ምንም እንኳን ሙስና እንደሚፈጸምበት ሁኔታ የተለያዩ ብያኔዎች ቢሰጡትም ፤ ስለሙስና ትርጉም የሰጡ ምሁራን ሙስና ማለት በግል ወይም በቡድን፣ በመሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ሥልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለግል ጥቅም የማዋል ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊት ነው ሲሉ ይገልጹታል።
በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ማጭበርበር መፈፀም፤ ሕግና ሥርዓትን በመጣስ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት አድልዎ መፈፀም፣ ፍትሕን ማጓደል እና ሥልጣንና ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ሕገወጥ ጥቅም ማግኛ እንደሆነም ብዙዎች ይስማሙበታል።
ኢትዮጵያ በሙስና ከተጎዱ ሀገሮች አንዷ ነች። ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ይፋ እንዳደረገውም እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2009፣ ባሉት ዓመታት 11.7 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት የቀረበ አንድ ጥናት ደግሞ በኢትዮጵያ ብልሹ አሠራር፣ ሙስናና ምዝበራ ባይኖሩ ኖሮ አገሪቱ በምን ደረጃ ልታድግ እንደምትችል ይጠቅሳል። በኢትዮጵያ ሙስና ባይኖር ኖሮ ያስቀመጠቻቸውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ቀድማ የማሳካት አቅም የነበራት ሀገር እንደነበረች ጥናቱ አሳይቷል።
በተለይም የቀድሞ የኢህአዴግ ስርዓት ሙስናን አንዱ የስርዓቱ ማስቀጠያ አድርጎ መጠቀሙ በሀገሪቱ ትላልቅ ሙስናዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል። የቀድሞ ስርዓት ሜቴክን የመሳሰሉ ተቋማትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም የስርዓቱ ባልደረቦች ሀገሪቱን ሲበዘብዙ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። በዚህም ምክንያት የህዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱና በሂደትም ከስመው እንዲቀሩ የማድረግ ትልም ነበራቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የተመዘበረውና እርቃኑን የቀረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አንዱ ማሳያ ነው።
በአጠቃላይ ሙስና የሀገር ጠንቅ ነው። ትውልድን ገዳይና ለበርካታ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መንስኤ በመሆን ሀገርን እስከ ማፍረስ አቅም ያለው እኩይ ተግባር ነው። በኢትዮጵያም እየታየ ያለው ሁኔታም ከዚህ ብዙ የዘለለ አይደለም። በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ካሉ በርካታ የፀጥታ ችግሮች ጀርባ ሙስና አለ። የገንዘብ ዝውውር፣ እንዲሁም ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው ሕገወጥ እንቅስቃሴ፣ አገሪቱን ለማያባራ ግጭት እየዳረጋትና በከባዱ እየፈተናት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳሉት ሙስና ሳይሠሩ የሚበሉ ብቻ ሳይሆን የሚሠራን የሚበሉ ክፉ ሰዎችን ፈጥሯል። የገጠመውን ሃገራዊ ችግር እንደ ዕድል ተጠቅመው “ቀይ መስመር የተባለውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል” ያሉትም ሙስና ምንያህል አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው።
በተለይም ከፖለቲካ ንግድ ማትረፍ የሚፈልጉ አካላት ሙስና ዋናው የገቢ ምንጫቸው ነው። የፖለቲካ ነጋዴዎች የብሄር፤ የሃይማኖትና የሰፈር ግጭቶችን በመቆስቆስና በማቀጣጠል ባልተረጋጋ ሁኔታ የውስጥ ጥቅማቸው እንዳይነጥፍ ይሰራሉ። ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም በየትምህርት ቤቶቹ የደረሱ ግጭቶች፣ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የተሞከሩ አለመረጋጋቶችና ሌሎችም የፀጥታ ቀውሶች የእነዚሁ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሴራ መሆኑንም መንግስት በተደጋጋሚ ሲጠቅስ ቆይቷል።
ሙስና በእንጭጩ ካልተገታ ብሄራዊ ስጋት ስለሚሆን መንግሥትም ለችግሩ እልባት ለመስጠት የፀረ- ሙስና ዘመቻ ከፍቷል። ለዚሁ ዘመቻ ስኬትም የፀረ- ሙስና ብሔራዊ ኮሜቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይሄው ኮሚቴ መቋቋሙን ተከትሎም ጥቂት የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚህም በሙስና የተማረረው ኅብረተሰብ በመንግስት ላይ ተስፋ ሰንቋል፤ በቀጣይም በተጨባጭ ርምጃ ተወስዶ ይፋ እንደሚደረግም ይጠበቃል።
ሆኖም መንግስት በሙሰኞች ላይ የሚወስደው እርምጃ ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል። ሙስና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቂቶችን ተጠቃሚ፤ ሰፊውን ሕዝብ ደግሞ ለጉስቁልና የሚዳርግ፣ የልማት ሥራዎችን የሚያደናቅፍ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚጎዳ፣ ፍትሕን የሚያዛባ፣ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት እንዲቀንስ የሚያደርግ ወንጀል በመሆኑ የተጀመረውን የጸረ ሙስና እንቅስቃሴ በተጀመረው ግለት ማስኬድ ይገባል ::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26 ቀን 2015 ዓ.ም