ሰሞኑን አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ባረፈበት ክልል ውስጥ አንድ ሁነት ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ እሱም ”ንባብ ለምክንያታዊነት” በሚል መሪ ቃል የተከናወነው የንባብ ሳምንት መርሀ-ግብር ነው። በቃ፣ ይኸው ነው። ይኸው ይሁን እንጂ ሁለት ጥልቅ እሳቤዎች (”ንባብ” እና ”ምክንያታዊነት”)ን ይዟልና ለዛሬ ልንነጋገርበት ወደድን።
ማንበብ ለማንም ብርቅ አይደለም፤ በየትኛውም ዘመን ብርቅ ሆኖ አያውቅም። በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የመብላትና መጠጣትን ያህል የእለት ተ’ለት ተግባር ነበር (ውይ … ውይ …፣ ”ነበር” ማለት እንዴት ያስጠላል?)። ይህንን ስንል ደግሞ (ስለ ምክንያታዊነት ነውና የምናወራው) ያለምክንያት አይደለም።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ስንመረምር የምንደርስበት እውነት ቢኖር፣ ”የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ ማን ነው?” ተብላ የተጠየቀችው የ11ኛ ክፍል ተማረ ”ኃይሌ ገብረሥላሴ” ብላ እንደ መለሰችው ሳይሆን፣ አንባቢ ትውልድ የነበረበት ዘመን የነበረ መሆኑን ማሳየት ነው። ለዚህ ደግሞ መረጃና ማስረጃው ኢትዮጵያ የፈላስፎች ምድር የነበረች መሆኗ ነው። (ኤጭ፣ ይሄ ”ነበር” አሁንም በ”ነበረች” ተሸፍኖ መጣ።)
The African Enlightenment (Dag Herbjørnsrud፣ ዲሴምበር 2017) በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያስረዳው ከአለማችን ስመ ጥር ፈላስፎች (ጆን ሎክ፣ ሁም፣ እና ካንት) ሁሉ በፊት እነሱ ደረሱበት የተባሉትን አዳዲስ ሀሳቦች ከክፍለ ዘመናት በፊት ኢትዮጵያዊያን በዋሻ ውስጥ ተግብረውት የተገኘ መሆኑን ለማመን በሚያስቸግር አገላለፅ The highest ideals of Locke, Hume and Kant were first proposed more than a century earlier by an Ethiopian in a cave. በማለት አስፍረውት መገኘቱ ከመረጃም በላይ፣ ከማስረጃ ከፍ ያለ ነው። ይህ ደግሞ በበኩሉ የኢትዮጵያን የአንድ ዘመን ከፍታ ያሳያልና ጥናቱን ስናደንቅ በኩራት ነው።
እኝሁ የGlobal Knowledge: Renaissance for a New Enlightenment (2016) ደራሲ በቀዳሚ ማስረጃነት ፈላስፋው ዘርዓያዕቆንብን የሚጠቅሱ ሲሆን በሰለጠነው አለም ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ዲሞክራሲና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቅ ማለት መነሻው (ምክንያቱ ማለት ነው) ይኸው የኢትዮጵያ ፍልስፍና መሆኑን እየጠቀሱና እያጣቀሱ ይገልፃሉ። ታዲያስ ውድ አንባቢ፣ በኢትዮጵያ አንባቢ ትውልድ አልነበረም ይላሉ?
ዛሬ ዛሬ በአገራችን የሚታየው ያው ስብሀት ገብረእግዚአብሄር በአንድ ወቅት ብሎት እንደነበረው የተገላቢጦሽ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው። ”ምክንያት?” ሲባሉ ”ደሞ ለምክንያት …” ይሉና ምክንያታቸውን ይደረድሩታል።
እንዲህም እያሉ፡-
ዛሬ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ቁጥር፣ በስንት እጥፍ እንደሆነ እንኳን ለማስላት በሚያስቸግር ሁኔታ አድጓል። የምሩቃኖቻቸውን ቁጥር ከጨመርን ከሰማይ ኮኮብ ከምድር አሸዋ አይተናነሱም ነው የሚባለው። የዶክተርና ፕሮፌሰሮቹ እንኳን ብቻውን ቢወሰድ ከድሮ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከሚያስመርቋቸው (በስንት እጥፍ እንደሆነ ተረሳ እንጂ) ይበልጣል ይላሉ። ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ አንድ የሚያዝናና ነገር ቢኖር የጥናትና ምርምር ስራዎች ከድሮው ጋር ሲወዳደሩ የድሮዎቹ ከዘንድሮዎቹ (በስንትና ስንት እጥፍ እንደ ሆነ ተረሳ እንጂ) የሚበልጡ መሆኑ ነው። የሚያዝናናውና የሚያሳዝነውም ይኸው ነው። ከሁሉም ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ ”እኔ መጽሐፍ አላነብም።” የሚል ባለ ዲግሪ በአደባባይ ሲንጎማለል ማየቱና ቀረርቶውን መስማቱ ነውና ድሮና ዘንድሮን እዚህ ማወዳደር አንድ ራሱን የቻለ ልግጫ በመሆኑ በምድርም በሰማይም ያስጠይቃል የሚሉ መኖራቸው ደግሞ ሌላውና ኮስተር ያለው አስተያየት ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፣ እነዚህ ”ተቺዎች” (ከፈለግን ”የድሮ ናፋቂዎች”ም ልንላቸው እንችላለን) የማይሉት የለም፤ አንስተው የማያፈርጡት ጉድ አይገኝም፤ ሲያስፈልጋቸው ”የፌስቡክ መንጋ …” በማለት ይጀምሩና ”ሰውዬ አታናግረኝ …” በማለት ፈንጠር ፈንጠር እያሉ፣ እያናገራቸው ያለውን ሰው ባለበት ገትረው ፈትለክ ይላሉ።
አንድ ”’ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ በሚለው ይስማማሉ?” በማለት ጥያቄ ያቀረብኩላቸው ሰውዬ የተናገሩትን እዚህ ማንሳት ቢያስፈራም ስለማያስበረግግ እንጥቀሰውና እንለፍ።
ጋሼ ”’ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ በሚለው ይስማማሉ?”
ኤዲያ፣ ሙሉ አደረገ ጎደሎ ምን ዋጋ አለው። ይህ እሚባለው እኮ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያነብ ሲኖር ነው፤ አይደለም እንዴ? (መልሱን ለአንባቢ ትተን እንለፍ።)
በዚህ በያዝነው በ21ኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ”አንባቢን የበላ ጅብ አልጮህ ብሏል” የሚለውን አገላለፅ መስማት አዲስ ነገር አይደለም። እንግዳ ጉዳይም ሆኖ አያውቅም። በቃ፣ አንባቢን የበላ ጅብ አለ። ግን ”እኔ ነኝ …” ብሎ ሲጮህ አይሰማም። ብቻ ተሰማም አልተሰማም አንባቢ እንደ ሆነ ተበልቷል (ሲያስፈልግ በቴክኖሎጂ፣ አልያም በሱስ … ማለት ይቻላል፤ ብቻ አንባቢ ተበልቷል።)። ታዲያ ባይበላ ኖሮ የት ገባ? ምክንያታዊነትስ ከነ ልጅ ልጆቹ እምጥ ይግባ ስምጥ አይታወቅም ነበር? ይታወቅ ነበር።
የሰይጣን ጆሮ አይስማውና፣ አንዳንዶች እንደሚሉት በክፍል ውስጥ የመማር-ማስተማር ሂደት ወቅት ማጣቀሻ መጻሕፍትን የሚጠቁሙት ከመምህሩ ይልቅ አንዳንድ ተማሪዎች ናቸው። የበለጠ አንዳንዶቹ እንደሚሉት ደግሞ መምህሩ ከተማሪው በንባብ የሚቀድመው በአንድ አንቀፅ ብቻ ነው። ለዚህ ነው የትምህርቱ ጥራት ሰማየ ሰማያት የደረሰው ….. ነው የሚሉት። ጆሮ አይሰማው የለምና … ነገሩ ብዙ ነው።
ሌላውና በሹክሹክታ ሲወጋ (ወግ) የሚሰማው በአገራችን፣ በተለይም በዚሁ ባለፈው ሳምንት ”ንባብ ለምክንያታዊነት።” በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት በተከበረባት መዲናችን፣ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሳይቀር (እንደውም ይብሳል ነው የሚባለው) ሳያነቡ የምጽፉ ቁጥራቸው እየተበራከተ የመምጣቱና ከየእውቀት ምንጭነት ይልቅ አደንቋሪነታቸው ሚዛን እየደፋ የመምጣቱ ጉዳይ ነው።
ነፍሱን ይማረውና ደምሴ ፅጌ በአንድ ወቅት እንደዚህ አይነቶቹ (”ከእውቀት ነፃ”ዎቹ) እየበዙ መምጣታቸውና ከስራዎቻቸው ምንም አይነት ረብ በማጣቱ ምክንያት ”… ምን እነዚህ፣ ወይ አያነቡ፤ ወይ አይጠይቁ …” በማለት ምሬቱን መግለፁን አንብበናል። በአንባቢነቱና ደራሲነቱ የተከበረ ስፍራን የያዘው ስብሀትም፣ እያባበለም ቢሆን፣ ወጣቱን (”እሳቱ ትውልድ …፣ ”ነቄው ትውልድ …” በማለት) ”አንብቡ” ሲል መሸንቆጡ አልቀረም። ”ካላነበብክ ታዲያ ምን ልትሆን ነው …?”
በዓሉ ግርማም አፍቃሬ አንባቢ ሲሆን፣ ”ከአድር ባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ይሻላል።” የምትለው ዘመን ተሻጋሪ አባባሉም እየተነጋገርንበት ያለውን፣ ምክንያታዊነትን የሚያፀና ነው እዚህ ሊጠቀስ የግድ ይሆናል።
በተለይ ሳት ብሏቸው ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ጎራ ያሉ (የድሮ ናፋቂ) ጎምቱዎች በምሬት ሲናገሩ እንደሚሰማው ከሆነ የድሮዋ ኢትዮጵያ የለችም። ድሮ ድሮ መሳደብ ነውር ነበር ነው የሚሉት። ብልግና ቃላትን አይደለም መጠቀም፣ ማሰብ እንኳን የሚታሰብ አይደለም። ባጭሩ፣ ወዴት እንደ ሆነ አይታወቅም እንጂ፣ ምክንያታዊነት ከኢትዮጵያ ውስጥ ጓዙን ጠቅልሎ ከሄደ፤ በመንጋነት ከተተካ ሰንብቷል። አንባቢነት አይደለም በአግባቡ ማዳመጥና መደማመጥ እንኳን ተረት እየሆነ ነው። መጯጯህና አለመግባባት ቦታውን ከያዙት ጊዜው ዛሬ ሳይሆን ቆየ።
ማንበብ ስንትና ስንት ሳይንቲስቶችን እንዳላፈራ፣ ስንትና ስንት ከአለም ቁጥር 1 ባለ ሀብቶችን እንዳላበረከተ፣ ስንትና ስንት ወታደራዊ ጠበብትን ለአለማችን እንዳላስገኘ፤ ስንትና ስንት ፈላስፎችን ”እነሆ በረከት …” እንዳላለ ሁሉ ዛሬ አይንህ ላፈር ተብሎ ”እኔ መጻሕፍት አላነብም” እሚባልበት ዘመናዊ ዘመንና ትውልድ ላይ ተደረሰና ታረፈው።
ይህ ጸሐፊ ”መጻሕፍት ትፈልጋለህ? አራት ሺህ መጻሕፍት አሉኝ። ልሰጥህ እችላለሁ።” ያለው ሰው አጋጥሞት የነበረ ሲሆን፣ ”በምን በምን ጉዳይ ላይ የተጻፉ ናቸው?” ሲል ላቀረበው ጥያቄ ”አይ፣ አላነበብኳቸውም። ፒዲኤፍ ናቸው።” የሚል ምላሽን እንዳገኘ መቸም የሚረሳው ጉዳይ አይደለም። (እዚህ ላይ ይሄም አለ ለማለት ነው እንጂ በፒዲኤፍ ያሉ መጻሕፍትን ለማጣጣል አይደለም።)
”ከእውቀት ነፃ” እንደሚባለው ሁሉ፣”ከወረቀት ነፃ …” የሚል ወፍ ዘራሽ አነጋገር በአገራችን፣ በተለይም በከተሞች፤ በተለይ በተለይ በተቋማት ሳይቀር ከች ብሏል። (ወረቀት እየሸጡ፣ መተዳደሪያቸውም እሱው በሆኑት ሳይቀር) መቀንቀኑና መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ንባብ ጠል ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ መሆናቸው ነው። ይህ ከየት የተገኘ ”ቁም ነገር” እንደ ሆነ ባይታወቅም (ለምሳሌ አሜሪካን አገር በአመት ከ500ሺህ በላይ መጻሕፍት (ጋዜጦችና መጽሔቶችን፣ ማስተማሪያና አጋዥ ስራዎችን ሳይጨምር) ይታተማሉ)፣ የአቀንቃኞቹ ፍላጎት በቴክኖሎጂ አመጣሽ መሳሪያዎች መጠቀምን (መላላክን) መስበክ ይመስላል። ያ ከሆነ ቋንቋው ይህ አይደለምና፤ አገላለፁ የተወላገደ ነውና በአስቸኳይ መታረም አለበት ስንል አሁንም በትህትና ነው።
በአመታዊው ”የንባብ ሳምንት” መርሀ-ግብር መሪ ቃልን መሰረት ያደረገው ርእስና ርእሰ ጉዳያችን እንደሚነግረን ከሆነ ንባብና ምክንያታዊነት የሚነጣጠሉ አይደሉም፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ማለት ነው። በመሆኑም፣ ”ማንበብ” ከሌለ ”ምክንያታዊነት” የለም ማለት ነው። ለምክንያታዊነት ደግሞ ማንበብ የግድ ነው ማለት ነው – እንደምናውቀውም፣ እንደ መሪ ቃሉም።
ከመሪ ቃሉ መረዳት እንደሚቻለው ያለ ንባብ ምክንያታዊነት የለም። ምክንያታዊነት ከሌለ ደግሞ፣ ከላይ የጠቀስናቸው ”የድሮ ናፋቂ” ጎምቱዎች እንደ’ሚሉት ”መንጋነት …” ይሰፍናል ማለት ነው። አሁንም፣ እንዚሁ ሰዎች ሲናገሩ እንደሚደመጠው ደግሞ፣ ”መንጋነት … ሰፈነ” ማለት ደግሞ ሰብአዊነት ነጥፎ እንስሳዊነት በስፍራው ተተካ ማለት ነውና ጉዳዩ ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራልም።
እዚህ ላይ አንድ አቢይ ጉዳይ እናንሳ። ልብ በሉ፣ የንባብ ሳምንቱ መርሀ-ግብር የተካሄደው ከአዲሱና ዘመናዊው አብርኈት ቤተ-መጻሕፍት ጋር በተያያ ስፍራ (አራት ኪሎ) ላይ ነው። ”አብርኈት” ማለት ደግሞ በአቻ ስያሜው Enlightenment ነው። Enlightenment ማለት ደግሞ በርካታ የአለም አገራት ከነበሩበት አዘቅት የወጡበት የሽግግር ዘመን እና ራሱን የቻለ የፍልስፍና አካል ሲሆን፣ ማእከላዊ ትርጉሙም (ሰዎች ምክንያታዊነታቸውን በይፋ የሚያሳውቁበት፣ ምክንያታዊ የሚሆኑበት፣ ሰዎች ሁለንታን ጠንቅቀው የሚያውቁበት፣ እና የአኗኗር ዘይቤያቸውን የሚያሻሽሉበት (The use and celebration of reason, the power by which humans understand the universe and improve their own condition.) ሁኔታ ማለት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል። ይህ በበኩሉ የሚያሳየን አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ማንበብ ከምክንያታዊነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአብርኈት ጋር ሁሉ የጠበቀ ግንኙነት፣ ትስስር … ያለው መሆኑን ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአብርሆት ላይ ጥርሳቸውን የነቀሉ ምሁራን፣ ከላይኛው በማስከተል ”የሰው ልጅ ምክንያታዊነት ዋና አላማ ማሳያ ተደርገው የሚወሰወዱት ደግሞ እውቀት፣ ነፃነት፣ እንዲሁም ደስታ” መሆናቸውን፣ ”The goals of rational humanity were considered to be knowledge, freedom, and happiness.” ማለታቸው ነው። ባለ ዲግሪዎቹ፣ እነ ”እኔ መጽሐፍ አላነብም”፣ እነ ”ንባንብ ለምኔ …” እንዳይሰሙን ብለን ነው እንጂ ብዙ ማለት በተቻለ ነበር።
ከእነ ባለ ዲግሪዎቹም ሆነ ”ከእውቀት ነፃ”ዎቹ፣ ከእነ ”እኔ መጽሐፍ አላነብም” … ባይ ጎምላሌዎቹ በተቃራኒ ያሉቱ ሲሉ እንደሚሰማው ከሆነ (ለምንድን ነው ግን ጋዜጠኞች ይህችን ”… ከሆነ …”ን በፍቅር የሚወዷት? ”… እንደ ተናገሩት ከሆነ”፣ ”… እንዳሉት ከሆነ…”፣ ”እንደሚሉት ከሆነ …”) ”የማያነብ ሰው እና ደም የሌለው ሰው አንድ ነው።” (አናብራራውም።)
ማንበብ ከእነ ተጣማሪው ”ማንበብና መጻፍ / ዋናው ቁም ነገር …” ተብሎ ተዘፍኖለታል። ”አንብቡ / እናንብብ …” ተብሎም ተዜሞለታል። አያሌ መጻሕፍት ስለ ንባብና ጥቅሙ ለህትመት ብርሀን በቅተዋል። የእምነት ተቋማት ያለ ንባብ ግንዛቤ እንደ ሌለ አስተምረዋል፤ እያስተማሩም ነው። ያለ ግንዛቤ ደግሞ እምነት ከንቱ ነው።
የማንበብንም ሆነ ምክንያታዊነትን የተመለከቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች እለት በእለት ሲበረከቱ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ምሁራን የሚያነብን ሲያወድሱ፤ ፀረ-ንባብ እንቅስቃሴን ሲያወግዙና እነ ”ንባብ ጠሌ”ን ሲነቅፉ እድሜያቸውን ፈጅተዋል።
በልቶ ለሚከሳ፣
ተመክሮ ለሚረሳ፤
ለዚህ ምክር፣
ለዚህም ምግብ ንሳ።
እንደ ተባለው ምክራቸውን የሰሙ ሲለወጡበት ተመክረው የረሱትም (አብነት አጎናፍር ”ሲመክሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ …” እንዳለው) ወደ ”… መንጋነት” (ከላይ የጠቀስናቸው ”የድሮ ናፋቂዎች” እንደሚሉት ማለታችን ነው) እያቀኑ ይገኛሉ። (በነገራችን ላይ፣ መንጋነት ከጎዳቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች አንዱ ፌስቡክ ሲሆን፣ ኤፍቢ ቀድሞ የነበሩት ምሁራን ታዳሚዎቹ ወደ ቲውተርና ቴሌግራም እንዲጎርፉ ያደረጋቸው ይሄው መንጋነት መሆኑን ልብ ይሏል።)
ድሮ በሚያነብ የሚቀናበት ዘመን ሲሆን፣ ዘንድሮ የማያነብ የሚሞገስበት ዘመን ነው። ዘንድሮ፣ ”ሳያዩ የሚያምኑ ….” በሚለው ተሸውደውም ይሁን ሌላ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ሳያነቡ የሚጽፉ በርካቶች የሆኑበት፤ ድሮ ሳያነቡ የማይጽፉ የሞሉበት ዘመን ነበር። ድሮ መጽሐፍ በእጅ መያዝ (ይዞ መታየት) የሚያስመሰግንበትና የምሁርነት፣ አንባቢነት ምልክት የነበረበት ዘመን ሲሆን፤ ዘንድሮ ማዳመጫን አንጠልጥሎ፣ መስሚያንም በእሱው ደፍኖ ክው ክው ማለት፤ ከራስ በራስ መጠፋፋት፣ ድምፃዊ ዘሪቱ ከበደ ”ቴክኖሎጂ በላይ በላይ / ሰው ከራሱ እንዳይተያይ …” እንዳለችው የሆነበት ዘመን ነው።
ምንም እንኳን ”ዘመን የራሱን ሰው (ትውልድ) ይፈጥራል” ቢባልም፣ የእነ ሎሬት ፀጋዬ፣ ሀዲስ አለማየሁ ዘመን እነሱን እንደ ፈጠረው ሁሉ፣ የአሁኑ ዘመንም እነ አዳም ረታን፣ ቴዲ አፍረሮን … እንደ ፈጠረ ለማሳየት እንጂ ”ጫማው ልክ” የሆነ ትውልድ በነበረበት አገር ”ጫማው ሰፋፊ …”፤ ”… ጎመን ቀራፊ” ትውልድ ይፈጠራል ማለት አይደለም። በመሆኑም፣ ፈላስፋ በነበረበት አገር የበለጠ ፈላስፋ፤ አንባቢ በነበራት አገር የተሻለ አንባቢ … ይፈጠራል እንጂ ሎሬቱ እንዳለው ሁሉ ነገር ”… ምድረ በዳ” ይሆናል ማለት ሊሆን አይገባውምና፣ ምክንያታዊነት የግድ ያስፈልጋልና፣ ምክንያታዊ መሆን ከሰብአዊ ባህርያት አንዱ ነውና እናንብብ፤ ሳያነቡ የሚጽፉ ከመባል ይሰውረን !!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27 /2015