“ባህል” ለየትኛውም ዜጋ ቤትኛና “የእኔ” የሚለው ዋና ጉዳዩ ቢሆንም፤ ነገር ግን “ጽንሰ ሃሳቡና ትርጉሙ “እንዲህና እንዲያ ብቻ” እየተባለ ቁርጥ ያለ ብያኔ የሚሰጥበት የእውቀት ዘርፍ ከመሆን ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በራሳችንም ሆነ በባዕዳና ቋንቋዎች ውስጥ ለፍቺ አስቸጋሪ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ እጅግ ጥቂት ቃላት መካከል ምናልባትም “ባህል እና ወግ” የሚሰኙት ሁለቱ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ሊሰለፉ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል ሃሳብ ላይ ባለመደረሱም ይመስላል የመስኩ ምሁራን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጥሯቸው ድንጋጌዎች በብዙ መቶዎች ሊቆጠሩ ግድ ሆኗል፡፡
ለባህል የሚሠጠው ድንጋጌ እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት መሠረታዊው ምክንያት ቃሉ የተሸከመው ጽንሰ ሃሳብ በራሱ ውስብስብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ምሁራኑና ያገባኛል ባይ ባለድርሻዎች “ባህል” የሚለውን ቃል በራሳቸው ውሱን እውቀትና በሰለጠኑበት ሙያዊ ንፍቀ ክበብ ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር ብቻ እየወሰኑ ዐውዳዊ ፍች ለመስጠት ስለሚሞክሩ በጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ አዳግቷቸዋል፡፡
ለአንድ ቃል ፍቺ ለመስጠት ቢያንስ ሁለት ዋና የድንጋጌ አሠጣጥ ዘዴዎች መከተሉ ለአጠቃላይ ግንዛቤ እንደሚረዳ የእውቀት ዘርፉ ባለሙያዎች ምክር ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ዘዴ ለጽንሰ ሃሳቡ ይመጥናል ያሉትን ፍቺ (Conceptual Definition) መስጠት ሲሆን ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ዐውዳዊ ወይንም ተግባራዊ ፍች (Operational Definition) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡
ጽንሰ ሃሳባዊ ፍቺ በራሱ በሦስት ዋና ክፍሎች ይመደባል፡፡ የመጀመሪያው፡- የዕለት ተዕለት ፍቺ (Daily Definition) የሚባለው የብያኔ አሰጣጥ ዘዴ ነው፡፡ በዚህኛው የድንጋጌ አካሄድ ሰዎች ባህልን የሚተረጉሙት በተዘወተሩና በጋራ ሊያግባቡን ይችላሉ ብለው የሚያምኑባቸውን ማሳያዎች እየዘረዘሩ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በዚህኛው ጎራ ያሉ ሰዎች ባህልን የሚደነግጉት ወግ፣ ኪነ ጥበባት፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ የሥዕል ሥራዎች፣ አመጋገብ፣ አለባበስ ወዘተ. የሚሉትን መሠረታዊ የባህል መገለጫዎች ለድንጋጌአቸው ማጎልበቻነት በተናጠል እየጠቀሱ ነው፡፡
ሁለተኛውና በጽንሰ ሃሳብ ድንጋጌ ሥር የሚመደበው የአተረጓጎም ዘዴ ጥበባዊ (Poetic Definition) በመባል ይታወቃል፡፡ ይሄኛው የድንጋጌ ዘዴ የረቀቀ፣ ጥበባዊ ይዘቱ የጎላና የተጋነነ ዓይነት የብያኔ አሠጣጥ ዘዴ ነው፡፡ በጥበባዊ ዘዴ “ባህል የአንድ ማኅበረሰብ ኩራት፣ የገናናነት መገለጫ፣ የሥልጣኔና የኋላ ቀርነት መንስዔና ምክንያት ወዘተ.” እየተደረገ በሙዚቃው፣ በሥነ-ቃሉ፣ በሥነ-ጽሑፉ ወዘተ. ይበየናል፡፡
ሦስተኛው የድንጋጌ ዘዴ የተመራማሪዎች ምሁራዊ ድንጋጌ (Scholarly Definition) በመባል ይታወቃል። በዚህኛው የፍቺ አሰጣጥ ዘዴ ባህል የሚደነገገው፤ “አንድ ማኅበረሰብ ወይንም ቡድን የዕለት ኑሮውንና ሕይወትን የሚተረጉምበት” ዘዴ እንደሆነ እየተቆጠረ ነው፡፡
ዐውዳዊው ወይንም ተግባራዊው ፍቺ በአንድ ጉዳይ ላይ “እየኖርኩበት ስለሆነ አውቀዋለሁ፣ በራሴ ኑሮና ሕይወት ፈትኜ ተቀብዬዋለሁ፣ መዝኜና ለክቼ ወርድና ስፋቱን ደርሼበታለሁ ወዘተ. ስለዚህ እኔ የደረስኩበትና የማምንበት ፍቺ እንዲህ የሚል ነው” እየተባለ ድንጋጌ አከል መደምደሚያ የሚሰጥበት ዘዴ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት “ባህል” የሚለው ግዙፍና ውስብስብ ጽንሰ ሃሳብ ዛሬም ድረስ “ሃሌ ሉያ” አሰኝቶ የሚያስማማ የጋራ ፍቺ ላይ ለመድረስ አልተቻለም፡፡
እንዲያም ተባለ እንዲህ ምሁራኑ የባህልን ድንጋጌ በአሜንታ አጽድቀው ከጋራ ስምምነት ላይ ባይደርሱም “ባለመስማማት የተስማሙበትን” የነገረ ባህል ጉዳይ በይደር በማስተላለፍ ተሸንፈውና አጉራህ ጠናኝ ብለው እጅ በመስጠት ገበርን አላሉም፡፡ ስለዚህም፤ የባህልን ጽንሰ ሃሳብ “በቃ ይሄ ነው!” ብለው ለመደንገግ ከመሞከር ይልቅ ከባህል ፈጣሪውና ከባህል ባለቤቱ ከራሱ የሰው ልጅ ጋር በማቆራኘት እያጠኑ እጅግ በርካታና ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ የምርምር ውጤቶችን ስፍር ቁጥር በሌለው ልግስና አበርክተውልናል፡፡
አከራካሪውና አካዳሚያዊው ነገረ ባህል ዛሬም የሰከነ ድንጋጌ ያልተገኘለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ማንም ሰው በየትኛውም ደረጃ ላይ ሆነ ወይንም የሕይወት አቋም ላይ ቢገኝ ራሱን ከባህሉ ነጥሎ ለማውጣትና ልክ እንደ ደሴት ተለይቶ በራሴ የባህል ዐውድ ውስጥ ራሴን በራሴ አኖራለሁ ለማለት በፍጹም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ማሕበረሰባዊውና ኅብረተሰባዊው ባህል ከሰዋዊ ማንነታችን ጋር ልክ እንደ ነርቭ ንዝረት በፅኑ የተቆራኘን ስለሆነ ከምንኖርበት ማሕበር አፈንግጠን ከቶውንም መኖር አንችልም፡፡ “እችላለሁ!” ብሎ ይሞከር እንኳን ቢባል ሕይወትን ስለሚያመሰቃቅል የሚደርሰው ቀውስና ነውጥ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
ማንም ሰው ለባህሉ ተገዥ ነው የሚባለው ወዶ ሳይሆን የባህሉን ብርታት ለማስገበር አቅም ስለሌለው ብቻ ነው፡፡ የምሁራኑን አገላለጽ እንጠቀምና፤ “በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በሥጋ፣ በነፍስና በስሜት የተሸረበ ሰብአዊ ፍጡር መሆኑ የማያከራክር እውነታ ነው፡፡ ነፍሱ ከሥጋ ተለይቶ፣ ሥጋውም ከነፍሱ ተነጥሎና ስሜት አልባ ሆኖ መኖር ከቶውንም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚሁ እውነታ ባልተናነሰ መልኩ ያለ ባህል ሰብእና ትርጉም የለውም፡፡ ከባህል ተፋቶም መኖር አይሞከረም፡፡ የሰውን ልጅ ከሌሎች እንሰሳት ልዩ ፍጥረት ያሰኘው የሥጋ፣ የነፍሱና ስሜቱ ጥምረት ብቻም ሳይሆን የባህሉ ድርሻም የላቀ ነው።” ይሉናል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ባህል ነክ ዝርዝር ጽንሰ ሃሳቦች በሚከተሉት መሠረታዊ ማሳያዎች ማጠቃለል ይቻላል፡፡ ባህል ማኅበረሰቡ በአሜንታ በተቀበላቸው ቅቡል ተምሣሌታዊ ምልክቶች፣ አካላዊ የመግባቢያ እንቅስቃሴዎች፣ በሥዕሎችና በቁሳቁሶች የሚገለጥ ነው፡፡ ባህል ማኅበረሰቡ ባከበራቸው፣ በሕይወት ባሉና በሌሉ፣ በምናባዊ ጀግኖችና ተወዳጅ ባሕርያት በተላበሱ የፈጠራ “አንቱዎች” (Heroes/Heroines) የመልካም ተግባር ሞዴልነት ይገለጣል፡፡ ምሳሌ፡- ጀግኖች አርበኞች፣ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ የአገር መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወይንም አርዓያ ሰብ የሚባሉና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ግለሰቦች ባህሉ በጥንካሬው በርትቶ እንዲቆይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
ባህል በማኅበረሰቡ የእምነት፣ የአምልኮና ሌሎች ባህላዊ ክንውኖችም ጎልቶ ይንጸባረቃል፡፡ ሰላምታ፣ የአክብሮትና የእምነት መገለጫ ሥርዓቶች ወዘተ. ለባህል ህልውና የመሠረት አለቶች ናቸው፡፡ ባህል ማኅበረሰቡ ይሁነኝ ብሎ ባጸደቃቸውና እንዲሆኑለት በሚመኛቸው እሴቶቹ ውስጥም ይንጸባረቃል፡፡ ክፉና ደግ፣ ቸርና ንፉግ፣ መልካምና መጥፎ፣ ቆንጆና መልከ ጥፉ ወዘተ. የመሳሰሉትን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡
ወግ፡- ለባህል ግብዓት ከሆኑት “ንጥረ ነገሮች” መካከል አንዱ ነው፡፡ መገለጫዎቹም ባሕርያዊ ልምምዶች (Behaviors)፤ ቤተሰብ፣ የማሕበረሰብና የውሱን ቡድኖች አሜንታ ያገኘና እንደ እሴት የሚቆጠር ቅቡል የሕይወት ዘይቤ ነው፡፡ የወግ መገለጫዎች በርከት የሚሉ ቢሆንም የአመጋገብና የማዕድ ወግ፣ የአነጋገር ጥበብ፣ የአለባበስና የአጋጌጥ ሥርዓት፣ ሥራንና ተገልጋይን ማክበር፣ የታላላቆች ጥበባዊ አኗኗር፣ መከባበርና በዕድሜ እርከኖችን ከግምት በማስገባት መቀባበል ወዘተ. ወግ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለመደንገግ በእጅጉ ይረዳሉ፡፡
ለባህል ድንጋጌ በሰጠንበት ቀደም ባለው ክፍል ለመዳሰስ እንደተሞከረው ባህል የአንድ ሕዝብ የተከማቸ የዕውቀት፣ የልምድ፣ የእምነቶች፣ የእሴቶች፣ የአመለካከቶች፣ ለሕይወት የሚሰጡ ትርጉሞች፣ የማኅበረሰቡ የእርከን ተዋረድ፣ የሃይማኖቶች፣ ስለተፈጥሮና ስለ ቁሳዊ ሃብት ገላጭ እሴቶች የተከማቹበት ካዝና መሆኑን መግለጹ ያግባባ ይመስለናል፡፡
ባህል ከትውልድ ትውልድ፣ ከኅብረተሰብ ኅብረተሰብ ሲሸጋገር በቅብብሎሽ የሚያስተላልፋቸው እጅግ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ ጥበባዊ አገላለጾች፣ ምክሮች፣ ወጎችና ልማዶች፣ የአነጋገር ጥበቦች፣ ሥነ-ምግባር የተላበሱ የዕለት ተዕለት ድርጊቶች፣ ለሌላው ርህራሄ እንድናሳይና በጎ ተግባራት እንድንከውንና ማኅበረሰቡ “አታድርጉ” ብሎ የሚያዛቸውንና የማይፈቅዳቸውን ድርጊቶች እንዳንፈፅም፣ ከፍ ሲልም ማኅበረሰቡ በአክብሮት የተቀበላቸውን ፅኑ እሴቶች እንድናስቀጥል ባህል ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ አስነዋሪ የተባሉ ልምምዶችም የሚወገዙት የባህል ትሩፋት በሆኑ “አድርግ ወይንም አታድርግ” በማለት ማኅበረሰቡ ባፀደቃቸው እሴቶች አማካይነት ነው፡፡
የወረት ኮሶ ይጣፍጣል፤
የእወቁልኝ እብሪት ያሳንሳል፤
በነገረ ባህል ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ለማድረግ የተገደድነው አንድ አሳቢ ወቅት ወለድ ጉዳይ ግድ ቢለን ነው፡፡ ዘመነ ቴክኖሎጂውን እያስተናገድን ያለነው “በበረከተ መርገም” ባህርያቱ ተገዝተንለት መሆኑን በቀዳሚ ጽሑፎቻችን ደጋግመን ለማሳየት ሞክረናል። በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን እየተስተዋሉ ያሉ አሉታዊና አሸማቃቂ ክስተቶች በማሕበረሰባዊ አቋማችንንና በግል ሕይወታችን ላይ በሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽእኖ ምክንያት የወደፊቱ ነጋችንና ባህላዊ እሴቶቻችን ምን ሊመስሉ እንደሚችል ለመገመት አይከብድም፡፡
ከሕብረተሰቡ ባህልና ወግ ያፈነገጡ ልምምዶችና ድርጊቶች እየተስተዋለ ባለው የማሕበራዊ ሚዲያ ፍጥነት የሚቀጥሉ ከሆነ መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል በግላችን ከመጨነቅ አልፈን በቡድን ሳንመካከርበት እንዳልቀረን ጸሐፊው ይገምታል። ባህልና ተፈጥሮ ያከበረው ዕድሜ ሲቀል፣ ሽበትና ሃይማኖት የአንቱታ ፀጋ ያጎናጸፈቸው አንቱዎች ሲዋረዱና የትችት ናዳ እየወረደባቸው ሲብጠለጠሉ ማየትና መስማት እንግዳችን አይደለም፡፡ “ሽማግሌ ካለበት ነገር አይናቅበት” ብሂል ሙሉ በሙሉ ዋጋ አጥቶ ባህል የለሽና የመንፈስ ድሆች እንዳንሆን የጸሐፊው ስጋት ነው፡፡
“ሽማግሌ አይርገምህ፤ የሚያድግ ልጅ አይዘንብህ” አባባልም ፈሩንና መስፈርቱን ስቶ ነገሮች ከተገለባበጡ ሰነባበቱ፡፡ “ሽሽት ከኡኡታ በፊት” እንዲሉ፤ “ሳይቃጠል በቅጠል” እየተባለ ለእርማት ካልተዘመተበት በስተቀር የዛሬ አኗኗራችንም ሆነ የነገ ውርሳችን ምንና እንዴት እንደሚሆን ማሰቡ በራሱ ስሜትን ያውካል፡፡
በየማሕበራዊ ሚዲያው የሚነበቡትና በምስልና በድምጽ ተደግፈው የሚቀርቡት ሰቅጣጭ ስድቦችና የማዋረጃ ስልቶች ከባህልም፣ ከወግም ሆነ ከሃይማኖት ያፈነገጡ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ጽኑ ተቋማት በመናድ ጭምር ሌጣ ማሕበረሰብ እንዲፈጠር መሠረታቸውን እያጠበቁ ያሉ ይመስላል፡፡ በአግባቡ መወያየትና በልዩነት ተከባብሮ መደማመጥ፣ ሃሳብን በጨዋነት ገልጾ የእኔ እውነት የሚሉትን ለማስረዳት ያለመቻል ብቻም ሳይሆን “ባህልና ወግ ዱሮ ቀረ” እየተባለ እንዳይጠቀስ ስጋት ገብቶናል፡፡
የሚዲያ ማስታወቂያዎች፣ የኪነ ጥበባት ውጤቶች፣ የሃይማኖት ሰባኪያን “ሰይፍ አማዛዥ እንካ ሰላንትያዎች”፣ በውሸትና በቅጥፈት የተቀናበሩ የሴራና የአመጽ መቀስቀሻ ዜናዎችና ትንታኔዎች፣ ሰይጣናዊና የእርኩሰት ማለማመጃ ቁርጥራጭ ቪዲዮዎች ወዘተ. ባህልን በመናድ እሴት አልባ አድርገው እርቃን ከማስቀረት ውጭ ምንም ፋይዳ ስለሌላቸው እየታቀፍናቸውና እያንቆለጳጰስናቸው እሹሩሩ ማለቱ ፍም ታቅፎ ለመኖር ካልሆነ በስተቀር ለምንምና ለማንም የሚበጁ አይሆንም፡፡
በመሠረቱ ዘመነ ቴክኖሎጂ ብዙውን የሕይወታችንን ሸክም እንዳቀለለን የሚካድ አይደለም። እውቀት፣ ትምህርት፣ መረጃዎችና ማስረጃዎች፣ በጎ የሕይወት ተሞክሮዎችና ልምምዶች እንደ ተፈጥሮ ማዕድን ተዝቀውና ተቀድተው የማያልቁበት ዘመን ላይ መድረሳችን እድለኛነት ነው፡፡ ችግሩ አጠቃቀም ላይ ነው፡፡ አስተዋይ ሰው አላባውን ከገለባው እየለየ የቴክኖሎጂውን ትሩፋት ቢጠቀምበት ያተርፍበታል እንጂ ጉዳይ የለውም፡፡ ነገር ግን አሠሡንና ገሠሡን ሳይለዩ ማላመጥ ፍጻሜው ከሰብእና መጉደል መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ቅቡልነት ያለው የአንድ ማሕበረሰብ ባህል ተናደ ማለት እሴቱም አብሮ ወደ ሞት ፈጠነ ማለት ነው። እያንዳንዱ ዜጋ “ባህሌ” ብሎ የተጎናጸፈው ፀጋ ተሸምኖ እርሱ ዘንድ የደረሰው ዘመናትና ዓመታት እየተጓዘ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ “በነፃነት” ስም ባርነትን መምረጥ፤ ራስን በራስ በእግር ብረት ከማሰር ምንም ልዩነት የለውም፡፡ በተለይም የኑሯቸውን ማዕድ በሶሻል ሚዲያው ገቢ ላይ ያደረጉ አንዳንድ ሸንጋይ “ተማጻኞች” ማሕበረሰቡን እየተለማመጡ (subscribe share) አድርጉልን በሚሏቸው ቃላት በማባበል የሚዘሩት ክፉ ዘር የሚያዘምረው አዝመራ ጉዳቱ ሌላው ወገን ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም ላይ ሳይቀር ፍሬው ጎምርቶ እንደሚያፈራ ሊረዱት ይገባል ባይ ነን፡፡
የማሕበረሰቡን ጠቃሚ የባህል እሴት የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማሳደግ ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኪነ ጥበባዊና ማሕበራዊ ተቋማትና ቡድኖች ችግሩን እንደ ዋዛ ተመልክተው “መቼስ ምን ይደረጋል? ያመጣውን መቀበል ነው እንጂ” በማለት የሚያልፏቸው እንክርዳዶች ነገ ተነገወዲያ አድገውና ሰፍተው የባህል ፀጋችንን በመግፈፍ እሴት እልባ አድርገው እርቃናችንን እንደሚያስቀሩን ልብ ተቀልብ በመሆን ሊያስቡበት ይገባል፡፡
“በዶሮ ማታ” ሽንገላ የሚጠጣው የወረት ኮሶ የመራራነቱን ባህርይ እንደማይለውጠው ሁሉ፤ ‹ምናለበት› እየተባለ በየማሕበራዊ ሚዲያው የሚዘራው ክፉ ዘር ውሎ አድሮ ባህሎቻችንንና በጎ ማሕበራዊ ወጎችና እሴቶቻችንን በማጠየምና ማዲያት በማልበስ የቀጋ አጥር ሆኖ እንደሚያሰቃየን ልብ ልንል ይገባል። ሰላም ይሁን፡፡
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015