ግጭቶች በባህሪያቸው ሊያስከፍሉ የሚችለው ዋጋ በቀላሉ ሊገመት የማይችል፤ ከተከሰቱም በኋላ ለማስቆም ያለው ፈተና ከፍ ያለ ነው፤ ከዚህ የተነሳም ከግጭት በኋላ የሚገኝን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ከፍተኛ ቁርጠኝነት፤ ብዙ ዋጋ መክፈልንም የሚጠይቅ ነው።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት ሀገራት አንድ ጊዜ እርስ በርስ ግጭት ካጋጠማቸው በኋላ ተጨማሪ የእርስ በርስ ግጭቶችን የማስተናገድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። እ.አ.አ በ2010 በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ስለ እርስ በርስ ግጭቶች ማገርሸት እና በድህረ ግጭት ዘላቂ ሰላም ስለማስፈን የተጠና ጥናት እንደሚያመላክተው፤ ከ1945 እስከ 2009 ድረስ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ካስተናገዱ 103 ሀገራት የእርስ በርስ ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ ማድረግ የቻሉት 44 ሀገራት ብቻ ናቸው።
የእርስ በርስ ግጭት ካስተናገዱት ሀገራት መካከል 59 ሀገራት ቢያንስ አንድ ጊዜ ዳግም የእርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግደዋል። ይህም ማለት በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትን ካስተናገዱ ሀገራት ውስጥ 57 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ዳግም ወደ እርስ በርስ ግጭት ገብተዋል ማለት ነው።
በተለይም ከእ.አ.አ 2003 ወዲህ በዓለም ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ የእርስ በርስ ግጭቶች የቀደሙ የእርስ በርስ ጦርነቶች ቅጥያ ሆነው ተገኝተዋል። በ21ኛ ክፍለ ዘመን ከተቀሰቀሱ የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ቀደም ባሉት ዓመታት የእርስ በርስ ግጭቶችን ባስተናገዱ ሀገራት ውስጥ የተፈጠሩ ናቸው።
ጥናቱ በተጨባጭ እንዳመለከተው፤ ከግጭት በኋላ የሚገኝ ሰላም ከፍተኛ እንክብካቤ የሚሻ ፤ግጭቶች የፈጠሩትን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በቃ የሚያሰኝ ከልብ የሆነ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ፤ይህንንም ዕለት ተዕለት በተጨባጭ በተግባር ማሳየትን የሚሻ ነው።
በተለይም እንደኛ ያሉ ድህነትን አሸንፎ ለመውጣት አዲስ በሆነ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ፤ የድህነታቸውም ሆነ የኋላ ቀርነታቸው ምንጭ ግጭቶች ከመሆናቸው አንጻር፤ ግጭቶችን በተቻለ መጠን በውይይት የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ይህንን መፍጠር አለመቻል እንደ ሃገር በቀጣይ በሚኖራቸው እጣ ፈንታ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ቀላል አይደለም።
አሁን ባለው ዓለም አቀፍ እውነታ ድህነት ለአንድ ሀገርና ሕዝብ የቱን ያህል ፈተና እንደሆነ፤ይህንን ፈተና አሸንፎ ለማለፍ የሚደረግ ጥረት በራሱ ምን ያህል እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሚጠይቅ ያለፉት ዓመታት ተሞክሯችን በተጨባጭ ያሳየን ነው።
የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳችን ለመወሰን የጀመርነውን ሀገራዊ ንቅናቄ /ለውጥ / ተደማምጠን ማስቀጠል አለመቻላችን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ዛሬ ላይ ከፍ ባለ ቁጭት ልናስታውሰውና ልንዘክረው ይገባል። የትናንቱ ስህተታችን ከግጭት ነፃ የሆነች ሀገርና ትውልድ መፍጠር የሚያስችል ዕድል አድርገን ልንወስደውም ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ፈጥኖ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ያለ ወትዋች ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፤ ከመጠባበቅ ወጥቶ ከጊዜ ቀድሞ መሄድን ፤ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርንም ይፈልጋል።
የሰላም ስምምነቱ ህገመንግስቱን ፣ ህገመንግስታዊ ስርአቱን እና ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ፤ ከዚያም በላይ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ለመላው ሕዝባችን እፎይታ የፈጠረ ነው ይህን የሕዝባችንን ስሜት በተሻለ መልኩ አስቀጥሎ ለመሄድ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድኑን ወደ መቀሌ ከመላክ ጀምሮ ፣ በሰላም ስምምነቱ የድርጊት መርሀ ግብር ውስጥ ያልተካተቱ፤ ነገር ግን የበለጠ መተማመንን በመፍጠር የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሄደበት ያለው መንገድ የሚበረታታና ምስጋና የሚቸረው ነው።
የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ሕዝብ ይዞለት ከመጣው እፎይታ አንጻር ፣ ሕወሓት ስምምነቱ ዘላቂ እንዲሆን እየሄደበት ያለው መንገድ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ መንግስት እያደረገ እንዳለው ከጊዜና ከቅድመ ሁኔታ አጥር እየወጣ መተማመንን የሚፈጥሩና የሚያጠናክሩ ተግባራትን እውን ማድረግ ይጠበቅበታል።
ይህን ማድረግ የተጀመረውን ሰላም ጠብቆ ከማስቀጠል ባለፈ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ዋጋ እየተከፈለበት ያለው አዲሱ ሃገራዊ የፖለቲካ ባህል ችግሮችን በንግግርና በውይይት የመፍታት አቅም እንዲገዛ የተሻለ እድል የሚፈጥርም ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም