የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን እንዳላወደመ ተጠቆመ

አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳየ። ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው። ኢራን ያበለጸገችው የዩራኒየም ክምችት አሜሪካ ቅዳሜ፣ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በፈጸመችው ጥቃት አለመውደሙን የአገሪቱ የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ “ይህ ፍጹም የተሳሳተ” ግምገማ” በማይረባ የደህንንት ማህበረሰብ ሾልኮ የወጣ ነው” ሲል ውድቅ አድርጎታል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል በማለት በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው፤ “በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች መካከል አንዱ የሆነውን ለማዋረድ” በሚዲያዎች የሚደረግ ሙከራ ሲሉ ከሰዋል።

አሜሪካ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋን የተሰኙ ሶስት የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን 61 ሜትር ወደ መሬት ዘልቆ መግባት በሚችሉ “በንከር በስተር” በተሰኙ ቦምቦች ጥቃት ፈጽማለች። ነገር ግን የፔንታጎን የደህንነት ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች በበኩላቸው የኢራን ማብላያዎች በአብዛኛው እንዳልተነኩ እና የጥቃቱ ተጽዕኖ ከመሬት በላይ ባለው ብቻ የተወሰነ ነው ይላሉ።

የሁለቱ ኒውክሌር ይዞታዎች መግቢያዎች ተዘግተው እንደነበር የጠቀሰው ግምገማው፤ አንዳንድ መሰረተ ልማቶች ቢወድሙም ወይም ቢጎዱም፤ ነገር ግን ከመሬት ስር ያሉት አብዛኛዎቹ ይዞታዎች ከፍንዳታው ቃጠሎ አምልጠዋል ብሏል። እኚህ ማንነታቸው ያልተገለጹ ምንጮች ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት ጥቃቱ ኢራንን በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል መገመቱን ገልጸዋል።

ኢራን ማንኛውም የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንደገና ለመጀመር ቁፋሮ እንዲሁም አንዳንድ ጥገናዎች ምን ያህል ይወስዳሉ በሚለው ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚችልም ነው ምንጮቹ ያስረዱት። ኢራን ከጥቃቱ በፊት የተወሰነውን በበለጸገው የዩራኒየም ክምችቷን ወደ ሌሎች ስፍራዎች አዛውራም እንደነበር የደህንነት ግምገማው ማየቱን እኚሁ ምንጮች አረጋግጠዋል።

የኢራን ከመሬት በታች የተገነቡ የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን መድረስ የሚችለው የአሜሪካው 14 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ‘በንከር በስተር’ እንደሆነ ይታመናል። ኢራን ሁሉም የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስታሳውቅ ቆይታለች። ጥቃቱን ተከትሎ በነበሩት ሰዓታት የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን በይዞታዎቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም ጊዜ ይወስዳል የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር። ሆኖም አሜሪካ ጥቃት ያደረሰችባቸው ሶስቱም ይዞታዎች “ከባድ ጉዳት እና ውድመት” ደርሶባቸዋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የሳተላይት ምስሎች ዋነኛው በሚባለው የፎርዶ ኒውክሌር ማብላያ ሁለት መግቢያዎች ዙሪያ ስድስት አዳዲስ ጉድጓዶች እንዲሁም ግራጫ ብናኝ እና ፍርስራሾችን አሳይተዋል። ሆኖም ከመሬት በታች ከ80 እስከ 90 ሜትር ጥልቀት ላይ በሚገኘው በዚህ የኒውክሌር ማብላያ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እነዚህ የሳተላይት ምስሎች አያሳዩም።

የኢራን የመንግሥታዊ ሚዲያ ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሃሰን አብደኒ በበኩላቸው አሜሪካ ጥቃት ያደረሰችባቸው ሶስቱ የኒውክሌር ይዞታዎች፣ ከጥቃቱ ቀድሞ ክምችታቸው እንዲዛወር መደረጉን ተናግረዋል።”ቁሳቁሶቹ ቀድሞውኑ ተወስደው ስለነበር ኢራን ትልቅ ጉዳት አልገጠማትም” ብለዋል።

የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለስልጣናት ተልዕኮው የተሳካ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ሲያደንቁ ተደምጠዋል። የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ጥቃት ላይ የአሜሪካ መከላከያ (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ ሾልኮ መውጣቱን የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ “የአገር ክህደት” ሲሉ ጠርተውታል።

ፔንታጎን የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን አላወደመም የሚለው ግምገማው በሚዲያዎች ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ነው፤ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ ውግዘታቸውን ያሰሙት።“በጣም አሳፋሪ ነው፤ የአገር ክህደት ነው። ምርመራ ተካሂዶ ጥፋተኛው አካል ተጠያቂ ሊደረግ ይገባል” ሲሉ ለፎክስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አገራቸው በሶስቱ የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃቶች ግምገማ ሪፖርቶች ማንበባቸውን ገልጸው “ሙሉ በሙሉ ስለመውደማቸው ምንም ጥርጥር” የለውም ብለዋል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛቸው ከፎክስ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በመቀነጫጨብ በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

“በፎርዶው [የኒውክሌር ማብላያ] ላይ 12 በንከር በስተር ቦምቦችን ጥለናል። የይዞታውን ጣሪያ ጥሶ እንዳለፈ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንደወደመ ምንም ጥርጥር የለውም። እናም ግባችንን እንዳላሳካን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እርባና ቢስ ናቸው” ሲሉ አጣጥለዋል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You