በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመታወቂያ አገልግሎት ለተወሰኑ ጊዜያት ታግዶ ቆይቶ ከህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የመታወቂያ እድሳት አገልግሎት እየተሰጠ ነው። ለህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሆነውን አገልግሎት አሰጣጥ በምን መልኩ ቀልጣፋ፣ ከነዋሪው እንግልትና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ አስባችኋል? የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሞት፣ ልደት፣ ጋብቻና ፍችን የመመዝገብ ሥራ ምንነትን? እንዲሁም አገልግሎቱ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት መሰረታዊ የሚባሉ የአሰራርና መሰል የተቋም ስራዎችን ለውጦችንና ተያያዥ ጉዳዮች አንስተን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ምንድን ነው፤ የሚሰጠው ጠቀሜታስ?
አቶ ዮናስ፡- የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሞት፣ ልደት፣ ጋብቻና ፍችን የመመዝገብ ሥራ ነው። ምዝገባው ሦስት ዋና ዋና ጥቅሞች አሉት። ለኢኮኖሚያዊ፣ ለማህበራዊ ፣ ለሕግና ለሕዝብ አስተዳደር አገልግሎት ይውላል።
ለኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ሲባል በአገሪቱ የሚታቀዱ ፖሊሲዎችና እቅዶች መሠረት የሚያደርጉት የኩነቶችን መረጃ ነው። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት መነሻ የሚሆነው የአካባቢው ሕዝብ የቁጥር መረጃ ነው። ትክክለኛ የሕዝብ ቁጥርን መረዳት የሚቻለው በዓመታት ልዩነት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በማካሄድ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃና ሰከንድ የሚከሰቱ ኩነቶችን በመመዝገብ ነው።
ከሕግ አንጻርም በማስረጃ እጦት በሀሰት ምስክር ኢኮኖሚያዊ መብት የሚታጣባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አንዱን ብንመለከት ልጅነትን መካድ አንዱ ነው። ልጆች የቤተሰቦቻቸውን ንብረት በእኩል የማግኘት መብት እያላቸው መረጃ ባለመኖሩ በአንድ ቤተሰብ አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ተጎጂ ይሆናሉ። ምዝገባው ይህን ያስቀረዋል። የሕዝብ አስተዳደርን በተመለከተ ለምርጫ፣ ለበጀት ድልድልና የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ጊዜያት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ይካሄድ ነበር። አሁን ለምን በኤጀንሲ ደረጃ ማቋቋም አስፈለገ?
አቶ ዮናስ፦ከአሁን በፊት ምዝገባ ይካሄድ የነበረው በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች ነው። አስገዳጅ ሕግ የለውም። በአገልግሎት ጠያቂው በኅብረተሰብ ፈላጊነት ብቻ የሚካሄድ ነው። የሞት፣የልደት የፍችና የጋብቻ ሰርተፍኬት የሚሰጠው ባለጉዳዩ ፈልጎ ሲመጣ ነው ። አሁን ግን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በከተሞች ብቻ ተንጠልጥሎ የሚቀር ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመታወቂያ አገልግሎት ታግዶ መቆየቱ ይታወቃል፤ ታግዶ የቆየበት ምክንያት ምንድነው? አገልግሎቱን ለማስጀመር ምን አይነት ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል?
አቶ ዮናስ ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመታወቂያ አገልግሎት ታግዶ ቆይቷል፤ ከህዳር 1 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ተፈቅዶ መታወቂያ እድሳት አገልግሎት እየተሰጠ ነው። አገልግሎቱ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት መሰረታዊ የሚባሉ የአሰራርና መሰል የተቋም ስራዎችን ለውጦችን ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። አገልግሎቱ የታገደባቸው ምክንያቶች ዘርፉ ያለበት ሁኔታ ከሰላምና ፀጥታ ተጋላጭነት አንፃር ሲታይ መዋቅሩ መፈተሽ በማስፈለጉ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ታግዶ ቆይቷል።
አገልግሎቱ በድጋሚ ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል። ከእነዚህም መካከል ቀድሞ አገልግሎት ላይ የነበረውን ስርዓት የመፈተሽ ስራ፤ ወረዳዎች ያሉበትን ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ታይቶ ደረጃ በመስጠት ዝግጁ ያልሆኑትን ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረቶች ተደርጓል።
ከዛ ባሻገር ተገልጋይ የሚበዛባቸው ወረዳዎች ላይ መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች በተወሰነ መልኩ ተለይቶ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ከአሰራር ማሻሻያ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ስንሰጥባቸው የነበሩ ህትመቶችን ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ አዲስ አሳትመን ወደ አሰራር አስገብተናል።
ይህም የወሳኝ ኩነት ማስረጃዎችን ፣ ያላገባ ሰርተፍኬትን እንዲሁም የወረቀት መታወቂያን ጭምር ያካትታል። በዚህ መሰረት አገልግሎቶቻችንን ከመጀመራችን በፊት በዚህ ደረጃ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማከናወን ችለናል።
ማስረጃዎቹ የያዙት ፅሁፍና የይዘታቸው ፅሁፎች በሚስጠራዊ ህትመቶች የተለዩ ናቸው። ለተጭበረበረ (ለፎርጅድ) ሊጋለጡ የሚችሉበትን ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ቀንሰናል። በዚህም ጠንካራ የሆነ የአሰራር ስርዓትም ለመፍጠር ተሞክሯል።
አዲስ ዘመን፦ የመታወቂያ እድሳት አገልግሎት አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ዮናስ ፦ የመታወቂያ እድሳት አገልግሎት አሁን ያለበት ደረጃ በ3 ክፍለ ከተማ ስር ከሚገኙ 14 ወረዳዎች ማለትም አቃቂ ፤ ነፋስ ስልክና ከለሚ ኩራ ክፈለ ከተሞች ውጪ ሁሉም የድጅታል ምዝገባ እያከናወኑ ይገኛሉ። ኤጀንሲው ከህዳር 1 እስከ ታህሳስ 8 ጥቅል የተሰጠ የመታወቂያ አገልግሎት: 238 ሺህ 72 የዲጂታል አገልግሎት: 218 ሺህ 683 (91 ነጥብ 85%) የማንዋል (የእጅ ፅሁፍ) አገልግሎት: 18 ሺህ 989 (7 ነጥብ 97%) የታተመ ዲጂታል መታወቂያ 112ሺህ 325 (51 ነጥብ 36%) አገልግሎት እየሰጠ ነው።
ኤጀንሲው ለበርካታ ቀናት ቅዳሜ እና እሁድ ሙሉ ቀንን ጨምሮ እስከ ምሽቱ 2:30 በሁሉም ወረዳዎች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። የመብራት እና የቴሌኮም መስመር መቆራረጥ እንዲሁም የሲስተም መዘግየት እንደ ችግር ገጥሞታል። ይህንኑ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ ሲሆን ተገቢው ጥገና እንዲደረግ በማድረግ አገልግሎቱን ለመስጠት ጥረት ተደርጓል።
በዚህ ሂደት ነባሩና አገልግሎት እየሰጠ የነበረው ሲሰተም አቅሙ ውስን በመሆኑና ያለውን የከተማዋን አገልግሎት ሂደት የሚመጥን ባለመሆኑ
የተነሳ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ በአዲስ ሲስተም እንዲተካ እየተደረገ ይገኛል። አገልግሎቱን አግዶ ሲሰተሙ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ የሚፈጥረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎቱ በጥንቃቄ በነበረው ሲስተም እንዲቀጥል ተወስኗል። ከሁሉ በላይ ግን በነባሩ ሲስተም በአጠረ ጊዜ ውስጥ ይሄን ያህል ቁጥር ያለው የዲጅታል ምዝገባ ማድረግ ትልቅ እመርታ ነው። ህብረተሰቡንም አገልግሎቱን በማቋረጣችን ተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቀናል። አሁንም ስራው የተቃና እንዲሆን ወረዳዎችን እየዞርን እየተከታተልን ስራው በጥሩ መንገድ እየሄደ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አገልግሎትን በጥራት ለመስጠትና ዘመናዊ አሰራርን ለመጠቀም በተቋሙ ምን አይነት ጥረት እየተደረገ ነው?
አቶ ዮናስ፦ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ለአብነት ያህል ከዚህ ቀደም የዲጅታል መታወቂያ ህትመት የሚከናወነው በዋና መስሪያ ቤት ብቻ ነበር። አሁን ላይ 11 ክፍለ ከተማዎች ዲጅታል መታወቂያን አትመው እያሰራጩ ይገኛሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በስሩ ያሉትን ለዲጅታል መታወቂያ የተመዘገቡ ነዋሪዎችን መታወቂያ ባጠረ ጊዜ አትሞ የማሰራጨት ስራን በቅልጥፍና እየሰራ ነው ማለት ነው። መታወቂያም የደረሰላቸው ሰዎች እየተደወለ መታወቂያውን እንዲወስዱ እየተደረገ ነው።
በኤጀንሲው ከሞላ ጎደል ተቋሙ ስር ነቀል ሪፎርም እያደረገ ይገኛል። በዚህም አራት የሪፎርም መስኮችን ለይቶ እየሰራ ነው። አንደኛው ቴክኖሎጂን ማዳበር አዲስ ሲስተም ማልማት የራሳችንን መሰረተ ልማት መገንባት ነው። ከዚህ ቀድም በ2014 አዲስ ሞጁላር ዳታ ሴንተር ዘርግተን አጠናቀናል። አዲስ ሲስተምና አዲስ የዩፒኤን ስራዎችን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን እየሰራን እንገኛለን።
ሁለተኛው የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ ነው። የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን መፍታት። የምናሰራጫቸውን ህትመቶች በከፍተኛ ቁጥጥር ስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የመዋቅር ማሻሻያ አድርጎ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ። ከዛ ውጪ የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአሰራር የተቃኙ እንዲሆኑ ባለሞያው ስራውን እንዲመራ በመልካም ስነምግባር ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀም የአሲቲ ፖሊሲ መመሪያዎች ሲዘጋጁ ቆይተዋል።
ሶሰተኛው ሪፎርም የተሰራው የሰው ሀብታችን ላይ ነው። የሰው ሀብታችን የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ማብቃት ስልጠና መስጠት ህብረተሰቡን የሚመጥን ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ሰራተኛ ማብቃት ላይ እየተሰራ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ታታሪ የሆኑትን ከተቋሙ ጋር እንዲቀጥሉ ማድረግ የተለያዩ የስነ ምግባር ክፍተቶች ያሉባቸውንና ሌሎችን ደግሞ እያረሙ መሄድ የሚያስችል አሰራር ዘርግተናል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋሙ የሰጣቸውን መታወቂያዎችና ሰርተፍኬቶች ኦዲት አስደርገን አጠናቀናል። በዚህ መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑ አመራሮች ባለሙያዎች በየደረጃው ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል። ስለዚህ የሰው ሃይል ላይ ተቋሙ ተልዕኮውን ሊያሳካ በሚያስችለው መልኩ ብቁ የሆነ ባለሙያ አመራር ኃላፊዎችም ጭምር በዛ ደረጃ እንዲመሩ ለማድረግ የተለያዩ የስልጠና ስራዎችን በአግባቡ እየሰራን ነው።
አራተኛውና የመጨረሻው የመዋቅር ማሻሻያ ነው። ትልቁ ሪፎርም ተቋማችን ተልእኮውን ሊያሳካ የሚችል አደረጃጀት እንዲኖረው የሚያስችል መዋቅራዊ ጥናት አስደርገናል። በዚህ መሰረት ከማእከል ያሉ አደረጃጀቶች ለውጥ ተደርጎባቸዋል። በጤና ተቋማት ላይ የልደትና የሞት ምዝገባ ለማድረግ የሚያስችል መዋቅር ፈጥረናል።
አዲስ ዘመን፦ በጤና ተቋማት ላይ የልደት ምዝገባ ለማድረግ የሚያስችል መዋቅር ፈጥረናል ብለዋል፤ ይህ ምን ጠቀሜታ አለው?
አቶ ዮናስ ፦ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የልደት ምዝገባ ከሚከናወንባቸው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት አንዷ ስትሆን ይህ ዓይነቱ ዘመናዊ ስርዓት ያለውን ችግር ከመሰረቱ የሚፈታ እንደሆነ የዘርፉ ጥናት ያሳያል። በሃገሪቱ ያለው ልምድ ዜጎች ለግል ጉዳይ ሲፈልጉ ካልሆነ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የማድረግ ባህል የሌለ ሲሆን ቀጣይ ይህ አሰራር በህግ በተደነገገው መሰረት ወደ አስገዳጅ የሚሄድ እንደሚሆን ይታመናል።
በአዲስ አበባ በ2014 ዓ.ም የተጀመረውን የልደት እና የሞት ምዝገባ የሙከራ ፕሮጀክት መነሻ በማድረግ የተሰራው የመዋቅር ማሻሻያ አሁን በአዲስ አበባ በስራ ላይ ባሉ ሰላሳ ሶስት የመንግስት እና የግል ሆስፒታሎች ቀድሞ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በቀጣይ ከፍተኛ ውልደት እና ሞት በሚከሰትባቸው የጤና ተቋማት እየታየ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
አገልግሎቱ ከተጀመረባቸው የጤና ተቋማት መካከል አበበች ጎበና፣ ዘውዲቱ፣ ጋንዲ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ፣ ጴጥሮስ፣ አለርት፣ ምኒልክ እና ጳውሎስ ምዝገባ ከተጀመረባቸው ሰላሳ ሶስት ሆስፒታሎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በጤና ተቋማት እየተሰራ ያለው የልደት እና ሞት ምዝገባ አገልግሎት በታብሌት ነው። ይህም የምዝገባ ሽፋንን እና የመረጃ ጥራትን ያሳድጋል። ኤጀንሲው ከጤና ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በአስራ አንድ ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ የግል እና የመንግስት ጤና ተቋማት የሚከሰቱ የልደት እና ሞት ምዝገባን ሽፋንን ለማሳደግ በጤና ተቋማት እየተሰጠ ያለውን የታብሌት ምዝገባ አገልግሎት ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ስራውን ለማሳለጥ እየተሰራ ይገኛል።
የወቅታዊ ኩነት ምዝገባ ስራው በጤና ተቋማቱ መሰጠቱ የተገልጋይ እርካታን የሚጨምር ከመሆኑ በላይ ስለ ወቅታዊ የልደት ምዝገባ ግንዛቤው ለሌላቸው እናቶች ግንዛቤ ይፈጥራል በማለት በሆስፒታሉ አገልግሎቱን የወሰዱ እናቶች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋናል። በዚህም ግብረ መልስ ደስተኛ ነን።
ከዚህም በተጨማሪ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የፍቺ፣ የጉድፈቻ እና ሌሎች አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ተይዟል። ከዛ ባሻገር የህትመት ቁጥጥርና ስርጭት በአግባቡ እንዲመራ ይህንን የሚቆጣጠር ክፍል እያደራጀን እንገኛለን። ክፍሉም የቴክኖሎጂ ስራዎችን እንዲያግዝ በተደራጀ መልኩ ቴክኖሎጂው እየተመራ ይገኛል። በዚህም የዲጂታል ምዝገባን በቀጥታ የሚያሳይ ሶፍትዌር / Softwer/ በተቋሙ የውስጥ አቅም አልምቶ ስራ መጀመሩን ፤ በሁሉም ወረዳዎች ያለውን አገልግሎት በመመዝገብ በቀጥታ /live/ በማሳየቱ የሲስተም መቆራጥ ችግር ሲያጋጥምም በፍጥነት ለመፍታት እድል የሚሰጥ እና አጠቃላይ ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት የዕለት አፈጻጸም በቀላሉ ለማወቅ የሚያግዝ ሶፍትዌር ነው። ይህም ስራው ሳይጓተት በተሳለጠ መልኩ እንዲከናወን እያደረገው ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ከመታወቂያ እድሳት ወጪ ሌሎች አገልግሎቶቸ ለምሳሌ አዲስ መታወቂያ መስጠት፤ መታወቂያ የጠፋበትን መተካት የመሳሰሉት አገልግሎቶች እየተሰጡ አይደለም ለምን?
አቶ ዮናስ ፦ ከመታወቂያ እድሳት ውጪ ሌሎች አገልግሎቶች ያልተጀመሩበተ ምክንያት አሁን ካለው የመታወቂያ እድሳት ፈላጊ ተገልጋይ ብዛት ታይቶ ቅድሚያ ታግዶ የቆየውን የመታወቂያ እድሳት እናስተናግድ በሚል ነው። ሁለተኛው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪነት የሚመጣው ሰው መታወቂያ ሲፈልግ ይዞት የሚመጣው ማስረጃ መጣራት የሚኖርበት ሲሆን በማጣራት ሂደቱ የተነሳ ሊዘገይ ይችላል። አዲስ ወደ ከተማዋ ተቀላቅለው በነዋሪነት መመዝገብ የሚፈለጉ ሰዎች የግድ ስድስት ወራትን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። የተለየ ምክንያት ኖራቸው ከሚፈቀድላቸው ግለሰቦች በስተቀር ሁሉም አዲስ መታወቂያ ፈላጊ ለስድስት ወራት በከተማዋ ውስጥ መኖር አለባቸው።
ሌላው መታወቂያ መጣል በሌላው አለም ያስቀጣል። ማስቀጣት ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያሉ ነዋሪዎች መታወቂያ የመያዝ ባህላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑ አሳሳቢ ነው። መታወቂያ ማለት ማንነትን መግለጫ ነው። መታወቂያውን አጥቦ መጥቶ፤ ጥሎ መጥቶ አዲስ ስጡኝ ማለት እንዝላልነት ነው። በሚጥሉና በሚያበላሹ ሰዎች የተነሳ የሀገር ገንዘብንና ጉልበትን የሚያባከን በመሆኑ ቅድሚያ እጁ ላይ ለያዘ ሰው ይሰጣል። ከፀጥታ ሁኔታም አንፃር የመታወቂያ አገልግሎትም እንደሚያስፈልገው አምኖ በጥንቃቄ መያዝ ይኖርበታል። ከዛ ምትክ መታወቂያ የሚባለው ግን ይቆይ ተብሎ ቆሟል።
አሁን ግን ለጠፋ መታወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አጠናቀናል። ይህንንም በቀጣይ ሳምንት ውስጥ ወደ ተግባር ለማስገባት እየሰራን እንገኛለን። ሌላው በእድሜ እርጅና እና በጤና እክል ምክንያት በአካል ተገኝተው መገልገል ላልቻሉ ዜጎችም የቤት ለቤት አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
አዲስ ዘመን፦ መታወቂያ ለማደስ ብዙ ሰው ፍላጎት አለው። መጨናነቁ ሲበዛና ወረፋ መጠበቅ ሲሰለቸው ያልተገባ አካሄድን ቢመርጥ ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ ባለሙያዎች ቢኖሩ በምን መልኩ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል?
አቶ ዮናስ፦ በቅድመ ዝግጅት ስራ ውስጥ የተሰራው ስራ ብልሹ አሰራር የሚፀዳበት መንገድ ማመቻቸት ነው። ህብረተሰቡን በማወያየት ሰፊ ንቅናቄ ተፈጥሯል። ስራው የሚመራው በከተማው ዋና ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ነው። በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከተማው አስተዳደር በሆኑት በአቶ ጥራቱ በየነ የሚመራ ታስክ ፎርስ ተቋቁሟል። በዋናው መስሪያ ቤት የሚሰሩ አመራሮች የአይቲ ባለሙያዎችን ጭምር ሁሉም ወረዳ ላይ በመዘዋወር የስራውን አካሄድ ይቆጣጠራል።
በቁጥጥር ስራ ውስጥ ከአመራር ጀምሮ የአይቲ ባለሙያ እና ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ ሙያተኛ የስራውን ጥራት ይቆጣጠራል። ሰልፍ ላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፤ የደንብ ማስከበር አባላት፤ ፖሊስ በመተባበር የፀጥታ ሁኔታውን ይቆጣጠራሉ። ሰልፍ የመሸጥ ዝንባሌ ከታየ ወዲያው የእርምት እርምጃ ይወሰዳል። ያሉ ብልሹ አሰራሮች የሚበረክቱባቸውን ቦታዎችን በመለየት የተሻለ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በዚህም ትክክለኛ ያልሆኑ መታወቂያዎችን ለማግኘት ተችላል።
አዲስ ዘመን፤ ትክክለኛ ያልሆነ መታወቂያዎች የት አካባቢ ነው ያገኛችሁት ማወቅ ብንችል?
አቶ ዮናስ ፦ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ አንድ ከንግድ ባንክ የማስረጃ ማጣሪያ ጥያቄ የቀረበለት የወረዳው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ጽህፈት ቤት የቀረበለትን የዲጂታል መታወቂያ ኮፒ ትክክለኛ ያልሆነ መሆኑን ከዋና መስሪያ ቤት የመረጃ ቋት አረጋግጦ ምላሽ ለባንኩ የሰጠ ሲሆን ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ሁለት ግለሰቦች ሁለት መታወቂያ ለማውጣት ባደረጉት ጥረት፣ አንድ ግለሰብ ሃሰተኛ መሸኛ ይዞ በመቅረብ፣ 13 ሰራተኛ በስነ-ምግባር ግድፈት ፣ ሁለት ሰራተኛ በወንጀል ድርጊት እንዲሁም ሁለት አመራር ስራን በአግባቡ ባለመምራት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
የሃሰተኛ ሰነድ በከተማው እየተበራከተ የመጣ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ይህንን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከህዳር አንድ ቀን ጀምሮ የወረቀት መታወቂያ ለጊዜው ከተፈቀደላቸው አስራ አራት ወረዳዎች ውጪ በከተማው እንዲቆም በማድረግ ባለው መሰረተ ልማት በዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ይገኛል።
በተጨማሪም ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ሲውሉ የነበሩ ህትመቶችን በማስወገድ በአዲስ የመተካት ስራ የሰራ ሲሆን ሃሰተኛ ሰነድ መለየትን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን እያሟላ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ መነሳት ያለበትና በጥያቄ ያላካተትኩት ሀሳብ ካለ እድል ልስጥዎት?
አቶ ዮናስ፦ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ምስጋና ነው። መታወቂያ ተቋርጦ በነበረበት ወቅት ህብረተሰቡ በትእግስት ስለጠበቀን ሊመሰገን ይገባዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ የOnline ምዝገባ አገልግሎት እስካሁን ያልጀመረ መሆኑን እየገለፅኩ በከተማው በተለያዩ ቦታዎች እና የኢንተርኔት ካፍቴሪያዎች ያለው የመታወቂያ ምዝገባ የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባ እንጂ ከከተማው የዲጂታል የነዋሪነት መታወቂያ ጋር የማይገናኝ መሆኑን ማሳወቅ እወዳለሁ።
በአንዳንድ ስፍራዎች የነዋሪነት መታወቂያ ምዝገባ እንደሆነ በመግለፅ ምዝገባ እያከናወኑ ያሉ እንዳሉ መረጃ የደረሰን ሲሆን ፤ በዚህ የማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማራችሁ ከድርጊቱ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን ኤጀንሲው አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ከወዲሁ ያስገነዝባል።
አዲስ ዘመን፦ ውድ ጊዜዎን ሰውተው መረጃውን ስለሰጡን እናመሰግናለን።
አቶ ዮናስ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015