አቶ ገብርኤል ንጋቱ የአትላንቲክ ካውንስል አፍሪካ ሴንተር ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በዓለምባንክ ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ አሁንም በማማከር ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊና ፕላኒንግ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕዝብና ዓለምአቀፍ አስተዳደር እንዲሁም ማህበራዊ ልማት ከፒትሶርያል ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
በሀርቫርድና በማንቺስተር ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ የፖሊሲና የፕሮግራም መምራት ልምድ አካብተዋል፡፡ እአአ እስከ 2019 ድረስ የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ልማት ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው ሰርተዋል፡፡ የተለያዩ አገራትን ኢኮኖሚና ግጭቶችን የተመለከቱ ጽሁፎችን ጽፈዋል፡፡ የዛሬው የ “ዘመን እንግዳችን” አድርገን የመረጥናቸው አቶ ገብርኤል የብዙ ልምድ ባለቤት፣ የበሰለ እውቀት ያላቸውና በትምህርቱም የገፉ በመሆናቸው ፌደራል መንግስትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ያካሄዱትን የሰላም ስምምነት በሚገባ ለመተንተን ብቁ ናቸው ብለን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ውጤት እንዴት አገኙት?
አቶ ገብርኤል፡– በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ የሚሆን በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ምክንያቱም ዋናውና ነገር በመጀመሪያ ተኩስ መቆሙ ነው፤ ይህ መሆን ችሏል። በእዚህ ደግሞ ሁለቱም ወገኖች ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ተኩስ በመቆሙ ምክንያት ዛሬ የሚጣፋ የሠው ህይወት እንደዳይኖር ሆኗል። ቢያንስ በጥይት ድምጽ ምክንያት የሚረበሹ ሕጻናትና እናቶች አይኖሩም።
ጦርነቱ በተካሄደባቸው ክልሎች ያሉ ዜጎች ከጦርነቱ በተጨማሪ ኮቪድን እና የተለያዩ ችግሮችን አሳልፈዋል። ስምምነቱ ከነበሩባቸው ተደራራቢ ችግሮች ኡፎይታ ሰጥቷቸዋል የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ምክንያቱም ከስምምነቱ የተነሳ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ እናቶች ልጆቸቻው ወደ ጦርነት ይገባሉ ብለው አይሰጉም። ይልቁንም ከዚህ ሀሳባቸው ወጥተው የሠለም እንቅልፍ ይተኛሉ።
ለስምምነቱ እውን መሆን የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ሰላም የነበረው አቋም እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ ትልቅ ሚና ነበረው። ሁለቱ ተዳምረው ወደ ሰላም ሀሳብ ተመጥቷል። እናም ይህንን ሰላም አሁን ወደ መሬት የማውረድ ሥራ ነው የሚያስፈልገው። ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ማድረግ አለበት። የሰላም ምልክቶቹን እያየ ማስቀጠሉ ላይ ማገዝ ይገባዋል።
አሁን ስምምነቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነው። ስምምነቱ ወደ ተግባር እንዲቀየር ሁሉም መረባረብ አለበት። በተለይም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከሱ ብዙ እንደሚጠበቅ መረዳት አለበት። ለምሳሌ የሰው ኃይል፤ የገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ይጠበቅበታል። መንግስት ይህን ሰላም እንዲመጣና በቋሚነት እንዲቀጥል እንዲሁም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ማንኛውንም ነገር ያደርጋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን እንደማንኛውም አገር የአቅም ውስንነት አለበት። ስለሆነም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን ሆኖ ማገዝ አለበት። ከመንግስት ጎን በመሆን አጀንዳ መቅረጽ፣ ወደ ተግባር መቀየር ይገባልም።
ይህን ነገር ከዚህ በፊት በኮንጎ ውስጥ አይተነዋል፣ እንዴት እንደሚፈታ ልምዱ አለን የምንለው አይደለም። ይህ የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ የመስጠት ተልእኮ ነው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። እኛ ደግሞ ማድረግ ያለብን መልካም ነገር ይህ ብቻ ይመስለኛል። መንግስት ግልጽ የሆነ አቅጣጫ አስቀምጧል። ያንን ወደ ተግባር መቀየር ይገባዋል። የዓለም አቀፉ ማህበረሠብም ለእኛ መሳብ እንዲችል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡ የሰላም ስምምነቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው ሀሳብ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል ፤ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት ?
አቶ ገብርኤል፡- የሰላም ስምምነቱ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተካሄደ ነው። ይሄ የአፍሪካ ህብረት መር ልምምድ ነው። ይህ በጣም ጥሩ በአፍሪካዊያን የተመራ ሥራ ነው። የኢጋድ አገራት በታዛቢነት ቢኖሩና ታዛቢዎች የራሳቸውን ምክረ ሀሳብ ከጀርባ ሆነው የሚሰነዝሩበት ሁኔታ ቢኖርም ከሞላ ጎደል ግን በአፍሪካዊያን የተመራ ነው።
በአፍሪካውያን የተመራ ነው ማለት ግን የሚያካትተው አፍሪካዊያንን ብቻ ነው ማለት አይደለም። በአፍሪካውያን የተመራ ማለት አፍሪካ ውያን እስትራቴጂ የሚያወጡበት፣ የአፍሪካውያን ልምድና አኗኗር ላይ ተመስርተው አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ማለት ነው። አፍሪካውያን ተሰባስበው የሚመክሩበት ሠላም እንዲመጣ የሚያደርግበት ነው። ቢሆንም ግን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአፍሪካ ጋር መስራት አለበት።
አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካ ችግር ማለት ከእቅዱ ጀምሮ እስከ አተገባበሩ ድረስ በአፍሪካውያን ብቻ የሚፈጸም ማለት አይደለም። አፍሪካዊ መፍትሄ ማለት አፍሪካ የራሷን የመፍትሄ አቅጣጫ ታስቀምጣለች። ከዚያ ግን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሳተፋል ማለት ነው። በአንድ አካል ብቻ የሚደረግ ሳይሆን አንዱ ሲመራ አንዱ የሚከተልበት እንዲሁም ሌላው ሲመራ ሌላው ደግሞ የሚከተልበት ሂደት ነው። ይህንን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተረድቶ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ረጅም ርቀት ተጉዟል፤ በቀጣይስ ምን ይጠበቅበታል?
አቶ ገብርኤል፡– ዋናውና ወሳኙ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚጠበቀው የአመራርነት ሚናውን መወጣት ነው። ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ ከውጭ አገራት ጫና ሲደርስባት በተለያየ መንገድ በመንግስት ጠንካራ መሪነት ተቋቁማ አልፋለች። ልክ እንደዚህ ሁሉ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ መምራትና ሠላምን በማስፈንም በኩል መስራት ይጠበቅባታል። አሁን ሰላም መጥቷል፤ የተሀድሶ ካምፖች ተሰናድተዋል፣ ተዋጊዎቹ ወደዛው እየገቡ ነው፣ ትጥቅ እየፈቱ ነው። ይህን የመጀመሪያው እርምጃ አድርጎ መውሰድም ይቻላል። ነገር ግን መምራት ሲባል ዝም ብሎ አይደለም። ዳግሞ ክልሎችን መልሶ መገንባትን ያስከትላል።
በዚህ ግጭት የተጎዱ ሁሉ ድጋፍን ይፈልጋሉ። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት መሪነቱን ወስዶ የደረሰውን ጉዳት መከታተል አለበት። ግጭቱ ምን አስከተለ፤ ምን ያህል ትምህርት ቤቶች ተጎዱ፣ ምን ያህል ሆስፒታሎች ወደሙ፤ ምን ያህል ሴቶች ችግር ደረሰባቸው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በስነልቡና የመሳሰሉትን ተከትሎ የደረሰውን ጉዳት ማጥናት ይገባል።
በተጨማሪም ግጭቱ ከኢኮኖሚ፤ ማህበረሰብ፣ ከቁስና ከስነልቦና አንጻር ያስከተለውን ጉዳት ለይቶ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። በመቀጠልም በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል እንደሆነ መስራት ይገባል። ለዚህ ደግሞ የራሱ እውቀት ያስፈልገዋል። ከዚያ በኋላ ይሄን ነገር መልሶ ወደ መገንባት ይኬዳል።
መልሶ ግንባታው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ወጪ በዋናነት የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት ነው። ለዚህም ደግሞ መንግስት በቢሊየን የሚቆጠር ብር ያወጣል። መንግስት በራሱ ወጪ ሰዎችን ወደ ነበሩበት የመኖሪያ ቀያቸው የመመለሱን ሥራ እየሠራም ነው። ይሄ ደግሞ ብዙ ወጪን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና አምጥቷል። ምክንያቱም እየወጣ ያለው ብር ታቅዶ በጀት የተያዘለት አይደለም። ያልተጠበቀ ወጪ ነው።
በመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከትላል። እያስከተለ እንደሆነም የሚታዩ ነገሮች አሉ። ስለዚህም አሁን መንግስት ማድረግ ያለበት የደረሰውን ውድመት አጥንቶ በግጭቱ ይሄን ያህል ሀብት ወድሞል ማለት ነው። ለመልሶ ግንባታው ይሄ ያስፈልጋል ሊል ይገባል። ለመልሶ መገንባት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት አለበት።
የዚህን ጊዜ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያግዘው ፈቃደኛ ይሆናል። የቻለውንም እንደሚያደርግ እምነት አለኝ። ሳይሰሩ መጠየቅ እንጂ እየሰሩ መጠየቅ ማንንም የሚያሳምን ጉዳይ ነውና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሚሰራው ስራ ድጋፍ ያደርጋል፤ ያግዛል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ መንግስት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ ጥያቄ ያቀርባል ብለው ያስባሉ?
አቶ ገብርኤል፡- አዎ! እንደምገምተው የኢትዮጵያ መንግስት አንዴ የግጭቱ ተጽዕኖ ወይም በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት አጥንቶ ከጨረሰ በኋላ የሚከለከለው ነገር አይኖርም። ምክንያቱም የለጋሾች እና የአጋሮች ኮንፈረንስ አዘጋጅቶ ሁሉንም የኢትዮጵያ ወደጆች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲገኙ ጋብዞ የደረሰውን ውድመትና ጉዳት ካስረዳ ማንም እንቢ ሊል አይችልም። ሁሉም ቴክኒካል፤ የቁሳቁስ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አይከለክሉትም። ምክንያቱም ሁኔታውን በአግባቡ አስረድቷል። መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም በግልጽ እያረጋገጠ ነው። ይህ ማለት በአገር ቤት መንግስት ለሚያሰባስበው ለዚሁ ጉዳይ የሚውል ሀብት በተጨማሪ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለጋሽ ድርጅቶች በመልሶ ግንባታው ሊኖራቸው የሚችለው ሚና ምንድን ነው ይላሉ ?
አቶ ገብርኤል፡- እንደሚመስለኝ ሁላችንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመልሶ ግንባታው በስፋት እንዲሳተፍ /እንዲተባበር ጥሪ ማቅረብ አለብን። ለሠላም መስፈን ሲከራከሩ የነበሩ አካላት ሁሉ አሁን ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን መረባረብ አለባቸው። ምክንያቱም ስምምነቱ አሁን ሠላምን አምጥቷል። ይህን ሠላም ለማስቀጠል ደግሞ ድጋፍ ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ የአውሮፓ ህብረት፤ ቻይና፤ ህንድ፤ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና የአፍሪካ አጎራባቾች ሁሉም ድርሻ አላቸው። ይሄ የመጀመሪያው ሂደት ነው። ለቀጣይነቱ ሁሉም የኢትዮጵያን ጥረት ሊደገፍ ይገባል። ምክንያቱም የመደገፍ ግዴታው የህሊና ጉዳይ ነው። እናም አገሪቱን መልሶ ለመገንባት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
በመልሶ መገንባት የመጀመሪያው ኃላፊነት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝቦቿ ላይ የወደቀ ነው። ይህ ምንም የሚያከራክር ነገር አይደለም። ነገር ግን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ወደቀደመው ሁኔታዋ እንድትመለስ የመደገፍ የሞራል ግዴታ አለባቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በስሩ ያሉ ተቋማት ምግብ ማቅረብ አልቻልንም ብለው ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩ አሁን በሦስትና በአራት መስመሮች ምግብ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች ማቅረብ ችለዋል። ስለዚህም አሁንም ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ያለገደብ ሰብአዊ ድጋፍ አድርሱ የሚለው ጥሪዬ ነው።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) አይነት ተቋማትም ቀደም ሲል መድሀኒት ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ማቅረብ አልቻልኩም በማለት ቅሬታ ሲያሰማ ነበር። አሁን የሚያስፈልጉ የህክምና ግብዓቶችን ወደ ሰሜኑ ክፍል ማስገባት ይቻላልና ድጋፋችሁ ይጠናከር እላለሁ። የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስት ወደ ሰሜኑ ክፍል እንዳንገባ ድጋፍ እንዳናደርግ በሮችን ዘግቷል በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበርም ይታወሳል። አሁን ድጋፉን መሬት ማውረድና ተጨባጭ ማድረግ ይችላሉና አድርጉት ማለት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ቅሬታው የሚፈታበትና ለሰብዓዊ ድጋፉ መድረስ ጊዜው አሁን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በስምምነቱ የተገኘውን ሰላም ለማፍረስና አገርን ዳግም ወደ ግጭት ለመክተት የሚሰሩ አካላት አሉ ፤ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለእነዚህ ኃይሎች ምን አይነት ምላሽ መስጠት አለበት ይላሉ ?
አቶ ገብርኤል፡- የሰላም ስምምነቶች ሰጥቶ የመቀበል ጉዳይን የያዙ ናቸው። ስለዚህ የትኛውም የሰላም ስምምነት ሁልጊዜም ተግዳሮት አያጣውም። ሕወሓት እና የፌደራል መንግስት ስምምነትን ሲፈጽሙ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊቱ ከመቀሌ የተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። መንግስት በጊዜው ያንን ማድረግም ምርጡ ውሳኔ ነበር። የሕወሓት ተወካዮችም በመሬት ላይ ያለውን እውነታ በሚገባ ተረድተው ወደ ስምምነቱ መምጣታቸው ትክክለኛ ውሳኔ ነው ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አንድ ስምምነት መቶ በመቶ የተዋጣለት ነወይ ካልን፣ መልሱ ግልጽ ነው። መቶ በመቶ የሆነ ስምምነት የለም። ነገር ግን በጊዜው የተዋጣለት ነበር። ምክንያቱም በአገሪቱ ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። ይህንን የማይቀበሉ አካላት ግን አይኖሩም ተብሎ መታሰብ የለበትም። ሰላምን የማይፈልጉ በየአቅጣጫው አይጠፉም።
አንዳንድ ጊዜ ምንም እንደማይነካቸው የሚያምኑ አካላት ማለትም በምዕራቡ አገራት ከተሞች በየካፌ ውስጥ በምቾት ተቀምጠው ስምምነቱ አያስፈልግም ሊሉ ይችላሉ። ውጊያው መቀጠል አለበትም ሲሉ ይሰማል። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ በምቾት ላይ መቀመጣቸው ነው። የድሀውን ገበሬ ልጆች ስቃይ አያውቁትም፤ ወላጆቻቸውን በጦርነት ያጡ ህጻናትን አልተመለከቱም። ስለዚህም እነዚህ ህዝቡን አይወክሉም። እናም ይህንን አይነት ወሬ የሚያራግቡ አካላትን የሰላም እንቅፋት መሆናቸውን ተረድቶ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተው ሊላቸው ይገባል።
ስምምነቱን የትግራይ ህዝብ እንዴት በደስታ እንደተቀበለው በአገር ውስጥና በውጪ ሚዲያ ሲገልጽ እንደነበር ተመልክተናል። ስለዚህም ትኩረታችን መሬት ላይ ያለው ሕዝብ እንጂ ከላይ በምቾት የተቀመጠው በለንደንና በፓሪስ የተንደላቀቀው ላይ መሆን የለበትም። ለእነርሱ ግጭቱን ማራገብ ሥራቸው ነው። ሰላም መጥቷል፤ የትግራይ ሕዝብ በሰላም ተቀብሎታል። የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም በደስታ ተቀብሎታል።
አሁን ወደኋላ ልንመለስበት የሚገባ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ወደኋላ እንዲመለስ የሚፈልግ በክልሉ ከሚኖረው ግጭት ትርፍ የሚፈልግ ነው። ስለዚህም የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊሰማቸው አይገባም። በዚህ ላይ ማስመር የምፈልገው ነገር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን ይህንን ተረድቷል። እናም እነዚህ ሰዎች አሁን ድምጽ እያጡ ነው። የዓለም ሚዲያዎች ቀን በቀን ስለኢትዮጵያ የግጭት ዜናዎች ይዘው ይወጡ ነበር።
ከግጭት ብዙ ትርፍ የሚያስገኙ ዜናዎችንም ሰርተዋል። ግጭቱን ተከታትለው በመዘገብ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ማትረፍም ችለው ነበር። የሰላም ስምምነቱ ሲደረግ ግን እነዚህ ነገሮች ተቋረጡ። ስምምነቱ ላይ ፍላጎት አጡ። ስለዚህ ልክ ሰላም እንዲፈጠር እንደማይፈልጉት ሁሉ ለእነዚህ ዜናዎችም ትኩረት ልንሰጣቸው አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ጎን ለጎን በራስ አቅም የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ነው፤ ይህንን እንዴት አገኙት ?
አቶ ገብርኤል፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። በራስ ሀሳብ መመራት ለምንም ነገር ወሳኝነት አለው። ለራስህ ልታስቀምጠውና ልታሳካው የምትፈልገውን ግብ ማንም ሳያቅድልህ መከወን ለእድገት አስተማማኝ ጉዳይ ነው። በራስ መመራት ስንል ግን ዛሬ ወይም ነገ ከሌሎች ድጋፍ አንፈልግም ማለት አይደለም። ራስ የመቻል ራዕይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ይህንን ራዕይ ለአገሪቱ አስቀምጠዋል። በምግብ ራሳችንን የቻልን መሆን አለብን ብለዋል። ይህ ግብ ነው። ይህንን ነገር በዚህ ዓመት ወይም በሚቀጥለው ዓመት ልናሳካው እንችል ይሆናል። ጉዳዩ ይህ አይደለም።
አንዳንድ ሰዎች አምና በምግብ ራሳችንን እንችላለን ብለው ነበር። ግን አሁንም ከውጪ ምግብ እናስገባለን ይላሉ። ይህ ራዕይን የምንለካበት መንገድ አይደለም። ራዕይ የሚለካው በዓመታት ነው። በቀናት ወይም በወራት አይደለም። ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ግብ አስቀምጣለች። አገሪቱ 120 ሚሊዮን ሕዝብ የያዘች ነች። ህዝቡን ሁለቴና ሦስቴ በቀላሉ በመመገብ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ራስን መቻል ይቻላል ማለት አይደለም። ነገር ግን ሂደቱ ተጀምሯል። እያደ ር ደግሞ ይሳካል።
ፖሊሲዎችም ወደመሬት ወርደው እየተተገበሩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየጎበኙ ነው። እነዚህ ደግሞ ራስን ለመቻል የሚደረጉ ሂደቶች ማሳያ ናቸው። ነገር ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ ይህንን ራዕይ በአንድና በሁለት ዓመት ለመገምገምና ለመተቸት አንቸኩል። ለማሳካት የሚያስፈልገውን ጊዜ ያህል እንስጠው። ዋናውና አስፈላጊው ነገር በትክክለኛ መንገድ እየተጓዝን መሆኑ ነው።
እነዚህን አቅደን በአጭር ጊዜ ለማሳካት እንቅፋት የሚሆኑን ነገሮች በርካታ ናቸው። በዚህም ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ነገር ግን ፖሊሲ ተቀርጿል። ኢንቨስትመንት ተጀምሯል። ስለሆነም በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን። በቅርብ ሊሆን ይችላል ወይም ከጊዜ በኋላ በምግብ ራስን የመቻሉ ራዕይ ይሳካል።
በአገር ደረጃ የተያዘ እቅድ ነው። ጎረቤት አገራት ከዚህ መማር ያለባቸው ወይም መውሰድ ያለባቸው ልምድ የአፍሪካ አገራት በጣም ለምና ምርታማ መሆናቸውን ነው። በራሳቸው አምርተው በምግብ ራሳቸውን መቻል ይችላሉ። ኬኒያ በጣም ለም አገር ናት። ስለዚህ ኬኒያ ደቡብ ሱዳንን መመገብ የማትችልበት ምክንያት የለም። ሱዳንም እንዲሁ መላው መካከለኛው አፍሪካን መመገብ የማትችልበት ሁኔታ የለም። ሱዳን በስፋት ከኢትዮጵያ ትበልጣለች። ለም አፈር አላት። ሰፊ የውሃ ሀብት አላት፤ የናይል ወንዝ አንዱ ሀብቷ ነው። እናም ሱዳን ከውጪ ምግብ ሳታስገባ እነዚህን አገራት መመገብ የማትችልበት ምክንያት ምንም አይኖርም።
የአፍሪካ አገራት ያለውን አንጻራዊ ጥቅም በማስተዋል ራስን ችሎ ራስን በራስ የመመገብ ብቃትን ሊያዳብሩ ይገባል የሚለው መውሰድ ያለባቸው ነገር ነው። ይህ ማለት ግን ምዕራባውያን አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ቴክኖሎጂያቸው ያስፈልገናል፤ የገንዘብ ድጋፋቸው ያስፈልገናል፤ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ወርልድ ባንክን ጨምሮ ድጋፋቸው ሊኖር ግድ ነው። ሌሎች አገራት ላይ ተግባራዊ ያደረጉበትን ልምድ ከእነርሱ መውሰድ አለብን። ነገር ግን ከእነርሱ ጋር የምንገናኝበት መንገድን ማጤን ያስፈልጋል። በጉዳዩ ምን ድረስ እንደሚገቡ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። በእነርሱ ላይ እድሜ ልካችንን ጥገኛ መሆን አያስፈልግም።
በከፍተኛ ሁኔታ ከጥገኝነት ለመላቀቅ መስራት ግድ ነው። በራሳችን መስራት የምንችለውን በራሳችን መስራት ይገባናል። ከዚያ ያለፈውን ደግሞ የተለያዩ የዓለምአቀፍ ማህበረሰብና የዓለም የገንዘብ ተቋማት አብረውን እንዲሰሩ ማድረግ አለብን። ራሳችንን ችለናልና ምዕራባውያን አያስፈልጉንም ልንል አንችልም። ለገበያ እንኳን ያስፈልጉናል። ለምሳሌ፡- ኢትዮጵያ ስንዴ አመረተች ከዚያ ግን የተመረተው ምርት ወደ ገበያ መግባት አለበት። ይህንን ገበያ ደግሞ በምዕራባውያን አገራት ጭምር መጠቀም ካልቻልን ዋጋው አናሳ ነው። ዶላርን እንደልብ ማግኘት አንችልም። ስለሆነም የእነርሱን የገበያ አማራጭ መጠቀም ግድ ነው። እናም ራስን መቻል ማለት ራስን መጠበቅ ተጨማሪ ማምረት ነውና ይህንን ማድረግ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያውያን ምን መልዕክት አለዎት?
አቶ ገብርኤል፡- በአገራችን ሰላም በመምጣቱ ኢትዮጵያ ወደ መልሶ መገንባቱ ገብታለች። በዚህም ሁሉም ደስተኛ ነው። እናም እንደ ሕዝብ መደረግ ያለበት ያለፉትን ሁለትና ሦስት የጦርነት ዓመታት ማስታወስ ሳይሆን ዛሬ ያለንበትን የሰላምና የደስታ ጊዜ ማጣጣም ነው። የዛሬዋን ደስተኛ ኢትዮጵያን በማሰብ ወደፊት መራመድ ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ከፍታ ለማሸጋገር ሊሰሩ ይገባል። በሁሉም የአገሪቱ ክልል ሰላም ማምጣት መቻል አለብን። ምክንያቱም አሁንም እዚያም እዚህም ግጭቶች አሉ። እነዚህን ፈትተን ለአገራችን እድገት መስራት ይጠበቅብናል። ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነውና እርሱን በመስራት ማሸነፍ አለብን። መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አምነንም ዘወትር ልንተጋ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከጎናችን ሊቆም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊና ጠቃሚ ሀሳብ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ስም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
አቶ ገብርኤል፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015