅልሎች እንደሚመሰክሩት ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ተቀራራቢ ዓመታት ውስጥ በቄሳራዊያን ገዢዎቻቸው የግፍ ድርጊት ምክንያት በርካታ አይሁዳዊያን በጭካኔ ተጨፍጭፈዋል፡፡ የሮም መንግሥትን ትቃወማላችሁ እየተባሉም ብዙዎች በአደባባይ ተሰይፈዋል፡፡ ከፈሪሳዊያንና ከሰዱቃዊያን የአይሁድ እምነት አስተማሪዎችና መምህራን መካከልም ብዙዎች ተገድለዋል፡፡
እነዚህን መሰል መከራዎችና ግፎች የተሸከመው የአይሁድ ሕዝብ ምንም እንኳን ሰማይ ምድሩ እንደ ወስከንባይ የተደፋበት ቢሆንም ተስፋ ቆርጦ ለጠላቶቹ አልተበገረም፡፡ አምላካቸው ያህዌም እስከ መጨረሻው በዝምታው ሊገፋ አምላካዊ ፍቅሩ አላስቻለውም፡፡ ስለሆነም ከአራት መቶ የዝምታ ዓመታት በኋላ ቀደም ሲል በነብያቱ የተነገሩ የተስፋና የትንቢትን መልእክቶችን ለመፈጸም ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶና ሥጋ ለብሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንዲወለድ ሉዓላዊው አምላክ አንድያ ልጁን መሲህ አድርጎ ወደ ምድር ላከ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በዚያ ሌሊት የመላእክት ሠራዊት ፡- “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ” በማለት የልደቱን የምሥራች ያበሰሩት በሌሊት መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ላደሩት እረኞች ነበር፡፡ ለዘመናት መከራና ፍዳ ሲያስተናግዱ ለኖሩት ግፉዓን ይህ የምሥራች ትርጉሙ ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
ተስፋቸው ወድቆና እግዚአብሔር ረስቶናል “በዝምታውም ቀጥቶናል” ባሉበት በዚያ አስጨናዊ ወቅት የምሥራች ብሥራት መስማት ምን ያህል ከፍ ያለ የትድግና መገለጫ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም፡፡ የክርስቶስ መወለድ የትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የተገባው የመጭው አዲስ ዘመን አዲስ ኪዳን ማብሰሪያም ጭምር ነበር፡፡
እውነታው ይህን ይምሰል እንጂ ይህ አምላካዊ የተስፋ ብርሃን ለብዙ አይሁዳዊያን ሊበራላቸውና እንደ በረከት ሊቀበሉት አልፈለጉም፡፡ አለመፈለግ ብቻም ሳይሆን የሰውን ሥጋ ልብሶ በመካከላቸው የተገኘውን የሰላም አምላክ “የሰላም ግብዣ ባቀረበላቸው” እንደምን በጭካኔ ተነሳስተው ለመስቀል ሞት አሳልፈው እንደሰጡት በክርስትና አማኒያን ዘንድ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ይኼኛውን ታሪክ በተመለከተ በዕለተ ፋሲካ የምንመለስበት ይሆናል፡፡
“ሀገራዊው የአዲስ ኪዳን አዲስ ዘመን መባቻ”
ኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ይህንን የዛሬውን የጌታችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የሚያከብሩት ምናልባትም እንዳለፉት ዘመናት በተለመደ የባህል አከባበር ወግና ሥርዓት ብቻ እንደማይሆን ይታመናል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታትና ወራት ሀገራችን በምን ዓይነት የእርስ በእርስ መራራ ጦርነት ውስጥ እንዳለፈች በፍጹም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ዓላማ ቢስ በሆነ ጦርነትና የሽምቅ ውጊያ ደማቸው በከንቱ የፈሰሰው ዜጎቻችን ቁጥር በአግባቡ ተሰልቶ “ይህን ያህል ነው” የሚለው ሪፖርት ገና ለሕዝቡ ይፋ አልሆነም፡፡ በሚሊዮን ይቆጠር ወይንም በመቶ ሺህዎች እውነቱ ይፋ ሲሆን የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥርም እንዲህ በዋዛ በእርግጠኛ አሀዝ የሚገለጥ አይደለም፡፡
የወደመው የዜጎችና የመንግሥት ንብረትም በገንዘብ ተተምኖ ጠቅላላ ግምቱ “ይህን ያህል ቢሊዮን” ይገመታል ለማለት የዓመታት ሥራ ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ ለተመን የማይመቸው የዜጎች የሥነ ልቦና ቀውስ፣ የፈሰሰው የንጹሐን ደምና እምባ በቁጥርም ሆነ በስፍር ከቶውንም ሊለካ አይችልም፡፡
በአጭሩ ያለፉት ዓመታት ለኢትዮጵያ የመከራና የስቃይ ዓመታት ነበሩ ብሎ መደምድሙ ይቀላል፡፡ የውስጥ የፖለቲካ ትርምሱን፣ የኑሮውን ጫናውን የብረት ቀንበር፣ የውጭ ጠላቶችን ሴራና ተንኮል፣ በእኩይ የዲፕሎማሲ ጫና የተረባረቡብንን በሙሉ ስሌት ውስጥ እናስገባ ብንል በምንም ዓይነት መለኪያና መስፈሪያ የጉዳቱን ተመን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡
“የዛሬው ይበልጥ አንዘረዘረኝ” እንዲል ባለ ሀገሩ ወገኔ፤ የትናንቱ የሀገራችን ታሪክም ቢሆን እንደ ምንጭ ውሃ የኮለለ፣ እንደ ማር የጣፈጠ አልነበረም፡፡ በጥቂቱ እናስታውሰው፡- ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊ ሀገር ተረጋግታና ሰክና ኖራለች የሚባልላቸው ዘመናት ከመከራዋና ከፈተናዋ ዘመናት ጋር ሲነጻጸሩ በእጅጉ አናሳ እንደሆኑ ማረጋገጫችን በጥቁር ቱቢት የተለበጠው መልከ ብዙው የሀገራዊ ታሪካችን ውሎ ነው፡፡
ባእዳን ወራሪዎች ሉዓላዊ አንድነታችንንና ድንበራችንን ለመዳፈር ያልሞከሩበት ዘመን አልነበረም፡፡ በአያት በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ብቻም ሳይሆን፤ በእኛ ዘመንም በስንቱ ፈተና ውስጥ ለማለፍ እንደተገደድን የበቀደሙ ታሪክ ሊዘነጋ የሚችል አይደለም፡፡የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተንበርካኪነት ሳይሆን በአንበርካኪነት ምሥጢር የጸና ስለሆነ ወራሪና ተስፋፊ ጠላቶቻችን በሙሉ ወደመጡበት የተመለሱት በፍጥነት እርምጃ እየገሰገሱ ሳይሆን “የወኔ ብራኳቸው ተሰብሮ” በእንፉቅቅ ዳዴ እያሉ ነበር፡፡
ባዕዳኑን ወራሪ ጠላቶች በመራራ መስዋዕትነት ለመመከትና ድል በድል ላይ ለመረማመድ የተቻለውን ያህል ተፈጥሮን አስገብረን ከድህነትና ከርሃብ ግዞት ነፃ ለመውጣት ግን ወኔና ቁርጠኝነት አልነበረንም፡፡ በዚህም ምክንያት በዓለም ማኅበረሰብ ፊት የሀገራችን መታወቂያ እንደምን የከፋ እንደነበር የምናስታወሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ የትናንትናና የትናንት ወዲያዎቹ ሀገራዊ ፈተናዎቻችንና መከራዎቻችን ያነሱ ይመስል ዛሬ እያለፍንባቸው ያሉት አበሳዎች ምን ያህል ዋጋ እያስከፈሉን እንዳሉ መዘርዘሩ “የአዋጁን በጓዳ” እንዳያሰኝ እናልፈዋለን፡፡
ከላይ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው የዜጎች ሞትና መፈናቀል፣ የንብረት መውደምና የእርስ በእርስ ሽኩቻችን የት አድርሶ ወዴት እንደተመለስን “ጣዕመኑ” ገና ስላለቀቀን “ጣታችንን የምንጠቁምባቸው” ሀገራዊ ጉድፎቻችን አበዛዛቸውና ዓይነታቸው ለእኛም ሆነ ለባዕዳን ታዛቢዎች “ዕንቆቅልሽ” እንደሆኑብን መክረማችን አይዘነጋም፡፡
በዚህ ውጥንቅጡና ቀወሱ በበዛበት ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ እያለን ነው ስለ ሰላም ተነጋግረን ወደ መግባባት ለመቀራረብ የተሞከረው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህንን የልደት በዓል እያከበሩ ካሉ የዓለም ሀገራትና ሕዝቦች ይልቅ ለእኛይቱ ኢትዮጵያና ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ” (ሉቃስ 2፡14) የሚለው የመላእክቱ የምሥራች ይበልጥ ትርጉም ያለው ይመስለናል፡፡
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ስለምን ዝም ይላታል? የመከራችን ማብቂያውስ መቼ ነው? እስከ መቼስ ፈጣሪ ፊቱን አጥቁሮብን እንዘልቀዋለን?” በማለት በየግላችንና በየቤተ እምነታችን እግዚአብሔርን ስንወቅስ መክረማችንን አንክድም፡፡ በየደጀ ሰላሙና በየመስጊዱ የፈሰሰው የእናቶችና የአባቶች እምባ ለዚህ አገላለጽ በአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ሰላምን ተርበን፣ ሰላምን ተጠምተን፣ ሰላም ብርቅና ድንቅ ሆኖብንና የሌሎች ሀገራትንና ሕዝቦችን ሰላም እያስተዋልን የቀናንባቸው ዓመታት ርዝመት ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ የሚወሰን አልነበረም፡፡ በዘመናችንና በእድሜያችን በሙሉ ስንመኝ የኖርነው፣ ስንቃትት የባጀነው “የሰላም ያለህ!” እያልን ነበር፡፡ ዛሬም ሰላማችን ምልዑ ነው ባንልም አበረታች ለመሆኑ ግን የምንክደው አይደለም፡፡
ሰላም በምልዓት የሚረጋጠው የዜጎች በጎ ፈቃድ ሲታከልበት እንጂ ሰላምን በመናፈቅ ብቻ ምኞታችን ይሞላል ማለት አይደለም፡፡ በጎ ፈቃድ ከሌለ በስተቀር ነጩ ጥቁር፣ ጣፋጩ መራራ፣ ብርሃኑ ጨለማ፣ በጋው ክረምት መስሎ መታየቱ አይቀርም፡፡ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰብአ ሰገል በይሁዳ ቤተልሔም ተገኝተው “የሰላም አለቃ” ተብሎ በነብያት ለተነገረለት ለሕጻኑ ኢየሱስ እየሰገዱ የወርቅ፣ የእጣንና የከርቤ ስጦታ ሲያዥጎደጉዱለት በአንጻሩ በጎ ፈቃድ የጎደለውና የደም ጥማተኛው ሮማዊው ሄሮድስ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ጨቅላ ሕጻናት በሙሉ ያስጨፈጭፍ ነበር፡፡
በጎ ፈቃድ ሳይኖር ለይስሙላ ያህል “ሰላም! ሰላም! ሰላም!” በማለት ራስንም ሌላውን መሸነገል ከቶውንም የሚከብድ አይደለም፡፡ “ሰላም ለሀገራችን፤ ለሰዎችም በጎ ፈቃድ” የምንለው ሰላምና በጎ ፈቃድ በፍጹም ሊለያዩ ስለማይችሉ ነው፡፡ የዓለም ታላላቅ ሀገራት እስኪደነቁ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት አያዋጣንም በማለት ለሰላም እሺታውን ያረጋገጠው ለተከፈለው መስዋዕትነት፣ ለወደመው የዜጎችና የሀገር ሀብት፣ ለቆሰለው የግፉዓን ስሜትና ለደረሰብን ሀገራዊ ስብራት ቁብ ሳይሰጥ ቀርቶ ሳይሆን “በጎ ፈቃድ ከጦርነት ድል እንደሚበልጥ” በማመኑ ነው፡፡
በመንግሥትና በሌላው ወገን ከስምምነት ላይ የተደረሰበት “አዲስ ኪዳን” የምር ሆኖ ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን የዜጎች በጎ ፈቃድ ሲታከልበት ስለሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፀብና ለሴራ አሻፈረኝ፣ ለከንቱ መቆራቆዝና ደም መፋሰስም እምቢኝ ብሎ ሊጨክን ይገባል፡፡ በአንጻሩ በየዕለቱ ለሚታዩት መልካም ሀገራዊ የልማት ክንውኖችና ጅምሮች ዜጎች ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያን ከከፍታ ማማ ላይ ለማውጣት እጅ ለእጅ ተያይዘው፤ ልብ ለልብ ተናበው ሊተባበሩ ይገባል፡፡ ሰላም ለሀገራችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡ መልካም በዓል!
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም