ታዳጊ ከድር ቢላል ተወልዶ ያደገውና አሁንም ከሴት አያቱ ጋር የሚኖረው በሐረር ከተማ ነው።የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ መኖሩን ካወቀ አመታት ተቆጥረዋል። ቫይረሱ በደሙ ውስጥ መኖሩን የሰማው ልጆች ትምህርት በሹክሹክታ ሲያወሩ ነው ።በሁኔታው ሆድ ብሶት አያቱን መጥቶ ሲጠይቃቸው ቫይረሱ እንዳለበት አረዱት። እሳቸው ከሆስፒታል እያመጡለት በየቀኑ እንዲውጥ የሚያደርጉት መድሃኒትም የኤች አይቪ እንደሆነ ነገሩት።እሳቸው እያሳደጉት ያሉትም እናቱና አባቱ በበሽታው በመሞታቸው እንደሆነም አስረዱት።ነገሩ ግር አለው፤ መቀበል አልቻለም።
ታዳጊ ከድር ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል‹‹ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤት ሄዶ መማር አስጠላኝ።ከወር በላይም ከትምህርት ቤት ቀረሁ።መድሃኒቱንም አልውጥም፤ ምግብ አልበላም ብዬ አያቴን አስቸገርኳት።ኤች አይቪ ገዳይ መሆኑን በትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ስለሰማሁ ልሞት ነው ብዬም ስለፈራሁ ሳላቋርጥ አለቅስ ነበር››ይላል።
አያቱ በግድ ወደ ሆስፒታል ወስደውት የምትከታተለው ሐኪም ከመከረችውና እንደማይሞት ከነገረችው በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሶ ያቋረጠውን ትምህርት ቀጠለ።ታዳጊው እንደነገረን ግን ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ስለኤች አይቪ ሲወራ እሱን ይመስለው ስለነበር ይሸማቀቃል።በተለይ ከሰፈር ሰምተው ቫይረሱ በደሙ ውስጥ መኖሩን በሹክሹክታ ሲነጋገሩ የሰማቸው ልጆች ክፍሉ ውስጥ ስለነበሩ ዞር ብለው ሲያዩትና የሁሉም ተማሪ ዓይን ወደ እርሱ ሲወረወር ከክፍል በመውጣት እያለቀሰና እየሮጠ ወደ ቤቱ ሄዶም ያውቃል።
የህክምናውን ሁኔታ ለምትከታተለው ሃኪም ይሄን ከነገራት በኋላ አያቱን እንዲያመጣችው አዘዘችው።ከዛም ለብቻቸው ካወራቻቸው በኋላ ደብዳቤ ሰጠቻቸውና አብረውት ወደ ትምህርት ቤቱ ሄደው ለዳይሬክተሩ ሰጡት። ዳይሬክተሩ ክፍል ቀየረው።በቀጣይ ዓመት ሌላ ትምህርት ቤት እንደሚገባም ነገረው።በቀጣይ ዓመትም ሌላ በአቅራቢያው ያለ ትምህርት ቤት ገባ።ጎበዝ ተማሪ ሆኖም አንደኛ ለመውጣት መድሃኒቱን መውሰድ ቀጠለ፤አያቱ በእሱ ስም የሚያመጡትን መድሃኒት መውሰድ ቀጠለ፣ ተመጣጣኝ ምግብም በብዛት መመገብ ጀመረ።ቢሆንም እንደ ዱሮው ስለ ኤች አይቪ በትምህርት ቤት ውስጥ ሲወራ ባይሸማቀቅም ኤች አይቪ በደሙ ውስጥ መኖሩን ማንም እንዲያውቅበት አይፈልግም።
ታዳጊ ቤቢ ዳኔኤል በተመሳሳይ የሀረር ከተማ ነዋሪ ናት።ከህፃንነቷ ጀምሮ መድሃኒት እየዋጠች ነው ያደገችው።ታዳጊዋ እንደነገረችን ከፍ እያለች ስትመጣ የምትውጠው መድሃት የምን እንደሆነ እናቷን ስትጠይቃት የቲቪ መሆኑን ትነግራት ነበር።ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን ያወቀችው የምትውጠው መድሃኒትና የኤች አይቪ መድሃኒት ተመሳሳይ መሆኑን ትምህርት ቤት ውስጥ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ተማሪዎች ከሚውጡት ጋር አስተያይታ ነው።
‹‹ለልጆቹ እኔም እንደዚህ ዓይነት መድሃኒት እውጣለሁ ስላቸው የኤች አይቪ እንደሆነ ነገሩኝ።ይሄን ለእናቴ ስነግራት ትክክል መሆኑን ነገረችኝ።››ቢሆንም እስከ 15 ዓመቷ ድረስ ቆይታ በዚህ አጋጣሚ ድንገተኛ መርዶ መስማቷ ደስተኛ አላደረጋትም።ምክንያቷን ስትናገር ‹‹ከልጆች ጋር ተደበድቤ በመሞንጨር ደምቼ አውቃለሁ።ስወድቅም ጉልበቴ ደምቶ የሚያውቅበት ጊዜ አለ።ከአፋችን ውስጥ ምግብ እያወጣን እንጎራረስ ነበር።ኤች አይቪ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው የሚተላለፈው ደግሞ በደምና በምራቅ አማካኝነት ነው።በተለይ ቫይረሱ በምራቅና በደም ውስጥ እንዳለም አውቃለሁ።በዚህ አጋጣሚ ለጓደኞቼ ቫይረሱን አስተላልፌ ሊሆን ይችላል›› ትላለች።
ቤቢ ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸውና የሚያውጧቸው መድሃኒትም የኤች አይቪ እንደሆነ ሊነግሯቸው ይገባል ባይ ነች።ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ግንዛቤ ካላቸው ከራሳቸው አልፈው ሌሎቹን ከቫይረሱ ይጠብቃሉ የሚል ምክር ታስተላልፋለች።
ሌላኛዋ ወጣት አክሱማዊት መዝሙር ትባላለች። 23 ዓመቷ ሲሆን የምትኖረው ሐረር ከተማ ውስጥ ከአባቷ ጋር ነው።ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ቢኖርም ከመማር ስላላገዳት በኪሊኒካል ነርሲንግ ተመርቃለች። ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን ያወቀችው የ14 ዓመት ታዳጊ ሆና ነው። ፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት መውሰድም ከጀመረች እንዲሁ 14 ዓመቷ ነው።
የዛሬ ሁለት ዓመት የተመሰረተው የህፃናትና ወጣቶች ማህበር መስራችና ሊቀመንበር ነበረች።ማህበሩ 98 ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ህፃናትን አቅፎ በመያዝ ነው የተመሰረተው።አባላቱ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው በመሆናቸው ምክንያት በሕይወት ፋናና በጀብላ ህክምና ተቋም የምክር አገልግሎትና የሕክምና ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው።ለአባላቱ የሐረር ጤና ቢሮ የደብተር፤የትራንስፖርትና ቡና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።ግን መድሃኒቱ ምግብ ስለሚፈልግ የምግብ ድጋፍ የግድ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን አሁን የምግብ ድጋፍ ስለሌለ ህፃናትና ታዳጊዎች መድሃኒቱን መዋጥ ይከብዳቸዋል።በዚህም ምክንያት በሽታው የሚጠናባቸው ብዙ እንደሆኑ አክሱማዊት ትናገራለች።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ግን ለህጻናቱ የሚወስዱት ምድሃኒት ምን እንደሆነ ብዙ ጊዜ አይነገራቸውም። የሚውጡት መድሃኒት አንድ ጊዜ የጉንፋን ሌላ ጊዜ ደግሞ የቲቪ ነው እያሉ በመዋሸት እንዲወስዱ የሚያደርጉ ልጆች ብዙ ናቸው። ይህ ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው መኖሩ ዘግይቶ ሲነገራቸው ተስፋ በመቁረጥ ትምህርት አንማርም ምግብ አንበላም አልፎ ተርፎ ወላጆቻቸው ሁለቱም ወይም አንዱ ካሉ ለምን ወለዳችሁኝ የሚል ጥያቄ እንዲነሱ ምክንያት ይሆናል ።
ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ሌላ ሰው የሚያውቅባቸው የሚመስላቸውንና ራሳቸውን የሚያገሉም አሉ።መድሃኒቱን ቅዳሜ ቅዳሜ ሰው ሳያያቸው ልጆቹ ብቻቸውን ሆስፒታል ሄደው እንዲወስዱ ነው የሚደረገው።ሊደርስባቸው የሚችል አድሎና መገለልን በመፍራት ሚስጥራቸውም የተጠበቀ ቢሆንም እስከ መጨረሻው ግን ከሰው ደብቆ መኖር ግን አዳጋች ነው። ።በተለይ በየትምህርት ቤቶቹ ራሳችሁን ከኤች አይቪ ጠብቁ ተብሎ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ሁሉም ሰው የሚጠላቸው የሚመስላቸውና ራሳቸውን የሚያገሉ በርካታ ናቸው።አብዛኞቹ ልጆች ሁለቱንም ወላጆቻቸውን፤ አንዱን ወላጃቸውን በበሽታው ያጡና ከአንዱ ወላጃቸው ፤ከአያቶቻቸው ወይም ከዘመድ ጋር ተጠልለው የሚኖሩ ናቸው ብላናለች ወጣት አክሱማዊት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27 /2015