የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት በፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ካደረጉ ታህሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ሁለት ወር ሞላው። በሁለት ወራት ውስጥ የሰላም ስምምነቱን ለማፅናት የተለያዩ ተግባሮች ሲከናወኑ ከመቆየታቸውም በላይ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በአቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት የልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ መሄዱ መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
መንግስት የሰላም ስምምነቱ መሬት እንዲረግጥ ባሳየው ቁርጠኝነት ዙሪያ ያነጋገርናቸው ፖለቲከኛና የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (የኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መንግስት ለሰላሙ መፅናት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚያስመሰግነው መሆኑን ይናገራሉ።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ መንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ በክልሉ የተነሱ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራሉ። ጦርነቱ ከመጀመሩም በፊት ሆነ ከተጀመረ በኋላ ሽማግሌ በመላክ፤ የተለያዩ አለም አቀፋዊ የማህበረሰብ ተቋማትን በማሰማራት፤ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አባላት፣ታዋቂ ሰዎች ጭምር ሽምግልና በመላክ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን ፤ ከዛኛው ወገን ተቀባይነት ያላገኘበት ሁኔታ እንደነበረ አስታውሰዋል። በጦርነቱ ህይወት ከጠፋና ንብረት ከወደመ በኋላም ቢሆን ለሰላም እጅ መዘርጋት መቻሉ መልካም መሆኑን በመጥቀስ ለህዝብ የሚጠቅም ነገር መደረጉ የመንግስትን የሰላም ፍላጎት የሚያሳይ ነው ይላሉ።
ከሁለት አመታት በኋላ የአፍሪካ ህብረት ጥሪን በመቀበል ወደ ፕሪቶሪያ በመሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የሚበጅ፤ የሀገርን ሉአላዊነት ፈር የሚያስይዝና ለሁሉም እፎይታ የሚሆን ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የሰላም ስምምነት በተለይም ለትግራይ ህዝብ ታላቅ እፎይታን የፈጠረ ሲሆን፤ ሁሉም አካላት ያሳዩት የሰላም ስምምነቱ መሬት ላይ ወርዶ የሚተገበር ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ተስፋ መኖሩን ነው።
ዶክተር አረጋዊ፤ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ መቀሌ ማቅናት የሁለት ወገኖች ስምምነት በተግባር እየዋለ ነው አይደልም? የሚለውን በቅርበት ለመከታተልና ለማወቅ ያስችላል ይላሉ። በሰላም ስምምነት ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬ ሳይኖር በፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት ማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም ጉዳዮች ላይ የሚታየው ሂደት ምን እንደሚመስል፤ የጎደሉና ያልተስተካከሉ ጉዳዮች ካሉ እሱን ለማቅናት መሄዳቸው ተገቢና የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነው። የትግራይ ህዝብ ለሁለት አመታት፤ ወጣቱ ከትምህርት ገበታው ርቆ ቆይቷል፤ ነዋሪው ያለስራ በስጋት እየኖረ፤ ሁሉም አይነት አገልግሎቶች በተቋረጡበት በጨለማ እየዳከረ የእውር ድንብር መኖራቸው አብቅቶ ወደ ሰላም መገባቱ ታላቅ እመረታ ነው። ይህ ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ የተገኘን ወርቃማ ሰላም ደግሞ መንከባከብ ግድ ነው ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው፤ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ መቀሌ ማቅናት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት አበረታች ደረጃ ላይ መሆኑንና መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያመላክታል ይላሉ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በአቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ መሄዱ ልዩ ደስታን የፈጠረ ሲሆን የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ ማቅናት ሰላምን ከማብሰር በዘለለ በወረቀት ላይ የሰፈረው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነቱ ወደ መሬት መውረዱን፣ ለትግራይ ሕዝብ የሚደረገው ሰብዓዊ እርዳታ ከሪፖርት ባሻገር በተጨባጭ ምን እንደሚመስል እና የመሰረተ ልማቶችን ግንባታ መገምገም እንደሚጨምር ተናግረዋል።
ያለፉት ሁለት አመታት የፈተናና የሩጫ ጊዜ የነበር መሆኑን ያስታወሱት ኡስታዝ ካሚል፤ በተሰራው ዲፕሎማሲያዊ ስራ ችግሮች እየተፈቱ ወደ መደበኛ አሰራር መመለስ እየተቻለ ነው ብለዋል።
ጦርነቱ በተለይ ለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ያም ሆኖ በህዝቡ፣ በሰላም አስከባሪ ሀይሎችና ዲፕሎማቶች እልህ አስጨራሽና የተባበረ አንድነትና ጥረት ፈተናዎች መፈታታቸውን ገልጸዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው አለመግባባት በስምምነት እልባት ማግኘቱ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ኃይል በንግግር ካልሆነ በቀር በጦርነት ማሸነፍ እንደማይችል እንዲሁም ሌሎችም ወደ ሰላም እንዲመጡ መንገድ ያሳየ ክስተት መሆኑን ይናገራሉ። በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የሰላም ስምምነት በር ከፋችና መላውን ሰላም ወዳድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደሰተ እንደመሆኑ የአሁኑ የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ መጓዝም ለመላ ኢትዮጵያውያንና ለውጭ ኃይሎች ትልቅ ትርጉም ያነገበ ነው ብለዋል።
በተለያዩ አገራት የሰላም ስምምነት ተደርጎ ግማሹ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ተግባራዊ የተደረገ፣ ግማሹ ደግሞ ያልተሳካበት ሁኔታ በመኖሩ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ አለበት ፤ ከዚህ አንጻር ግለሰቦችና ሚዲያዎች የነበረውን ቁስል ከሚያስታውሱና ጠላትነትን ከሚያባብሱ ነገሮች መቆጠብ አለባቸው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (የኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበከሉላቸው፤ መንግስት ሰላሙን ለማፅናት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የሚደገፍና ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ። መላው የሀገሪቱ ህዝቦች የሚፈለጉት ሰላም ነው። ሰላምን ደግሞ ካልተንከባከቡትና የሚያስቀጥልን ነገር ካልሰሩ ሰላም ሊመጣ አይችልም። ይህንን ደግሞ መንግስት በመረዳት ሰላምን ላለማደናቀፍና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ ሰላማዊው ህዝብን ያካተተ የሰላም እንቅስቃሴ መደረጉ ታላቅ ደስታን እንደሚፈጥር ይናገራሉ።
የመንግስት የልዑካን ቡድኑ የመቀሌ ጉዞ ለሰላም ቅድሚያ የሰጠ በፍፁም የሰላማዊነት መንፈስ በህዝብና ህዝብ መካከል ፈርሶ የቆየውን የግንኙንት ድልድይ የጠገነ በመሆኑ ታላቅ ስኬት ነው ።
ማንኛውም አካል ከሰላም ለመሸሽ የሚደረድረው ምክንያት እንዳይኖር ቀጥተኛና ቀና መንገዶችን በመምረጥ ክፍተትን መድፈን ያሻል የሚሉት ፕሮፌሰሩ የህዝቡ ኑሮ መኖር ወደ ሚገባው ሰላማዊ ሁኔታ ለመቀየር መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነትም እጅግ ታላቅ ተግባር ነው ብለዋል።
በህገ መንግስቱ መሰረት ሁሉም የፌደራል መንግስቱ አካላት የሆኑ ክልሎች በሙሉ በፌደራል መንግስቱ መተዳደር አለባቸው የሚለውን ሀሳብም ለማስቀጠል ይህን የሚያረጋግጥ ስራ እየተሰራ ነው። ህዝቡ ጦርነት ሰልችቶት ሰላም በሚሻበት ጊዜ ላይ መደረሱም ለህዝቡ የሚገባውን ሰላም ለመስጠት ምቹ መደላድልን ይፈጥራል።
ለቀጣይ መፍትሄ ነው ያሉትን ሀሳብ ፕሮፌሰር በየነ ሲያስቀምጡ ትናንት በስህተት ብዙና ያለተገባ ዋጋ ከፍለናል፤ ከጦርነት ይልቅ የሰላሙን መፍትሄ እስከ ጥግ ድረስ የሚታይበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል።
ጥያቄ ያላቸውም አካላት በሰላማዊ መልኩ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡ፤ መሪው አካልም እነዚህ ባለጥያቄ አካላት የሚያቀርቡት ጥያቄ ከህገ መንግስት አንፃር ምን ፍሬ አለው ብሎ በመቃኘት የሚያቀራርቡ ሀሳቦች ላይ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው ይላሉ።
አሁንም ወደ ሰላም ስምምነቱ ሲገባ የተለያዩ ጉዳዮች በሂደት ሊፈቱ በይደር ተከድኖ የተቀመጠና ቅድሚያ ለሰው ህልውና መስጠት ያለውን አማራጭ አይተው ቀሪ የቤት ሥራዎችን በሂደት ከመደርደሪያ ላይ በማንሳት ለመፍትሄ ትኩረት የሚሰጥበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ ወደ ሰላም ተገብቷል። አሁንም ግን ዳግም ስህተት ውስጥ ላለመግባት በሰከነ አእምሮ ማሰብ ለሁሉም ሰላማዊ ግንኙነት ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ፤በቀጣይ የትግራይ ህዝብ ከጎረቤቶቹ አፋርና አማራ ህዝብ ጋር ቀደም ሲል የነበረውን የሰላም፤ የልማት ሁኔታ ከፍ አድርጎ ማስቀጠል ላይ ትልቅ የቤት ስራ ይቀራል ። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ላይ ቀጣይነት ያለውን ስራ መስራት የሚያስፈልገው። ከስር መሰረቱ በጥንቃቄ ተይዞ ለስኬት የሚበቃ የቤት ስራ፤ ሰላሙን በደንብ ለማጥበቅ መከናወን ያለበት ተግባር ነው ይላሉ።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጦርነቱ ድባብ ሞት፣ ስደት እና አካል መጉደልን ብቻ ነው ያተረፈው። በተለይ የጦርነቱ ቀጠና አካባቢ የነበረው ህብረተሰብ ወደ ሰላም መምጣቱና አሁንም የተገኘውን ሰላም መንከባከብ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ። ሰላሙንም ለማስቀጠል ሁሉም ማህበረሰብም ሆነ የመንግሰት አካላት እልህ እና ቂም በቀልን ወደ ጎን በመተው የሚያቀራርብ መልካም እሴት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አብራርተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚያደርገውን ተመሳሳይ የጦርነት ቀጠና በነበሩት አማራ ፣ አፋር አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያደርስበት አና የወደሙትንም መሰረተ ልማቶች መልሶ የሚገነባበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል ብለዋል። ለአማራና ለአፋር ክልሎችም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ኡስታዝ ካሚል ድጋፉን በአፋጣኝ እውን ለማድረግ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት ከሚደረገው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ ክልሎችን በማስተባበር ያሉንን የውስጥ አቅሞች ለመጠቀም መጣር ወሳኝ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
እንደ ኡስታዝ ካሚል ማብራሪያ፤ አንዳንድ የዓለም መንግሥታት እርዳታ ለመስጠት የሚያስቀምጡት ቅደመ ሁኔታ ተገቢ አይደለም። አሁን ላይ ከሁሉም የሚቀድመው ለተራበው ምግብ፣ ለተጠማው ውሃ፣ ለታመመው መድኃኒት፣ ጨለማ ውስጥ ላለው ደግሞ ብርሃን ማቅረብ ነው። አሁን የተጀመረው ግንኙነት ወደ ሕዝብ ወርዶ የነበረውን ወንድማዊ ፍቅርም ወደ ቦታው መመለስ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ቀድሞም በወንድማማችነት ተከባብሮ የሚኖረው ህብረተሰብ በቅድሚያ ሰብአዊነትን አስቀድሞ ህይወት የማትረፍ ተግባር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት ኡስታዝ ካሚል ፤ ከዚህ በመቀጠል የፈረሰውን የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት ድልድይን ጠግኖ በመቻቻልና በመከባበር ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ለዘላቂ ሰላም መፍትሄ መሆኑን ያስረዳሉ ።
እንደአስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ፤የሰላም ስምምነቱ መሬት እንዲረግጥ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ያለው ስራ ማሳያ ነው። በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በቅድሚያ ሰብአዊ ድጋፍ ያለገደብ እንዲገባ፣ መሰረተ ልማቶች ስራ እንዲጀምሩ የተደረገበት ፈጣን እንቅስቃሴ እንዲሁም
ካለ ሶስተኛ ወገን የፌደራል መንግስት የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ ማቅናት የሰላም ስምምነቱ ወደ መሬት እየወረደ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በአጠቃላይ የመንግስት ሰላም ወዳድነት የተገለፀበት ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015