የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ነገ “የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ” የልደት /ገና/ በዓልን በደማቅ ስነስርአት ያከብራሉ። መላ የእምነቱ ተከታዮችን እንኳን ለዚህ ታላቅ በአል በሰላም አደረሳችሁ እንላለን!
እንደሚታወቀው፤ በሀገራችን እንደ ገና/ “የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ” የልደት በዓል/ ያሉ መንፈሳዊ በዓላትን በደማቅ ስነስርአት ለማክበር በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዝግጅት ይደረጋል። የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በመንፈሳዊ እና ባህላዊ መንገድ ነው የሚያከብሩት።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዓል ለብቻ አይከበርም፤ መተሳሰብን ይጠይቃል። በርካታ ዜጎች ከሀገር ውስጥም ከውጭ ሀገሮችም በዓሉን ከቤተሰብ ጋር ለማክበር ብለው ብዙ ርቀት ተጉዘው ከቤተሰብ ጋር ይገናኛሉ፤ ሌሎች ደግሞ ኑሮ ማለት እግር የቆመበት ነው ብለው ባሉበት ቦታ ተሰባስበው፣ በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
የበዓል ትርጉሙ ሰፊ ነው። ከኢትዮጵያዊ ባህል በእጅጉ ርቆ የኖረ ካልሆነ በቀር በዓል ሲባል ትርጉሙ ሰፊ መሆኑን የማይረዳ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። በዓል ለብቻ አያምርም፤ ተካፍሎ መብላት መጠጣትን፣ የተገኘውን አብሮ መቋደስን ይፈልጋል፤ አብሮ መብላትና መጠጣት የኢትዮጵያውያን መለያ ነው። ስላለ ብቻ ሳይሆን እጅ አጥሮም መተጋገዙ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የቆየ ልምድ ነው። ለዚህም ነው በበዓላት ወቅት የኢትዮጵያውያን እጆች ለተቸገሩ ሲዘረጉ የኖሩት፤ አሁንም እየተዘረጉ ያሉትም።
የበዓል ሌላው ትሩፋት የገበያው ድባብ ነው፤ በግ ተራው፣ ዶሮ ተራው፣ በሬ ተራው፣ እህል አትክልትና ፍራፍሬ ተራዎቹ፣ የአልባሳት፣ የስጦታ እቃ መሸጫዎቹ ሞቅ ደመቅ ብለው የብዙዎችን ቀልብ ይገዛሉ። ይህን ግርግርና የገበያው ጠረን የሚናፍቁ ብዙዎች ናቸው።
ነገ ለሚከበረው የገና በዓል የሚደረገው ዝግጅት ተጧጡፏል። በጉልቱ በዘመናዊው ገበያ ገዥዎችን ለመሳብ የሚደረጉ ዝግጅቶች በእርግጥም ሳቢዎች ናቸው፤ ለእዚህ ገበያ የሚያስፈልጉ ምርቶች ከገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎችም በስፋት ገብተዋል፤ እየገቡም ነው። ኅብረተሰቡ በኑሮ ውድነት ውስጥ ሆኖም እንኳን አደረሰን እያለ በዓሉን ለማክበር አቅሙ የሚፈቅደውን ለመሸመት ገበያ እየወጣ ነው።
መንግስትም የኑሮ ውድነቱ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ነው። ባለፉት የበዓል ወቅቶች ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በዚህ የገና በዓልም ዶሮንና በሬን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችንም ሆነ እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ያሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች በስፋት ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የተለያዩ የመንግስት አካላትና የኅብረት ስራ ማኅበራት እያረጋገጡ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ብቻቸውን ትርጉም ላይኖራቸው ይችላል። ያለፉት ጥቂት ዓመታት ያስገዘቡንም ይህንኑ ነው። የሁሉም ጉዳይ ማሰሪያው አንድ ነገር ነው፤ ሰላም። ያለ ሰላም አይመረትም፤ መብላት መጠጣትም ቢሆን በሰላም ሲሆን ነው የሚጥመው። ግብርናውም፣ ንግዱም ጉዞውም፣ ትምህርቱም ሰርጉም ተዝካሩም በሰላም ነው የወጉን ያህል የሚሆነው። ሰርጉ በሰላም ያምራል፤ ይደምቃል፤ እዬዬም ሲዳላ ነው እንደሚባለው ችግርን ለመቋቋምም ቢሆን ሰላም አጥብቆ ይፈለጋል።
ሰላም ከሌለ የቀብር ወግ ይቀራል፤ ያለቅሱበት ይጠፋል። ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለረጅም ዘመናት ኖሯል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰላም እጦት ሳቢያ አያሌ ዜጎች ከበዓል ተፋትተው ነበር፤ በዓል እንደነገሩ የሆነባቸውም ብዙ ነበሩ። የሰላም እጦትን ተከትሎ በተፈጠሩ ጫናዎች ሳቢያ የግብርና ምርቶች በአግባቡ ወደ ከተሞች እንዳይገቡ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ከውጭ ሀገር እንዳይገቡ፣ ወደ ገጠርም በሚፈለገው ልክ እንዳይጓጓዙ የሆነባቸው አካባቢዎች ጥቂት አልነበሩም።
ይህ ሁሉ ሰላም የበዓላት ትልቁ ግብአት መሆኑን ያመለክታል። ሰላም ከሌለ ነጋዴዎች መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ዶሮውም እህሉም ገበያ ሊወጣ አይችልም፤ ሰላም ከሌለ ያረዱትን አጣጥሞ መብላትም አይቻልም፤ ሰላም ከሌለ የበዓል ወግ የሆነው ተሰባስቦ ማክበር አይታሰብም፤ ቤቱን በዓል በዓል ላድርግህ ቢሉትም በጄ አይልም።
በአንድ አካባቢ ሰላም ስላለ ብቻ በዚያ አካባቢ በዓሉን ጣእም ያለው ማድረግም አይቻልም፤ በዓል ከጥንት ጀምሮ ያለውን ቃና ይዞ ሊከበር የሚችለው በሁሉም አካባቢ ሰላምና ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። በአንዱ አካባቢ ሰላም ሆኖ በሌላው አካባቢ ሰላም ከታጣም የበዓል ድባብ ይጠይማል፤ይረበሻል።ነግ በእኔ እየታሰበ መቆዘምም ይከተላል፤ በሀገራችንም የሆነው ይሄው ነው።
ሰላም በሌለበት ሁኔታ የሚከበር በዓል ከመታሰብ የዘለለ ድምቀትም አይኖረውም፤ እንዳይቀር ለወጉ ያህል ብቻ የሚከበር ከመሆኑ ውጪ የተለመደውን የበዓል ድባብ የተላበሰ ሊሆን አይቻልም። ስለዚህ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን አይነገርም፤ አሳምረው ኖረውታልና በሚገባ ያውቁታል።
መንግስትና ሕወሓት ያካሄዱትን የሰላም ውይይትና እሱን ተከትሎ የደረሱባቸውን ስምምነቶች በመተግበር በኩል በተወሰዱ ጠንካራ እርምጃዎች የታዩ ለውጦችም የሰላምን ዋጋ በሚገባ አመላክተዋል። በእስከ አሁኑ እርምጃዎች የተገኙ ለውጦች የሰላምን ዋጋ በሚገባ ያስገነዝባሉ።
በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሰው እየተገነቡና አገልግሎቶችም እየተመለሱ ያሉበት ፣ በጦርነቱ ወደ ተጎዱ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰብአዊ አቅርቦቶች በስፋት እየደረሱ ያለበት፣ በጦርነቱ የተነሳ ተለያይተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በስልክ ማውራት፣ በአካል መተያየት የጀመሩበት ሁኔታ የሰላምን ፋይዳ በሚገባ አመላክተዋል።
በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎቶች ከተመለሱ፣ በጦርነት የተራራቁ ቤተሰቦች ከተገናኙ፣ በሕዝቦች መካከል መልካም አመለካከት ከሰረጸ፣ የነገው በዓልም ሆነ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት በዚያው ልክ ደማቅ ይሆናሉ። እየተመለሰ ያለው ሰላም የገና በዓልና የቀደመ ደማቅ ድባብ እንደሚመልስ አንድ ማስረጃ ይሆናል።
ሰላም የሁሉም ነገር ማሰሪያ መሆኑን መንግስትና ሕወሓት የደረሱበት የሰላም ስምምነትና እሱን ተከትሎ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና የተገኙ ውጤቶች በሚገባ አመላክተዋል።
ይህን ሰላም ማጽናት በሁሉም መስክ የተያዙ እቅዶችን ለማሳካትና የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው። ለእዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን ጠንክረው መስራትና ሰላሙን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም