በሁላችንም አካባቢዎች ሊስፋፉ፣ ሊዘወተሩ . . . የሚገባቸው፤ በችግር ፈችነታቸውና መሰረታዊ የሰላም ምንጭነታቸው ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች አሉ። እነዚህ እሴቶች ሀገርን እንደ ሀገር ዘመናት ተሻግራ እንድትመጣ ያስቻሉ ከፍ ያሉ ብሔራዊ አቅሞች ናቸው።
እነዚህ እሴቶቻችን ዛሬም ቢሆን ከዘመናዊው የችግር አፈታት ዘዴ /ጥበብ/ ባልተናነሰ መንገድ በግለሰቦች በቡድኖችና በማህበረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ ያላቸው ስፍራ የጎላ ነው። ከነዚህ እሴቶቻችን መካከልም አንዱ ጎሜ ነው።
የቱባ ባህላዊ እሴቱ ዋና ባለቤት በሆነው የጎፋ ሕዝብ ብያኔ መሰረት፣ “ጎሜ” ማለት እርምት (መታረም) ማለት ሲሆን፣ የጎፋ ሕዝቦች በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ዳግም እንዳይነሳና በዘላቂነት በመፍታት የነገ መጻይ ዕድል ተስፋቸውን በጋራ የሚያልሙበት የፍትህ ሥርዓት ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ጽንሰ ሀሳቡን የበለጠ ለመረዳት የተወላጁንና ፍፁም ኢትዮጵያዊያን፣ የአሰፋ ጨቦን ስራዎች ማንበብ ጠቃሚ ነው። ጋሽ አሴ ነፍሱን ይማረውና ውሸት (መዋሸት) ጎሜ መሆኑን ከመናገር ጀምሮ ከበቂ በላይ ጽፏል፤ መክሯል፤ ዘክሯልም። ግጭት ይወገድ፣ ሰላም ይሰፍን ዘንድም ሕይወቱን ሙሉ፤ ያለ ምንም መታከት ተሟግቷል። (ጋሽ አሴ እናመሰግንሃለን!!!)
በስፋት ሲነገር እንደ ነበረው፤ በተግባርም እንደታየው፣ የጎፋ ዞን ሕዝቦች የውስጥ አንድነትን የሚያጠናክር “ጎሜ”ን የሚያወጣ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት አላቸው፡፡“ጎሜ ማውጣት” ማለት ኃጢያትን መናዘዝ ወይም እርምን ማውጣትና የነገን ተስፋ በመልካም መሠረት ላይ ማቆም ነው።
ዕርቁም የሚከናወነው በተለያዩ ቦታዎች፣ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ከነበሩ የአካባቢው ተወላጆች ጋር ነው። ይህ ደግሞ፣ እነሆ ቀጥሎ ዛሬ እጅግ ወሳኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሁሉ አገራዊ መፍትሄ፤ የሰላም አስኳል በመሆን ላይ ሲሆን፣ ለዚህ ማሳያው ደግሞ (ጠላቶቻችን እየደገሱልንና ሲደግሱልን እንደ ነበሩት ሳይሆን) ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት በመንግሥትና ሕወሓት መካከል እየወረደ ያለው እርቅና እየሰፈነ ያለው ሰላም ነው። ወደ ጎሜ እንመለስ።
በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገር ሽማግሌዎች የሚመራው የጎሜ ሥነ ሥርዓት የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብን ከማጠናከር ባሻገር፤ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን የማረጋገጥ ሚና አለው። ማለትም ፋይዳው ግጭትን ማስወገድ ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። ፋይዳው ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም ባለፈ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ … ችግሮችን እስከ መፍታት ድረስ የሚዘልቅና በተግባርም የተፈተነ ነው።
ፖለቲካዊ ፋይዳ
ይህንን ንኡስ ርእስ ተጨባጭ ለማድረግ አንድ ግዙፍ ሁነትን ብቻ መጥቀሱ፤ እንዲሁም፣ በደቡብ ሕዝብና ክልሉን በሚያስተዳድረው ፓርቲ መካከል የሆነውን (ጥር 2011 ዓ.ም) ብቻ ማየቱ በቂ ነው። (ይህ ደግሞ፣ ዝቅ እያልን እንደምናየው፣ በሌሎች የአገራችን ክፍሎችም እየተስፋፋ፣ ሰላምና እርቅ እየወረደና እየሰፈነ ነውና እሴቶቻችን የዋዛ አይደሉም ማለት ነው።)
ቀደም ባለው ጊዜ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ “በወቅቱ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ባለመሰጠቱ፣ በአግባቡ ባለማገልገላችንና ሕዝብን በማስቆጣታችን ይቅርታ አድርጉልን” በማለት ፓርቲው በአባላቱ አማካኝነት ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቁን፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘው ሕዝብም ይቅርታውን መቀበሉን ሰምተናል።
በጎሜ ስነስርአት መሰረትም ሕዝቡ ይቅርታ ስለማድረጉና ችግሩ ዳግም እንዳይነሳ፤ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ኅብረትን ለማጠናከር በማሰብ የጋሻና ጦር ስጦታ ለአቶ ተስፋዬ ያበረከተላቸው መሆኑንም በወቅቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከተላለፉት ዜና ዘገባዎች ተረድተናል። ይህ ማለት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት እስከ ክልሉ ገዢ ፓርቲ ድረስ የዘለቀ፣ በፖለቲካና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሁሉ ሳይቀር መፍትሄን የሚሰጥ ባህላዊ እሴት ነው ማለት ነው።
ይህ የሚያሳየን ወይም የሚያስተምረን አቢይ ጉዳይ ቢኖር ልክ እንደ ጎሜ ሁሉ በገዳውም ሆነ በሰሜኑ በየአገራችን አካባቢዎች (ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግራይ…) የሚታወቀው “የአባት ባህላዊ ሕግ ሥርአት” (“የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የአስተዳደር፣ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቶች ማውጫ ቅጽ 1”ን ይመለከቷል) እንዲሁም በሌሎች እሴቶቻችን ዘንድ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው መሆኑን ነውና መታደል ነው። የኦሮሞ ባህላዊ እሴት ወደ ሆነው ገዳ ስርአት እንዝለቅና አንድ ጉዳይ ብቻ እናንሳ።
ባይሳ ኩማ ጎንፋ (Baay’isaa Kumaa Gonfaa) የተባሉ የድረገጽ ጦማሪ በማህበራዊ ድረ-ገጻቸው ላይ፡-የኦሮሞ ፍልስፍና ምንጩ ገዳ ነው፡፡ የዓለም ቅርስ ከሆነው ታላቅ ስርዓት የሚቀዳው ፍልስፍና ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ ሕይወትና አስተዳደራዊ ጥበብን፤ የግጭት አፈታትና ጠላትን መመከትን ያሰለጥናል፡፡
በገዳ ባህል፤ ወግና ስርዓት የሰለጠነ ልጅ ሆደ ሰፊነትን፤ ማቀፍና መደመርን አሳምሮ ያውቃል። እንቅፋትን እንዴት እንደሚያነሳና ጠላት ሆኖ የመጣበትን እንዴት እንደሚመክት፤ በጦር ውሎ የማረከውን እንዴት ኦሮሙማን እንደሚያላብሰው ያውቃል፡፡ ኦሮሞ ሲጀመር ጠላትነትና ምቀኝነት ውስጡ ቢኖር የማረከውን ልጁ አያደርግም፡፡
ምሎና ተገዝቶ ከአብራኩ ከተከፈለው እኩል ማንነቱን አያወርስም፡፡ በመሰረቱ በአፋን ኦሮሞ ውስጥ ምቀኝነትን በአማርኛ እንደምናውቀው አሳምሮ የሚገልፅ ቃል አይገኝም፡፡ ምክንያቱም የለበትምና፡፡ ከላይ ርእስ አድርጌ የተጠቀምኩት ብሂል (“ኦቱማ ሞርቱን ሞርቱ ሆርቱን ሆርቲ … ሟርተኞች ጎሜ እያያዙ ቅኖች ባለጠግነትና ፀጋቸው ይበዛል!!!” የሚለውን ማለታቸው ነው) የኦሮሞ አባቶች ስነቃል ነው፡፡ ሟርተኞች ጎሜ ይዘው ቢውሉ ቢያድሩ ቅኖች ባለጠግነትና ፀጋቸው ይበዛል በሚል እንድምታ ሊፈታ ይችላል።
ይህን ሀሳብ ሳነሳ ኦሮሞ በመሆኔ ይህንን ሕዝብ ከውሃ የጠራ፤ ከፀሐይ ብርሃን የላቀ ጥቅምና ደረጃ እየቸርኩት አይደለም፡፡ ገዳ እንዲህ ልጁን ሊያሳድግ ግድ ስለሆነ እንጂ፡፡ በእርግጥ ከባህሉ የሚያፈነግጥ፤ ከአባቱ ትእዛዝ ውጭ የሚሆንና የእናቱን ማጀት የሚያስበረብር ገልቱም አይፈጠርም ማለቴ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነቱን ከንቱ እንዴት እንደሚገራውም ያውቃል፡፡
በጅ አልል ሲልም መፍትሄው በእጁ ነው። እናም እነሆ እንዲህ ሆነ፡፡ የአባ ገዳ ልጆች በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ወደ ጥንት ነገራቸው ተመለሱ። ለዓለም እነሆ ብለው ሰጥተው ለራሳቸውም በባርነት እንዲማቅቁ እጣ የሆናቸውን ሰበብ ፈልገው አገኙና መፍትሄ አበጁለት፡፡
እነሆ ከመራራቅ መቀራረብ፤ ከመጠላላትና በጠላትነት ከመተያየት በሚያግባቡ ጉዳዮች ወደ መግባባት፤ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም አብሮ የመቆም፤ በደልን በይቅርታ በመተላለፍ ሁሉን ስለማቀፍ፤ ለጠላት ብርቱ ክንድ፤ ለወዳጅ ማር ስለመሆን፤ ሀቅ፤ ፍትህና ወንድማማችነትን ስለማስፈን መዘመር ጀምረዋል፡፡ አድርገውታልም።
አትጠራጠሩ በዚህኛው ዘመን የኢትዮጵያ ትንሳኤ የላቀ ድል ነው፡፡ ገዳ ለወለዳቸው ልጆች በተወለዱበት ቀበሌነት መታጠር አይመጥናቸውም፤ በሚኖሩበት ወረዳና ዞናዊ ጎጠኝነትና ለኔ ብቻ ጥቅም አይገልፃቸውም። ለኔና ለኔ ብቻ የሚል ክልላዊ መታጠርም ያንሳቸዋል፡፡ ይህንን አጀንዳ ሳነሳ ማንነት፤ ባህልና ወግ እንዲሁም የሞትንለትን የቋንቋ አጀንዳ ይቀብሩታል ማለቴም አይደለም፡፡ ይልቅስ ያበለፅጉታል፡፡
የብዙ አንድነት እንጂ የመጨፍለቅ አንድነት አይገባቸውም፡፡ እንዲህ ባለው ግልፅ አስተሳሰብ ሁሉም ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሸናፊ አስተሳሰብ ይገባቸዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ማሰብና መትጋትም አይበቃቸውም፡፡ ሩቅ መሻገር ነው ህልማቸው። ሁሉንም ደረጃና ማንነት አጠንክረው አፍሪካን ስለማግነን ማሰብ ጀምረዋልና እንግዲህ ማንም አያቆመንም … ይልቅዬ፣ ጠላት ሆይ ከዚህ ብሩህ ዘመን መደመር ትተህ ላትዘልቀው አትብገን በሉልኝማ!!!!
በማለት ያሰፈሩትን ከዚሁ፣ እየተነጋገርንበት ካለው ጎሜ እና ፋይዳዎቹ አኳያ ማየት ይቻላል፤ ይገባልም። ወደ ጋሞዎች እንመለስና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን እናንሳ።
“ወጋ ኦጋ”፣ “ቱጌ”፣“ጫቆ”፣ “ጎምታ”፣ “ማካ”፣“ዮ…”
ጋሞዎች ባልና ሚስት፣ ጎረቤት ከጎረቤት ማሕበረሰብ ከማሕበረሰብ ጋር ሲጣላ የሚፈቱበት ዘመን የተሻገረ ባሕላዊ ስርዓት ያላቸው ሲሆን፤ አንዱም “ወጋ ኦጋ” ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጋሞ ውስጥ ብቻ ከ300 በላይ ጎሳዎች ይገኛሉ። ይገኙ እንጂ ሁሉም በዚህ ስርአት ይገዛሉ። ማንም ከዚህ ስርአት በላይ ወይም ውጭ አይደለምን።
በ“ወጋ ኦጋ” ስርዓት የማይፈታ ችግር፣ የማይወርድ ዕርቅ የለም። ሁሉም ችግር ከዚህ ስርዓት በታች ነው። የወንጀልም ይሁን የፍትሐብሔር ጉዳዮች በዚህ ባሕላዊ ስርዓት በአጭር ጊዜ፣ በትንሽ ጉልበት ይፈታሉ። በዚህ የዕርቅ ስነ ስርዓት በዳይ፣ ተበዳይ ተገናኝተው ጉዳያቸውን ያስረዳሉ። የአካባቢው ሽማግሌዎችም ቂም በሚሽር መልኩ ያስታርቋቸዋል። ሌላው “ቱጌ” ነው።
ቱጌ ማለት ያልታሰበ ችግር ወይንም ግጭት ሲፈጠር የሚፈታበት የሽምግልና ስነ ስርዓት ነው። በዛ ቀውጢ ወቅት የጋሞ አባቶች እንዳደረጉት ሁሉ ድንገተኛ ግጭት ሲነሳ አባቶች ለምለም ሳር በእጃቸው ይዘው ከፊት ለፊት ይቆማሉ። የሽምግልና ስርዓቱም ከፊት መቆም ነው። ሽማግሌዎቹ ከፊት ለፊት ቆመው ፀቡ ካልበረደ ተንበርክከው ይለምናሉ። ፀቡን በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱ ቃል ይገባሉ።
በዚህ ሰዓት አባቶቹን የሚያልፍ አንድም ሰው አይኖርም። እናቶች ደግሞ በዚህ ድንገተኛ ግጭት ጊዜ መቀነታቸውን ፈትተው፣ ጡታቸውን በመያዝ ፀብ እንዳይኖር፣ ሰላም እንዲሰፍን ይለምናሉ። ፀቡ ከጠና ከተጋጩት መካከል ይተኛሉ። እናቶችን “ማሪዣም” ይሏቸዋል። ማርያም እንደ ማለት ነው።
እናቶችም ፀብ ሲመጣ “እኔን ውሰዱ፤ እኔ ማርያም ነኝ፤ ማርያምን ረግጦ መሄድ አይቻልም፤ አትጋጩ።” በማለት ይማፀናሉ። ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ለበቀል የተዘጋጀ እጅ ቢመጣ ክንዱን ለበቀል አይዘረጋም። ይህን ቢያደርግ “ጎሜ” ነው። ጎሜ ማለት ሀጥያት፣ እርግማን ማለት ነው። የእናቶችና የአባቶች እርግማን ይደርሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ጎሜን ደፍሮ የሚፈፅም ማንም የለም።
ከ“መረጃ ዶት ኮም” የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በጋሞ ብሔረሰብ 42 ደሬዎች (የተለያዩ ስም ያላቸው ማኅበረሰቦች) እንዳሉ ይነገራል። ደሬዎችም የራሳቸው ድንበር አላቸው። አንዱ የአንደኛውን ላለመንካት በመሀላ ቃል የታሰረ ነው። መሃላው “ጫቆ” ይባላል። ቢጋጩ እንኳን ለመዳኘት አስቀድመው ቃል ይገባሉ።
በድንገተኛ ግጭት ሞት ቢኖር በአጭር ቀን እርቅ ይፈፀማል። እርቅ ሲፈፀምም የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች አብረው በመብላትና በመጠጣት ነው። ይህም ሰነስርዓት “ጎምታ” ይባላል። የእርቅ እርድ ሲፈፀም እርዱን የሚፈፅመው “ማካ” ይባላል። ማካ ማለት ባህላዊ የጋሞ ቄስ ነው። ከታረደ በኋላ “ኮይራፍሬ” ወይም የጎሳ መሪው ከሟችና ከገዳይ ጎሳ መሪዎች ጋር በመሆን ደም እና ፈርሱን በመርገጥ ሦስት ጊዜ ዮ… ዮ… ዮ… በማለት ጎማታ አውርደው ምግቡን በጋራ ይመገባሉ።
ዮ….ማለት ሰላም አውርደናል፤ እርቅ አድርገናል ማለት ነው። ከዚህ በኋላም ቂምና በቀል የለም፤ አካኪ ዘራፍ የለም፤ ጉዳዩ በእርቅ ተሽሯልና። ታዲያ ከዚህ በላይ ባህል፣ ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰ እሴት፣ አገር በቀል እውቀት …. ከየት ሊመጣ ይችላል? አይችልም። በመሆኑም በመላ አገሪቱ ሊሰራ፣ የጋራ እሴትም ሊሆን ይገባልና ችላ ማለቱ ይበቃል።
ይህ ቱባ ባህል ደግሞ ሁሉም እንደሚስ ማሙበት፣ ምክር ቤት ሳይፈጠር፣ ክልልና ዞን ሳይከፈል፣ ድንቅ ስርዓት በጋሞች ዘንድ እንደ ነበረ እራሱን የቻለ ማረጋገጫ ነው።
ይህ እድሜ ጠገብ ባህላዊ ስርአቱ የቱባ ባህሉን ባለቤት፣ ያለእንከን፣ እዚህ ድረስ አዝልቋልና ተጠናክሮ ሊቀጥል የግድ ይሆናል ማለት ነው። (ጋሞ በቀድሞው በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ስር የነበረ፣ ቆይቶ በጋሞ ጎፋ ዞን ስር የነበረ፣ በቅርብ ደግሞ ራሱን ችሎ የጋሞ ዞን የሆነ ነው።)
ወደ ሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ስንመጣ የምናገኘው ያው ሲሆን፣ የኖርነውም ሆነ እያኖረን ያለው ይሄው እድሜ ጠገቡ ባህላዊ እሴታችን ሲያደርግ በኖረውና እያደረገልን ባለው አስተዋፅኦ እንጂ፣ ባእዳን እንደሚሉት የማንረባ፣ ችግሮቻችንን እራሳችን መፍታት የማንችል … ቀሽሞች አይደለንም።
የፌደራሉ መንግሥትና ሕወሓት ከገቡበት ማንንም የማይጠቅም ጦርነት ውስጥ ይወጡና እዚህ አሁን ያሉበት ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ይገኙ ዘንደ ያደረጋቸው የማንም ግፊትና ተጽእኖ ሳይሆን፤ ያኖረንና እያኖረን ያለው አገር በቀል እውቀታችን፣ ማህበረ-ባህላዊ እሴታችን፣ የግጭቶች አፈታት ስርአታችን ወዘተርፈ መሆኑን ሁሉም በደማቁ ሊያሰምርበት ይገባል። ጉዳዩን ትንሽ ገፋ አድርገን እንየው።
በመንግስትና በሕወሓት መካከል በተካሄደው ጦርነት አገርንና ሕዝብን ላልተፈለገ ስቃይና መስዋእትነት ተዳርጓል። ይሁን እንጂ፣ የውጭ ሀይላት ኢትዮጵያ አለቀላት፤ ዜሮ ገባች፤ ተበታተነች ወዘተርፈ እያሉ በሚያሟርቱበት ወቅት፣ ሁለቱ ሀይሎች በራሳቸው ጊዜና ፍላጎት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመምጣት ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት፤ ልዩነቶቻቸውን በድርድር ለማጥበብ፤ ፍላጎቶቻቸውን ለሕዝብ ጥቅም ለማስገዛት … ተስማምተው እነሆ ወደ ተግባር እያዋሉት ይገኛሉ። ዛሬ መቀሌና አዲስ አበባ የድሮ ሕይወታቸውን የጀመሩትም በዚሁ፣ በኢትዮጵያዊ መፍትሄ አማካኝነት ነው።
ይህ ፖለቲካዊም እንበለው ርእዮተ ዓለማዊ ጣጣ ዞሮ ዞሮ አገር በቀል እውቀት ላይ፣ ባህላዊ እሴቶቻችን እግር ስር ወድቋልና በእውነት ኢትዮጵያዊነት ያኮራል። ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት መቻላችን ያስደስታል። በተራዛሚውም “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ማለት ይሄው ነውና ሌሎችም ይህንን የኢትዮጵያን አርአያነት ሊከተሉ ይገባል። ካላደረጉት ራሱ ጎሜ ነውና ዋጋ ማስከፈሉ የግድ ይሆናል። ከዛ በፊት ግን፣ ጎሜን ለማስወገድ መፍትሄው ጎሜን ማውጣት ነውና ጎሜን ልናወጣ የግድ ይሆናል። ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015