የግብርናው ዘርፍ የሁለተኛው ትራንስፎር ሜሽን እቅድ አፈፃፀም አራተኛ ዓመት ላይ ይገኛል። በአገሪቱ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ በተቀመጠው ግብ መሠረት በመሠረታዊ እድገት አማራጭ ስምንት በመቶና በከፍተኛ የእድገት አማራጭ ደግሞ 11 በመቶ ለማድረስ ግብ ተጥሏል። የተመዘገቡ ውጤቶች ሲታዩ ግን ከአራት በመቶ መብለጥ አልቻሉም። ይህ ውጤት የሚያሳየው የተቀመጠው ግብ አለመሳካቱን ነው። ለዚህ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ የሰው ኃይል የማስፈፀም አቅም፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የሀብት ውስንነት እንዲሁም በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ተጠቃሽ ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴር የስምንት ወራት የሥራ አፈፃፀሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በግብርና ቴክኖሎጂዎች በተለይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪ አጠቃቀም፣ የመስኖ ልማት መዳከም፣ የውጭ ገበያ የሚቀርቡ ጥራጥሬዎች ጥራት በማነስ ምክንያት የውጭ ገበያ መቀዛቀዙ እንዲሁም የቁም እንስሳ የውጭ ገበያው በሕገወጥ የቁም እንስሳት ገበያ ምክንያት መዳከሙን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ይናገራሉ።
የምርጥ ዘር አቅርቦት በዚህ ዓመት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ዘር የማቅረብ ሥራ ሲሆን በስምንት ወራት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ኩንታል እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ዘር አባዝተው የሚያቀርቡ የመንግሥትና የግል ተቋማት ለአቅርቦት ማነስ ምክንያት የሆነው በምዕራብ ኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት በተለይ በበቆሎ ምርት ላይ በደረሰ ጉዳት መሆኑን አቶ ዑመር ገልጸዋል።
ለግብዓት መግዣ የቀረበ ብድር አመላለስ በተመለከተ 2003/2004 ዓ.ም ዘመን ጀምሮ እስከ 2009/2010 ዓ.ም ለግብርና ግብዓት መግዣ ከቀረበ ብድርና በክልሎች ሳይመለስ የቆየው አምስት ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር ውስጥ አንድ ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር እንዲመለስ ተደርጓል። በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። ለአፈፃፀሙ ማነስ ዋናው ምክንያት የክልሎች በተለይ ትግራይና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ትኩረት አድርገው አለመስራትና በአንዳንድ ቦታዎች መረጃ
አለማግኘት መሆናቸውን ሚኒስትሩ ይጠቅሳሉ።
የውጭ ምርቶች ግብይት ላይ የተሰሩ ሥራዎች በተለይ የቡና እና የቁም እንስሳ ግብይት ተጠቃሽ ናቸው። በተያዘው በጀት ዓመት 136 ሺ 597 ቶን ቡና ለመላክ ታቅዶ 103 ሺ 950 ቶን በስምንት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ተልኳል። ከተላከው ቡና ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 431 ሚሊዮን ዶላር 297 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። የቡና የውጭ ገበያ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በመጠንም በገቢም ቅናሽ አሳይቷል። ለቅናሹ በምክንያትነት የተቀመጠው የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፉ ዋጋ ጋር የማይናበብ በመሆኑ፣ ላኪዎች የገቡትን ኮንትራት ከምርት ገበያ ገዝተው ማሟላት ባለመቻላቸው፣ የዓለም የቡና ገበያ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ እና በአምራች አገራት በቂ ምርት በመኖሩ ፍላጎት መቀዛቀዝ በመፈጠሩ መሆኑን አቶ ዑመር ያመለክታሉ።
በቁም እንስሳት ግብይት በተያዘው በጀት ዓመት ከታቀደው የዳልጋ ከብቶች 13 ሺ፣ ግመል 8 ሺ እና በግና ፍየል 234ሺ መላክ ተችሏል። አጠቃላይ ከቁም እንስሳት የውጭ ገበያ 24 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። የቁም እንስሳት በተለይ የዳልጋ ከብት በግመል የታየው የአፈፃፀም ማነስ መንስኤ ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን የመከላከል ሂደት ከክልሎችና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የነበረው ቅንጅት አናሳ መሆኑ፣ በክልሎች በኩል ያለው ድጋፍና ክትትል ሥራ አነስተኛ መሆኑ፣ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ለሚውሉ የቁም እንስሳት የማቆያ ቦታ አለመኖርና ያሉትም ቢሆኑ በተፈለገው ፍጥነት ወደ ሥራ አለመግባታቸው ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን አቶ ዑመር ያስረዳሉ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ማምጣት ያልቻሉት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ በመሆኑ በተለይ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ውስንነቶች አሉ። ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርት ማምረት ላይ ቀሪ ሥራዎች ያሉ ሲሆን በዚህ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም እንዲኖር አድርጓል። በውጭ አገራት ለሚላኩ ምርቶች ዋጋ መተመንና መደራደር ላይ ተሳትፎ ባለመደረጉ የምርቶች ተፈላጊነት እየቀነሰ ይገኛል። በቀጣይ የምርት ጥራትን በማሻሻል እና እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ እቅዶች አሉ።
አብዛኛው አርሶ አደር ምርት ለማምረት ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ሲከሰት የምርት መቀነሶች እንደሚኖሩ አቶ ሳኒ ይጠቅሳሉ። አርሶ አደሩ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። በአጠቃላይ ሲታይ የግብርና ዘርፉ የማስፈፀም አቅም ማነስ፣ የሀብት አጠቃቀም ማነስ እንዲሁም በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ የአመራረት ዘይቤ መከተል ዝቅተኛ ውጤት እንዲመጣ ማድረጉን ያብራራሉ።
ግብርና ሚኒስቴር በስምንት ወራት ውስጥ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአገዳ ሰብሎች ምርታማነት እየጨመረ ሲሄድ የጥራ ጥሬና የቅባት እህሎች ምርት እንደሚቀንስ የምርት ትንበያው አሳይቷል። በቆሎ አንድ ነጥብ ሰባት በመቶ እና ማሽላ አንድ ነጥብ ስድስት በመቶ ጭማሪ ሲያሳዩ ነጭ ቦሎቄ ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ ሽንብራ ሦስት ነጥብ አምስት በመቶ የምርታማነት ቅነሳ አሳይተዋል። የበልግ ሥራ እንቅስቃሴ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈን የተቻለ ሲሆን አፈፃፀሙ ዝቅተኛ የሆነው በተወሰኑ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በተለይ በቦረና፣ በምሥራቅና በምዕራብ ጉጂ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞና ጎፋ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ የእርሻ ዝግጅቱ ላይ እክል ፈጥሯል።
በቀረበው ሪፖርት እንደተጠቀሰው፤ የእን ስሳት ምርትን በተለይ የወተት ምርትን ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች በአጠቃላይ ከላም፣ ከግመልና ከፍየል አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሊትር ለማምረት ታቅዶ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሊትር ማግኘት ተችሏል። በስጋ ምርት ደግሞ ከዳልጋ ከብት፣ ከበግና ከፍየል አንድ ነጥብ 27 ሚሊዮን ቶን የስጋ ምርት ለማምረት እቅድ ተይዞ አንድ ነጥብ ዜሮ ስምንት ሚሊዮን ቶን ተገኝቷል። በተጨማሪ ከቆዳና ሌጦ ከዳልጋ ከብት እና ከበግና ፍየል 21 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ምርት ተገኝቷል።
የዶሮ ስጋ ምርት 52 ሺ ቶን ለማምረት ታቅዶ 27 ነጥብ አራት ሺ ቶን ማምረት የተቻለ ሲሆን፣ የዶሮ እንቁላልን አንድ ነጥብ አራት ለማግኘት እቅድ ተይዞ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን መገኘቱ በሪፖርቱ ተቀምጧል። ለዶሮ ስጋ አፈፃፀም አነስተኛ መሆን የስጋ ዶሮ ዝርያ አቅርቦት በመንግሥትና በግል ባለሀብት የተፈጠረ አቅም አለመኖር መሆኑ ተጠቅሷል። የዶሮ ስጋና እንቁላል ምርት ለመጨመር የኤክስቴንሽን አገልግሎት ማዘመንና የፓዌ የዶሮ ማባዣና ማራቢያ ማዕከልን የጫጩት ማስፈልፈል አቅም ማሳደግ እንደሚገባ በሪፖርቱ እንደ መፍትሄ ተቀምጧል።
የተፈጥሮ ሀብት በላቀ ደረጃ ለመጠቀም የተፋሰስ ሥራ፣ አነስተኛ የመስኖ ልማት፣ የመሬት አስተዳደር አጠቃቀም ማሻሻልና የአፈር ለምነትንና ጤንነት ማሻሻል ሥራዎች ዋነኞቹ ናቸው። የተፋሰስ ሥራዎችን ለመተግበር የአካባቢ ማህበረሰብን በማስተባበር አንድ ነጥብ 37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሥነ አካላዊ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተጨማሪም አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት በመከለል እንዲያገግም ተደርጓል። አነስተኛ የአርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ሽፋን ለማሳደግ የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ በማጠናከር በተፈጠሩ የመስኖ ውሃ አማራጮች በመጠቀም አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።
የገጠር መሬት አስተዳደር ለማሻሻል አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ማሳዎችን የልኬትና የምዝገባ ሥራ ተሰርቷል። አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተሰጥቷል። በተጨማሪም የብሔራዊ ገጠር መሬት አስተዳደር የመረጃ ሥርዓቱ ለማጠናከር በትግራይ፣ አማራና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና የተመረጡ ወረዳዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታና እቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል። የአፈር ጤንነትን ለመጠበቅና በተለይ አሲዳማ አፈር ለማከም 17 ነጥብ ዘጠኝ ሺ ቶን ኖራ ተመርቶ ሦስት ሺ 488 ቶን ኖራ ተሰራጭቷል።
በአጠቃላይ፤ ከላይ በተጠቀሰው የስምንት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሂደት የተስተዋሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ የሰው ኃይል የማስፈፀም አቅም፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የሀብት ውስንነት እንዲሁም በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋትና የመሳሰሉት ችግሮች ተቀርፈው፣ በተለይ የአፈፃፀም ችግር ከፍ ብሎ የታየባቸው ክልሎች ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመስራት የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው መሆኑ የብዙዎች ምክር ቤት አባላት አስተያየት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
መርድ ክፍሉ