
የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስትራቴጂክና ኢንቨስ ትመንት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገመቹ ይመር ናቸው። ከሥራ አስፈጻሚው ጋር ባደረግነው ቆይታ የተቋሙን የእዚህ ዓመት አፈጻጸም፣ በደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን፣ አሠራሮችን ለማዘመን እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ተመልክተናል።
አዲስ ዘመን፡- እያገባደድን ያለነው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸማችሁ ምን ይመስላል?
አቶ ገመቹ፡– በ2017 የበጀት ዓመቱን ስትራቴጂና ዓመታዊ ዕቅድ አዘጋጅተን ነው ዓመቱን የጀመርነው። በእዚህም ተቋማችንን ወደፊት ለማሻገር፣ ተገልጋዮቻችንን በተሻለ ደረጃ ለማገልገል እና ለሀገራችን ኢኮኖሚ የበለጠ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዋና ዋና ግቦችን ወጥነን ነው ወደ ሥራ የገባነው። ከሞላ ጎደል ዋና ዋና ዕቅዶቻችንን እያሳካን ያለንበት በጀት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የተቋሙን ዓመታዊ የንግድ ሽያጭ ገቢ ማሳደግ አንዱ ግባችን ነበር። ከእዚህ አኳያ እስከ ሚያዚያ ወር ባለው ጊዜ ብቻ የእቅዳችንን 99 በመቶ አሳክተናል። በበጀት ዓመቱ ስድስት መቶ ሺህ ያህል አዲስ ደንበኞችን ለማስተናገድ አቅደን የነበረ ሲሆን፤ እስከ ግንቦት መጨረሻ 440 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል። በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የዕቅዳችንን 80 በመቶ እናሳካለን ብለን እናስባለን።
ባለንበት በጀት ዓመት ከግሪል ብቻ 140 የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ነበር እቅድ የያዝነው። እስከ ሚያዚያ 30 ድረስ ባለው አፈጻጸም 130 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል። የበጀት ዓመቱ ሲቋጭ እቅዳችንን መቶ በመቶ እናሳካለን ብለን ነው የምናምነው። ከእዚህ ባሻገር ከግሪል በራቁ የመንገድ ችግር ባለባቸውና የመሬት አቀማመጡን መስመር ለመዘርጋት ምቹ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከሌላ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ኤሌክትሪክ ለመስጠት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በእዚህም አምስት የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ወደፊትም ከግሪል የራቁና በግሪል ለማድረስ በጣም ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡትን አካባቢዎች ለመድረስ እንደ አማራጭ የምንጠቀመው የፀሐይ ግሪሎችን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ያጋጠማችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ?
አቶ ገመቹ፡- ኅብረተሰባችን ጥራቱን የጠበቀ የማይቆራረጥ ኃይል ማግኘት ይፈልጋል። የአገልግሎት ጥራት ችግር አሁንም ድረስ ያልተሻገርነው ተግዳሮታችን ነው። ለኃይል መቆራረጡ ዋናው ምክንያት የመሠረተ ልማቱ ማርጀት ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ሥራ እየሠራን ነው ያለነው። በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች መስመር ውስጥ የገቡ በርካታ ዛፎችና ቅርንጫፎች አሉ። በእኛ ስታንዳርድ አንድ ማሰራጫ መስመር ላይ ያሉ ነገሮች ቢያንስ ሦስት ሜትርና ከእዚያ በላይ መራቅ አለባቸው። እውነታው ሲታይ ግን ኅብረተሰባችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መስመሮች ላይ ዛፍ የመትከል ልምድ አለው። ጭራሽ ምሶሶውን የቤት አካል ማድረግም አለ። ኅብረተሰባችን የሚያውቀው ኤሌክትሪክ መጥፋቱን እንጂ መንስኤው መልሶ ከራሱ ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ መኖሩን አያጤነውም። እነዚህ እንቅፋቶች መኖራቸው ለምናየው የኃይል መቆራረጥ እንደ መንስኤ የምንወስዳቸው ነገሮች ናቸው።
ይህን ችግር ለመቅረፍ አዲስ አበባ ላይ መስመር ላይ ያሉ ዛፎችንና ቅርንጫፎችን በስፋት ያነሳንበት ሁኔታ አለ። ያረጁ መስመሮችን ቅድመ ጥገና ሠርተናል። ያረጁ ኮንዳክተሮችን ወጥረናል። በእዚህም አዲስ አበባ ላይ ብዙ ለውጥ አይተናል። በከተማዋ ላይ ያለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ የመቶ ቀን ዕቅድ አቅደን ነው የተነሳነው። እቅዱ ግንቦት ላይ ነው የተጠናቀቀው። በሠራነውም ሥራ ውጤት አይተንበታል። እንደ ፓይለትም እየተጠቀምንበትም ነው። ክረምት ተጠናክሮ ከመግባቱ በፊት በሁሉም ክልል ከተሞች ለመሥራት ገብተናል። እንደ አጭር ጊዜ መስመር ውስጥ የገቡ ዛፎችን በመቁረጥ የረገቡ ኮንዳክተሮችን በመወጠር የኃይል መቆራረጡን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እየሠራን ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር በአገልግሎት አሰጣጣችሁ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ይመስላል?
አቶ ገመቹ፡- በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ተቋማችን በዓመቱ አከናውናቸዋለሁ ብሎ ያቀዳቸው ሥራዎች ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሯል። ሰው የተገለገለበትን ክፍያ በአግባቡ መሰብሰብ አይቻልም። ብልሽት ተከስቶ ኅብረተሰቡ አገልግሎት ተቋርጦበት ሄዶ ለመጠገን ፈተና ነው። ሆነ ተብሎ ይሁን በሌላ መልኩ ከፍተኛ ውድመት ይደርሳል። ኤሌክትሪክ የሚሰራጭበት ምሶሶ ተቆርጦ የሚጣልባቸው አካባቢዎች አሉ። እንዲህ ያለው ተግባር ኅብረተሰቡ ኃይል እንዲቋረጥበት ያደርጋል፤ ተቋሙ ደግሞ ባላስፈላጊ የጥገና ወጪ ለኪሳራ ይዳርጋል። ይሄ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች አገልግሎቱን ለማስፋፋት የምናደርገውን እንቅስቃሴ ስለሚጎዳብን ተጽእኖው ከባድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኃይል ሆነ ብሎ በማቋረጥ ኅብረተሰቡን ያልተገባ ክፍያ መጠየቅን ጨምሮ የተለያዩ ብልሹ አሠራሮች አለ በሚል ከዜጎች የሚቀርብ ወቀሳ አለ። ችግሮቹ መኖራቸውን የምታምኑ ከሆነ ምን ዓይነት የመፍትሔ ርምጃ እየወሰዳችሁ ነው?
አቶ ገመቹ፡- አፌን ሞልቼ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች የሉም ማለት አልችልም፤ አሉ። ኅብረተሰባችንም እየነገረን ነው። በተለያዩ ሚዲያዎችም እንሰማለን። ተቋማችን ችግሮቹን ለመቅረፍ ብዙ ሥራ እየሠራ ነው። አንዱ መንገድ የሪፎርም ሥራ ነው። የሪፎርም ሥራችን ሦስት ነገሮች ላይ ነው የሚያተኩረው።
የመጀመሪያው ሰውን ማብቃት አመለካከቱን መቀየር ክህሎቱን ማሳደግ ነው። ሁለተኛው አደረጃጀታችንን በማስተካከል ለሕዝቡ ቅርብ ለመሆን እየሠራን ነው። አሁን ማዕከላዊነትን ስላስቀረን በክልል ከተሞች በሙሉ ሪጂኖች አሉን። በእነዚህ በሙሉ ራሱን የቻለ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት እንዲኖር አድርገናል። ሦስተኛው ሲስተም ነው። የአሠራር ሥርዓታችን ጉራማይሌ ነበር። በአንድ የአገልግሎት ዓይነት ድሬዳዋና አዲስ አበባ የነበረው አሠራር ይለያይ ነበር። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ አዲስ ደንበኛን ተቀብሎ አገልግሎቱን ሰጥቶ እስኪጨርስ የሚከተለው መንገድ ሌላ አካባቢ ላይ ካለው የሚለይ ነበር። አሁን ይህን ችግር ቀርፈን የእያንዳንዱ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት በሀገር ደረጃ ወጥ እንዲሆን አድርገናል።
ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ሌላው የተከተልነው አማራጭ ቴክኖሎጂን መጠቀም ነው። የአሠራር ሥርዓታችንን ዲጂታላይዝድ በማድረግ አገልግሎት ሰጪውና ተቀባዩ በአካል የሚገናኙበትን ዕድል በመቀነስ ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራን ነው። አሁን የምንሰጣቸው አብዛኞቹ አገልግሎቶቻችን በቴክኖሎጂ የተደገፉ ናቸው።
ሙስናን ድሮ በነበረው ዓይነት የቅሬታ አቀራረብ ሳጥን ወይም ቅሬታ የሚጻፍበት መዝገብ አስቀምጠን መከታተል አንችልም። ስለዚህ ሞባይል መተግበሪያ ፈጥረን ወደ አገልግሎት አስገብተናል። መተግበሪያውን ተጠቅመው 80 ያህል ቅሬታዎች ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ እየተጣሩ ያሉ ችግሮች አሉ። አሁን ስልክ ያለው ሰው ሁሉ መጠቆም ይችላል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ አውቆ እንዲገለ ገልበት ምን ያህል አስተዋውቃችሁታል?
አቶ ገመቹ፡– በሁሉም ሚዲያዎች በፕራይም ሰዓት ጭምር የማስተዋወቅ ሥራዎች ሠርተናል። በቂ ነው የሚል ግምገማ ግን የለንም። አሁንም በማስተዋወቁ እንገፋበታለን። በእዚህ አጋጣሚ አዲስ ዘመንም ያስተዋውቅልናል ብለን እናምናለን። መተግበሪያው ጎግል ፕሌይ ላይ ይገኛል። ሁሉም ሰው አውርዶ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ደንበኞች የተጋነነ እና ዝቅተኛ ሂሳብ የሚጠየቁበትን ሁኔታ ለመግታት ቴክኖሎጂን መጠቀም መፍትሔ አይሆንም ?
አቶ ገመቹ፡– ትክክል ነው። ችግሩን ልንቀርፍ የምንችለው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ነው። ለከፍተኛ ተጠቃሚዎች የተገበርነው ስማርት ሜት የሚባል አሠራር አለ። ዛሬ ላይ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆቴሎች እና የንግድ ተቋማትን የመሰሉ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞቻችን ቁጥራቸው ከ42 ሺህ በላይ አልፏል። ስማርት ሜትድ የተባለው ቆጣሪ አንባቢ ሳይሄድ የደንበኛውን ወርሃዊ ፍጆታ ወደ ማዕከል ይልካል። መቶ በመቶ ስኬታማ የሆነ ሥርዓት ነው። ተገልጋዮች የኃይል ስርቆት ለመፈጸም አስበው ቆጣሪያቸውን የሚነካኩ ከሆነ ቆጣሪው የስርቆት ሙከራ መደረጉን የሚገልጽ መረጃ ወደ ማዕከል መረጃ ይልካል። ከአንድ ማዕከል ተቀምጠን እያንዳንዱ ቆጣሪ ብልሽት ሲገጥመው በቀላሉ ማወቅ የምንችልበትን ሥርዓት ዘርግተናል። እስከ 2030 ባለው ጊዜ ያሉንን ደንበኞች በሙሉ የእዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅደን እየሠራን ነው። በእዚህም የኃይል ብክነትን ጨምሮ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ እንችላለን ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች ተቋሙ ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ገመቹ፡– ለጊዜያዊ ጥቃቅን ጥቅም ብለው የመሠረተ ልማቱን አካል ቆርጠው የሚወስዱ አሉ።
ለምሳሌ በብረት ከሚሠሩ ኃይል ተሸካሚዎች ላይ ቀጫጭን ብረቶችን ፈትቶ ወስዶ በመሸጥ ስርቆት ይፈጸማል። ትራንስፎርመር ጥሎ ከውስጡ መዳቡን የመስረቅ ነገር አለ። መስመር ተበጥሶ ሽቦ ተቆርጦ ይወሰዳል።
ችግሩን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረቶች እያደረግን ነው። በዋናነት መሠረተ ልማቱ የሕዝብ ስለሆነ ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍል ሲጠብቀው ነው ለዘለቄታው ችግሩን መቀነስ የሚቻለው። የትኛውም መሠረተ ልማት የእዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የቀጣዩም ትውልድ ሀብት ነው። እየተፈጸሙ ያሉት ስርቆቶች የተቋሙን የፋይናንስ አቅም እየፈተኑ ነው። እዚህ ላይ ኅብረተሰቡም የሚዲያ አካላትም በጋራ ተረባርበው ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዓመታት በፊት የተጀመረው ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ምን ያህል ስኬታማ ሆኗል?
አቶ ገመቹ፡– ፕሮግራሙ በ1998 ዓ.ም በመንግሥት ተቋቁሞ ነው ወደ ሥራ የተገባው። እስካለንበት ጊዜ ድረስ አዲስ አበባን ጨምሮ ከ8329 ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል። ፕሮግራሙ ከጀመረ ጊዜ ወዲህ እንኳን ከ7600 በላይ የዞን እና የወረዳ ከተሞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል። ቁጥሩን ብቻ ብንመለከተው ትልቅ ስኬት ነው የተገኘው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዜጎቻችን ጨለማ ውስጥ ስለሆኑ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን የኃይል አስተላላፊ መሠረተ ልማት ችግር እንጂ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንደሌለ ይገለጻል። ምን ማለት ነው?
አቶ ገመቹ፡– በሀገራችን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት 54 በመቶ ነው ማለት የማሰራጫ መስመሩ ሁሉም ሰፈር አልደረሰም ማለት ነው። ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቢጠናቀቅም የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሁሉም ቀዬ ካልደረሰ በቀር እያንዳንዱ አካባቢ በቀጥታ ኤሌክትሪክ ያገኛል ማለት አይደለም። ግን የጊዜ ጉዳይ ነው። ግድቡን ለመገንባት ኢንቨስት እንዳደረግነው ሁሉ በማሰራጫ መስመሮች ላይ ደግሞ ኢንቨስት አድርገን በእያንዳንዱ ቀበሌ መስመሩን ካደረስን በማግስቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙበት ምክንያት የለም።
ሰዎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እና የማመንጨት አቅም ይምታታባቸዋል። ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚገኘው ኃይል፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በተዘረጋባቸው አካባቢዎች ብቻ ነው ተጨማሪ ኃይል ማድረስ የሚቻለው እንጂ ግድቡ ስለተጠናቀቀ ብቻ የመሠረተ ልማት ዝርጋታው በሌለበት በመላው ኢትዮጵያ ኃይል ማዳረስ አንችልም። የምናመነጨው ኃይል የራሳችንን ፍላጎት አሟልቶ ይተርፈናል። የሚተርፈውን ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እናገኝበታለን።
የምናመጨው ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሌለባቸው አካባቢዎች እንዳይደርስ ያነቀው እያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ መስመሩ ስላልደረሰ ነው። ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዙ ነው። አንዱ አሁንም ድረስ መንገድ የሌላቸው በርካታ ቀበሌዎች አሉ። በመልክዓ ምድር አቀማመጣቸውም ተራራ፣ ገደል፣ እና ቋጥኝ የሚበዛባቸው ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች አሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችን በሚፈለገው መልኩ ለማሳለጥ የመንገድ መሠረተ ልማት መቅደም አለበት። ኤሌክትሪክ መስመር ስንዘረጋ የኮንክሪት ምሶሶ ነው የምንጠቀመው፤ ትናንት ተተክሎ ዛሬ ምስጥ በልቶት የሚበሰብስ የእንጨት ምሶሶ ብዙም አይመከርም። ኮንክሪት የሆነ ቦታ ደርሶ ለመትከል ደግሞ ክሬን ያስፈልጋል። መንገድ ከሌለ ክሬን እዚያ ቦታ መድረስ አይችልም።
ለእነዚህ አካባቢዎች መፍትሔ የለም ማለት አይደለም። ከሌሎች ታዳሽ ኃይሎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። በተለይ ሰብሰብ ብለው የሚገኙ ነዋሪዎች ባሉበት አካባቢ አንድ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በመትከል የማሰራጫ መስመር በመዘርጋት ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል።
አንዱ አስቸጋሪ ነገር ሰዎች እርሻቸውን ተከትለው ተበታትነው መስፈራቸው ነው። አንድ ሰው እዚህ ካገኘህ ሌለውን ሰው ምናልባት ከአንድ ኪሎ ሜትር ወይም ከ500 ሜትር በኋላ ይሆናል የምታገኘው። እነዚህን ዜጎች እያንዳንዳቸውን እንድንደርስ ብንል ኢኮኖሚካል ውጤታማ አያደርገንም። ስለዚህ በተናጠል ቤታቸው ላይ ሶላር በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ወደፊት አቅም ተፈጥሮ የኃይል ማሰራጫ መስመሮች ሲስፋፉ ተጠቃሚ እየሆኑ ይሄዳሉ።
አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪው በዝቷል በሚል የሚሰሙ ቅሬታዎች ላይ እናንተ ያላችሁ ግምገማ ምንድን ነው?
አቶ ገመቹ፡- ቀደም ያለው ታሪፍ በሥራ ላይ የቆየው ከ 12 ዓመት በላይ ነው። በእዚህ ሁሉ ጊዜ ተቋሙ የሚያወጣውን ወጪ እየሸፈነ አልነበረም የሚሠራው። በነበረው ታሪፍ አገልግሎት ሲሰጥ ያገኝ የነበረው ታሪፍ ለኦፕሬሽን የሚያወጣውን ወጪ የሚሸፍን አልነበረም። ስለዚህ በድጎማ ነበር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው። በጊዜ ሂደት ተቋሙ ወጪውን መሸፈን አቅቶት ኔጌቲቭ ውስጥ ሲገባ ነው ታሪፉን ያስተካከለው።
ተቋሙ ወጪውን መሸፈን ካቃተው አገልግሎት የለም ማለት ነው። የጥገና ጥያቄን ማስተናገድ፣ አዳዲስ መስመሮችን መዘርጋት፣ አገልግሎትን ማዘመን እና ጥራቱን ማስጠበቅ አይችልም ማለት ነው። እነዚህን ሥራዎች ካልሠራ ደግሞ የተቋሙ ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ተቋሙ የለም ማለት ደግሞ የሀገሪቱን ልማት መደገፍ አይቻልም ማለት ነው። ስለዚህ ትክክለኛ በሚባል ጊዜ ላይ መንግሥት የታሪፍ ማሻሻያውን አድርጓል።
ጭማሪው የተደረገውም በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው። ታሪፍ ገና ጅምር ላይ ነው ያለው። ተተግብሮ የሚያልቀው በቀጣይ አራት ዓመታት ነው። በእዚህ በጀት ዓመት የተገበርነው የታሪፍ ጭማሪ እንኳን 18 በመቶ ብቻ ነው ወጪያችንን የሚሸፍነው። ወጪያችንን መመለስ የምንችለው ከአራት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ትግበራው ሲጠናቀቅ ነው። ስለዚህ የታሪፍ ጭማሪው የተደረገው የተቋሙን ትርፋማነት ለመጨመር ተብሎ ሳይሆን ወጪውን መሸፈን እንዲችል ነው።
ታሪፉ ሲተገበር ደግሞ አቅመ ደካማ፣ ገቢያቸው በጣም ዝቅተኛ ለሆኑ በወር አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚጠቀሙ ዜጎቻችን ድጎማ ተደርጓል። ዝቅተኛ ፍጆታ ላላቸው ሰዎች ከቀድሞ ታሪፍ የተለየ ክፍያ እየጠየቅን አይደለም። ጭማሪው የታየው አቅም ባላቸው ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በኃይል ለመተሳሰር የጀመረችው ጉዞ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ገመቹ፡- ሀገራችን ወደፊት ብሩህ የሆነ ተስፋ አላት። ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከቡና፣ ከወርቅ እና ከጥሬ ዕቃ ንግዶች ብቻ አይደለም። ከኃይል ኤክስፖርትም ጭምር ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ 13 ሀገሮች ጋር የኤሌክትሪክ ትስስር እንዲኖራት ለማድረግ እየተሠራ ነው ያለው። ይሄን ውጥን ኤሌክትሪክ ኤክስፖርት አድርገን ከምናገኘው የውጭ ምንዛሪ አንጻር ብቻ ማየት አያስፈልግም። ጂኦ ፖለቲክሱን የተለሳለሰ በማድረግ ረገድም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የአፍሪካን ምሥራቅ ክፍል ሰላማዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ምክንያቱም ዲፕሎማሲው የሰጥቶ መቀበል መርህን የሚከተል ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት ሀገራት በአንጻራዊነት ርካሽ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ያላት ኢትዮጵያ ናት። በእዚህ ምክንያት በቀጣናው ያሉ ሀገራት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከመንቀሳቀስ ይልቅ ከኢትዮጵያ ኃይል መግዛት ይቀላቸዋል። አንድ ጊዜ ደግሞ የኃይል አቅርቦቱ ተጀምሮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ማግኘት የጀመረ ሀገር ከኢትዮጵያ መጋጨትን ስለማይመርጥ ወንድማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውሃ ብቻ ከ45 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት። የአፍሪካ የውሃ ማማ ነው የምትባለው። ይሄንን ሁሉ ኃይል ማመንጨት የምንችልበት ደረጃ ላይ ስንደርስ የት እንወስደዋለን? ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አልፈን ወደ ደቡብ አፍሪካ እና አውሮፓ ጭምር መላክ እንጀምራለን።
አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሪካ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የሚገኘው ገቢ መልሶ ለአገልግሎቱ ይውላል?
አቶ ገመቹ፡– በሀገራችን ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትልቁና ዋነኛው ነው። የኃይል ማመንጨት አቅማችን ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ደርሷል። ከውሃ ብቻ የምናመነጨው የኃይል አቅም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን አርክቶ ይተርፈናል። በእዚህ ጊዜ በስትራቴጂ መልክ የተያዘው ያለውን ትርፍ ኃይል ኤክስፖርት ማድረግ ነው።
የሀገርን ፍላጎት ለማርካት ተብሎ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቻችን ሃያ አራት ሰዓት ይሠራሉ። ውሃ መፍሰሱና ኤሌክትሪክ ማመንጨቱ ስለማይቀር ትርፉን ኃይል ኤክስፖርት ካላደረግነው ይባክናል። ስለዚህ ለጎረቤት ሀገሮች እንሸጣለን። በአንድ መልኩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ሀገራችን ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናክራል። ኤክስፖርት የምናደርገው በዶላር ስለሆነ የሚመጣው ምንዛሪ በተለያየ ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኙ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ እናውለዋለን።
በኃይድሮ ዶላር ካገኘን ከግሊር በጣም የራቁና ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችንን በሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እናደርጋቸዋለን። ስለዚህ ጉዳዩ ሀገራችንን አስርቦ ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሚዋዥቅ ወርሃዊ የክፍያ ሂሳብ ይመጣብናል በሚል ተገልጋዮች የሚያቀርቡት ቅሬታ አለ። ችግሩ የሚፈጠረው በምን ምክንያት ነው?
አቶ ገመቹ፡– ለችግሩ መፈጠር መንስኤ የሚሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉ። እኛም እንደ ተቋም ያለብን የአቅም ውስንነት አለ። የምናካሂደው የቆጣሪ ንባብ መቶ በመቶ ትክክል ነው ማለት አልችልም። የንባብ ችግር የሚፈጠረው በተለያየ መልኩ ሊሆን ይችላል። አንደኛ ራሱ ሠራተኛው ባለው ችግር ነው። ሁለተኛ አንዳንድ ቤቶች ዝግ የሚሆኑበት ወይም ውሻ የማያስገባበት ቤት አለ። እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ቆጣሪው ካልተነበበ ሲስተሙ የራሱን ግምት ይወስዳል ወይም አንባቢውም የራሱን ግምት ሞልቶ ተገልጋዩ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ወይም የተጋነነ ክፍያ እንዲከፍል ሊጠየቅ ይችላል። ችግሩ ሲፈጠር ደንበኞች ክፍያው በዝቶብኛልም ሆነ አንሷል ጤናማ አይደለም ብለው ከመጡ ታይቶ ይስተካከላል።
አዲስ ዘመን፡- በኃይል ዙሪያ ከሚሠሩ ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት ረገድ ያላችሁ ልምድ ምን ይመስላል?
አቶ ገመቹ፡– ያለንበት ዘመን ከምንጊዜውም በላይ ተቋማት ተሳስረው እየሠሩ የሚገኙበት ጊዜ ነው። እንደ ቀድሞ ዳርና ዳር ቆሞ ድንጋይ መወራወሩ አክትሞ ተቀናጅቶ፣ ተመካክሮና ተነጋግሮ የሚሠራበት ጊዜ ነው። በኃይል ጉዳይ ባለቤቶች ከሆኑ ተቋማት ጋር በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አስተባባሪነት ተቀናጅተን የምንሠራበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለጥያቄዎቻችን የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ገመቹ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም