ከታሪክ መረዳት እንደምንችለው ሀገራት አንድ ጊዜ እርስ በርስ ግጭት ካጋጠማቸው በኋላ ተጨማሪ እርስ በርስ ግጭቶችን የማስተናገድ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በሰላም ድርድር ያልተቋጩ የእርስ በእርስ ግጭቶችን እጅግ አሳሳቢ ከሚያደርጋቸው ምክንያች አንዱ ግጭቶቹ ከቆሙ በኋላ ዳግም የማገርሸት እድል መኖሩ ነው።
እ.አ.አ በ2010 በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የፓሲፊክ ጥናት የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት በርባራ ዋልተር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ስለ እርስ በርስ ግጭቶች ማገርሸት እና በድህረ ግጭት ዘላቂ ሰላም ስለማስፈን ያጠኑት ጥናት እንደሚያመላክተው፤ ከ1945 እስከ 2009 ድረስ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ካስተናገዱ 103 ሀገራት የእርስ በርስ ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ ማድረግ የቻሉት 44 ሀገራት ብቻ ናቸው።
የእርስ በርስ ግጭት ካስተናገዱት ሀገራት መካከል 59 ሀገራት ቢያንስ አንድ ጊዜ ዳግም የእርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግደዋል። ይህም ማለት በነዚህ ዓመታት ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትን ካስተናገዱ ሀገራት ውስጥ 57 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ዳግም ወደ እርስ በርስ ግጭት ገብተዋል ማለት ነው። ይህ አሃዝ እንደሚያሳየው ሀገራት አንድ ጊዜ የእርስ በርስ ግጭትን ካስተናገዱ በኋላ በቀላሉ ከእርስ በርስ ግጭቶች አዙሪት ለመውጣት እንደሚያዳግታቸው ነው።
በተለይም ከእ.አ.አ 2003 ወዲህ በዓለም ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ የእርስ በርስ ግጭቶች የቀደሙ የእርስ በርስ ጦርነቶች ቅጥያ ሆነው እናገኛቸዋለን። በ21ኛ ክፍለ ዘመን ከተቀሰቀሱ እርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ቀደም ባሉት ዓመታት የእርስ በርስ ግጭቶችን ባስተናገዱ ሀገራት ውስጥ የተፈጠሩ ሲሆኑ 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቀደም ባሉ ዓመታት እርስ በርስ ግጭቶችን ባላስተናገዱ ሀገራት ውስጥ የተከሰቱ ናቸው።
ከእርስ በርስ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ያለው ችግር አዳዲስ እርስ በርስ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የመከላከል ብቻ ሳይሆን ነባር ግጭቶች ዳግም በማያገረሽ መልኩ እልባት ያለመስጠት ችግር መሆኑን እላይ ከተጠቀሱት አሃዞች መገንዘብ እንችላለን። ሀገራት ከእርስ በርስ ግጭት እንዳይወጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ግጭቱን በሀቀኛ የሰላም ድርድር የማይቋጭ ከሆነ ሀገራት የግጭት አዙሪት ውስጥ የመቆየት እድላቸው ይሰፋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ አውዳሚ የእርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግዳለች። በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ግጭት ሀገሪቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏታል። ብዙዎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎች አካላቸውን አጥተዋል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬቸው ተፈናቅለዋል። ብዙ ንብረቶች ወድመዋል። ብዙ ዋጋ ከተከፈለ በኋላም ቢሆን ካለፈው ትምህርት በመውሰድ የእርስ በርስ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተደረሱ የሰላም ስምምነቶችን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማ የት ጀምረናል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ድርድር እንደ ዋና አማራጭ መወሰዱ ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት መሰረት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። በግጭቱ ሁሉም ወገን ተጎድቷል። በሰላም ስምምነቱ ደግሞ ሁሉም ወገን አሸናፊ ነው። ይህ መሆኑ በቀጣይ በቂም ለዳግም ግጭት የሚነሳ ሀይል እንዳይኖር እድል የሚጠብ ነው። ሀገሪቱ አሸናፊ በምትሆንበት መልኩ በንግግር እና በድርድር ለመቋጨት የተደረገው ጥረት ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ መልካም መሰረት የሚሆን ነው።
ከዚያ ባሻገር ሁለቱም አካላት የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግስቱን ለማክበርና ለህግ የበላይነት መከበር ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸው ግጭቱ ዳግም የማገርሸት እድሉን የሚያጠብ ነው። ከግጭት አዙሪት በዘላቂነት ለመውጣት የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር ጠንካራ የፖለቲካ ተቋማትን መገንባት እና የበለጠ እምነት የሚጣልበት የመንግስት መዋቅሮችን መገንባት የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ናቸው።
ድህነት እና የመንግስት አቅም ማነስ የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲያገረሹ የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ። ድህነት እና የመንግስት አቅም ማነስ በዓለማችን ከሚስተዋሉ የእርስ በርስ ግጭቶች ጀርባ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም ሀገሪቱን ከድህነት ለማስወጣት እና ወደ ብልጽግና ለማሻገር በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት። ከዚህ ጎን ለጎን ጠንካራ የመንግስት ተቋማትን ለመገንባት በትኩረት መሰራት አለበት። እነዚህ ተቋማት በቀጣይ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን መወጣት መቻል አለባቸው።
የኢኮኖሚ ብልጽግና እውን ማድረግ እና ጠንካራ የመንግስት ተቋማትን መገንባት ብቻቸውን ግጭቶችን ሊያስወግዱ አይችሉም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ድህነት እና የመንግስት አቅም ማነስ በራሳቸው እርስ በርስ ግጭቶች ዳግም እንዲያገረሹ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም። ከሁሉ በላይ ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን ለማቆም ቁርጠኝነት ማጣት የእርስ በርስ ግጭቶች ዳግም እንዲያገረሹ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በተለይም ሀገርን የሚያስተዳድር መንግስት ቁርጠኝነት የአንበሳውን ድርሻ ይወጣል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ግጭትን ለማቆም እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት እጅግ የሚያስደስት ነው። መሰረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ወደ ስራ ማስገባት፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች በተሳለጠ መልኩ እንዲዳረሱ በማድረግ ረገድ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው። በዚህ ረገድ ያለው መልካም ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
የሕወሓት አመራሮችም በበኩላቸው ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ እና የሰላም ስምምነቱ መሬት ላይ እንዲወርድ እያደረጉት ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው። ሁለቱም ወገኖች የታየውን የድህረ ግጭት ሰላም መንከባከብ አለባቸው። ከሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች በተጨማሪ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት። ግጭትን ዳግም ለመቀስቀስ ጥረት ለሚያደርጉ አካላት ጆሮ መስጠት የለበትም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም