በአንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ጠቢብ የሚባሉ አንድ አዛውንት ነበሩ። መቼም በየቦታው ተጠራጣሪና ተፈታታኝ ስለማይጠፋ አንድ ሰው እኚህ አዛውንት ምንኛ አዋቂ እንደሆኑ ሊፈትናቸው ተነሳ። አንድ ቀን አዛውንቱ አደባባይ ላይ እንደተቀመጡ ይህ ሰው ብድግ ብሎ አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው። ‹‹አባታችን እንደሚያዩት እጄ ላይ አንድ ወፍ አለች። ዝነኛና አዋቂ እንደመሆንዎ ይህች ወፍ በሕይወት መኖሯን ወይም መሞቷን ሊነግሩኝ ይችላሉ›› ብሎ በስላቅ መልክ ጠየቃቸው።
ይህን በሚናገርበት ወቅት ተንኮለኛው ሰው በእጆቹ ውስጥ ሸፍኖ አንዲት ጫጩት ወፍ ይዟል። አዛውንቱ ወፏ ሞታለች ቢሉት እጁን ከፍቶ ሊለቃትና እንድትበር አድርጎ አዛውንቱ መሳሳታቸውን በሕዝብ ፊት ሊያጋልጣቸው ይችላል። በሕይወት ያለች ናት ቢሉት ወፏ ጫጩት ስለሆነች እጆቹን ጫን አድርጎ ጨፍልቆ ሊገላትና በድን መሆኗን ለተመልካቾች ሁሉ ሊያሳይና አዛውንቱ መሳሳታቸውን ሊያስመሰክርና ሊረታቸው ይችላል። አዛውንቱ በጥያቄው ላይ ጥቂት ካሰላሰሉ በኋላ ‹‹አይ ልጄ ለጥያቄህ የምስጠው መልስ ወፏ በእጅህ ነች›› የሚል መልስ ነው ብለው የተፈታተናቸውን ሰው ረቱት ይባላል።
የአዛውንቱ አባባል ‹‹ወፏ ትኑር ትሙት የምትወስነው አንተ ብቻ ነህ። ስለዚህ ያቀረብክልኝ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ የሚገኘው በአንተ ብቻ እንጂ በሌላ ሰው አይደለም›› የሚል አንድምታ አለው። በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ሰላም ልክ እንደወፏ በእጃችን ላይ ነው ያለችው። ሰላም እንድትኖር ወይ እንድትሞት፣ እንድትለመልም ወይም እንድትከስም ችሎታው በእጃችን ላይ ነው ያለው። ይህን በእጃችን ላይ ያለን ችሎታ እንዴት አድርገን እንጠቀምበት የሚለው ግን ዋነኛው ገዢ ሀሳብ ነው።
እንደሚታወቀው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሁለት አመታትን ተሻገሮ ለበርካቶች ሞት፣ የአካል መጉደል፣ የንብረትና ሀብት መውደም ምክንያት ሆኗል። የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጫናም በዜጎች ላይ አስከትሏል። ይህ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት ሰላምን የማለምለምና የማኖር አማራጭ ነበረ። ግን አልሆነም።
በዚህም መጠነ ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ተከተለ። በርካታ ዜጎችም ለሞት፣ አካል ጉዳትና መፈናቀል ተዳረጉ። የበርካቶች ቤት ንብረትም ወደመ። ጦርነቱ የእርስ በርስ መሆኑ ደግሞ እጅግ አስከፊ አድርጎታል። በዚህ መሃልም ሀገር ተጎዳች።
ቢዘገይም አልረፈደምና ነው ነገሩ መንግስትና ሕወሓት የሰላም ዋጋዋ፣ የመኖሯና የመለምለሟ ጉዳይ የገባቸው ዘግይቶ ነበር። ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለማስቆምና ዘላቂ ሰላም ለዜጎች ለማምጣት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ላይ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። ሁለቱም ለሰላም ትልቅ ዋጋ በመስጠታቸው፣ የሰላም አስፈላጊነቷ ስለገባቸውን መኖሯ የግድ መሆኑን በመረዳታቸው ሰላምን ምርጫቸው አደረጉ። የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ነጥቦች ላይም በኬኒያ ናይሮቢ ተስማሙ። በዚሁ የሰላም ስምምነት አተገባበር ዙሪያም ዳግም ስብሰባ በናይሮቢ አደረጉ።
ከፕሪቶርያ እስከ ናይሮቢ የነበረው የሰላም ሂደት ያልተጠበቀና በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ጅማሮ ነው። ኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ ያላቸውና ጠላቶቻቸውንም አሳፍረው የመመለስ አኩሪ ታሪክ ቢኖራቸውም የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነትን በሰላማዊ መልኩ የመፍታት ጉልህ ታሪክ አልነበራቸውም። ይልቁንም ሁሉንም ነገር በኃይል የመፍታት ዝንባሌ በአመዛኙ ይታይባቸዋል።
በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ታሪክ ጽፈዋል። አስራ ሁለት አንቀጽ ያለው የሰላም ስምምነት በማውጣት ሰላምን አውጀዋል። በፕሪቶርያ የተካሄደው ስምምነት ለዘመናት መፍትሄን በጠብመንጃ ለማምጣት ሲኬድበት የነበረውን ኋላቀር አስተሳሰብ የሰበረና ስልጡን የሆነ አካሄድን ለሀገራችን ያስተዋወቀ ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሰረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤የአማራና የአፋር ህዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል።
ከፕሪቶርያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው። በፕሪቶርያው ስምምነትና እሱን ተከትሎ በናይሮቢ በተካሄደው የማስፈጸሚያ ውል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከደረሰው ዕልቂት፣ ውድመትና ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት የሚያስችል ዕድል ተገኝቷል።
ጦርነት አውዳሚና የዜጎች ሕይወት ቀጣፊ ነው። ከጦርነት የሚገኘው ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይደለም። ስለሆነም ጦርነት አዋጪ አይደለም። ሰላም ሲኖር ግን ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለም። ሁሉም የሚሆነው ሰላም ሲኖር ነው። በሰላሙ ጊዜ ሰዎች እንደልባቸው ተንቀሳቀሰው ሰርተው መብላት ይችላሉ። በሰላሙ ጊዜ ደስታ እንጂ ትካዜ የለም። ሰላም ካለ ዜጎች በጠንካራ ስነልቦና ሀገራቸውን ለመለወጥ ይታትራሉ። ሰላም ካለ እድገትና ብልፅግና አለ።
ብዙዎች ግን የሰላም ዋጋን የሚረዱት ጦርነትንና ሰቆቃን ካዩ በኋላ ነው። የሰላም ጠቀሜታን የሚረዱት ፀጥታ ሲደፈርስና አለመረጋጋት ሲኖር ነው። የሰላም አስፈላጊነት የሚገባቸው ልክ እንደወፏ በእጃቸው ላይ ያለውን አማራጭ ትተው ባልሆነ አቅጣጫ ከተጓዙ በኋላ የሄዱበት መንገድ እንደማይጠቅማቸው ሲረዱ ነው።
በሀገሪቱ ከሚታዩት ግጭቶች ውስጥ አንዱና እየተባባሰ የመጣው በብሔር፣ ጎሳና ዘር ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ግጭት መሆኑ አይካድም። እዚህ ላይ ሁሉም በጥልቅ ሊያጤነውና ሊያብሰለስለው የሚገባው ጉዳይ ከሁሉም ግጭት በማንነት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ማለትም በዘር፣ በብሔር፣ በጎሳ፣ በቀለምና በቋንቋ ላይ ለተመሰረቱ ግጭቶች መፍትሄ ለማግኘት አስቸጋሪና አደገኞች መሆናቸው ነው። በወለጋ፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎችና በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተው ይኸው ነው። ለዚህም መንስኤው ግጭቶቹ ከመከሰታቸው አስቀድሞ ሌሎች የሰላም አማራጮችን መውሰድ አለመቻሉ ነው።ለሰላምም ያለው ፍላጎት በሁሉም ወገን በኩል እኩል አለመሆኑ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል።
ኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ ዘመናትን ተሻግራለች። ሀገሪቱ እንደ ሀገር ከጸናችበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈችው በግጭትና ጦርነት ውስጥ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁንም ያላባሩትን እነዚህን ግጭቶች ለማስቆም በመጀመሪያ ደረጃ ከግጭት አያያዝና አፈታት ጥናት በመነጨ ፅንሰ ሀሳብ መሰረት ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት የግጭቱ ስረ መነሻዎች የሆኑት ችግሮች ምን እንደሆኑ ተመርምረው ለነዚሁ ስረ ምክንያቶች መፍትሄ ሲያገኝ ብቻ ነው። ይህም ማለት ግጭት ብዙ ጊዜ አታላይ ነው። ከላይ ከላይ ሲመለከቱትና ወደውስጥ ገብተው ሲመረምሩት የተለያዩ ገፅታዎችን ሊያመለክት ይችላል።
ከላይ ለሚታየው ችግር ብቻ መፍትሄ ቢሰጥ ጊዚያዊ እንጂ ዘላቂ ሰላም አይገኝም። እንዲያውም ይህ መፍትሄ ነው ተብሎ የሚመጣው ፈውስ ትክክለኛ ፈውስ ከመሆን ፋንታ ችግሮችን ሊያባብስ ይችላል። በብሔሮች መካከል ለሚከሰቱ ግጭቶችና መተላለቆች ዋናው ስረ ምክንያት በብሔሮች ምክንያት ካለው የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የርእዮተ ዓለም ልዩነት የተነሳ የሚመጣው አለመጣጣምና አለመቻቻል፤ ሲከርም ጥላቻ ነው ብለው የሚያስቡ ብዙ ሰዎች አሉ።
ታዲያ ምክንያቱ ይህ ከሆነ ዘላቂው መፍትሄ የሚጣሉትን ብሔሮች መለየት፤ ማለትም እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ክልል፣ ቦታና ቀጠና ቢይዝ በብሔሮች መካከል ያለው ግጭት ሊቆምና ሰላም ሊመሰረት ይችላል ወደሚል አስተሳሰብ ሊያመራን ይችላል። ነገር ግን ይህ መፍትሄ በራሱ ሌሎችን ግጭቶች ሊፈጠርና ያሉትንም ግጭቶች ሊያባብሳቸው ይችላል።
እያንዳንዱ ብሔር የራሱ ቀጠና ይኑረው ሲባል እንዴት ድንበሩን ማካለል ይቻላል። የጋራ ሀብቶች እንደውሃ፣ የግጦሽ መሬት፣ የደን ሀብትና ማዕድን ለማን ይሰጣሉ ወይም እንዴት ይከፋፈላሉ። ሲከፋፈሉስ ለሁሉም በቂ ይሆናሉ ወይ ከሁለቱ ብሔሮች ጋብቻ የተወለዱ ልጆችስ የት ይሆናሉ የሚሉትና ሌሎችንም ከባድ ጥያቄዎችን ያስነሳል።
በብሔሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶች አፋጅና አስተላላቂ የሚያደርጋቸው የመሪዎች፣ የምሁራንና የሊህቃን ሚና ነው። በብዙ ሀገራት የብሔሮች ኢኮኖሚና የፖለቲካ ፉክክር ተብሎ የሚተረጎመው በነዚህ ብሔሮች መሪዎች መካከል ያለ የኃይል፣ የስልጣን፣ የኢኮኖሚና የጥቅም ሽኩቻ ፉክክር ነው። የተደበቀው የተጽእኖ ፈጣሪዎች(ኢሊቶች) የግል ፍላጎትና ዓላማ የብሔራቸው ፍላጎት ወይም ብሶት ተደርጎ ስለሚቀርብ ሕዝቡ በቀላሉ ይቀሰቀሳል።
ንቃተ ህሊና የጎደላቸው የብሔሩ አባላትም የተደበቀውን አጀንዳ በጥልቀት ሳይረዱ ብሔራችን ተጠቃ ወይም ተነፈገ በማለት መሪው ለብሔራችን መብት ወይም መጠቀም መሰናክል ናቸው ካላቸው የብሔር ሰዎች ጋር ሰው ሳይለዩ፣ ማነው አጥፊ ማነው አልሚ ሳይሉ በጅምላ ይጣላሉ፤ በጅምላ ያጠቃሉ። እንዲህ አይነት ግጭቶች ከላይ ከላይ ሲታዩ የሕዝብ ግጭቶች ቢመስሉም ስረ ምክንያታቸው ግን የልሂቃን ግጭት እንጂ በብሔሮች መካከል በቋንቋ፣ በባህል፣ በዘር መለያየት ወይም አለመጣጣም አይደለም።
ከዚህ አንፃር የመሪዎችንና የሊህቃንን አተያይ ሚና ከማገት በላይ መልካም አስተዳደርን መገንባት፣ ዜጎች እኩልነታቸው ሙሉ በሙሉ የሚጠበቅበትና ከአንድ ወይም ከሌላው ብሔር የተወለዱ በመሆናቸው ብቻ የማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ አድልዎ ሰለባ እንዳይሆኑ አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጡ ህጎችንና አሰራሮች ሊኖሩ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ዜግነትን ማጠናከርና የሕዝቡን ንቃተ ህሊና ማስፋትና ማስተማር ያስፈልጋል።
ብሔሮችን የሚያስተባብራቸውን፣ ባህላቸውንና እሴታቸው ምን ያህል ተመሳሳይና ተቀጣጣይ እንደሆኑ ትልቅ ጥናት ቢደረግ ምን አልባት የኢትዮጵያ ሕዝቦች መመሳሰልና አንድነት ከተጠበቀው በላይ ሊያስደንቅ ይችላል። ይህንኑ ስራ ለተመራማሪዎች እንደቤት ሥራ መስጠትና ውጤቱን ለሕዝብ ማስተማር ያስፈልጋል። ይህ በራሱ አንድ የሰላም እቅድ ሊሆን ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችና ግጭቶች ለመቅረፍ የሀገር ሽማግሌዎች ታላቅ ኃላፊነትና ሚና አለባቸው።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከሰሞኑ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራውና የመሰረተ ልማት ተቋማትን የሚመሩ አመራሮችን ያቀፈው ቡድን መቀሌ መግባቱና ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያደረገው የሰላም ውይይትም ከጦርነት ይልቅ የሰላም አማራጭ ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ያሳያል። ከጦርነቱ ይልቅ ሰላም ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው በጉብኝቱ ወቅት የነበረው ድባቡ በራሱ በቂ ማስረጃ ነው።
ሁለቱ አካላት ከሁለት አመታት ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቀሌ ገፅ ለገፅ ሲገናኙ የነበራቸውን ስሜትና በፊታቸው ላይ የሚታየውን ደስታ በቀላሉ ለመረዳት አያዳግትም። አዎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጦርነቱ ምን ያክል ጎጂ እንደሆነና አንድም ጥቅም እንደማያስገኝ ተረድቷል። በተለይም በጦርነቱ ውስጥ የነበረው የትግራይ፤ አማራና አፋር ሕዝብ የሰላም ትርጉም ከየትኛውም ዜጋ በበለጠ የሰላምን ዋጋ የተረዱት ይመስላል።
ታኅሣሥ 19፣ 2015 ዓ.ም ለመቀሌ ነዋሪዎች የተለየች ነበረች። ለአስራ ስምንት ወራት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል። ደም አፋሳሹን ጦርነት ተከትሎ ትራንስፖርትም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎቶች በተቆረጡባት ትግራይ ክልል በረራ እንደገና ተጀምሯል።
ቢቢሲ እንደዘገበውም ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እኩለ ቀን ላይ የተነሳው አውሮፕላን መቀሌ ካረፈ በኋላም በተለያዩ ስሜቶች የተዋጡ መንገደኞች ታይተዋል። መንገደኞችም በመቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርሱም መሬቱን ሲሳለሙ፣ በርካቶች ሲላቀሱ፣ ሲተቃቀፉም ታይተዋል። ለአንድ ዓመት ተኩል ያላይዋቸውን ቤተሰቦች፣ ወዳጆች ዘመዶችም ጋር አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ሲላቀሱ ተስተውለዋል።
የስልክ አገልግሎት በመቋረጡና ከ18 ወራት በላይ ከቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው የተቆራረጡ የትግራይ ተወላጆች በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ አያውቁም። በዚህ በረራ ተሳፍረው እንደሚመጡ የማያውቁ ቤተሰቦችም መቀሌ ሲደርሱና በየቤታቸው ሲገቡ የነበረውን ድንጋጤ፣ ደስታ፣ ለቅሶ የተለየ ነበር።
ስለዚህም የሰላም ዋጋው መተኪያ የለውም። ሰላም ሁሉም ነገር ነው። በፕሪቶርያና በናይሮቢ የተፈረሙት የሰላም ስምምነቶች ይዘውት የመጡትም ጸጋ ይህንኑ የሚያሳይ ነው።
ይህ ጅምር ደግሞ በርቱ የሚያስብል ነው። ቀጣዩ ስራም የሚሆነው አሁን የተጀመረውን የሰላም ጉዞ ዘላቂ ነው። ሁሌም ቢሆን የሰላም ዋጋዋ ከበስተኋላ ነው የሚባለውም በምክንያት ነው። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015