ኢትዮጵያ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት፣ውሀ እና የሰው ጉልበት አላት። በ12 ተፋሰሶች ሊለማ የሚችል ሰፊና ለም መሬት ባለቤት ናት። ለግብርና ሥራ ተስማሚ የሆነ 36 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት ቢኖራትም እስከ አሁን አገልግሎት ላይ የዋለው 13 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታሩ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሄ ማለት ሊታረስ ከሚገባው መሬት ሥራ ላይ የዋለው ከግማሽ በታች ማለት ነው።
መሥራት የሚችል ሰፊ የሰው ኃይል፣መሬትና ውሀ በበቂ ሁኔታ ባለበት ሀገር ደሀ የሚለውን ካባ ተሸክሞ ዓለም አደባባይ መቆም ማብቃት አለበት ብሎ በቆራጥነትና በትጋት የተነሳው መንግሥት በምግብ ዋስትና ራስን የመቻል ግብ አስቀምጦ ወደ ሥራ ገብቷል።
ሀገሪቱ በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከውጪ የምታስገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጭምር ሰፊ ጥረት እያደረገች ነው። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎንም የግብርና ምርቶችን የውጪ ገበያ ለማሳደግ ሰፊ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህንን ውጤታማ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ግብርናውን በግብዓት አቅርቦት፣ በመካናይዜሽን፣ በኩታ ገጠም እርሻ በመደገፍ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። ሆኖም ግን ዛሬም በግብርና ልማቱ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ነው ማለት አይቻልም። ከግብርና ምርቶች የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ ገቢም በቂ አይደለም። በመሆኑም መንግሥት የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ ግብርናውን በማዘመን ጭምር የተለያዩ ጥረቶች ማድረጉን ቀጥሏል።
ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በየዓመቱ ከውጪ ለማስገባት ተገድዳ ኖራለች። በምግብ ዋስትና ራሷን መቻል አቅቷት ደሀ የሚለውን ስም አንግባም ለዘመናት ቆይታለች። የበለጸጉ ሀገራት ተረጂ በመሆንም የፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እስከመሆን አድርሷታል። አሁንም ድረስ ይሄው የእርዳታ ሰጪና ተቀባይነት ግንኙነት የቀጠለ ቢሆንም ይሄን ታሪክ የሚቀይር ጠንካራ እንቅስቃሴ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በመኸርና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀም ሯል።
እንደ ሀገር ባለፈው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 400 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት በአማካኝ ከአንድ ሄክታር ከ30 እስከ 60 ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል። ይሄ አበረታች ጅምር ተጠናክሮ በመቀጠሉም ዘንድሮ በተሻለ ውጤታማ ለመሆን በየክልሎቹ ሰፋፊ እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አምራቾች፤ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት በዓመት እስከ አራት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ያመርታሉ። የግብርና ሚኒስቴር ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትልቅ ትኩረት በመስጠት የባለሙያ ድጋፍ፣ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ከሎጅስቲክስ አኳያ የመስኖ ስንዴ ልማት በሚለማባቸው አካባቢዎች ላይ ሥራውን በተቀናጀ ሁኔታ መሥራት እንዲቻል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህም በተሠራው የስንዴ ልማት ሥራ ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ሌሎች አገሮችም የመላክ አቅም መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል። በዘንድሮ ዓመትም የስንዴ ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን የስንዴ ምርት ለመግዛት ኬንያ፣ ጅቡቲ እንዲሁም ሌሎች ሀገራትም ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ ናቸው። ምርቱን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመምራት የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። ይሄ እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው ።
እንደ ሀገር የተያዘውን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረትንም የሚፈታ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። ለረጅም ዘመን የቆየውን የተረጂነት ስምም ይፍቃል። የስንዴ ልማት ለኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የአሸናፊነት ትርጉም አለው። ሠርቶ መለወጥን ማሳያና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በምሳሌነትም የሚጠቀስ ሊሆን የሚችል ነው። ስለሆነም ይህንን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ልማት በዕቅዱና በታሰበው ልክ ተግባራዊ እንዲሆንና ከግብም እንዲደርስ ሁሉም በየመስኩ ሊረባረብ ይገባል። የቆየ የድህነት ታሪክን በአዲስ ስኬት የማረጋገጥ እንቅስቃሴውንም ሁሉም ሊደግፈው ይገባል!
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም