ጦርነት የቱን ያህል አስከፊ እንደሆነ ለኛ ኢትዮጵያውያን ነጋሪ አያስፈልገንም። የዛሬ ብቻ ሳይሆን ዘመናት ያስቆጠረ ታሪካችን ሰፊ አካል ሆኖ ቆይቷልና። በየዘመኑ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ትውልዶች ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል፤ ከፍለዋልም። ከዚህ የተነሳም ድህነትና ጉስቁልና ዋነኛ መለያችን ሆነዋል።
ይህን ታሪካዊና አሁነኛ አገራዊ ችግራችንን ለዘለቄታው ለመፍታትና በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገታችንን ከሚያስደፋው ድህነት እና ጉስቁልና ለዘለቄታው ለመውጣት የለውጥ ኃይሉ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል።
አገራዊ የፖለቲካ ሽግግሩ በሰላማዊ መንገድ፤ የመላው ህዝባችን ፍላጎት የሆነውን ሰላም ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን፤ እርቅን እና ፍቅርን መሰረት ያደረገ አዲስ የፖለቲካ እሳቤ እውን በማድረግ ለተግባራዊነቱም በሆደ ሰፊነት ረጅም ርቀት ተጉዟል።
እንደ አገር ከመጣንበት የሽግግር ወቅት ፖለቲካ አንጻር አዲሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በተለያዩ ወገኖች ከተሰጠው የተሳሳተ አረዳድ የተነሳ፤ ከታሰበው ይልቅ ያልታሰበው፤ ተስፋ ከተደረገው አዲስ ብርሀን ይልቅ በቀደመው የፖለቲካ አስተሳሰብ ፈተናዎችን ለማለፍ ተገድዷል።
ከዚህ የተነሳም ላለፉት አራት ዓመታት በመላው አገሪቱ ግጭቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ ግልጽ የሆነ የጦርነት አዋጅ እስከ ማወጅ የደረሱ ተግዳሮቶች አጋጥመውናል። በዚህም መላው ሕዝባችን ከፍ ያለ ያልተገባ ዋጋ ከፍሏል።
በመላው አገሪቱ የተስተዋሉት ግጭቶች እና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ካስከተለው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ባለፈ፤ አገርን እንደ አገር የህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት መንገጫገጭ አስከትሎ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም።
ይህንን ሁሉ አገራዊ ፈተና ከመላው ሕዝቡ ጋር የተጋፈጠው መንግስት፤ ከጅምሩ ይዞት ለተነሳው ሰላም ቁርጠኛ በመሆን፤ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ኃላፊነቱን ቀድሞ በመውሰድ ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር የሚገባበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ችሏል።
ይህን ተከትሎ አፍሪካ ህብረት በዋንኛነት የአደራዳሪነት ሚናውን በመውሰድ፤ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋር በመሆን የደቡብ አፍሪካው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ተደርጓል። ይሕንንም ተከትሎ በፌደራል መንግስት ብዙ ተጨባጭና ተስፋ ሰጭ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
የፌደራል መንግስት ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ርዳታዎችና ድጋፍ ያለ ገደብ ለማስገባት፤ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፤ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን የገባውን ቃል ለመፈጸም፤ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ ባለው አቅም፤ ከአቅምም በላይ በዘመቻ ስኬታማ ስራዎችን ሰርቷል፤ እየሰራ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን ባለው ሂደት ከ113ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ እህል ወደ ክልሉ ገብቷል፤ በክልሉ አብዛኞቹ ከተሞች በጦርነቱ የወደሙ የስልክ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በከፍተኛ ወጪ ተጠግነው ወደ ስራ ገብተዋል። ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በዚህም በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረው እፎይታ ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ በረራ ጀምሯል፤ 61 የባንክ ቅርንጫፎች ወደ ስራ ገብተዋል። የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣንም ግጭት በነበረባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ነዳጅ የሚያከፋፍሉ 14 ኩባንያዎች በቀጥታ ከጅቡቲ ነዳጅ እንዲጭኑ ፈቅዷል፡፡
መንግስት በስምምነቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የገባቸውን ቃሎች ከሞላ ጎደል ተግባራዊ በማድረግ በክልሉ ሕይወት ወደ ቀድሞ ስፍራው የሚመለስበትን የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛል። ሕዝቡም ጦርነቱ ከፈጠረው ጽልመት እየወጣ ብርሃን ማየትና በተመለከተው ብርሃንን የጦርነትን አስከፊነት በአደባባይ እየመሰከረ ይገኛል።
የጦርነት አስከፊነት ከሚያስከትለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባልተናነሰ መንገድ፤ ቤተሰብን በመለያየት የእለት ተእለት ህይወታቸው የጣር ሕይወት እንዲሆን የሚያስገድድ መሆኑንም፤ በጦርነቱ ምክንያት ተለያይተው የነበሩ የከልሉ ነዋሪዎች ሲገናኙ የነበረው የስሜት ሲቃ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ከፍ ባለ የመንግስት ቁርጠኝነት እየተጓዘ ያለው የሰላም ስምምነቱ፤ ቀደም ባለውም ጊዜ ከነበረው የመንግስት የሰላም መሻትና ቁርጠኝነት አንጻር የመንግስት አዲስ የጉዞ አቅጣጫ ባይሆንም፤ የተፈጠረውን እድል ፈጥኖ ለመጠቀም እየሄደበት ያለው መንገድ እውቅና ሊቸረው፤ በመላው ሕዝባችን ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባ ነው።
ይህ የመንግስት የሰላም ቁርጠኝነት ከጦርነት ማግስት የተፈጠረ ሳይሆን፤ ለሰላም ካለው ጽኑ እምነት የመነጨ፤ ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ እንደ አንድ የፖለቲካ መርህ ሲከተለው የነበረ፤ በተግባርም በተጨባጭ ያረጋገጠው፤ በአስቸጋሪ ወቅቶች ሳይቀር ብዙ ዋጋ ከፍሎ የተጓዘበት መንገድ ነው !
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015