የሰሜን ዕዝ ጥቃትን ተከትሎ ጥቅምት 24 ቀን 2103 የኢትዮጵያ መንግስትና ህውሓት የለየለት ጦርነት ውስጥ ገቡ። በሁለት አመታት ውስጥም ለሶስት ጊዜያት ያህል ተከታታይ ጦርነቶች ተካሂደው የበርካታ ሰው ህይወት ተቀጥፏል፤መጠነ ሰፊ ንብረትም ወድሟል። በአጠቃላይ በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ክፉኛ ተጎድታለች። በትግራይ፤አማራና አፋር የደረሰውም ከሁሉም የከፋ ነው።
ኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ ያላቸውና ጠላቶቻቸውንም አሳፍረው የመመለስ አኩሪ ታሪክ ቢኖራቸውም የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነትን በሰላማዊ መልኩ የመፍታት ጉልህ ታሪክ አልነበራቸውም። ይልቁንም ሁሉንም ነገር በሃይል የመፍታት ዝንባሌ በአመዛኙ ይታይባቸዋል።
እንደ ህዝብ ሁሉንም ነገር በነፍጥ ብቻ እንፈታለን የሚል ዘመናትን የተሻገረ አስተሳሰብ ስናራምድ ቆይተናል። በጦርነት አንዱ ድል አድራጊ ሌላው ድል ተደራጊ፤አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እስካልሆነ ድረስ ጥማችንን አንቆርጥም። የፈለገውን ያህል የሰው ህይወት ቢጠፋ፤ንብረት ቢወድም፤ዜጎች ቢራቡ ፤ቢሰደዱና ቢፈናቀሉ ጦርነት በአንዱ ድል አድራጊነት አስካልተደመደመ ድረስ ማባርያ የለውም።
ሁሉም በየፊናው ግፋ በለው በማለት ማባርያ ወደ ሌለው ዕልቅት መጓዝና በመጨረሻም መቆርቆዝ ለዘመናት ስንመላለስበት የቆየነው ጎዳና ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው። ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተ ልማድ ነው። በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው የጋራ ችግሮችን ለመፍታት ከሚጥሩ ይልቅ የሃይል አማራጭን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው ኖረዋል ።
በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ኃይልና ጉልበት እንደ መፍትሄ በመወሰዱ ምክንያት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የሴረኝነት መነሻ ይሆናሉ። መደማመጥ በሌለበት መተማመን ስለማይኖር የአገር ችግሮች የመፍትሔ ያለህ እያሉ ዓመታት ይነጉዳሉ። መነጋገርና መወያየት በሌለበት ድግሞ መጨረሻው ጦርነት ነው። ጦርነት ድጎ አውዳሚና ለየትኛውም ወገን ውድቀትን የሚያስከትል ነው።
የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ግን ይህንን የታሪክ ሰባራ ጠግነውታል። ለሁለት አመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በውይይት ለመፍታት በመወሰናቸው አዲስ ምዕራፍ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ታሪክ ጽፈዋል። አስራ ሁለት አንቀጽ ያለው የሰላም ስምነምነት በማውጣት ሰላምን አውጀዋል።
በፕሪቶርያ የተካሄደው ስምምነት ለዘመናት መፍትሄን በጠብመንጃ ለማምጣት ሲኬድበት የነበረውን ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሰበረና ስልጡን የሆነ አካሄድን ለሀገራችን ያስተዋወቀ ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሰረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤የአማራና የአፋር ህዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው። በፕሪቶርያው ስምምነትና እሱን ተከትሎ በናይሮቢ በተካሄደው የማስፈጸሚያ ውል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከደረሰው ዕልቂት፣ ውድመትና ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት የሚያስችል ዕድል ተገኝቷል።
ከስምምነቱ በፊት የነበረውን የትግራይ ህዝብ ሁኔታ ብንመለከተው ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በቀላሉ እንድንረዳ ያስችለናል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የትግራይ ገጠሮችና ከተሞች በጦርነት መታመስ ጀመሩ። በርካታ ወጣቶችም መሳርያ ታጠቁ። በተለይም በከተሞች አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ጠፋ። ነዋሪዎችም የሰላም እጦት አንጃበባቸው ፤በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆነ። በተለይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የትግራይ ኃይሎች በድጋሚ መቀለ ሲገቡ “እነዚህን ሁሉ ታጣቂዎች እንዴት መቆጣጠር ይቻል ይሆን?” የሚል ስጋት በርካቶች ያነሱት ጉዳይ ነበር። በወቅቱ ክልሉ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከነትጥቃቸው የሚታዩ ወጣቶች የስጋቱ ምንጭ እንደነበሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በበርካታ የትግራይ ከተሞች በተለይ ደግሞ በመቀለ የሚታዩ የሌብነትና የዘረፋ ወንጀሎች በርካታዎችን ያስጨነቀ ጉዳይ ነበር። በከተማዋ ውስጥ ዘረፋና ለዘረፋ ሲባል አስከ ግድያ የሚደርሱ ወንጀሎች እየተፈፀሙ እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።ወጥቶ መግባት ብርቅ ነበር። የመንገድ ላይ ንጥቂያ፣ በሥራ ቦታ ስርቆት እንዲሁም ዘረፋ ያጋጥማል።
በየሰፈሩ የተቧደኑ ወጣቶች ‘አለው’ ብለው የጠረጠሩት ግን ምንም የሌለውን ሰው ሳይቀር አደጋ ያደርሱበታል” ።የተለያዩ ነገሮችን ከሰዎች እጅ ላይ ለመዝረፍ ሲባል ሕይወት የሚያጠፋበት ሁኔታ በከተማዋ ውስጥ የተለመደ ነበር። ሠራተኞች ያለ ደሞዝ ለሁለት አመታት ያህል ለመኖር ተገደዋል። ፣ ነጋዴዎች የሚሸጡት ሸቀጥ አጥተው ሱቆቻቸው ባዶ የሆነበትና የቀን ሠራተኞች ሥራ ፈትተው እርዳታ የሚጠብቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከታሪካዊው የፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ ግን ነገሮች ተለውጠዋል። የትግራይ፤የአማራና የአፋር ገጠሮችና ከተሞች ከጦር መሣሪያ ጩኸት ለመገላገል ችለዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እፎይ አለች። ከሰሞኑ ደግሞ በአፈ ጉባኤ ታደሰ ጫፎ የተመራ ልኡካን ቡድን መቀሌን መርገጡ ደግሞ በሰላም ስምምነቱ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ ወደ መተማመን እንዲሸጋገር አድርግጓል። የተቋረጡ መሰረተ ልማቶች ሰብአዊ ድጋፎችም በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረተ ልማቶችንና ሰብአዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ማድረስ ተችሏል። አስከአለፈው ዕሮብም 105ሺ910 ቶን ምግብ ነክ እና 8ሺ 624 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ወደ ትግራይ የተላከ ሲሆን ከ780 ሺ 755 ሊትር ነዳጅ ተጓጉዟል። በጥሬ ብር ደረጃም ከ800ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል።
በተጨማሪም የሰላም ስምነቱን ተከትሎ 80 የትግራይ ከተሞች የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል። መቀሌን ጨምሮ 27 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። ባንክን በተመለከተም ከ22 በላይ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን ስራ ለማስጀመር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከ18 ወራት በኋላ ወደ መቀሌ በረራ ጀምሯል።
ታህሳስ 19/ 2015 ዓ.ም ለመቀለ ነዋሪዎች የተለየች ነበረች።ለአስራ ስምንት ወራት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል።ደም አፋሳሹን ጦርነት ተከትሎ ትራንስፖርትም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎቶች በተቆረጡባት ትግራይ ክልል በረራ እንደገና ተጀምሯል። የበረራ አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እኩለ ቀን ላይ የተነሳው አውሮፕላን መቀለ ካረፈ በኋላም በተለያዩ ስሜቶች የተዋጡ መንገደኞች ታይተዋል።መንገደኞችም በመቀለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርሱም መሬቱን ሲሳለሙ፣ በርካቶች ሲላቀሱ፣ ሲተቃቀፉም ታይተዋል።ለአንድ ዓመት ተኩል ያላይዋቸውን ቤተሰቦች፣ ወዳጆች ዘመዶችም ጋር አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ሲላቀሱ ተስተውለዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሰላም አየር መንፈስ በመጀመሩ ዜጎች ወደ ተረጋጋ ህይወታቸው መመለሰ ጀምረዋል። መቀሌ ያሉት ወደ አዲስ አበባ ፤አዲስ አበባ ያሉት ወደ መቀሌ መንቀሳቀስና ለሁለት አመታት የናፈቋቸውን ዘመዶቻቸውን በማግኘት ላይ ናቸው። በትግራይ አሻቅቦ የነበረውም የሸቀጦች ዋጋ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መውረድ ጀምሯል። 18ሺ ደርሶ የነበረው የመቶ ኪሎ የጤፍ ዋጋ አሁን ወደ 5ሺ ብር ወርዷል። የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው።
ይህ ነው የሰላም ትሩፋት። ዜጎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ፤ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ፤እንዲማሩ፤ እንዲኩሉ፤እንዲድሩ ያስችላቸዋል። ሰላም ከግለሰብ አልፎ እንደ ሀገር ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ለጦርነት ይውል የነበረውን ኢኮኖሚ ይታደጋል፤ኢንቨሰትመንትና ቱሪዚምን ያበረታታል፤ዜጎች በሀገራቸው ላይ ተረጋግተው እንዲሰሩና ትርፋማ እንዲሆኑ ያስችላል፤ሀገር ከድህነት ወጥታ በብልጽግና ጎዳና እንድትጓዝ መንገድ ይጠርጋል።
ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሁለት አመታት የጦርነትን አስከፊነት በውሉ ተረድተውታል። ጦርነት ልዩነትን የሚያሰፋ፤ጠላትነትን የሚፈጥርና ጥላቻን የሚያነግስ ነው። ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ዜጎች በጦርነት ምክንያት የተሳሰሩበት ገመድ ሊላላ ብሎም ሊበጠስ ይችላል። የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ ምክንት ተፈጥሮ የቆየውን የሕዝቦች መራራቅ መልሶ ለመቀጠልና ኢትዮጵያዊነት ቦታውን እንዲይዝ ያደርጋል። የህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር መልሶ እንዲጠናከር በር ይከፍታል። በቀልና ቁርሾን ይሽራል። ጠላትን ያሳፈፍራል፤ወዳጅን ያኮራል።
ጦርነት የሀገርን ገጽታ ያበላሻል። የውጭ ጣልቃ ገብነትንም ያበረታታል። ስለዚህም ሰላም ውይይቱ መተግበር መጀመሩ ላለፉት ሁለት አመታት ጎድፎ ነበረውን የኢትዮጵያ ገጽታ መ ልሶ እንዲታደስ ያደርጋል። በዚህም ሸሽ ተው የቆዩ የውጭ ኢንቨስተሮች መልሰው ወደ ኢትዮጵያ እንዲያማትሩና ኢኮኖሚውም እንዲነቃቃ ያደርጋል። በሰላም ዕጦት ምክንያት ፊታቸውን አዙረው የነበሩ ቱሪስቶችም መልሰው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ዕድል ይሰጣል።
ሆኖም ሰላምን መጠበቅና መንከባከብ ካልተቻለ መልሶ በጦርነት አዙሪት ውስጥ የመግባት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ዘመናትን በጦርነት ውስጥ ለቆየ ሀገር ዘላቂ የሆነ የጦርነት ማስወገጃ ስልት መንደፍ ከመንግስት የሚበቅ ቢሆንም ዋነኛው የሰላሙ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የተገኘውን ሰላም ጠብቆ የማቆየት ግዴታ አለበት።
የኢትዮጵያ ህዝብ በየዘመናቱ በሚነሱ ጦርነቶችና ግጭቶች ሰለባ ሲሆን የቆየ በመሆኑ ከእንግዲህ ወዲህ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ባሻገር ጦርነት ጊዜው ያለፈበት አማራጭ መሆኑን መንገድ ማመላከት አለበት፤አሻፈርኝ የሚሉትንም አንቅሮ ሊተፋቸው ይገባል። በህዝብ ተቀባይነት የሌለው አካል ያለመውን እኩይ ሃሳብ ማስፈጸም አይችልምና የጦርነትና የግጭት እሳቤ ያላቸው አካላት ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር ስፍራ ሊኖራቸው አይገባም።
ኢትዮጵያ በርካታ የቤት ስራዎች ያሉባት ሀገር ነች። እነዚህ የቤት ስራዎች ሊሰሩ የሚችሉት ደግሞ ሰላም ሲኖር ነው። ስለዚህም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ፅኑ የሆነ የምግብ ችግር አለ። የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት ነው። የሥራ አጥነቱ መጠን በፍጥነት እያሻቀበ ነው። የአገሪቱ የዕዳ ጫና ከባድ ነው። ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ህዝብ የሚጠይቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ሕዝብ የሚፈልገው ሰላሙን በዘለቄታዊነት የሚያረጋግጥለት፣ ከድህነት አረንቋ ውስጥ የሚያወጣውና ነገን ብሩህ የሚያደርግለትን አካሄድ ነው። እናም በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ መጓዝ ጀምራለች።
ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሆና በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ትንግርታዊ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። ስንዴ ከራሷ አከልፎ ወደ ውጭ ለመላክ በመጨረሻው ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች። በአካባቢ ጥበቃ ረገድም በአራት አመታት ውስጥ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አለምን አስደምማለች። እነዚህ ስኬቶች ሌሎች ተጨማሪ ስኬቶችን እንዲወልዱ አሁን የተፈጠረውን አንጻረዊ ሰላም በዘላቂነት ማስጠበቅ ይገባል።
በፕሪቶርያ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ታሪካዊና ለኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም የማስፈን አቅም ያለው ነው። በጦርነት ውስጥ ለነበረው ህዝብም ትልቅ መድህን ይዞ ከመምጣቱም ባሻገር በታሪክም ተጽፎ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ይመስላል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በተሞክሮነት እንደሚቀርብ በአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ የተናገሩት ።
የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ከትናንትም ሆነ ከዛሬ ታሪካችን ከኛ በላይ ሊያውቅና ሊረዳ ይችላል ብሎ ማሰብ ከየዋህነት በላይ ሞኝነት ነው ፤ከዚሕ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት በሀገራችን የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም አስጠብቆ ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድረስ ሁላችንም መረባረብ ይጠበቅብናል ።ለዚህ ደግሞ የእለት ተእለት አእም ሯዊ እና መንፈሣዊ ዝግጁነት ያስፈልገናል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015