በግብርና ልማት ውስጥ የአርሶ አደሩ ድርሻ ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከአርሶአደሩ ጀርባ ሆነው ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ በማቅረብ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ፣ ለግብርና ምርቶች ገበያ በማፈላለግ፣ አርሶአደሩ እሴት እየተጨመረበት አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚነቱ እንዲጎለብት በማድረግ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ የሚገኙት የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኖች የሚወጡት ሚና ከፍተኛ ነው። በሥራ ጥንካሬያቸውና ወጤታማ ከሆኑት ዩኒየኖች መካከል ውጤታማ ሆኖ ያገኘነውን አንዱን ዩኒየን የስኬት አምዳችን እንግዳችን አድርገናል፡፡ ይህ ዩኒየን በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ መርከብ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን ይባላል፡፡ ከተመሰረተ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ እድሜ አስቆጥሯል፡፡ በነዚህ ዓመታት ዩኒየኑ እንደአገር በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ቁልፍ ሚና ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ጥረቱንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ስለዩኒየኑ አመሰራረትና አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው እሸቱ እንዲህ አጫውተውናል፡፡ ዩኒየኑ በሶስት ዞኖች ውስጥ ማለትም ከፊል ደቡብ ጎንደር፣ ከፊል ምዕራብ ጎጃም ዞንና የባህርዳር ከተማ አስተዳደርን የሥራ ክልል አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ካፒታሉንም ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ወደ 71 ሚሊዮን ብር አሳድጓል፡፡
ሲመሰረት ምርትና ግብዓት ማቅረብ ብቻ የነበረውን የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት፣ በአሁኑ ወቅት የሜካናይዜሽን አገልግሎት በአነስተኛ ኪራይ ለአባል አርሶ አደሮች ማቅረብ ጀምሯል፡፡ የአርሶ አደሩን ምርቶች እሴት በመጨመርም ለገበያ ያቀርባል፡፡ አንዳንዶቹንም ተጠቃሚው በሚፈልገው መንገድ ተደራሽ ያደርጋል፡፡
በተለይም የስንዴ ዱቄት ለገበያ ለማቅረብ ወፍጮ ቤት አቋቁሟል፡፡ በቀን 820 ኩንታል የስንዴ ዱቄት የማቅረብ አቅም ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡ አንደኛ ደረጃ የስንዴ ዱቄትና የስንዴ ቅንጬን ጨምሮ ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግል ፉርሽካ ያመርታል፡፡ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በቀን 160 ኩንታል የመቀየጥ አቅም ያለው ሲሆን፤ ለጥጆች፣ ለወተት ላሞችና ለሌሎችም በማቀነባበር ለአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበላቸው ይገኛል፡፡
የዩኒየኑ አባል አርሶ አደሮች በስፋት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ አኩሪ አተርና ቦለቄ በስፋት ያመርታሉ፡፡ ዩኒየኑ በአገር ውስጥ ያለውን ገበያ በመጠቀም ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በስፋት ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ በአገር ውስጥ በስፋት እየተቋቋሙ የሚገኙትን የማቀነባበሪያ (አግሮ ኢንዱስትሪ) ፓርኮችን መጠቀም ጠቃሚ እንደሆነ ረድተዋል፡፡ ዩኒየኑም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን ጥሬ ዕቃ እያቀረበ ሲሆን፤ እያቀረበ ካለው ግብአትም ለዘይት ምርት የሚውል አኩሪ አተር ይጠቀሳል፡፡ ለዘይት አገልግሎት ከሚውለው አተር የሚወገደው ተረፈምርት ለውጭ ገበያ በመዋል ገቢ ያስገኛል፡፡ ለቅንጬና ለዱቄት የሚውል በቆሎም በማቅረብ ዩኒየኑ እየተጠቀመ ይገኛል። ከዩኒየኑ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቡሬ አግሮ ኢንደስትሪ ግብአት በመቀበል የሚጠቀስ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አንድ የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ተጠናቅቋል፡፡ መርከብ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየንም በቆሎ ለፋብሪካው ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡
ዩኒየኑ በተመሳሳይ ባህርዳርና ቡሬ ላይ እየተገነቡ ለሚገኙት የዘይት ፋብሪካዎች ግብዓት መሆን የሚችለውን አኩሪ አተር በብዛትና በጥራት ያመርታል፡፡ ምርቶቹን በተለያየ አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የገበያ ትስስር ፈጥሯል፡፡ ምርቶቹ ከቅርበት አንጻር በዋናነት በአማራ ክልል ተደራሽ ይሁኑ እንጂ በሌሎች አካባቢዎችም ተደራሽ ናቸው። በክልሉ ከሚገኙ ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብረው ቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመሆኑ ዩኒየኑ ለፓርኩ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡
‹‹አርሶ አደሩ በዩኒየን መታቀፍ በመቻሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አግኝቷል›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ አርሶ አደሩ ምርቱን በተናጠል ከመሰብሰብና ከመሸጥ ይልቅ በጋራ ሰብስቦ ለሚፈልገው አካል ተደራሽ ማድረግ ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ከሚኖረው ምቹ ሁኔታ በተጨማሪ የሚሸጥበት ዋጋ አስተማማኝ ይሆንለታል፡፡ ዩኒየኑ ምርቱን ሲሸጥ ከሚያገኘው ትርፍም ተቋዳሽ በመሆን አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ከመንግሥት የሚገኙ አገልግሎቶችን በቀላሉ በማግኘት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል። ለአብነትም አርሶ አደሩ በተናጠል ከሚያቀርበው ጥያቄ መሰረታዊ ማህበራት የሚያቀርቡት ጥያቄ ፈጥኖ የመደመጥ ዕድል አለው። ምክንያቱም እያንዳንዱ አርሶ አደር በተናጠል የሚያቀርበውን ጥያቄ ለመመለስ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው በአደረጃጀት ሲቀርብ መንግሥትም ጥያቄውን ለመመለስ ምቹና ቀላል ይሆንለታል። ስለዚህ ጥያቄውን ለሚያቀርበው አርሶ አደርም ሆነ ጥያቄውን ለሚመልሰውና ውስን አቅም ላለው መንግሥት ምቹ የሚሆነው ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ›› እንዲሉ አበው በጋራ በመደራጀት ነው።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እህል ራስን ለመቻልና ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ዋና ተዋናይ ከሆኑት መካከል አንዱ ሆኖ የራሱን አሻራ እያኖረ ያለው ዩኒየኑ፤ የግብአት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ኋላ ቀር ከሆኑ የአስተራረስ ዘዴዎች በመላቀቅም ማሳውን በዘመናዊ መንገድ አንዲያርስ፣ ማሳውን በዘመናዊ መንገድ በዘር እንዲሸፍን፣ አዝመራውን እንዲሰበስብ የራሱን አስተዋጽ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በተለይም መንግሥት በአሁኑ ወቅት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት በስንዴ ማምረት ላይ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ችሏል፡፡
በክልሉ ስንዴን በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ዩኒየኑ ያመረተውን ጨምሮ ስድስት መቶ ሺ ኩንታል የሚደርስ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተትረፈረፈ ምርት ማምረት በመቻሉ ዩኒየኑ ከአገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሆነም አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡
ሙሉ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የመንግሥትን አቅጣጫ እየጠበቀ ያለው ዩኒየኑ፤ በመደበኛ ሥራው የአገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት በአካባቢው የሚመረተው የስንዴ፣ የበቆሎና የጤፍ ምርትን አዲስ አበባ ድረስ እየላከ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል ትርፍ የሆነውን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡ ትርፍ ምርት ካለ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የግድና አስፈላጊ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ሲያስረዱ፤ በገበያ ውስጥ የተትረፈረፈ ምርት ካለ የገበያ መውደቅ ይመጣል። የገበያ መውደቅ ካጋጠመ አርሶ አደሩ ምርቱን ዳግም የማያመርትበት ሁኔታ ይከሰታል ነው ያሉት፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ከአገር ውስጥ ፍጆታ ውጭ ያለውን ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያደርጋል፡፡ አርሶ አደሩም ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ዕድል ይፈጠርለታል፡፡ አርሶ አደሩም ምርቱን በስፋት ለማምረትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይነሳሳል፡፡ ይህም ተወዳደሪነት እንዲጨምር ያግዘዋል። በአሁኑ ወቅት በዩኒየኑ ሥር ከሚገኙ 140 መሰረታዊ ማህበራት መካከል 52ቱ በስንዴ ማምረት የተሰማሩ ስለመሆናቸው የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ የተመረተውን ስንዴ ሰብስቦ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ምርቱ የሚከማችበትን መጋዘን ማዘጋጀት አንዱ ሲሆን፤ የመጋዘን እጥረት እንዳይገጥም ዩኒየኑ መጋዘኖች ለስንዴ ብቻ አዘጋጅቷል፡፡ በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በእህል ንግድና በእርሻ ሰብል ውስጥ ሆነው አገልግሎት የማይሰጡ መጋዘኖችን ለስንዴ ምርት ማከማቻነት ዝግጁ አድርገዋል፡፡
ዩኒየኑ 101 ለሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ደምወዝ ይከፍላል፡፡ ለክልሉ አርሶ አደሮች የግብዓት አቅርቦት ተደራሽ የሚያደርገው ዩኒየኑ፤ በዓመት እስከ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ያሰራጫል፡፡ ይህ የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ መጥቶ ሲራገፍ ጀምሮ እንዲሁም በየአካባቢው ሲጫንና በአርሶ አደሩ መንደር ሲራገፍ በማውረድና በመጫን ለሚሠማሩ ከ150 እስከ 250 ለሚደርሱ የአካባቢው ዜጎችም በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ዩኒየኑ አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ ከህብረት ሥራ ማህበራትና ከንግዱ ማህበረሰብ የሚለይባቸው ባህሪያቶች አሉት፡፡ አንደኛው ለትርፍ የተቋቋመ አለመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና የራሱን ወጪ መሸፈን ስላለበት አነስተኛ ትርፍን መሰረት አድርጎ ይሠራል፡፡
ከሚገኘው ትርፍም ለማህበራዊ አገልግሎት በሚል ከአንድ እስከ አምስት በመቶ ተቀናሽ ያደርጋል፡፡ በዚህ ገንዘብም በመንግሥት አቅም ውስንነት የተነሳ ያልተገነቡ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማህበረሰቡ ይሰራል፡፡ ለአብነትም በሰሜን አቸፈር ወረዳ ጤና ጣቢያ ገንብቶ ለመንግሥት አስረክቧል፡፡ በባህር ዳር ዙሪያ ቅንባባ በሚባል ቀበሌ ለትምህርት ቤት ማስፋፊያ አራት ክፍል ያለው አንድ ህንጻ ገንብቶ በመርከብ ዩኒየን ስም አስረክቧል፡፡ በደቡብ ጎንደር ደረሀሙሲት አንበሳሜ ከተማ በአንበሳሜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የላብራቶሪ ክፍል ገንብቶ ለማህበረሰቡ አስረክቧል። በተጨማሪ ዩኒየኑ የአባል ልጆችና አቅመ ደካማ 32 ተማሪዎችን በተለያየ ጊዜ አግዟል፡፡ በዚህም ከመጓጓዣ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ወጪያቸውን በመሸፈን ለአምስት ዓመታት አስተምሮ ወደ ለቁምነገር አብቅቷል፡፡
በተያዘው ዓመትም በክልሉ የእንስሳት ሃብት ኤጀንሲ በተመረጠ ቦታ አንድ የእንስሳት ጤና ኬላ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ሠርቶ ለማስረከብ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ግንባታውም በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ይነሳ በተባለ ቀበሌ ነው የሚገነባው፡፡ ዩኒየኑ እነዚህና መሰል ተግባራትን በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በቀጣይም አሁን ያለበትን ሥራ በማስፋት በተለይም የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመከተል በድህነት ቅነሳ ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት አቅዷል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮቹ የተሻለና ዘመናዊ አርሶ አደር እንዲሆኑ፣ የተሻለ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖራቸውና ጤናቸውን የሚጠብቁ እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ ሞዴል በመሆን ድህነትን የሚታገሉ አባላት እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡ ዩኒየኑ የስንዴ ዱቄት ከማቅረብ በተጨማሪ ዳቦ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ዕቅድም አለው፡፡ የጤፍ ዱቄት ለማቅረብ የሚያስችል አቅምም እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችንም ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡
መንግሥት በምግብ እህል ራስን ለመቻል በሚያደርገው ጥረት በየአካባቢው ግብርና ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ከባንክ ብድር የማያገኝበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን አርሶ አደሮች ተደራጅተው መቆጠብ በመቻላቸው ትራክተሮችን፣ ኮምባይነሮችንና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎችን መግዛት እንዲችሉ ባንኮች ተባባሪ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማህበሩም የመንግስትን ጥረት ለመደገፍ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015