አገራችን ኢትዮጵያ በእርቅ በተፈጠረ ሰላም ውስጥ ናት። የሁለት ዓመት የጦርነት ሰንኮፏን ጥላ በተስፋና በኃይል ብቅ እያለች ነው። የያዛትን የመገፋፋት መንፈስ አባርራ፣ የሸፈናትን የጥላቻ ደመና ጥሳ በልጆቿ የተስፋ ምስራቅ ላይ እያቅላላች ነው። ትንሽ ሰላም አንፈልግም። ላመል ሰላም አይበቃንም። የምንፈልገው ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ..ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚተማመኑበትን ሰላም ነው።
ይሄ ሠላም ዋስትና እንዲያገኝ መንግስት ብቻ አይደለም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም፣ እኔና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደለንም ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። የጀመርነው ሰላም ሩቅ እንዲሄድ፣ አጽናፍ እንዲደርስ እኛ ወንድማማኞች ነን፤ ጥልና መገፋፋት አይበጀንም እንበል። የጀመርነው ሰላም እድገትና ብልጽግና፣ አንድነትና ከፍታ እንዲያመጣልን ጥላቻን በፍቅር እንግደለው። በልባችን ምስራቅ ላይ ያቅላላው የተስፋ ጭላንጭል በደመና እንዳይያዝ፣ በጉም እንዳይሸፈን ኃላፊነታችንን እንወጣ።
ብዙ ሰላም እንሻለን። ጥላቻን የሚገድል፣ መለያየትን የሚኮንን እልፍ ሰላም እንሻለን። አንድነትን የሚያመጣ ኢትዮጵያዊነትን የሚመልስ ብዙ ሰላም ግድ ይለናል። አዲሷ ኢትዮጵያ በትንሽ ሰላም የምትገነባ አይደለችም። ብዙ የፖለቲካ ነውር፣ ብዙ የፖለቲከኛ እድፍ ያቆሸሻት ናት። ብዙ ጥላቻ፣ ብዙ የትርክት ታሪኮች ያዛነፏት ናት። ብዙ እኔነት፣ ብዙ ራስወዳድነት ያጣመማት ናት። ብዙ ጦርነት፣ ብዙ ማንአለብኝነት ያጠየማት ናት። ይቺ አገር በትንሽ ሰላም አትቆነጅም።
ይቺ አገር በላመል ተስፋ፣ በቁራጭ እውነት አትነጻም። አስተማማኝ ሰላም ነው የሚያበጃት። አስተማማኝ ፍቅር ነው የሚበጀን። እንዴትም ሆነን አገራችን ዳግመኛ ወደጦርነት የማትገባበትን መላ መፍጠር አለብን፤ እንዴትም ብለን ማህበረሰባችን በፖለቲከኞቻችን ዕቃቃ ዳግመኛ እንዳይሰቃይ ማድረግ አለብን። እንዴትም ብለን መጪውን ትውልድ ከጥላቻና ከዘረኝነት መታደግ አለብን። እንዴትም ብለን በመነጋገርና በመግባባት የምታምረውን ኢትዮጵያ መፍጠር አለብን።
አገር እንደ ሠላም ውበት የላትም። ህዝብ እንደ ሠላም ደምግባት የለውም። ሠላም ያላቸው ነፍሶች ሁሉ ቆንጆዎች ናቸው። እናምር ዘንድ የክብር አክሊል የሆነውን ሰላም መቀዳጀት አለብን። የሠላም ስምምነቱ በሁለቱም ወገን ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን እያስተናገደ ነው። መንግስትም ሆነ ሕወሓት የገቡትን ቃል በመፈጸም ላይ ናቸው። ከሰሞኑ ተስፋችንን ከፍ ያደረገ ነገር በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ እየተስተናገደ ይገኛል። የፌደራል መንግስት ልዑክ ቡድኑን ወደ መቀሌ ልኮ የሠላም ስምምነት ትግበራው ምን እንደሚመስል ክትትል አድርጎ ነበር።
በዚህ ስቀን ሳናበቃ ወደ መቐለ የአየር በረራ ተጀመረ። ብዙ ሳቅ..ብዙ ደስታ ተስተናገደ። ከሰሞኑ የመቐለውን የአየር በረራ መጀመር አስመልክቶ የታየው የመንገደኞች ስሜት በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ነበር። ብዙ የትግራይ ተወላጆች ለሁለት ዓመት ከተለዩዋቸው ዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ሲገናኙ የነበረው የደስታ ስሜት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም። ናፍቆትና ደስታቸውን ከመተቃቀፍና ከመሳሳም ባለፈ በለቅሶ ሲገልጹ ነበር። ይሄን ነው የፈለግነው..ይሄ ነው የሚያስፈልገን።
የሰላም ፍሬዎች ሁልጊዜም ጣፋጮች ናቸው። በደስታና በእንባ የሚገለጡ ናቸው። ሰላም የገባበት ነገር ሁሉ ለሌላው ረፍት ነው። እነዛ ሳቆች..እነዛ ፈገግታዎች ሰላም የወለዳቸው ናቸው። እነዛ እልልታዎች..እነዛ ፈንጠዝያዎች በእርቅ የተጸነሱ ናቸው። ለዓመታት በሰላም እጦት በጨፈገገ ፊት ላይ፣ በናፍቆትና በትዝታ በባባ ልብ ላይ ያን የሚያክል ጽኑ ሀሴት ማስተናገድ ከሠላም ውጪ ምንም እንዳናስብ የሚያደርግ ነው። ለሰላም መልፋት የቤት ስራችን ነው።
ሰላም እንዲህ ካሳቀን፣ መከራዎቻችን እንዲያስለቅሱን ለምን እድል እንሰጣቸዋለን? ልዩነት ሊኖረን ይችላል፣ እንደ ፖለቲከኛና እንደምናራምደው ርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሊኖረን ይችላል፣ እኚህ ሁሉ ልዩነቶቻችን ግን ከአገርና ህዝብ የሚበልጡ አይደሉም። ፖለቲከኛ የሆነው፣ በሀሳብ ልዩነት የቆምነው ለህዝብ ስንል ከሆነ ለህዝብ ስንል ልንግባባና ልዩነቶቻችንን ማጥበብ ይኖርብናል። ለህዝብ ከሆነ የቆምንው፣ ለህዝብ ከሆነ የምንታገለው ስለህዝብ ስንል አንድ በሚያደርገን ነገር ላይ መግባባት ይኖርብናል። ለህዝብ ከሆነ የምንሟገተው፣ ለህዝብ ከሆነ የምንለፋው ለህዝብ ስንል መከራዎቻችንን በሰላም መቋጨት አለብን።
በነገራችን ላይ ህዝብ ጦርነት አይፈልግም። የቱንም ያክል የሀሳብ ልዩነት በፖለቲከኞቻችን መሀከል ቢፈጠር ህዝብ ሰላምን እንጂ ጦርነትን አይፈልግም። እስካሁን ድረስ ያስተናገድናቸው ጦርነቶች በጥቂት ቡድኖች ፈቃድ እንጂ በብዙሀኑ ፍቃድ የሆነ አይደለም። ለህዝባችን ልንሰጠው የሚገባን ብቸኛው ነገር ሰላም ነው። እንደ ፖለቲከኛም ሆነ እንደ ማንኛውም ዜጋ ለአገራችን ልናውለው የሚገባ ተቀዳሚው ውለታ የሰላም ውለታ ነው። የሰላም ውለታ ደግሞ በእርቅና በይቅርታ፣ በውይይትና በወንድማማኝነት የሚገለጽ ነው። የሰላም ውለታ አሁን አገራችን ላይ እየሆነ እንዳለው የሰላም አማራጮችን በማስፋትና በዛ እውነት ውስጥ በመመላለስ የሚገለጽ ነው።
አሁን ጊዜው በሰላም ሀሳብ ኢትዮጵያን የምንክስበት ነው። አሁን ጊዜው በእርቅና በይቅርታ ቆሜልሀለው የምንለውን ህዝብ የምናገለግልበት ነው። ህዝብ በፍቅር ካልሆነ በምንም አይገለገልም። ከፍቅር ውጪ ልናገለግለው ብንሞክር እንኳን ጥሩ ነገር አንሰጠውም። አገር በሰላም ካልሆነ በምንም አትገለገልም። ከሰላም ውጪ በሆነ መንገድ ልናገለግላት ብንሞክር አንጠቅማትም።
አገራችንንም ሆነ ህዝባችንን በሰላም ሀሳብ የምናገለግልበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን። ይሄን ጊዜ ለሰላም ካልሆነ ለሌላ ለምንም ልንጠቀመው አይገባም። ይሄን ጊዜ ለአንድነትና ለወንድማማችነት ካልሆነ ለሌላ ለምንም ልንጠቀመው አይገባም። ይሄን ጊዜ በሰላም እጦት የባከኑብንን በረከቶቻችንን ለመመለስ ካልሆነ ለሌላ ለምንም ልንጠቀመው አይገባም።
በሠላም ቤት እንስራ። እንደ አገር..እንደ ዜጋ ለሁለት ዓመታት ሁሉንም ዓይነት መከራ ስናስተናግድ ነበር። ትንሽ ዞር ማለት አቅቶን..ትንሽ ማሰብ ተስኖን በማይመጥነንና በማይገባን ስፍራ ላይ ነበርን። አሁን እንደ አገር አሸንፈናል። አንድነታችን እንደሚበልጥ ተረድተን፣ ፍቅር እንደሚሻለን ተምረን መደናቅንው እውነት ተመልሰናል። አትችሉም ላሉን፣ ከጦርነት ውጪ እውቀት የላቸውም ለሚሉን፣ እንድንባላና እየተገዳደልን እንድንኖር ከኋላ ሆነው በለው ለሚሉን ጠላቶቻችን ችግርን በመነጋገር ፈትቶ አብሮ መኖር እንደሚቻል አሳይተናል። አሁን ጊዜው በፍቅር ወደፊት የምንራመድበት ነው። በጋራ የፈጠርናቸውን ችግሮቻችንን በጋራ መፍትሄ እየሰጠን የጋራ አገር የምንሰራበት ነው።
መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተለያየ ጊዜ አሳይቶናል። ለሰላም የተዘረጋ እጁ መቼም እንደማይታጠፍ ከቃል ባለፈ በተግባር አስተውለናል። በገባው ቃል መሰረት ሁሉም በመፈጸም ላይ ነው። እያየነው ያለው ነገር እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። በሰላም ስምምነቱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሁሉም ነገር ጊዜውን ጠብቆ ሰላም ፈጣሪ በሆነ መንገድ እንደሚቀጥል እናምናለን። ከሁለቱም ወገን ማለትም ከሕወሓትም ከፌደራል መንግስትም የሰላም ስምምነቱ የሚፈልገው ነገር ሁሉ በመፈጸም የጓጓንለትን ሰላም የምናጣጥምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ሠላም ይርባል..እሾህን በእሾህ እንዲሉ የሰላም ርሀብ በራሱ በሰላም ካልሆነ በምንም አይፈወስም። እንደ እኛ በሰላም ርሀብ የተጎሳቆለና የከሳ የለም። ስለሰላም ለማውራትም ሆነ ለመጻፍ ከእኛ የተሻለ የሚያውቅ አለ ብዬ አላስብም። ሰላም በደንብ የገባን በደንብ ስለተሰቃየንበት ነው። በደንብ የተረዳነው በደንብ ስለተራብነው ነው። ጎምርቶና ፍሬ አፍርቶ ወደ መሬትም ወርዶ የርሀባችንን ያክል፣ የጉስቁልናችንን ያክል እስክንዋሃደው ድረስ ለሰላም ማንኛውንም መስዋዕት መክፈል ይጠበቅብናል።
ተስፋን የሰነቁ የሰላም ፍሬዎች ያስፈልጉናል። ህመሞቻችን በነሱ ነው የሚድኑት። ቁስሎቻችን በነሱ ነው የሚሽሩት። በሰላም አማራጮች ለቁስሎቻችን መድሀኒት እንጂ ጥዝጣዜ መሆን የለብንም። እስከዛሬ በሚያስፈልገን ልክ ለሰላም ለፍተን አናውቅም። እርግጥ ስለሰላም አውርተንና ለፍልፈን እናውቅ ይሆናል ሰላም ለማምጣት ግን ብዙ ርቀት ተጉዘን አናውቅም።
አብዛኞቻችን ከተግባር ይልቅ ለወሬ ቅርብ የሆነ ማንነት ነው ያለን። እስከዛሬም ሰላማችንን የሰወርነው ከቃል ያለፈ የትግበራ አቋም ስለሌለን ነው። ሰው አዋቂና አስተዋይ ከሆነ ስለሰላም ማውራት ብቻ ሳይሆን ስለሚመጣበት መንገድም ማሰብ አለበት። የአሁኑ የሰላም ተስፋችን ከወሬ ባለፈ የወሰድነው የተግባር ውጤታችን ነው። ከዚህ በኋላም ለሚኖሩብን አገራዊና ግለሰባዊ ችግሮች ከወሬ ባለፈ ለተግባር የሚሆን ቁመና ያስፈልገናል።
ለህመሞቻችን መድሃኒት ከመፈለግ ይልቅ ህመሞቻችንን እሽሩሩ ማለት የሚቀለን ነን። ብዙ ግዜ መፍትሄ ላይ ከማተኮር ይልቅ ችግሮቻችን ላይ ማተኮር የሚቀናን ነን። ሰላምን አምጦ መውለድ ያቃተንም ለዚህ ነው፤ አሁን የተወለደው ሰላም በብዙ ምጥ ነውና እንደ ዓይናችን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል። በጋራ ኃላፊነት፣ በጋራ ተቆርቋሪነት ትንሽዋ ሰላም ከፍ ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል።
ሠላም ቡቃያ ነው.. አድጎና መንድጎ ዋርካ እስኪሆን ድረስ ክትትል ይፈልጋል። ሠላም ችግኝ ነው..አድጎና መንድጎ ስር እስኪሰድ ድረስ እንክብካቤ ያሻዋል። በዚም ሆነ በዛ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ሰላም አብቦና እሸት አሽቶ መከራዎቻችንን እስኪያስረሳን ድረስ ተስፋ ማድረጋችን ይቀጥላል። በኢትዮጵያ ምድር እንዲሆን የምንፈልገው እድገትና ብልጽግና፣ ለውጥና ስኬት ሰላምን ተደግፎ የሚሆን ነውና ስለ ሰላም ዝም አንልም።
ተስፋን የሰነቁ የሰላም ፍሬዎች..የአገር ሰብል፣ የህዝብ አዝመራዎች ናቸው። በእኛው ተተክለው በእኛው የሚጸድቁ። የሠላም ፍሬዎቻችን እንዳይጠወልጉ ውሀ ማጠጣት፣ ማዕድን ማስታቀፍ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ተስፋ ካለመኖር ወደመኖር የምንሸጋገርበት ድልድይ ነው። ማንም ሰው በዚህ ድልድይ ላይ ሳይራመድ ወደ ዛሬና ወደ ነገ መሄድ አይችልም። ማንም ሰው በዚህ ድልድይ ላይ ሳያልፍ መኖር አይችልም።
የተስፋ አብራክ ሰላም ነው። ተስፋ በሰላም ውስጥ ተረግዞ ሲወለድ ነው መኖር የሚጣፍጠው። ተስፋ በእርቅና በፍቅር ሲጸና ነው ህይወት የሚያጓጓው። አሁናዊው የአገራችን ገጽታ ከዚህ እውነት ጋር ልክክ ያለ ነው። አገራችን ለሁለት ዓመታት ሠላምና ፍቅር፣ አንድነትና ተስፋ ርቋት ነበር። አሁን ያጣነውን ሠላም አግኝተነዋል።
ከጦርነት ይልቅ ሠላምን፣ ከመገፋፋት ይልቅ መነጋገርን አስቀድመን ወደቀደመ ክብራችን እንመለስ። አሁንም ገና ነን፤ ስለሰላም ብዙ ይቀረናል። እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭል ዋርካ ሆኖ ጥላ እስኪያጠላልን ድረስ ለሠላም መድከማችን ይቀጥላል። የሆነ ቀን ላይ ፍቅር ባልነካው ልብ ተቀያይመን ነበር። የሆነ ቀን ላይ በወንድማማቾች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ተስፋችንን፣ ዕምነታችንን፣ ሠላማችንን አጥተን ነበር። አሁን ወደዛ ወዳጣነውና ስንፈልገው ወደነበረው መንፈስ ተመልሰናል።
ጥልን ገሎ በፍቅር መተቃቀፍ እንዴት ደስ ይላል? ቂምን ረስቶ በሠላም መጨባበጥ እንዴት ያረካል? አገሬ የሚያስፈልጋት ይሄ ነው። አሁን ጊዜው ሞትን የምንገልበት ጊዜ ነው። አሁን ጊዜው ጥላቻን አርቀን የምንጥልበት ሰሞን ነው። ሞት ይሞታል..የሞት ሞቱ ሠላም ነው። ሞትን እንግደለው..ጥላቻን እናሳፍረው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015