ወቅቱ ሥራ ለመቀጠር ከወዲያ ወዲህ የሚሉበትና ጊዜ የሚያጠፉበት አይደለም፤ ሥራ የሚፈጥሩበት እንጂ:: አብዛኞቹ ወጣቶች ከተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ውጭ ሥራ እየፈጠሩም በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው የምንመለከተውም በዚሁ ምክንያት ነው::
ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ውስጣቸው ያለውን ችሎታ፣ ዕውቀትና ፍላጎት ለይተው ወደ ሥራ መቀየር እየቻሉ ነው:: ወጣቶች አካባቢያቸውን አጥንተው አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ሥራ ለማዋል በሚያደርጉት ጥረት ውስጥም መንግሥት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል::
ወጣቶች ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው:: በርካታ ወጣቶች በግል የሥራውን ዓለም እየተቀላቀሉ፣ ለሌሎች ዜጎችም የሥራ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ:: ይህ ብቻ አይደለም፤ በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱም ይገኛሉ::
የዕለቱ የስኬት ገጽም ‹‹ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ ሥራ ፈጣሪ መሆንና ውስጥን አድምጦና አድምቶ መሥራት አዋጭና ተመራጭ ነው›› በምትለው በወይዘሮ ኤልሻዳይ ተካልኝ ስኬታም የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረቱን አድርጓል:: የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ያገኘችው ወይዘሮ ኤልሻዳይ፤ እንደ ማንኛውም ተማሪ በተመረቀችበት ሙያ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል አላጋጠማትም፤ ተቀጥሮ የመሥራት ውስጣዊ ፍላጎቷ አልነበራትም፤ ይህ ሁሉ ሁኔታ የተለያዩ ሥራዎችን እንድትሞካክር አድርጓታል::
ልዩ ልዩ ሥራዎችን ሞክራ አሁን በእንጀራ አቅርቦት ሥራ የተሰማራችው ኤልሻዳይ፤ የ‹‹እንደ እናት›› እንጀራ አምራች ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ናት:: ሻሸመኔ ከተማ ተወልዳ አዲስ አበባ ያደገችው ኤልሻዳይ ፣ በመደበኛነት ካገኘችው ዲግሪ በተጨማሪም በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ጠቃሚ ናቸው የተባሉ የተለያዩ የሶፍትዌር ስልጠናዎችን ተከታትላ የምስክር ወረቀቶችንም አግኝታለች:: ይሁንና የምስክር ወረቀቶቹም ልክ እንደ ዋናውና በመደበኛነት ተምራ ያገኘችው ዲግሪ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩላት አልቻሉም::
ኤልሻዳይ ሥራ እስኪገኝ በሚል እጅና እግሯን አጣጥፋ አልተቀመጠችም:: በሙያዬ ካልሰራሁ ብላም አልተቀመጠችም:: ከዛ ይልቅ የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ጥረቷን ትቀጥላለች::
ላርጎ ወይም ፈሳሽ ሳሙና የማምረት ሥራ የመጀመሪያ ምርጫዋ እንደነበር ያስታወሰችው ኤልሻዳይ፤ በወቅቱ ስልጠናውን ወስዳ ወደ ማምረት ገብታ እንደነበርም ትናገራለች:: ሥራውም ጥሩና አዋጭ እንደነበር ታስታውሳለች::
ሥራው ትልቅ ካፒታልና ሰፊ የማምረቻ ቦታ እንደሚጠይቅ ትናገራለች:: ይህን ማግኘት ከመሆኑ በተጨማሪ ለሳሙና ምርት አስፈላጊ የሆነው ኬሚካል ለጤናዋ ምቹ አለመሆኑ ሥራውን መቀጠል እንዳትችል አድርጓታል። በዚህ ምክንያት ሌሎች የሥራ አማራጮችን ማማተር ቀጠለች:: በመሀል ከተማረችው ሙያ ውጭ መረጃ (Data) የማሰባሰብ ሥራን በኮንትራት ትሰራ እንደነበር አጫውታናለች::
‹‹ተቀጥሮ መሥራትን ሙሉ ለሙሉ ከውስጤ አውጥቼ የራሴን ሥራ መፍጠር እንዳለብኝ ሁሌም አስብ ነበር›› የምትለው ኤልሻዳይ፤ እንጀራ አምርቶ ማቅረብ ከመጀመሯ አስቀድማ ስልጠናዎችን እንደወሰደች ትናገራለች:: ስልጠናዎቹም ምን መሥራት እንዳለባት እንዳመላከቷት ጠቅሳ፣ በውስጧ ያለውን የሥራ ተነሳሽነት ተጠቅማ ብዙ አስባ፣ አውጥታና አውርዳ እንጀራ ሥራ ላይ ማረፏንና ይህም ትክክለኛ ውሳኔዋ እንደሆነ ትናገራለች:: ምክንያቱም እንጀራ ሁልጊዜ ተፈላጊና የኢትዮጵያውያን የምግብ ሁሉ ቁንጮ መሆኑን ገልጻለች::
‹‹የምግብ ሥራ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ይፈለጋል:: በተለይም እንጀራ ከኢትዮጵያውያን ማዕድ የማይጠፋ እንደመሆኑ ሥራው አዋጭና ተመራጭ ነው›› የምትለው ኤልሻዳይ፤ በወቅቱ በኮንትራት ተቀጥራ ስትሰራ ያገኘችውን ገንዘብ ይዛ ወደ ሥራው እንደገባች ትናገራለች:: እንጀራ ጋግሮ መብላት እንጂ እንጀራን ለገበያ የማዘጋጀት ልምድና ዕውቀቱ ባይኖራትም፣ በብዙ ተስፋና በከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ሥራው መግባት ችላለች::
በተባራሪ እያገኘች ከምትሰራው የኮንትራት ሥራ ውጭ ይህ ነው የምትለው ሥራ ባልጀመረችበት ወቅት አንድ አጋጣሚ ተፈጠረላት:: ይሄውም እንጀራ እየጋገረች ለገበያ የምታቀርብ አንድ ሰው መተዋወቋ የሥራ አጋጣሚውን ፈጥሮላታል:: አጋጣሚውን ተጠቅማም ሥራውን እንድታሳያት ጠይቃለች:: አይታ የተረዳችውን ሥራም ሳትውል ሳታድር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልታ ተግባራዊ አድርጋለች::
‹‹የጀመርኩት በሁለት በርሜልና በሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ›› ነው የምትለው ኤልሻዳይ፤ ስትጀምር ከመኖሪያ አካባቢዋ ርቃ እንደነበርና በኋላም ወደ መኖሪያ አካባቢዋ (ወይራ ሰፈር) መምጣቷን ትናገራለች:: በመኖሪያ አካባቢዋ አነስ ያለ ክፍል ተከራይታ እንደ እናት እንጀራን እያመረተች ለገበያ ስታቀርብ ሥራዋ ዕለት ዕለት እያደገ መጥቷል:: በጥራትና በከፍተኛ ጥንቃቄ በመሥራት የደንበኞቿን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገች የመጣችው ኤልሻዳይ ፍላጎቱ ከእሷ አቅም በላይ ሲሆን፤ በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትን መርጣለች::
ኤልሻዳይ ሁለት ምጣድና ሁለት በርሜል ይዛ በግሏ የጀመረችው እንጀራ የመጋገር ሥራ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞች ማፍራት ችሏል:: ሰፊ የማምረቻ ቦታና የሰው ኃይልም እየፈለገ መምጣቱን ስታስብ መንግሥት የሚያቀርበው የመሥሪያ ቦታ /ሼድ/ እንዳለ ትረዳለች:: ሼድ ለአንድ ሰው እንደማይሰጥ ስታስበው ደግሞ ሌሎች አራት ሰዎችን መፈለግ እንዳለባት ታሰባት:: አራቱን ሰዎች ጨምራ ከእሷ ጋር አምስት ሆነው በመደራጀት 60 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የማምረቻ ሼድ አገኙ:: ይህ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የተገኘው ሼድ ሥራዋን አስፋፋት መቀጠል እንድትችል ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላት ትናገራለች::
እሷ እንዳለችው፤ መንግሥት የፈጠራላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የምጣድ፣ የበርሜል፣ የሰው ኃይልና የተለያዩ ቁሳቁስን አሟልታ ሥራውን አጠናክራ መቀጠል ችላለች:: በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ስድስት እንጀራ መጋገሪያ ምጣዶችን ጨምሮ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስን አሟልቶ በየዕለቱ ትኩስ እንጀራ እያመረተ ለገበያ ያቀርባል:: በአራት ምጣድ በቀን እስከ 2000 እንጀራ ማምረት የሚችል ሲሆን፤ ስድስቱንም ምጣዶች መጠቀም ሲቻል ደግሞ በቀን ከ2000 እንጀራ በላይ የማምረት አቅም ይኖረዋል::
እንደ እናት እንጀራ ለሚያመርተው እንጀራ የተለያዩ የገበያ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፤ በተናጥል ከሚገዙ ግለሰቦች ጀምሮ በዋናነት ሆቴሎች፣ ሱቆችና አንድ ትምህርት ቤትም እንዲሁ ቋሚ ደንበኞቹ ናቸው::
ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ ጊዜ በሚያጋጥሙ የሀዘንና የደስታ ወቅቶች እንጀራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሳ፣ ይህ ሲሆን ደግሞ በትዕዛዝ ያቀርባል:: ለሆቴሎችና ሱቆች ላይ እንጀራ በየቀኑ እንደሚቀርብ የጠቀሰችው ኤልሻዳይ፤ ወይራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች ምገባም እንዲሁ በሳምንት ሶስት ቀናት እንጀራ እያቀረበ እንደሆነ ገልጻለች::
እንጀራ በየዕለቱ የሚፈለግና ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማዕድ የማይነጠል ቢሆንም፣ ያለው ገበያ በየጊዜው የሚለያይ እንደሆነም አመልክታለች:: በቋሚነት ከሚወስዱ ደንበኞቿ ውጭ ረቡዕ እና ዓርብ፣ በጾም ወቅት እንዲሁም እሁድ ቀን አብዛኛው ሰው ቤቱ ስለሚሆን የእንጀራ ገበያው በጣም እንደሚቀንስ ገልጻ፣ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ለትምህርት ቤት የሚቀርበው መጠንም እንዲሁ እንደሚቀንስ ተናግራለች:: ከዛ ውጭ ባሉት ቀናት ግን ድርጅቱ ከ1500 እስከ 2000 እንጀራ በቀን እያመረተ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቃለች::
በየዕለቱ ለሚዘጋጀው እንጀራ በዋናነት ጤፍን እንደምትጠቀም የገለጸችው ኤልሻዳይ፤ የደንበኛው ፍላጎትና የመግዛት አቅምን መሰረት በማድረግ ከጤፍ በተጨማሪ ሩዝ የሚጨመርበት እና አብሲቱን የበቆሎ ዱቄት በማድረግ እንደምታዘጋጅም አጫውታናለች::
ከዋጋ አንጻርም ሙሉ ለሙሉ ጤፍን ተጠቅማ የምታመርተው እንጀራ ከፍ ባለ ዋጋ እንደሚሸጥ ጠቅሳ፤ ጤፍ ውስጥ መጠነኛ ሩዝ ገብቶ እንዲሁም አብሲቱ የበቆሎ ዱቄት ሆኖ የሚዘጋጀው እንጀራ ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብ ጠቁማለች:: በመሆኑም ደንበኛው የሁለቱን ልዩነት አውቆ እንደ አቅሙና እንደ ምርጫው እንዲገዛ እንደሚደረግም አስታውቃለች::
ጤፍ እየተወደደ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሩዝን በመቀላቀል አብሲቱን የበቆሎ ዱቄት አድርጋ የምታዘጋጀው እንጀራ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ አልማ የምታዘጋጀው መሆኑን የጠቀሰችው ኤልሻዳይ፤ ሙሉ ለሙሉ ጤፍ ለሚፈልገው ሁሉም በጤፍ ዱቄት ብቻ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብም አስረድታለች:: አማራጩን በማቅረብ ደንበኛው በሚፈልገው አግባብ ትዕዛዝ ሰጥቶ በትዕዛዙ መሠረት እንደሚዘጋጅለትም ጠቁማለች:: ሩዙም ሆነ በቆሎው ከጤፉ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ቅናሽ ስላለው እንጂ ሁሉም ንጹህ እህል ነው ብላለች::
እሷ እንዳለችው፤ በዚህ መንገድ የሚዘጋጀው እንጀራ በየደረጃው ዋጋው ይለያያል፤ ሩዝ ተቀላቅሎ የሚዘጋጀውና አብሲቱ በቆሎ የሚገባበት አንድ እንጀራ በ30 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አብሲቱን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ በጤፍ ብቻ የሚዘጋጀው የአንድ እንጀራ ዋጋ ደግሞ 35 ብር ነው:: ይህ ዋጋ በቋሚነት ደንበኛ ለሆኑ የሚቀርብበት ዋጋ ነው፤ በተባራሪ ለሚመጣ ገዢ ደግሞ የተወሰነ ጭማሪ ይደረግበታል::
ኤልሻዳይ ወደ እዚህ ሥራ የገባቸው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ነው:: የጥረቷ ውጤት ወደ ስኬት ጎዳና እየመራት ሥራው ከአቅሟ በላይ ሲሆን፤ ቤተሰቧን ጨምራ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ ሥራውን የበለጠ ለማስፋትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ችላለች፤ አንድ ሆና የጀመረችው ሥራ አሁን ላይ ለስምንት ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏታል::
እንደ እናት እንጀራ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የበቃው በቀላሉ እንዳልሆነ ያጫወተችን ኤልሻዳይ፤ ወደ ሥራው በገባችበት ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበርና ያ ወቅት እጅግ ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች:: የእህል ዋጋ በየጊዜው መጨመር፣ የኤሌክትሪክ ፍጆታና ሌሎችም ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገጥሙ እነሱን ተቋቁማ ማለፍ በመቻሏ ዛሬ በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች:: ከዛሬ ነገ የተሻለ እንደሚሆን በማመን ሰፋፊ ዕቅዶችን ይዛለች::
ለአብነትም በቀጣይ እንደ እናት እንጀራ በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን አቅዳለች:: በከተማዋ እንደ ዳቦ ማምረቻና መሸጫ ሱቆች ለእንጀራ ብቻ የተባሉ መሸጫ ሱቆች የሉም:: ስለዚህ ይህን ዓይነት ሱቅ መክፈት የመጀመሪያ ዕቅዷ ነው:: ምክንያቱም እንጀራ የማህበረሰቡ ቀዳሚና ዋነኛ ምግብ በመሆኑ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንደ ዳቦ ሁሉ እንጀራ ተዘጋጅቶ የሚሸጥበት ሱቅ ሊኖር ይገባል የሚል ዕምነት አላት::
ሱቆቹን በየአካባቢው የመክፈት ዕቅድ አላት:: ይህም በየቤቱ ሥራ አጥ ሆነው የተቀመጡ እናቶችን ወደ ሥራው በማስገባት እንጀራ ጋግረው ለእንደ እናት እንጀራ የሚስረክቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስችላል ትላለች:: ከዚህ ባለፈም እንደ እናት እንጀራ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በቀጣይ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆነም አመላክታለች::
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም በአካባቢዋ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ሰዎች በቋሚነት እና በበዓል ወቅት እንጀራ በመስጠት እንዲሁም መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎች የአቅሟን እንደምታደርግ ትገልጻለች:: በቀጣይም ማህበራዊ ኃላፊነቷን አጠናክራ ለመቀጠል እንዲሁም የሥራ ዕድል ለማስፋትና ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት አሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቃለች:: በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ድርጅቶች ፈጥነው ለማደግ የተሻለ ብድር ቢመቻችላቸው የተሻለ ውጤት ይመጣል ባይ ናት::
‹‹ወጣቶች በተማሩት ሙያ መሥራትን ቢናፍቁም፤ የግድ አይደለም›› የምትለው ኤልሻዳይ፤ ዝቅ ብሎ መሥራትን መልመድ እንዳለባቸውም ትመክራለች:: ውስጣቸው ያለውን አቅም መለየትና በዙሪያቸው ያሉትን አማራጮች በሙሉ አሟጠው በመጠቀም እችላለሁ የሚሉትን ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ቢዘጋጁ በብዙ ያተርፋሉ ስትልም ትገልጸለች:: ምክንያቱም ዛሬ ትንሽ የመሰላቸው ሥራ ነገ ትልቅ ደረጃ ላይ ያደርሳቸዋል ስትል መክራ፣ የወጣትነት አቅም፣ ጉልበትና ድፍረትን ጭምር ተጠቅመው ጥረት ቢያደርጉ ለራሳቸው ሥራ ከመፍጠር ባለፈ ለሌሎች እንጀራ በልቶ ማደር ምክንያት መሆን ይችላሉ በማለት ትመክራለች::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም