
በካናዳ የውጭ አገር ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን እንዳይገዙ ለሁለት ዓመታት እግድ ተላለፈ።የአገሪቱ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ዋጋን ለማረጋጋት ነው ተብሏል።ካናዳ በዓለም ላይ መኖሪያ ቤት በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። በአሁኑ ወቅት የአንድ አማካይ የመኖሪያ ቤት ዋጋ 568 ሺህ ዶላር ገደማ ነው።
ይህ አሃዝ ከግብር በኋላ አንድ ቤተሰብ ከሚያገኘው ዓመታዊ ገቢ በ11 እጥፍ ይበልጣል።አንዳንዶች ይህ የአገሪቱ መንግሥት ውሳኔ በካናዳ የቤት ገበያ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም ይላሉ።የመኖሪያ ቤት ዋጋ የማይቀመሰ ነው በሚባልባቸው ኦንታሪዮ እና ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ከአጠቃላይ የቤት ባለቤቶች መካከል የውጭ አገር ዜጎች ከ6 በመቶ በታች ናቸው።
ተፈጻሚ የሆነው እግድ ዜጎች እና የካናዳ ቋሚ ነዋሪ ከሆኑት የውጭ ዜጎች መኖሪያ ቤት እንዳይገዙ የከለከለ ሲሆን፤ መመሪያውን የሚተላለፉ10ሺህ የካናዳ ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።የአገሪቱ የፌደራል ቤቶች ሚኒስትር አሕመድ ሁሴን ክልከላው ሰዎች ቤቶች እንደ መኖሪያ ቤት እና ቤተሰብ ማሳደጊያ እንጂ እንደ ሸቀጥ እንዳይመለከቱት ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
“በዚህ የሕግ ውሳኔ፤ በዚህ አገር የሚኖሩትን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑት ካናዳዊያን እንዲሆኑ እርምጃ እንወስዳለን”። ባለፉት ዓመታት በካናዳ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።እ.ኤ.አ 2013 ላይ ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ባለፉት 10 ዓመታት የመኖሪያ ቤት ዋጋ በ48 በመቶ ጨምሯል።
በሌላ በኩል የዜጎች ገቢ ከፍተኛ ጭማሪን አላሳየም። ከ2015 እስከ 2020 በነበሩት ዓመታት የአንድ ቤተሰብ አማካይ ገቢ የጨመረው በ9 ነጥብ 8 በመቶ ነበር።ከካናዳ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ከፍተኛ ከሆኑባቸው አገራት መካከል ኒው ዚላንድ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ይጠቀሳሉ።
ኒው ዚላንድ እ.ኤ.አ 2018 ላይ በተመሳሳይ የመኖሪያ ቤት ዋጋን ለማረጋጋት በሚል የውጭ አገር ዜጎች ቤት እንዳይገዙ እግድ ጥላ ነበር።ኒው ዚላንድ እገዳውን ብትጥልም የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን እንደቀጠለ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 /2015