የአንድ ሀገርና ሕዝብ የነገ ብሩህ ተስፋ በተጨባጭ መሰረት የሚያደርገው ሰላምን ነው። ያለ ሰላም ስለአንድ ሀገር ነገዎች ቀርቶ ሕልውና ማሰብ አይቻልም። ለዚህ ደግሞ ትናንት ያጋጠመን የሰላም እጦት የቱን ያህል ለህልውናችን አደጋ ሆኖ እንደተፈታተነን ለማሰብ የሚከብድ አይደለም።
በርግጥ ለረጅም ዘመናት ይዘነው የመጣነው ኋላቀር የፖለቲካ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ የፈጠረው የሴራና የመጠላለፍ ፖለቲካ እንደ ሀገር በየዘመኑ ትውልዶችን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ሀገሪቱን የደም ምድር፤ ህዝቦቿን የድህነትና የጉስቁልና ተምሳሌት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
አለመግባባቶችን ጦር ሰብቆ በኃይል የመፍታት የጦረኝነት ባህል፤ ባህሉ የወለደው እልኸኝነትና ነገሮችን በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ዘግቶ የመውጣት መሻት ፤ ዘመናት ተሻግረው ዛሬም የዚህ ትውልድ ፈተና ሆነው ትውልዱን ዋጋ አስከፍለውታል።
ትውልዱ በዘመናዊ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ በሚወልዳቸው መርሆዎች ራሱን ለመግራት የሚያደርገው ጥረት የሚፈልገውን መስዋእትነት ለመክፈል /በማወቅም ይሁን ባለማወቅ/ አለመቻሉ ጥረቱን በተጨባጭ አካል ለብሶ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠበቀውን በረከት ይዞ እንዳይመጣ አድርጎታል።
ከቋንቋ ባለፈ ተስፋ እንደተጣለበት ዘመናዊ ትውልድ ፤ ሀገርና ሕዝብን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማሻገር የሚያስችል፤ ለራሱ የታመነና ለመጪው ትውልዶች ጭምር የሚታመን ኃላፊነት የሚሰማው እንዲሆን አላስቻለውም።
በተለይም ራሱን ፖለቲከኛ አድርጎ የሰየመውና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን አንግቦ ወደ ሀገራዊ የፖለቲካ ገበያው የወጣው ትውልድ ለፖለቲካው ገበያው ስኬት ሀገራዊ ሰላም አልፋና ኦሜጋ መሆኑን በአግባቡ ማስተዋል ተስኖት ራሱንም ሆነ ሀገርን ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል።
የትውልዱ የፖለቲካ እውቀቶች ትናንትን በተጨባጭ ከማረም ያልተነሱ፤ ከዛ ይልቅ ባልታረመ የፖለቲካ ባህል ላይ የተዘሩና የበቀሉ በመሆናቸው ፍሬ አልባ ሆነዋል። መላው ሕዝብንም ግራ በሚያጋባ እንቆቅልሽ ውስጥ እንዲያልፍ አድርጎታል።
ትውልዱ /አሁን ያለው ፖለቲከኛ ትውልድ / የቱንም ያህል የዘመናዊ እውቀትና መገለጦች ባለቤት ቢሆንም ፤ መድረኮችን ከነዚህ እውቀቶች በሚቀዱ ዲስኩሮች ቢያጣብብም ፤ ሀገራዊ ሰላምን በቀዳሚነት አጀንዳ ማድረግ የተሳናቸው ብዙ በመሆናቸው ከቋንቋ ያለፈ ትሩፋት ማምጣት አላስቻሉም።
እነዚህ መድረኮችን የሚያጣብቡ ዲስኩሮች እየቆዩ ሲሄዱ፤ የሕዝባችንን የነገ ተስፋ ከማቀጨጭ ባለፈ ብዙ ዋጋ ከፍሎ ባስተማራቸውና ለብዙ ማዕረግ ባበቃቸው የአብራኩ ክፋዮች ላይ የነበረውን መተማመን እንዲያጣና ትናንቶችን ናፋቂ እንዲሆን አድርገውታል። ለዚህ ደግሞ ላለፉት አራት አመታት በሀገሪቱ የፖለቲካ ገበያ የነበረውን እውነታ በአግባቡ ማጤን ተገቢ ነው።
ባለፉት አራት አመታት በሀገሪቱ የሽግግር የፖለቲካ ገበያ አትራፊ ሆኖ ለመገኘት አንቱ የተባሉ የዘርፉ ስመጥር ምሁራን ሳይቀሩ፤ ከገበያው ከመርህ ውጭ ሀገራዊ ሰላምን በመናጥ ፤ በሀገራዊ ሰላም ለመሸቀጥ በብዙ ሲሞክሩ ማስተዋል ችለናል።
አንዳንዶች የፖለቲካ ገበያውን ፍጹም በኃይል በማተራመስ በሚፈጠር የፖለቲካ ክፍተት ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሄዱበት የጥፋት መንገድ መላው ሕዝባችን ከተመሳሳይ ትናንቶች የከፋ እና ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል አስገድደውታል።
ሕዝባችን ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቆ፤ ብዙ ዋጋ ከፍሎ የጀመረው ለውጥ እንደ ቀደሙት ዘመናት የለውጥ ተሞክሮዎች፤ በደም ተጀምሮ በደም እንዲያበቃ ፤ በብዙ ተስፋ ተጀምሮ ቅዥት በሚመስል መንገድ ወደ ፍጻሜው እንዲጓዝ በብዙ ተግተዋል።
እነዚህ ኃይሎች የፖለቲካ ገበያውን እንዳይረጋጋ በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን የሄዱበት መንገድ አንድም ለገበያው መርህ የተገዛ አለመሆኑ አትራፊ አላደረጋቸውም፤ ከሁሉም በላይ በሀገራዊ የፖለቲካ ገበያው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን መልካም አጋጣሚ ችግር ውስጥ በመክተት የለውጥ ጉዞው አዝጋሚ እንዲሆን አድርገውታል።
ይህ ራስን ቀድሞ በፖለቲካ ገበያ መርህ ካለመግራት የሚመነጨው የፖለቲካ ባህላችን፤ ብዙ ትናንቶችን እንዳሳጣን ፤ ከዛም ባለፈ እንደ ሀገርና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዳስከፈለን ተረድቶ ለመታረም ለፖለቲከኞቻችን ይህ የተሻለው ጊዜ እንደሆነ ይታመናል።
ፖለቲከኞቻችን ብዙ ተስፋ ሰንቀን በጀመርነው ለውጥ ማግስት እንደ ሕዝብና ሀገር ያስከፈሉን ዋጋ ከልብ ሊጸጽታቸው ይገባል ፤ ጸጸታቸው እንደ ሰው አዕምሯቸው ለሚጠይቃቸው ጥያቄ ምላሽ ከመሆን ባለፈ ተመሳሳይ ስህተት ላለመስራት ፤ አልያም ከፖለቲካው ገበያው ራሳቸውን እስከማግለል የሚደርስ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015