መንግሥት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ወደ ሰላም ውይይት ለመምጣት የደረሰበትን ውሳኔ ተከትሎ በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ መልኩን ከቀየረ ውሎ አድሯል። በተለይም በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት እና በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ድጋፍ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረሙ ሁኔታዎች በፍጥነት መልካቸውን እንዲቀይሩ እያደረገ ነው።
የሰላም ስምምነቱ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን የኢትዮጵን የግዛት አንድነት እና ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገና በዚሁ እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ በተለይም መንግሥት እንደ መንግሥት የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ እድል ፈጥሮለታል። አገርን ከተጨማሪ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መታደግ አስችሏል። ጦርነቱ በአካባቢው ፈጥሮት የነበረውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ለማቃለል ረድቷል።
በተለይም መንግሥት ባለው አቅም ሌሎች የርዳታ ተቋማትን በማስተባበር ለትግራይ ሕዝብ የዕለት ደራሽ የምግብ እህል አቅርቦቶች ያለ ገደብ በስፋት እንዲቀርብ ያሳየው ቁርጠኝነት ፤ ጦርነቱን ተከትሎ ሊፈጠሩ ይችሉ የነበሩ ከዕለት ምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በአስተማማኝ ሁኔታ መቋቋም አስችሏል።
ከመድሃኒትም ጋር በተያያዘም ሕዝብ በተለይም አስቸኳይ የሆኑ መድሃኒቶችን ፈጥኖ እንዲያገኝ ቀደም ባለው ጊዜ በቂ ዝግጅቶችን አድርጎ እየተገበረ ያለበት መንገድ ፤ አጠቃላይ ከሆነው ሀገራዊ አቅም አንጻር የሚበረታታ፤ ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው። በቀጣይ ለሚያደርገውም ተጨማሪ ጥረትም የረድኤት ድርጅቶችን ድጋፍ የሚሻ ነው።
ከዛም ባለፈ በሰላም ስምምነቱ ያልተካተቱ ነገር ግን ስምምነቱን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ የተሻለ አቅም መፍጠር ያስቻሉ ፤ በእርግጥም በአደባባይ አቅም ሆነው የተገኙ ፤ የመንግሥት የልዑካን ቡድን በመቀሌ ያደረጉት አይነት ጉብኝት፤ የመንግሥትን የሰላም ቁርጠኝነት ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ በተግባር ማሳየት ያስቻለ ነው። ለሰላም የቱንም ዋጋ ለመክፈል ያለውን ዝግጁነት ያመላከተ ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና ጭምር ያገኘው የመንግሥት የሰላም ቁርጠኝነት በሕወሓትም ሆነ በመላው ሕዝባችን ተገቢውን ትርጉምና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ከመንግሥት የሰላም ቁርጠኝነት በስተጀርባ ስላለው የበለጸገች ሀገር ግንባታ እያንዳንዱ ዜጋ ሊያስብና፤ ሊያሰላስል ተገቢ ነው። ከሰላም ውጪ ይህንን ራዕይ እውን ማድረግ እንደማይቻል ግንዛቤ ሊወሰድበትም ያስፈልጋል።
አሁን ባለው አገራዊ የፖለቲካ አውድ ፣ ብሄራዊ ጉዳያችን ከአሸናፊና ከተሸናፊ ትርክት ያለፈ ፤ ሀገርን አሸናፊ የሚያደርግ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠርን መሰረት ያደረገ ነው፤ መንግሥትን እንደ አንድ የለውጥ መንግሥት ቀደም ባለው ጊዜም ሆነ አሁንም ስለ ሰላም እየከፈለ ያለው ዋጋ ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ይህ ከዚህ ትውልድ ባለፈ ለመጪው ትውልድ የተሻለች /የበለጸገች አገር የመመስረት ራእይ ፤ ከመጣንበት ረጅም የታሪክ ምእራፍ እና በምእራፉ ውስጥ ካሳለፍናቸው አስቸጋሪ ውጣ ውረዶች አንፃር ፤ ከዛም በላይ ከቆምንበት የታሪክ ምእራፍ ተሻግረን ማየት የማይሹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ክፉ ሴራ አኳያ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የመገደዳችን እውነታ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ቁጭ ብለን በሰላማዊ መንገድ ተወያይተን መፍታት የምንችላቸው ችግሮቻችን ከእኛ ከራሳችን ቆሞ ቀር የፖለቲካ ባህል (የሴራ ፖለቲካ) አንጻር እኛን ሆነ መጪውን ትውልድ ያልተገባ ዋጋ ሊያስከፍሏቸው አይገባም። ለዚህ ከቀደመው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን ከትናንቶችም በአግባቡ ተምረን አገርን ለሚጠቅም ነገር ልንበረታ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ግትርነት አገርና ሕዝብ ዋጋ የሚያስከፍልበ እውነታ ዛሬ ላይ ታሪክ ሊሆን ይገባል።
ከዚህ አንፃር ከሁሉም በፊት ለሀገር ለሕዝብ ፤ ከዚያም በላይ ለመጪዎቹ ትውልዶች ያሳስበኛል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎች ሆኑ የትኛውም ዜጋ መንግሥት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሄደበት ያለውን ቁርጠኝነት መደገፍ እና አብሮት መሰለፍ ይኖርበታል።
ይህ የራስንና የሚወልዷቸውን ልጆች እጣ ፈንታ የመወሰን ያህል ከባድ የሆነ፤ የእያንዳንዱን ዜጋ ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ አጀንዳ በአግባቡ ትኩረት ሰጥተን ልንከታተለው ይገባል። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቀደም ባለው ዘመንም ሆነ አሁን እየተከፈለ ያለው ዋጋ ትርጉም ኖሮት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው !
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015