የትናንቱ ታሪካችን፤
ከመደበኛ ትምህርት ቤት የማናገኘውና “ክፉም ይሁን ደግ” ትምህርት አስተምሮን ያለፈው ትናንታችን እንደ ሀገር በእምባም በፈገግታም የምንተርክለትን ብዙ ታሪክ ሸሽጎ ይዟል። ያስፈነደቁን፣ ያስከፉን፣ ያሳቁን፣ ያስለቀሱን፣ ያቅራራንባቸው፣ የተከዝንባቸው፣ የከሰርነባቸው፣ ያተረፍንባቸው እንዲያው በጥቅሉ ኢትዮጵያና ዜጎቿ የተጓዝንባቸው ጎዳናዎች በአቀበትና በቁልቁለት ብቻ የሚገለጹ ሳይሆኑ የእርምጃዎቻችን ውጣ ውረዶች በቀላሉ ተተርከው የሚጠናቀቁ አይደሉም።
ነፍሰ ሄሩ የጥበብ አንጋፋችንና “አይከናችን” ጸጋዬ ገብረ መድኅን ካወረሰን የብዕር ትሩፋቶቹ መካከል በጥቂት ስንኞች የተዋቀረውና ጥልቅ መልእክት የተሸከመው መልእክቱ “የብሔራዊ መዝሙር ያህል” በብዙዎቻችን ሲጠቀስና ሲዘመርለት ኖሯል፤ ለወደፊቱም የሚሰለች አይመስልም። ኦርጂና ግጥሙን ከዋናው ምንጭ በመቅዳት ቃል በቃል እንዳለ የሚጠቅሱ የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩ የራሳቸውን ጥቂት የማከያ ቃላት ደብለቅ እያደረጉ የሚጠቅሱም አልጠፉም። አንድ ብርቱ ጸሐፊ በሐቲቱ ውስጥ ጥቂት ቃላት ቀላቅሎ የጠቀሰውን ያንን ግጥም እንደሚከተለው ተውሼዋለሁ።
“ሰው የሚማረው ከሁለት ነገር ነው፣
አንድም ከፊደል ሆሄ፤ አንድም ከመከራ ኤሎሄ፣
አንድ ቃል ከፊደል ገበታ “ሀ” ብሎ፣
አለያም ከመከራ መዝገብ “ዋ” ብሎ።
እንደ ውቂያኖስ የጠለቀ ሃሳብ የተሸከመው ይህ አጭር ግጥም ለግል፣ ለቤተሰብ፣ ለማሕበረሰብም ሆነ ለኅብረተሰብ የሚያስተላልፈው “ዐዋጅ አከል” መልእክት በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም። “ልብ ያለው ልብ ቢለው” – “ልብ ጠለቅ” ትምህርት ሊሰጥ እንደሚችል አስረግጦ መመስከር ይቻላል።
“ዲሞክራሲ ያለ ገደብi?” የሚለው የጽሑፋችን ዋና ርዕስ አንደ ዋና የመታገያ “አጀንዳ” ይቀነቀን የነበረው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በነበሩ ነውጠኛ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ነበር። ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ ያንን “የለውጥ ርሃብተኛ አፍለኛ ትውልድ” በግጥሙ ለማስተዋወቅ የሞከረው ራሱን አቃጥሎና አክስሞ በሚጠፋ ተወርዋሪ ኮከብ በመመሰል ነበር። ዘለግ ካለው የባለቅኔው ግጥም ውስጥ ጥቂት ስንኞችን ቆንጥረን እናስታውስ።
“ተወርዋሪ ኮከብ የደረሰው ቦታ የጨለመ ምድር፣
አይታይም ነበር።
ጨለማ አካል ገዝቶ፣
ይዳሰስ ነበረ በየቦታው ገብቶ።
ብሩህ ነጸብራቁ፣
ውበቱና ድምጹ፣
አንድነት ተሰምቶው አንድነት ቢበርቁ፣
የሚያውቅለት ጠፍቶ፣
ምሥጢሩን አካቶ፤
ተወርዋሪ ኮከብ፣
በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ቃል ተቃጥሎ የጠፋ፣
ተወርዋሪ ኮከብ…
በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ። ”
“ዲሞክራሲ ገደብ ሳያስፈለግው በገፍ ይፍሰስልን!” እያለ ገና በሁለት እግሮቹ ጸንቶ መቆም የተሳነውን ወታደራዊውን ግልፍተኛ የደርግ መንግሥት በመፈክር ሲሞግት የነበረው ያ “በተወርዋሪ ኮከብ” የተመሰለው ትውልድ “ጩኸቱ የኩራ ጩኸት ሆኖ፤ ደሙም ደመ ከልብ ሆኖ” ማለፉ በታሪክ ሲጠቀሱ ከሚኖሩት ክፉ የሀገራዊ ስብራቶቻችን መካከል አንዱ፤ ምናልባትም ዋነኛው ሳይሆን አይቀርም። ያ የዘመኑ “አብዮታዊ ድምጽ” ዛሬም ድረስ ብዙ እየተወቀሰም ሆነ እየተደነቀ መታወሱ አልቀረም።
ይህ ዐምደኛ “የሃምሳና ስልሳዎቹ” ትውልድ እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋቡለትን መፈክር ያስታወሰው በትምህርተ ስላቅ (i)፣ በጥያቄ ምልክት (?) እና በትምህርተ ጥቅስ ቀንብቦ መሆኑን ልብ ይሏል። ሦስቱ ምልክቶች ተጣምረው አገልግሎት ላይ የዋሉት ምጸትን፣ ግራ መጋባትንና “እኔ አላምንበትም” የሚሉ አሉታዊ ትርጉሞች እንዲኖራቸው ተደርጎ መሆኑን ማስታወሱ አጋባብ ይሆናል።
የዛሬው እውነታችን፤
በትናንቱ “ጎፈሪያም” ትወልድ “ያለ ገደብ ተትረፍርፎ ይሰጠን!?” በሚል ሥልጣነ ድምጽ ሲጠየቅ የነበረው “አስካሪው የዲሞክራሲ የእንክርዳድ ወይን ጠጅ” በስሎና ፈልቶ ለመጠጥ የደረሰው በዚህ በእኛ አዚማም ዘመን መሆኑ ለትንግርትም፤ ለግርምትም የሚዳርግ ነው። “ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” የሚለው ክፉ ዘር ጎምርቶ ማፍራቱን የምናስተውለው “ብሔራቸውና የት መጣቸው” ምክንያት ሆኖ ብቻ የንጹሐን ዜጎች ደም በከንቱ ሲፈስ እያስተዋልን ነው።
ከሃምሳ ዓመት በፊት “ዲሞክራሲ ያለ ገደብ!” ከሚለው መፈክር ጋር አብሮ ይቀነቀን የነበረን ሻጋታ አስተሳሰብ እንደ አዲስ አቧራውን በማራገፍ “ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ነው!” እያሉ የሚጮኹ የ“ኅሊና ቢሶችን” እንጉርጉሮ ማድመጥ ውስጣዊ ስሜትን ያቅራል። አልፎም ተርፎ “ጦርነት በቃን! ሰላም ይሻለናል! የወድማማቾች ሰይፍ መማዘዝ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊቆም ይገባል!” የሚለውን የዜጎች መቃተት በረዣዥም ሴረኛ አንደበታቸው “የዲሞክራሲን ስም” እንደ ሽፋን እየተጠቀሙ በማላዘንና በመቃወም የባእዳንን አደባባይ የሚያረክሱትን “የእንግዴ ልጆች” ድርጊት መመልከት በእጅጉ ግራ ያጋባል።
በዚህ ጸሐፊ እምነት “ዲሞክራሲ ያለ ገደብi?” በማለት ታክሎበት በዚያ ነውጠኛ ትውልድ ይጠይቀው የነበረው ጥያቄ ዛሬ በእኛ ጀንበር እንደ አዲስ አቆጥቁጦ፣ በመርዝ ተለውሶና ሕዝብ እንዳይረጋጋ ተወጥኖ ምላሽ ማግኘቱ እጅግም የተስተዋለ አይመስልም። ምክንያቱ ደግሞ “የትግል ውጤት” ያስገኘው ፍሬ ሳይሆን ዘመነ ግሎባላይዜሽን “በበረከተ መርገምትነት” አነሆአችሁ ብሎ ነዶውን በማስታቀፉ ነው።
ያዳቆነው የትናንቱ የወጣቶች ትግል ዛሬ ለቅስና በቅቶ የኅሊናችንን ሩሕ ስለምን ሊያስተን እንደበቃ ቆም ብለን ማሰብ ካልቻልን በስተቀር ዛሬያችንም ሆነ ለትውልድ የምናስረክበው የነገ ጀንበር ጤነኛ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ዘብት ነው። ይህንን የጠነነና የመረረ ስጋት የምናብራራው በአንዳንድ ወቅታዊ ማሳያዎች እያዋዛን ነው።
ሀ. ገደብ አልባ “ዲሞክራሲን” እንደ ትሩፋት ተቀብለው ሃይማኖት ጠቀስ እንካ ሰላንትያዎችን በማወናጨፍ መቆራቆዝ ከተለመደ ውሎ አድሯል። ስመ እግዚሃርን የሚጠሩ “አገልጋይ ነን” ባይ የሃይማኖት አስተማሪዎችና ሰባኪያን ሰሞኑን እየተወራወሩት ያለው ጠብ ቀስቃሽ ትምህርት፣ አስተያየቶችና ፉከራዎች እንደ ሀገር የት አድርሰው ምን ላይ እንደሚያሳርፉን ለመገመት እያስቸገረን ነው።
በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያው ቅጥር ውስጥ ምሽግ ይዘው የሚያስወነጭፏቸው የአተካራ ጠጠሮች ወደ ቋጥኝ ደረጃ ከማደጋቸውና ሀገራዊ አደጋ ከማስከተላቸው አስቀድሞ በአግባቡ ቢታረሙ የሚበጅ ይመስለናል። ያለበለዚያ “ማን ከማን ያንሳል” በሚል የትዕቢትና የትምክህት ግንፍልተኛ ስሜት መናቆሩና “ይዋጣልን” እያሉ መፎከሩ ለማንም የሚበጅ አይሆንም።
“የመስቀል ጦረኞች” ታሪክ የሚያስታውስ ሃይማኖተኛና የሃይማኖት አስተማሪ “የመጣው ይምጣ” ብሎ ለመፎከር ከቶውንም አይሽቀዳደምም። በተለይም ጦርነት ያጠለሸውን ሁለንተናችንን በሰላምና በንግግር ለማደስ ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወቅት ይህ “ውርድ እንውረድ” እየተባለ የሚፎከርበት “የሃይማኖት አስተማሪዎችና የእምነት ዋነኛ ጠበቆች ነን” ባዮች መጎሻሸም በአግባቡ ሊታይ ይገባ ይመስለናል። አንድም በምድራዊ ሕግ፣ አንድም በየሃይማኖቶቹ ቀኖናና ሥርዓት መሰረት።
ለ. “ዲሞክራሲ ያለ ገደብ!” የሚለውን የትናንቱን ያረጀ መፈክር እንደ አዲስ ግኝት በማቀንቀን በሠፈሬ አትለፍ፣ በቄዬ እንዳትገኝ፣ ወደ ክልሌ ድርሽ እንዳትል፣ የኖርከውም ያለ አግባብ ነው፣ ለወደፊቱም አብረን ልንኖር አንችልም ወዘተ. እየተባለ የዜጎች ሕይወትና ኑሮ ተመሳቅሎ የደም ዋጋ ጭምር እንዲከፈልበት መደረጉ የኋላ ቀርነት በሽታ ምን ያህል የከፋ ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ይህ ሁሉ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰው መከራና ግፍ “የዲሞክራሲ” ፍሬ እንደሆነ ታስቦ ከሆነ እብሪት ያፈራው ጅልነት ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል። ዲሞክራሲ እየተባለ የሚፎከርለት ፍልስፍና ውጤቱ ይህ ከሆነ ከቶውንስ የታሪክ ሾተላይ፣ የበጎነት ፀር ከመሆን የዘለለ ምን ፋይዳ ይኖረዋል። ደግሞስ ያ “ጎፈሪያሙ የሃምሳዎቹና የስልሳዎቹ ትውልድ” እርስ በእርሱ ይፋጅባቸው ከነበሩት “ፖለቲካዊ ስካሮች” በምን ሊለይ ይችላል።
ሐ. መሪዎች እንደማንም ሰው ይስታሉ ሊያሳስቱም ይችላሉ። የሃይማኖት አባቶችም እንደዚሁ “የአዳማዊ ዘር ውጤቶች ስለሆኑ” ፍጹማን ሊሆኑ አይችሉም። እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ በአግባቡ ከማረምና ከመውቀስ ይልቅ በማሕበራዊ የትሥሥር መድረኮች የሚጻፈውና የሚነገረው ኅሊና አለው ከሚባለው የሰው ፍጡር ቀርቶ የአእምሮ ጤንነቱ ከተቃወሰ አንድ ህመምተኛ ዜጋ እንኳን የሚጠበቅ አይደለም። ስድብ፣ ማንቋሸሽ፣ ማዋረድ፣ መዝለፍ፣ በማንነት ላይ መሳለቅ የሚያስንቀው ራስን ጭምር መሆኑ መዘንጋቱ እንደሚባለው “ያለ ገደብ” በሚል ግራ መጋባት ትናንት የተጮኸለት “ዲሞክራሲ” ያዥጎደጎደልን መርገም ሳይሆን ይቀራል?
መ. በብዙ ሀገሮች እንደሚስተዋለው ሕዝብን የሚያስተዳድር አንድ ሹመኛ የሥልጣኑ ከፍታና ዝቅታ ምንም ይሁን ምን የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት ከተሳነውና ግዴታውን ቸል ማለቱን ካመነ ያለ ምንም መሸፋፈን ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ በሚዲያ ፊት ቆሞ ድካምን መናዘዝ የተለመደ ነው። አልፎም ተርፎ “ይመጥናል ተብዬ ለተሾምኩበት ኃላፊነት የተቻለኝን ጥረት ባደርግም ውጤት ላስገኝ ስላልቻልኩ ኃላፊነቴን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ” ማለት ነውር ተደርጎ አይቆጠርም፤ የጀግንነት ተግባር እንደሆነም ይታመናል።
የእኛ ሀገሩ “ገደብ የለሽ የዲሞክራሲ ፈለግ” ግን ደካማውም በድካሙ እንዲቀጥል፣ ሰነፉም ስንፍናውን “በምንትስ አባልነት ስም ለብጦ እንዲጓዝ” የተመቻቸለት እስኪመስል ድረስ “እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ!” ማለት የባህል ያህል ሥር የሰደደ እስከ መሆን ተደርሷል። ይህ ጉዳይ አንዱ “የገደብ አልባ ዲሞክራሲያችን” ምኞት የተፈጸመበት አካሄድ ይሆንን?
“ስመ መልካም ግብረ ምንትስ” የሆነውን የጥንታዊ ግሪካዊያኑን “ዲሞክራሲ” ያህል ዓለማችንን ወርሮ ያስገበረ ሌላ ፍልስፍና ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ያዳግታል። ይህንን ሃሳብ በተመለከተ ከአሁን ቀደም በተብራራ መልኩ “ኦ! ዲሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” በሚል ርዕስ እንደቆዘምኩ ይታወስ ይመስለኛል።
ከአቴናዊያን የኮረጁትን ዲሞክራሲ እንደራሳቸው ግኝት ቆጥረው የፍልስፍናው ቁንጮ ነን በሚሉት ሀገራት ሳይቀር የሚፈጸሙ እኩይ ድርጊቶችን በነጋ በጠባ እያስተዋልን “በሆቸ ጉድ” ግርምት ማለፋችን የተለመደ ሆኗል። የእኛ ሀገር ዲሞክራሲ ደግሞ እምባም ደምም እያስከፈለ ስላንገሸገሸን ለጊዜው ስሜታችንን በአግባቡ ለመግለጽ መረጋጋት አልቻልንም። ለጊዜ ጊዜ ሰጥተን በትእግሥት መሰንበቱ የሚሻል ስለመሰለንም በሀዘን እየቆዘምንም ቢሆን ቤትኛ ማድረጋችን አልቀረም።
ቀደም ሲል በጅምላ ካስታወስናቸው “የሃምሳና ስልሳዎቹ የሻምላ ተፋላሚ አብዮተኛ” የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ገሞራው በሚል የብዕር ስሙ የሚታወቀው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ አንዱ ነበር። ገሞራው “በረከተ መርገም” የሚል ርዕስ በሰጠውና በ1959 ዓ.ም በኮሌጅ ቀን በዓል ላይ ባቀረበው ዘለግ ያለ ግጥሙ ውስጥ ከተራቀቀባቸው ዝንጉርጉር የሃሳብ ሙግቶች መካከል አንዱ “በሥልጣን” ላይ የተሳለቀበት አተያይ በእጅጉ የዚህን አምደኛ ቀልብ ማርኮታል። እንዲህ ይነበባል፡-
“በሰበብ አስባቡ ራስን ለመጥቀም፣
ንብረት ለማደርጀት እያጋነኑ ስም፣
በሕግ አመካኝቶ እየተወጡ ቂም፣
ደግሞም ለመፈንጠዝ በማዕዘነ ዓለም፣
ጭቆና ባርነት፣ አድልዎና አመጽ፣ እንዲስፋፋ በጣም፣
እንዲሆን ከሆነ አስበው መርምረው ሥልጣንን የሠሩት፣
ደግሞም አስተዳደር ሕግም ሆነ መንግሥት፣
እነዚያ ጅጁዎች፣ የዋሆቹ ፍጥረት፣
ፕሌቶ አርስቶትል፣ ሁላቸው ሊቃውንት፣
ይህን ግብዝ ሃሳብ፣ ከግብ ሳያደርሱት፣
በሥራ ላይ ሳይውል ገና ሲወጥኑት፣
ይሻላቸው ነበር፣ አፎቿን ከፋፍታ ብትውጣቸው መሬት። ”
የግማሽ ክፍለ ዘመን ዕድሜ የተቆጠረለት የኢትዮጵያ የቀድሞ ተማሪዎች “ዲሞክራሲ ያለ ገደብi?” መፈክር ነፍስ ዘርቶ በዚህ በእኛ ዘመን እንደምን በአኗኗራችን ላይ መከራ እንደጫነብን በጥቂት መሳያዎች ለማመላከት ተሞክሯል።
አንዳንዶች “ዲሞክራሲ በራሱ ችግር የለውም፤ በአተገባበር እንጂ” ብለው መከራከራቸው የተለመደ ነው። ከባህል አፋትቶ፣ ኅሊናን አስቶ፣ ሰብእናን አራክሶ፣ ለሰላም ዋጋ ነስቶ፣ አብሮነትን የሚንድና ከሰላም ትሩፋት ይልቅ እኔን አስቀድሙ የሚል “የጃጀ ዲሞክራሲ” ስሙም ሆነ ግብሩ ከምድራችን ላይ እንዲጠፋ እንደ ገጣሚው ገሞራው ይህ ጸሐፊ የእርግማን ጥበብ ባይካንም በብዕሩ ብርታት ሃሳቡን በድፍረት ለመሞገት ግን አይሰንፍም።
ማጠቃለያችን፡- ግሪኮች ካወረሱንና “ያለ ገደብ” ሲጠየቅ ከነበረው የዲሞክራሲ ፍልስፍና ይልቅ ሕዝቦችን አከባብሮ የሚያኖረው ተፈጥሯዊ ፍቅርና ሰላም በእጅጉ ይበልጣል። የደም ግብር እንዲከፈልበት ከሚወተውት “የዲሞክራሲ ምላስ ይልቅ” ዝምታን መርጦ ሰላምን የሚያስቀድም አንደበት በአያሌው ያስከብራል። “የአሸናፊነትህን ክብር አሳልፈህ አትስጥ!” ከሚል የዲሞክራሲ ሕግ ይልቅ “በመሸነፍ አሸንፍ” የሚል የብልሆች ምክር ዋጋው ከዕንቁ ይልቅ የከበረ ነው። ሀገሬ ሆይ የመረጥሽው የሰላም ጎዳና የጥበብም የጸሎትም ውጤት ስለሆነ አክብረንሻል። ለተግባራዊነቱም ዜጎችሽ በሙሉ ልብ እንደግፍሻለን። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015